Saturday, 07 September 2013 10:21

“መልሶ ማልማት” የሚሹ ኮንዶሚኒየሞች!

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(3 votes)

                      “እርግብ ነው የተረከብኩት፤ ቤት አይደለም” ያለኝ በሀያት ቁጥር ሁለት፣ ኮንዶሚኒየም ቤት ደርሶት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊረከብ በሄደ ጊዜ ቤቱ ሲከፈት እርግቦች የወጡበት ወጣት ነው፡፡ እርግቦቹ ጣራው በደንብ ባለመሠራቱ እርግቦቹ ቤቱን ቤታቸው አድርገው እንደኖሩ የተናገረው ወጣቱ፤ ኩሳቸውን አጽድቶ ለመግባት ቀናት እንደፈጀበት ይገልፃል፡፡
አራተኛ ፎቅ ላይ ባለ ሦስት መኝታ ቤት የደረሳቸው ሌላዋ ነዋሪ፤ በወጉ ባልተሰራው የጣራው ቆርቆሮ ዝናብ እየገባ በመቸገራቸው አቤቱታ ማቅረባቸውንና “የቆርቆሮ እጥረት አለ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በር መስኮት ተሰባብሯል፡፡ የተረከብነውን ቤት መኖሪያ ቤት ለማድረግ በራሳችን ወጪ እያሰራን ነው የገባነው ብለዋል፤ ነዋሪዋ፡፡
ውሃ በሳምንት አንድ ቀን ሐሙስ ብቻ እንደሚመጣ፣ ቤታቸውን ለማጠናቀቅ የጀሪካን ውሃ በ10 ብር ይገዙ እንደነበርና ቤቱ ፎቅ ስለሆነ የዝናብ ውሃ እንኳን እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዋ ቤቱ ሲተላለፍላቸው ምን ምን ተሟልቶላቸው እንደነበር ጠየቅኋቸው፡፡
“ምንም! ጣራና ግድግዳ ብቻ ነው፡፡ ውሃ፣ መንገድ እና መብራት ቢሟሉ እኮ ሰው ይገባ ነበር፡፡ መንገዱም እንዳየኸው ጭቃ ነው፤ መጓጓዣ ቢኖርም መንገድ አልተሟላልንም፡፡ ሰው ቤት ለማለት ስለተቸገረ ነው ከደረሰው በኋላ ለኪራይ የሚከፍለው፡፡” በማለት ያሉበትን ሕንጻ አዘዋውረው አሳዩኝ፡፡ ጥቂቱ ሰው ገብቶባቸዋል፡፡ ሌሎቹ የደረሳቸው ሰዎች መጥተው አይተው ያልገቡባቸው ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ጭራሽ ሰው አልተመደበባቸውም፡፡ ከነዚህ ክፍሎች አንዱ በምድር ቤት የሚገኝ ነው፡፡ በሩ ተገነጣጥሎ መጸዳጃ ሆኗል፡፡ እንኳን ውስጡ

