Saturday, 07 September 2013 10:37

አስገራሚ የሎተሪ ታሪኮችና ገጠመኞች

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(38 votes)

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከመቋቋሙ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሎተሪ ጨዋታ በተለያየ መልኩ ይካሄድ ነበር፡፡ ህግ ከመውጣቱ በፊት የሚካሄዱት ቁማር መሰል ጨዋታዎች በህብረተሠቡ ዘንድ “ኪሳራ” በመባል ነበር የሚታወቁት፡፡ በ1938 ዓ.ም ህገወጥ ሎተሪዎችን የሚያግድ አዋጅ ከወጣ በኋላ፣ “ኪሳራ” የሚባሉት የቁማር ጨዋታዎች ቀሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ግለሠቦች ፈቃድ እያወጡ ሎተሪ ማጫወት ጀመሩ፡፡ አንዳንዴ ገንዘቡን እየሰበሰቡ የሚጠፉ ሁሉ ነበሩ፡፡ በ1945 ዓ.ም ነው መንግስት ሎተሪ እንዲያካሂድ የሚፈቅድ አዋጅ የወጣው፡፡ በመጨረሻ በ1954 ዓ.ም የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ ታወጀ፡፡ ብሔራዊ ሎተሪ ሲመሰረት የሠራተኞቹ ቁጥር አምስት ብቻ ነበር አሁንስ? የአዲስ ዓመት ዋዜማ እንግዳችን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ፤ መ/ቤታቸው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሂደት እንዲሁም ከሎተሪ ዕድለኞች ጋር በተያያዘ አስገራሚ ታሪኮችንና ገጠመኞችን ለአዲስ አድማስ አዘጋጅ ኤልሳቤት ዕቁባይ በስፋት አውግተዋታል፡፡ እነሆ፡-

የመጀመርያዎቹ እድለኞች አምስት ኤርትራውያን ነበሩ…
የጐንደሩ ነዋሪ “መሐመድ ሎተሪ” 15 ጊዜ ሎተሪ ደርሷቸዋል…
አፄ ኃይለስላሴ የደረሳቸውን መኪና መልሰው ሸልመዋል…
የመጀመርያው እጣ 50ሺ ብር ነበር… አሁን 4ሚ. ብር ደርሷል…

ቢሮው የት ነበር? ዕጣው የሚወጣበትስ?
የመጀመሪያ ቢሮው በአሁኑ የመብራት ሀይል አዳራሽ ህንፃ ሲሆን በናዝሬት፣ በድሬዳዋና በአስመራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ነበሩት፡፡ በአዲስ አበባ ሶስት ማከፋፈያዎች ነበሩት፡፡ በመስከረም 1954 ዓ.ም ነው የመጀመሪያው ሎተሪ ገበያ ላይ የዋለው፡፡ ዕጣው ሀምሳ ሺህ የሚያሸልም መደበኛ ሎተሪ ነበር፡፡ አምስት ክፍልፋዮች አሉት፤ እያንዳንዳቸው አስር ሺህ ብር የሚያሸልሙ፡፡ የመጀመርያው ሎተሪ የወጣው ታህሳስ 29 ቀን 1954 ዓ.ም የገና ዕለት በአሁኑ ጃንሜዳ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተሠበሰቡበት ነው፡፡ ከዚያም ትንሿ ስታዲየም በምትባለው ቦታ በታጠረ ቆርቆሮ የሎተሪ እጣ ሲወጣ ቆየ፡፡ በመጨረሻም አሁን ባለው የመስሪያ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ የሎተሪ ዕጣ መውጣት ቀጠለ፡፡ ቢሮው ከመብራት ሀይል ህንፃ በመቀጠል የድሮው ፖስታ ቤት ሙኒ የሚባል አካባቢ ነበር፡፡ ከዛም ወደ አሁኑ ቢሮ የተዛወረ ሲሆን፡፡ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኤቦን ሚሞሪ የሚባሉ ግሪካዊ ነበሩ፡፡
የመጀመሪያዎቹ ዕድለኞች እነማን ነበሩ?
