Print this page
Saturday, 07 September 2013 10:57

ካልዲስ ኮፊ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በ30ሚ ብር የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከፈተ
በ200ሺ ብር ጀምሮ 11 ሚሊዮን ብር ደርሷል
አንድም ካፌ ፍራንቻይዝ አልተደረገም
በቅርቡ የታሸገ ወተት ለገበያ ያቀርባል
17 ቅርንጫፎችና 1,200 ሠራተኞች አሉት
ቦሌና ዙሪያውን አራት ቦታ፣ 22 አካባቢ ትራፊክ ጽ/ቤትን ተሻግሮና ሳይሻገሩ፤ መገናኛ፣ በቅሎ ቤት (ላንቻ)፣ ሳር ቤት፣ ሜክሲኮ፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ፣ ፊላሚንጐ፣ ጉርድ ሾላ፣ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት አካባቢ ኢ.ኢ ኤ፣ ብትሄዱ፣ አንድ የሚያጋጥማችሁ ካፌ አለ - ካልዲስ ኮፊ፡፡
አቤት! ጊዜው እንዴት ይሮጣል! ካልዲስ ኮፊ “ሀ” ብሎ ሥራ የጀመረው የዛሬ 10 ዓመት ነው -በ1995 ዓ.ም፡፡ የመጀመሪያው ካፌ ከኤድናሞል ፊት ለፊት ባለው አደባባይ አጠገብ የተከፈተው ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በወ/ሮ ፀደይ አሥራትና በካፒቴን ዳንኤል ከተማ ካልዲስ ኮፊ ኃ.የተ.የግማ (ፒ ኤል ሲ) ሆኖ የተቋቋመው በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡
አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ለ10 ዓመት ወይም ከዚያም በላይ ባሉበት ይቆያሉ። አንዳንዶቹ ሁለትና ሦስት ሊያደርሱት ይችላሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከዚያም በላይ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ የካልዲስ ግን የሚገርም ሆነብኝ፡፡ በብዙዎቹ የመዲናዋ አካባቢዎች ካልዲስ ካፌን መመልከት የተለመደ ሆኗል።
የስኬቱ ምክንያት ምንድነው በማለት ባለቤቴን ማነጋገር ፈለግሁና ወደ ካልዲስ ካፌ ጽ/ቤት ሄጄ ለምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ለአቶ ተስፋዬ ደገፉ የመጣሁበትን ምክንያት ነገርኳቸው፡፡
እሳቸውም ምክንያቴን ካዳመጡ በኋላ፣ ባለቤቶቹን ማግኘት እንደማልችል፣ የምፈልገውን መረጃ ከእሳቸው ማግኘት እንደምችል ነግረውኝ አጭር ቀጠሮ ሰጡኝ። በቀጠሮዬ ቀን ስንገናኝ አቶ ተስፋዬን ካልዲስ ስንት ቅርንጫፎች አሉት በማለት ቃለምልልሴን ጀመርኩ፡፡

 

አሁን 17 ቅርንጫፎች አሉን፡፡ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር 18ኛውን ቅርንጫፋችንን እንከፍታለን፡፡
የት?
ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ በአትሌት ብርሃኔ አደሬ ሕንፃ ላይ ይከፈታል፡፡
የካልዲስ ካፌ የስኬት ምስጢር ምንድነው?
ድርጅታችን በከተማችን ውስጥ በተመሳሳይ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ እያደገ ያለ ኩባንያ ነው፡፡ ለዕድገቱ ዋናው መሠረት፣ ሠራተኛው ለሥራ ያለው ጠንካራ ዲሲፕሊን፣ የሥራ አመራር አካሉ በወጣቶች የተገነባ መሆን፣ ሁልጊዜ ለለውጥና ለጥራት በጋራ የሚሠራ የሥራ አመራር ጥረትና ውጤት ነው ለዚህ ያበቃን፡፡
ድርጅታችን ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በፈጣን ዕድገት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለድርጅታችን ግብዓት የሚሆኑትን ወተትና ዕንቁላል የመሳሰሉትን ምርቶችን ለማምረት አንዳንድ ጥረቶች ጀምሯል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በሱልልታ ከተማ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት አድርጐ የወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቋቁሞ፣ ለራሱ የሚያስፈልገውን የወተትና የእርጐ ምርት ከተጠቀመ በኋላ፣ የተረፈውን ገበያ ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ፋብሪካ ለጊዜው ከ35 በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያውን ሥራ ከጨረስን በኋላ፣ ለድርጅቱ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን የማምረት ዕቅድ አለው። ያኔ የሠራተኛው ቁጥር ይጨምራል፡፡
በማቀነባበሪያው ምን ምን ታመርታላችሁ?