ለመግባት በአጠገቡ ሲያልፉም ይሰነፍጣል፡፡ በሳቸው ሕንጻ ሌሎች ሁለት “መጸዳጃ” የጋራ ቤቶች አይቻለሁ፡፡ በየነዋሪዎቹ ቤት ውሃ በሳምንት አንድ ቀን በመሆኑ መጸዳጃ ቤት ለጤና ጠንቅ እየሆነም ነው፡፡
ከሱ ቀጥሎ ባለው ሕንፃ አራተኛ ፎቅ ድረስ ባለቤት የሌላቸው ቤቶች በር ተገንጥሎ ለመጸዳጃነት ውለዋል፡፡ የመንግሥት አስተዳደርን በመወከል አገልግሎት የሚሰጠው የነዋሪዎች ኮሚቴ ጽሕፈት ቤትን ግድግዳ የሚጋራው ሌላ ባለቤት አልባ ምድር ቤትም መጸዳጃ ቤት ሆኗል፡፡
ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ደግሞ ምድር ቤት ነው የደረሳቸው፡፡ እሳቸውም ቤቱን ሲረከቡ መጸዳጃ ቤት ሆኖ ያገለግል እንደነበር ይናገራሉ፡፡ “ይኼ ብቻ አይደለም” ብለው አራተኛ ፎቅ ላይ ወደ መጸዳጃ ቤትነት የተቀየረ ቤት አሳዩኝ፡፡ የሳቸውም ሆነ ይኼኛው ርክክብ የተደረገበት ባለፈው መጋቢት ወር ቢሆንም ያረጀ ቤት ይመስላሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር ቤቱን አፀዳድተውት ገና መግባታቸው ነው፡፡ የስልክ እና የመብራት ገመዶች ስላልተቀበሩበት ለመላው ሕንፃ የሚሆኑ ኬብሎችን ከጎረቤታቸው ጋር በመሆን ከስድስት መቶ ብር በላይ አውጥተው አስቀብረዋል፡፡
“ስትረከቡ በምን ሁኔታ ላይ ነበር?” አልኳቸው ወይዘሮ አልማዝን፡፡
“በር አልነበረውም፤ የተሠጠህ እለት ፍራሼን ይዤ ልግባና ልተኛ ብትል የማይቻል ነው፡፡ በዚያ ላይ የአንዱ ቤት መክፈቻ የሁሉንም ስለሚከፍት ሌባም በጣም ያሰጋል፤ ካሁን በፊትም በር ተገንጥሎ በተመሳሳይ ቁልፍ የተዘረፉ አሉ” ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮዋ ገለፃ፤ በአያት ቁጥር ሁለት በቤቶች ኤጀንሲ ለጋራ መኖርያ ቤት ተጠቃሚዎች የተሰጠ መክፈቻ የሁሉንም ቤት ይከፍታል፤ ስለዚህም ነዋሪዎቹ ወዲያውኑ በራሳቸው ወጪ የገዙትን ቁልፍ ማስገጠም ነበረባቸው፡፡
ባለ ሁለት መኝታ የደረሳቸው አቶ አበበ በቀለ፤ እስካሁን ቤታቸው ያልገቡት መብራት ስላልገባላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ መንገድ ባለመሰራቱ የመብራት ሃይል ሠራተኞችን ማግኘት አልቻልኩም ይላሉ፡፡ ሆኖም መንገዱ ቢሰራ ሰው ሊገባ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ የገለፁት አቶ አበበ፤ “ባለቤት የሌላቸው የጋራ መኖሪያዎች ላይ እርምጃ ይውሰድ” ሲሉ መክረዋል፡፡
እሳቸው መንገድ ሲሰራ አካባቢው እንደሚሻሻል ተስፋ ቢያደርጉም አራተኛ ፎቅ ላይ ባለ አንድ መኝታ ቤት የደረሰው ጎልማሳ ግን “መንገድ የተባለው የጭቃ ባህር መሆኑን አላየኸውም እንዴ” ሲል ጠይቆኛል፡፡ ታክሲዎች፣ሚድባሶች፣ እንዲሁም 83፣61 እና 49 ቁጥር የከተማ አውቶብሶች ወደ አካባቢው ቢጓዙም መንገድ አለው ማለት ግን ያስቸግራል፡፡
ይኸው ጎልማሳ ስለ ቤቱ ጣራ፣ስለ መንገድ፣ስለ መብራትና ሌሎች አገልግሎቶች ለመስተዳደር አካላት ቅሬታውን አቅርቦ ነበር፡፡ “ግድግዳው በእጅ ሲነካ በጣም ይነቃነቃል፤ ይኼ ቤት አይደለም” ሲል ለሰነዘረው አስተያየት ከአንዲት የስራ ሃላፊ የተሰጠው ምላሽ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበታል፡፡ “አንዳንዱ ቤት ለማግኘት መከራ ያያል፤ የተሰጠው ግን አሻሽሎ እንደመግባት ያማርራል” ተብያለሁ ብሏል፡፡ የተባለ ሲሆን ከብዙ ምልልስ በኋላም “ተቋራጩን ጠይቅ” ተብሎ ስልክ እንደተሰጠውና ሲደውል “ምን ሆነብኝ ነው የምትለው? ስራ የለህም እንዴ? አትነዝንዘኝ” የሚል መልስ ማግኘቱን ገልጿል፡፡
የህዝብ አገልጋይ የስራ ሃላፊዎች ሳንቲም ስንጨምርበት እንደሚሰራ የህዝብ ስልክ መሆን የለባቸውም ያለው ጐልማሳው፤ “ነዋሪው ጋዜጠኛ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ቀኑን ሙሉ ብሶቱን ይነግርህ ነበር” ብሎኛል፡፡
በአያት ቁጥር 2 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ካሉ ሰፋፊ የጋራ መጠቀሚያ ክፍሎች አንዱ ለዲኤስቲቪ ቤት ማሳያነት ማን እንዳከራየው ሳይታወቅ እንደተከራየም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

Read 2585 times