የመጀመሪያዎቹ ዕድለኞች አምስት የቀድሞው የኤርትራ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አምስቱም የሚኖሩት በሀማሴን አውራጃ ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው አስር አስር ሺህ ብር አግኝተዋል፡፡ አንድ ትኬት ገዝተው ነው የተከፋፈሉት፡፡ የመጀመሪያው አሸናፊ ቁጥር 07260 ነበር፡፡
ሎተሪ ሲደርስ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ውዝግቦች እንዳሉ ይሰማል …
ትክክል ነው፡፡ ጊዜው ቆየት ብሏል፡፡ ሽሮሜዳ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ሠው ሎተሪ ይቆርጥና ለሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ይሠጣል፡፡ ሎተሪው ሎንቺና የሚያሸልም ነበርና አንዷ ይደርሳታል፡፡ በጣም ተደስታ ግብዣ ያደረገች እለት ሎተሪውን ለጓደኛዋ ያዥልኝ ብላ ትሠጣታለች፡፡ ጓደኛዋ ሎተሪውን ከራሷ ሎተሪ ጋር ቀያይራ አስተዳደሩ ጋ በመምጣት መኪናውን ለመውሰድ በሂደት ላይ ሳለች፣ “እውነተኛዋ” ባለዕድል ተጠራጥራ ትመጣና ሂደቱን በፍርድ ቤት ታስቆማለች፡፡ አራት አመት በክርክር ከቆየ በኋላ ፍርድ ቤቱ ለሁለት አካፍሏቸዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሰኔ ሀያ ስምንት በወጣው የቶምቦላ ሎተሪ አምስተኛው ባለዕጣ የመቀሌ ነዋሪ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን ይባላል፡፡ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሁልጊዜ ሎተሪ በጋራ ይቆርጣሉ። ስማቸውንም ሎተሪው ላይ ይፅፋሉ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የቶምቦላው ሎተሪ ላይ አንደኛው እኔ ገንዘብ የለኝም ይልና አንደኛው አንዷን ሎተሪ ለጋራ ይቆርጣትና ስማቸውን ይፅፋል፡፡ ሎተሪው በሚወጣበት ጊዜ አቶ ሰለሞን እንደደረሠው ሲያውቅ፣ ሌላ ሎተሪ ያወጣና “እስቲ ይሄን ቁጥር እይ” ይለዋል፡፡ ጓደኝየው እንዳልወጣ ያይና ይጥለዋል፡፡ በኋላ አቶ ሠለሞን በሚዲያ መሸለሙን ጓደኛው ሲያይ፣ የሽልማት መኪናውን በፍርድ ቤት ያሳግደዋል፡፡ ብሩን ግን ሰለሞን ቀድሞ ወስዷል፡፡ አሁን ጉዳያቸውን በቤተሠብ ዳኝነት ይዘው ለመካፈል ተስማምተዋል፡፡
ከግለሰቦች መተማመን ጋር በተያያዘስ የሚያወጉን ገጠመኞች ይኖራሉ?