እስካሁን ድረስ ቅቤ፣ አይብና ፓስቸራይዝድ ወተት ለራሳችን ነው የምናቀርበው፡፡ አሁን ግን ፍላጐቱ (ዲማንዱ) ከፍተኛ ስለሆነ ገበያ ውስጥ በስፋት ለመግባት እቅድ አለን፡፡
ወተቱን ከየት ነው የምታገኙት? የራሳችሁ ላሞች አሏችሁ እንዴ?
እኛ ላሞች የሉንም፡፡ ወተቱን የምናገኘው ከአካባቢው ገበሬ አሰባስበን ነው፡፡
ለካፌዎቻችሁ በቀን ምን ያህል ወተት እንቁላል፣ ስኳር… ትጠቀማላችሁ?
ለትኩስ መጠጦችና ለኬክ ሥራ በቀን በአማካይ ከ1,200 ሊትር በላይ ወተት እንጠቀማለን፡፡ እንቁላል ለፋስት ፉድና ለኬክም ግብአት ስለሆነ በቀን በአማካይ ከ15 ሺህ በላይ እንጠቀማለን። አሁን እንቁላል የምናገኘው ከኤልፎራ ነው፡፡ ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያው ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ፣ የራሳችንን የእንቁላል ምርት ለማቅረብ አቅደናል፡፡ ቦታውም ተዘጋጅቷል፤ የሚቀረን ወደ ሥራ መግባቱ ነው፡፡ ስኳር በቀን ከሦስት ኩንታል በላይ እንጠቀማለን፡፡ ወደፊት የካፌዎቹ ቁጥር ሲጨምር የምንጠቀማቸው ግብአቶችም ይጨምራል፡፡
ካልዲስ ፍራንቻይዝ አድርጐ (ስሙን ሽጦ) ሸጧል፡፡ አንዳንድ ካፌዎች የእሱ አይደሉም ይባላል። ይኼ ምን ያህል እውነት ነው?
ውሸት ነው፡፡ ካልዲስ ኮፊ በአሁኑ ወቅት አንድም ቅርንጫፍ ፍራንቻይዝ አላደረገም፡፡ ማኔጅመንቱም፣ ሀብቱም በራሱ ነው፡፡ ፍራንቻይዝ እንድናደርግ ከአገር ውስጥም ከውጪም ለምሳሌ፣ ከቻይና ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦልናል፡፡ ድርጅታችን አሁን ባለበት ሁኔታ ራሱን ለማስተዳደር፣ በፋይናንስም ሆነ በማኔጅመንት በቂ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ፍራንቻይዝ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡
እቅዳችሁ ስንት ካፌ መድረስ ነው? ካልዲስ ዋጋው ውድ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ምን ይላሉ?
የእኛ ዋጋ ውድ አይደለም፡፡ አንዳንድ ማቴሪያሎች ለምሳሌ አይስክሬም ከውጭ ነው የምናስመጣው፡፡ በከተማችን ያሉ አንዳንድ ካፌዎች ማኪያቶና ቡና በ10 ብር ነው የሚሸጡት፡፡ እኛም በ10 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ ስለዚህ ውድ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ከምንሰጠው አቅርቦት ጋር ሲተያይ ሚዛናዊ (ፌየር) ነው፡፡
ዕቅዳችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 40 ካልዲስ ካፌዎች መክፈት ነው፡፡ ዕቅዳችንን ካሳካን በኋላ ከአዲስ አበባ ከተማ መውጣት ነው ሃሳባችን፡፡ ይህንንም የምናደርገው ወደ ክልል ከተሞች ወጥተን ቅርንጫፍ ካፌዎች ለመክፈትና ለመምራት ጠንካራ የፋይናንሻልና የማኔጅመንት አቅም አለን ወይ? ብለን ጠይቀን ስናምንበት ነው፡፡
ካልዲስ ሲመሠረት ካፒታሉ ምን ያህል ነበር? አሁንስ?