በጣም የሚገርም ዕምነትም ይታያል፡፡ በ2003 ወንዶ ገነት አቅራቢያ ቡሳ የምትባል ቦታ ላይ አቶ መዝገበ ገ/ህይወት የተባለ ጠጅ ነጋዴ፣ ሎተሪ እንደደረሠኝ እይልኝ ብሎ ጠጅ ቀጂውን ይልካል። ጠጅ ቀጂው የእድለኞችን ዝርዝር አይቶ አንድ ሚሊዮን ብር ደርሶሃል ብሎ አምጥቶ ሰጥቶታል። ከሁለት ዓመት በፊት እሸቱ ሀሠን የተባለ የደሴ ነዋሪ የሚስቱ ወንድም ታመው መቀሌ ሊጠይቃቸው ይሄዳል፡፡ ሰውየውም ለራሳቸውና ሊጠይቃቸው ለመጣው የእህታቸው ባል ቶምቦላ ሎተሪ ገዝተው፣ ስም ይፅፉና ”ከደረሰህ አሳውቅሃለሁ” ይሉታል። እንዳጋጣሚ ቶምቦላው የተገዛለት ግለሰብ መኪና ይደርሰዋል፡፡ ሰውየው ደውለው “መኪናው በአንተ ስም ደርሷል፤ ና ውሰድ” ብለው ሰጥተውታል። በቅርቡ ፈጠነ ዋቅጅራ እና ግርማቸው ሳህሉ የሚባሉ ጓደኛሞች ድራፍት እየጠጡ የቢንጎ ሎተሪ ይገዛሉ፡፡ አንደኛው ቢፍቀውም ሌላኛው ግን ወሬ ይዞ ሳይፍቀው ይቀራል፡፡ በኋላም አንተ ጋ ይሁን ብሎ ለጓደኛው ይሰጠዋል፡፡ እየተጫወቱ ከቆዩ በኋላ ይለያያሉ፡፡ ጓደኛው፤ ቤት ሄዶ ቢንጐውን ሲፍቀው 150ሺ ብር ደርሶታል፡፡ ደውሎ 150ሺ ብር እንደደረሰው ነገረው፡፡
መቼም አስገራሚ ታሪክ ያላቸው ባለዕድለኞችም አይጠፉም …
በ2003 ተስፋዬ ዋዴዬ የተባለ ግለሰብ ሚስቱ ወተት እንዲገዛላት 10 ብር ትሰጠዋለች፡፡ ወተቱን ሊገዛ ሲወጣ ግን ሎተሪ ሻጭ ያገኝና ከብዙ ማቅማማት በኋላ በገንዘቡ ቶምቦላ ይገዛበታል፡፡ ቤት ሲመለስ ከሚስቱ ጋር ቀውጢ ሆነ፡፡ ተጣሉ፡፡ ሎተሪው ግን የጭነት መኪናና የመቶ ሰማኒያ ሺህ ብር እድለኛ አደረጋቸው፡፡ አንዲት ሴት ደግሞ በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በኩል ወደ ገበያ ሲሄዱ፣ አንዲት ሎተሪ ሻጭ “መደበኛ ሎተሪ፤ መደበኛ ሎተሪ” እያለች ትወተውታቸዋለች። እሳቸው ግን ብር የለኝም ብለው ሳይገዟት ያልፋሉ። ከገበያ ሲመለሱ አንድ ብር ተርፋቸው ነበር፡፡ አዟሪዋ አሁንም “መደበኛ ሎተሪ” ትላለች። በብሯ ሎተሪውን ገዟትና የመቶ ሀምሳ ሺህ ብር ባለ ዕድል ሊሆኑ ቻሉ፡፡
አንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪና ነጋዴ ደግሞ በ1986 ለጦር ጉዳተኞች ተብሎ የተዘጋጀ ሎተሪ ይቆርጣሉ፡፡ ነገር ግን ዕጣው መድረስ አለመድረሱን ሳያዩ ይዘነጉታል፡፡ ትዝ ያላቸው አንድ ቀን ለግል ጉዳያቸው አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ ነበር፡፡ አንድ ምግብ ቤት ምሳ በልተው ሂሳብ ሲከፍሉ፣ ሎተሪ ሻጭ ያዩና ማውጫ ይጠይቃሉ፡፡ የሁለት መቶ ሺህ ብር እና የአምስት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ዕድለኛ ነበሩ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ዕጣው የስድስት ወር ጊዜው ሊጠናቀቅ የቀረው ግማሽ ቀን ብቻ ነበር። መስሪያ ቤታችን የዛኑ ቀን ሚዲያውን ጠርቶ ተራሩጦ ነው ሽልማታቸውን የሰጣቸው፡፡
በቅርቡም ስምኦን ስዩም የሚባል ባሌ ጊኒር ውስጥ የሚሰራ ግለሰብ ከስራው ጋር በተያያዘ በሰራው ወንጀል ይታሰራል፡፡ ሁለት አመት ይታሰርና በተፈታ በሁለተኛው ቀን የዕንቁጣጣሽ ሎተሪ ይገዛል፡፡ እሱም ይረሳዋል፡፡ የስድስት ወሩ ገደብ ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ቀን ሲቀረው ትዝ ብሎት ማውጫ በማየቱ፣ የዘጠኝ መቶ ሺ ብር ዕድለኛ ሆኖ ገንዘቡን ወስዷል፡፡ ወጣት አየነው አሰፋ ደግሞ የአስራ ዘጠኝ አመት ወጣት ሲሆን ሰሜን ሆቴል አካባቢ ብርጭቆ አጣቢ ነው፡፡ ሰባት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር ደርሶት ሊወስድ እኛ ጋ ይመጣል፡፡ እጣውን ማሸነፉን በተመለከተ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ግን 750ሺ ብር ማለት አልቻለም፡፡ በተደጋጋሚ ሰባት ሺህ ብር ነበር የሚለው፡፡ ወንድሙ ወዳጄ የሰበታ ነዋሪ ሲሆን ገቢው አርባ ብር ነበር፡፡ በገዛው የገና ስጦታ ሎተሪ 1ሚ. ብር ይደርሰዋል፡፡ ገንዘቡን ሊቀበል የመጣው ከአሰሪው ጋር ነበር፡፡ ባለ ዕድሉ መናገር ሁሉ አቅቶት ነበር፡፡ ሊሸለም ሲሄድ የተነፈሰውን አተነፋፈስ ዕድሜ ልኬን አልረሳውም፡፡ ሁለት የባንክ ሠራተኞች በጋራ አንድ ትኬት ይገዙና አንዱ ቁጥሩን ፅፎ ይይዛል፡፡ ሌላው ትኬቱን ያስቀራል። ቁጥሩን ይዞ የሄደው የገልባጭ መኪና አሸናፊ መሆናቸውን አረጋገጠ፡፡ ሰኞ ስራ ሲገናኙ ሎተሪ እንደደረሳቸው ሲነግረው፣ ትኬቱን ቅዳሜ ዕለት የጠጣበት ቤት ቀዳዶ እንደጣለው ይነግረዋል፡፡ ተያይዘው ወደ ቡና ቤቱ ሲሄዱ ቤቱን ጠርገው ቆሻሻውን ወንዝ ዳር እንደጣሉት ይነግሯቸዋል። ቆሻሻው የተጣለበት ወንዝ ሲሄዱ የሎተሪ ቁርጥራጮች ተንሳፈዋል፡፡ እንደምንም አውጥተው ሲያዩት አንዷ ቅዳጅ ሙሉውን ቁጥር በፊደል ይዛለች፤ በአሀዝ ግን አንድ ቁጥር ይጎድላል፡፡ ነገር ግን ተሸልመዋል፡፡
አሸናፊ ዕጣ ደርሷቸው ያልወሰዱ ግለሰቦችስ? ቁጥራቸው ይታወቃል?