ካልዲስ ሲመሠረት ካፒታሉ 200ሺህ ብር ነበር። አሁን ከ10 ዓመት በኋላ፣ ለእህት ኩባንያዎች (ሱሉልታ ላይ የተገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ለእንቁላል ማምረቻ) የወጣውን ሳይጨምር ካፒታላችን በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በቀረጥና በታክስ በዓመት ምን ያህል ብር ለመንግሥት ታስገባላችሁ?
በታክስ፤ በቀረጥና በመሳሰሉት በዓመት ወደ መንግሥት ካዝና 12 ሚሊዮን ብር ፈሰስ በማድረግ ኢኮኖሚውን እንደግፋለን፡፡
አንድ ካልዲስ ካፌ ለመክፈት ስንት ብር ያስፈጋል?
በከተማው ውስጥ የቤት ኪራይ በጣም ውድ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቢያንስ የ6 ወር ኪራይ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ ይህንን ሳይጨምር የካፌዎቻችን ዕቃዎች (ጠረጴዛና ወንበር) ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የውስጥ ዕቃዎችን ለማሟላትና አስውቦ (ዲኮር አድርጐ) አንድ ካፌ ለመክፈት ቢያንስ 200ሺህ ብር ይጠይቃል፡፡
ካልዲስ ስንት ሠራተኞች አሉት?
በሁሉም ካፌዎች የሚሠሩ 1,200 ሠራተኞች አሉን፡፡
ሁሉም ካፌዎች አንድ ዓይነት ዕቃ በመግዛት ተመሳሳይ መልክ እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። የሰው ልጅ ግን አንድ ዓይነት ባህርይ አይኖረውም። እንዴት ነው ታዲያ ሠራተኞቻችሁ በሁሉም ካፌ ተመሳሳይ መስተንግዶ እንዲሰጡ የምታደርጉት?
በሥልጠና ነው፡፡ የራሳችን የሆነ የሥልጠና ማዕከል አለን፡፡ ሠራተኞቻችንን ቀጥረን ወደ ሥራ ከማሰማራታችን በፊት ወደማሠልጠኛው ገብተው የንድፈ ሐሳብ (የቲዎሪ) ትምህርት እንዲቀስሙና የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ድርጅቱ የራሱ መመዘኛ ስላለው፣ ያንን መለክያ ያለፉትን ብቻ ቀጥሮ ወደሥራ ያስገባቸዋል። ከዚህም በተማሪ በሁሉም ዘርፍ ለተሰማሩ ሠራተኞች በመስተንግዶ፣ በቁጥጥር፣ በምርት ሥራ ላይ የተሰማሩትን በየጊዜው የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት ክህሎታቸውን እናዳብራለን፡፡ ቁጥጥር በማድረግ፣ ጉድለት ለሚታይባቸው ሠራተኞች ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሠራተኞቻችን ተመሳሳይ መስተንግዶ የሚሰጡት ከአንድ የሥልጠና ማዕከል ስለሚወጡ ነው፡፡
ሥልጠናውን የሚሰጠው ማነው?