ለሀምሳኛ አመት በዓል ባዘጋጀነው የአምስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ሁለቱ ዕድለኞች አልመጡም። ከአራቱ ትኬቶች አንዱ ባለ ዕድል ጎዳና ላይና ሰው በር ላይ እያደረ በሊስትሮነትና በታክሲ ረዳትነት የሚሰራ ልጅ ነበር፡፡ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው የደረሠው፡፡ እሱ በአስራ አምስት ቀኑ መጥቶ ሲወስድ፣ በአራተኛው ወር ደግሞ አቶ አማኑኤል ስብሀቱ የተባሉ ዕድለኛ መጡ፡፡ እሳቸው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ባለ ዕድል ነበሩ። እኚህን ባለ ዕድል “ፎቶ እናንሳዎት” ስንላቸው “አይሆንም ሀኪም ከልክሎኛል” አሉ፡፡ ልብሳቸውን ገለጥ አድርገው ሲያሳዩን የልብ ትርታ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ተደግኗል። ያልመጡት ባለ ዕድሎች ግን ቀልጦ ቀረ ማለት ነው። በ1999 ቶምቦላ ሎተሪ ገዝታ የሶስት መቶ ካሬ ሜትር ቦታና የሁለት መቶ ሺህ ብር እድለኛ የነበረችው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር ሰራተኛ፣ ዕጣው ሰባት ወር ካለፈው በኋላ በመምጣቷ እጣው ከስሮ ቀርቷል። እንደዚህ አይነት አጋጣሚ አልፎ አልፎ አለ፡፡ አንዳንዶች መቁረጥ ይወዳሉ፤ ዕጣውን ግን አያዩትም፡፡
ከባለ ዕድለኞቹ በሀብት የሚታወቁ ወይም ዝነኛ ሠዎች አሉ?
አፄ ሀይለስላሴ የመኪና ባለዕድል ነበሩ፡፡ እሉን መልሰው ሸልመዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ዕድለኛ የነበሩት የፋብሪካ ባለቤት ናቸው፡፡ አርቲስት ሀረገወይን አሠፋም የአምስት መቶ ሺህ ብር ባለዕድል ናት፡፡
በተደጋጋሚ ሎተሪ የሚደርሳቸውስ…
ትልቁ ተደጋጋሚ እድለኛ የጎንደር ነዋሪ ናቸው፡፡ መሀመድ አብደላ ይባላሉ፡፡ አስራ አምስት ጊዜ ዕድለኛ ሆነዋል፡፡ ጉራጌ አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ሸዋንግዛው ደግሞ ስድስት ጊዜ ባለዕድል ሆነዋል። ሁለት ጊዜ ሀምሳ ሺህ ብር፣ ሶስት መቶ ሺህ ብርና ሁለት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ፣ መቶ ሺህ ብር፣ አምስት መቶ ብርና፣ ሬዲዮ ደርሷቸዋል፡፡ ወጣት ዳንኤል መሀሪ ወልዲያ ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ ሲሆን መስከረም 5 ቀን 2001 በቢንጎ ሎተሪ 20ሺህ ብር ደረሠው፡፡ ጥቅምት ላይ በመደበኛ ሎተሪ ሰባ አምስት ሺህ ብር ወሰደ፡፡ በደርግ ዘመን አቶ ዘውዱ አስፋው የጎንደር ከተማ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ነበሩ፡፡ በዝሆን ሎተሪ መቶ ሺህ ብር ደርሷቸው በአስራ አምስተኛው ቀን በመደበኛ ሎተሪ የሀምሳ ሺህ ብር ዕድለኛ ሆነዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ንጋቱ ተክለ ዮሀንስ፤ በ902 መደበኛ ሎተሪ ሀያ አምስት ሺህ ብር ከደረሳቸው በኋላ፣ በሚቀጥለው ሎተሪ በድጋሚ የሀያ አምስት ሺህ ብር ዕድለኛ ሆነዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ጥላሁን የቀጨኔ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ በ1971 በመደበኛ ዕጣ አስራ ሁለት ሺህ ብር፣ በድጋሚ በዚሁ መደበኛ ዕጣ ሰባ ሰባት ሺህ ብር አግኝተዋል፡፡ አቶ አሠፋ ቁጥሶ፤ አመዴ ገበያ ጫማ ቤት አላቸው፡፡ ከሎተሪ ተነስተው ነው እዛ የደረሱት። በ279 መደበኛ ሎተሪ ሀያ አምስት ሺህ ብር፣ በ1974 በሶስት ትኬት ስድስት ሺህ ብር አሸናፊ ሆነዋል፡፡ አቶ ካሳ ያደቴ የተባሉ ዕድለኛ ደግሞ በሚሊኒየም ሎተሪ ከአራት ትኬት አርባ ሺህ ብር ዕድለኛ ሲሆኑ ከሀያ አመት በፊት የሀምሳ ሺህ ብር ባለ ዕድል ነበሩ፡፡ አቶ ዘውዱ ተሰማ የፒያሳ አካባቢ ነዋሪና ጠበቃ ናቸው። በመደበኛ ሎተሪ የሀያ ሺ፣ ስምንት ሺ፣ አንድ ሺ፣ ስምንት ሺ እና ከዝሆን ሎተሪ የሶስት ሺ ብር ዕድለኛ ናቸው፡፡ የጎንደር ቆላድባ ወረዳ ነዋሪ በቅርቡ ደግሞ አቶ እርዚቅ ፍሬው የካቲት ውስጥ በዝሆን ሎተሪ የሁለት ሚሊዮን ብር አሸናፊ ሆነው፣ በሚያዝያ ወር ላይ የስምንት መቶ ሺህ ብር ባለእድል ሆነዋል፡፡
አሁን የድርጅቱ የሠራተኛ ብዛት ስንት ነው? ቅርንጫፎቹስ?
አሁን ስምንት መቶ ሠራተኞች እና ሀምሳ ቅርንጫፎች አሉ፡፡ የወኪሎች ብዛት ከሰማኒያ በላይ ደርሷል፡፡
ዕጣውስ?
ሲጀመር ሀምሳ ሺህ የነበረው የመደበኛ ዕጣ ሽልማት አራት ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በፊት መደበኛ ሎተሪ ብቻ ነበር የሚዘጋጀው፡፡ አሁን አስራ ስድስት የሎተሪ አይነቶች አሉ፡፡
የአስተዳደሩ ሰራተኞች ሎተሪ አሸንፈው ያውቃሉ?
አሁን ጡረታ የወጣ ሠራተኛ አስራ ሁለት ሺህ ብር ደርሶት ነበር፡፡ ደብረብርሀን ቅርንጫፍ ደግሞ የድርጅቱ ዘብ ስልሳ ሺህ ብር ደርሶታል፡፡ በጣም ትንንሽ ብር የሚያስገኙ ዕጣዎችም የደረሳቸው አሉ። በመቁረጥ ካየሽው ግን ሠራተኛው የሎተሪ ቆራጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ማስታወቂያ በየጊዜው ስለሚሰማና ዕድለኞችን ስለሚያይ ነው፡፡
የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ሎተሪ የመቁረጥ ልምድ እንዳለው ጥናት አድርጋችኋል?
ሁሉም የህብረተሠብ ክፍሎች የሎተሪ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የዕድለኞቹ ስብጥር ያንን ያሳያል። በአኗኗር ካየነው አርብቶ አደር አካባቢዎች የሎተሪ መጫወት ባህል ዝቅተኛ ነው፡፡
እስቲ ስለ አስተዳደሩ ማህበራዊ ተሳትፎ ይንገሩኝ … ምን ምን ጉዳዮች ላይ ተሳትፏል?
ብሄራዊ ሎተሪ ላለፉት ሀምሳ ሁለት አመታት በአገሪቱ በተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ላይ ተሳትፏል። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የፊደል ሠራዊት በሚል መሀይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተካሄደው ዘመቻ አስተማሪዎችን በማስተማር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ወወክማና ቼሻየር ሲቋቋሙ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከህንፃው ማሰሪያ ሩቡ የተሸፈነው በብሄራዊ ሎተሪ ድርጅት ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋምም ብሄራዊ ሎተሪ ዋና የገንዘብ አስተዋፅኦ ካደረጉት አንዱ ነበር፡፡ በአገሪቷ የመኪና መሪ ከቀኝ ወደ ግራ ሲለወጥ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ለድርቅና ለጎርፍ ተጐጂዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡ በ1968 ዓ.ም ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ከሜክሲኮ ኦሎምፒክ ጀምሮ እስከ ባርሴሎና ድረስ ከአትሌቲክስ ጐን አልተለየም፡፡ ሯጮች ወደ ኦሎምፒክ ሲሄዱ ሙሉ ሱፍ ልብስ በማልበስና ወጪያቸውን በመቻል ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ የአክሱም ሀውልት በልዩ ሎተሪ ገንዘብ አሰባስቧል፡፡ የልብ የህክምና ማዕከል ሲሰራ ሎተሪ አዘጋጅቶ ግንባታውን አግዟል፡፡ በባርሴሎና እነ ደራርቱ አሸንፈው ሲመጡ ያጌጡ መኪኖችን በማዘጋጀት ተቀብሏል፡፡ ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ተያይዞ ብዙ ሠርቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሙዚየም ሲከፈትም አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
በዓለም ላይ የሎተሪ አጀማመር ታሪክ ምን ይመስላል?
አንዳንድ ሠዎች ሎተሪ የተጀመረው በቻይና ነው ሲሉ፤ ሌሎች ጣሊያን ይላሉ፡፡ ሎተሪ የሚለው ቃል ሎቶ ከሚለው የጣልያን ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ሠውና መልካም አጋጣሚ ማለት ነው። የተለያዩ የሎተሪ ጨዋታዎች በጥንታዊት ቻይና እንደነበር ቢታወቅም የመጀመሪያው ሎተሪ በጣሊያን የሮም ግዛት በሆነችው ፍሎረንስ ከተማ መጀመሩ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
በመላው አለም ሎተሪ የህብረተሰቡን መሠረታዊ ጉዳዮች በመደገፍ የህብረተሰቡን ድንገተኛ አደጋዎች በመከላከል ላይ ሲሳተፍ ነው የኖረው፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ይሠራል፡፡ የረሀብ፣ የእሳት አደጋና ጎርፍ ችግሮችን ለማቃለል እንዲሁም የተለያዩ በሽታዎች ሲከሰቱ ለመከላከል፣ መድሀኒት በመግዛት ማህበራዊ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃል። ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ፍርድ ቤት ግንባታ፣ ለህፃናት ማሳደጊያዎች አስተዋፅኦ አድርጓል። በአዲስ አበባ የንፁህ ውሀ ችግር ለማቃለል የመጀመሪያ ፕሮጀክት የተሠራው በሎተሪ በተገኘ ገንዘብ ነው፡፡
የውጭ አገር ዜጐች ሎተሪ ቆርጠው ቢደርሳቸው ይሰጣቸዋል? ህጉ ምን ይላል?
የሎተሪ እድል ከኢትዮጵያውያን ውጪ ሲሆን የተለየ ነገር አለው፡፡ የአስተዳደሩ የማቋቋሚያ አዋጅ ሎተሪ የሚሸጠው በአገሪቷ ግዛት እንደሆነ ይደነግጋል። ስለዚህ ከዛ ግዛት ውጪ የብሄራዊ ሎተሪ ስራ የለም፡፡ በዛ ግዛት ስር ተጫውተው አሸናፊ የሆኑ ግለሰቦች በሙሉ የአሸናፊነት ቁጥራቸውን ይዘው ከመጡ ሽልማታቸው ይሠጣቸዋል፡፡ ከመጀመሪያዎቹ አምስት ዕድሎች መካከል ሁለቱ በኤርትራ ነዋሪ ለነበሩ ጣሊያኖች ደርሷል፡፡ አንድ ፈረንሳዊም የሚፋቀውን ሎተሪ ተጫውቶ አምስት ሺህ ብር ደርሶት ተቀብሏል። የብሄራዊ ሎተሪ ከድንበር ከወጣ ምንዛሬ ይዞ እንደወጣ ይቆጠራል፡፡ ብሩን ቢቀበልም ይዞ መውጣቱ በሌላ ህግ ይታገዳል፡፡

 

Read 18193 times