ሥልጠናው የሚሰጠው በተለያዩ የኦፕሬሽን ክፍሎች ነው፡፡ ከኦፕሬሽን ክፍሉ ሥራዎች አንዱ በየቅርንጫፉ እየተዘዋወረ ቁጥጥር ማድረግ ነው። ቁጥጥር አድርጐ ጉድለት ሲገኝ ወዲያውኑ እንዲታረም ያደርጋል፤ የሠራተኞችንም የሥራ አፈጻጸም ይገመግማል፡፡ ዕድገት የሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች ካሉ ዕድገት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ድክመት ያለባቸው ሠራተኞችም ካሉ ሥልጠና አግኝተው ከሌሎች ጋር የተስተካከለ መስተንግዶ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
ታታሪ ሠራተኛ ያድጋል ብለዋል፡፡ እንዴት ነው የሚያድገው?
በካልዲስ የዕድገት በሩ ክፍት ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ አንድ ሠራተኛ በተመደበበት ስፍራ ብቃት ካለው፣ ድርጅቱ በሚፈልገው መንገድ ኃላፊነቱን የሚወጣ ከሆነ ዕድገት ያኛል፡፡ ለምሳሌ ከመስተንግዶ ላይ ተነስተው የአመራር አባል በመሆን ከፍተኛ ዲፓርትመንቶችን የሚመሩ ሠራተኞች አሉ። እነዚያን ሠራተኞች፣ ምንም ሙያ ሳይኖራቸው ተቀብለን አሠልጥነን በየጊዜው ክትትል በማድረግ ነው ለዚህ ያበቃናቸው፡፡ በሩ ክፍት ነው ስል፣ ብቃት ያለው፣ የድርጅቱ አሠራር ሲስተም የገባቸውና ጥረት የሚያደርጉትን ማለቴ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በትላልቅ ድርጅቶች (በባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ሁሉ) ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ አይስማሙም፡፡ ያለመግባባት እየተፈጠረ ፍ/ቤት የሚቆሙበት ጊዜም አለ፡፡ እናንተስ? በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት (መግባባት) ምን ይመስላል?
እንደሚታወቀው ለአንድ ድርጅት ትልቁና ዋነኛው ሀብት ሠራተኛው ነው፡፡ ቤቱን የቱንም ያህል በውበት ብናንቆጠቁጠው፣ ሠራተኞቹ ጥሩ ካልሆኑ ያ ሁሉ ድካም ሜዳ ላይ ነው የሚቀረው። ይህን ግምት ውስጥ ስለምናስገባ፣ ሠራተኞቻችንን እናሠለጥናለን፣ እናሳድጋቸዋለን፣ ለመሪነት ደረጃም እናበቃቸዋለን፤ ይህም ሠራተኞቹን ያተጋቸዋል። በተጨማሪም ድርጅቱ በዓመት ለሠራተኛው 6 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የተገኘው ውጤት ይገመገምና ድርጅቱ በማንኛውም ጊዜ የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዓመቱ መጨረሻም ገቢና ወጪው ተሰልቶ የተገኘው ውጤት ይመዘንና ለሠራተኞች ቦነስ እንሰጣለን፡፡ ድርጅቱ የተገኘውን ትርፍ ብቻውን አይበላም፡፡ ትርፉን ካስገኙለት ሠራተኞች ጋር ይካፈላል፡፡
ሌላው መተማመኛችን በማንኛውም ሰዓት አንድ ሠራተኛ ኃላፊዎች በድለውኛል ካለ ለበላይ አካል ቅሬታውን ለማቅረብ በሩ ክፍት ነው፡፡ ይኼ የምንኮራበት ሲስተማችን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ በደለኝ ካለ፣ ከእኔ በላይ ላለ ኃላፊ (አለቃ) ለዋና ሥራ አስኪያጇና ባለቤቷ ድረስ ቀርቦ ቅሬታውን የማቅረብ መብት አለው፡፡ ይኼ ነገር ሠራተኞቻችንን የሚያስደስታቸው ይመስለኛል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም (የካፌዎች) ኢንዱስትሪ እያደገ ነው ያለው፡፡
ካልዲስ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ለመሥራት ብቁ መሆናቸውን ስለሚያውቁ፣ እኛ ጋ መሥራቱን እንደማሠልጠኛ ተቋም ነው የሚቆጥሩት፡፡ እነዚህ ነገሮች ናቸው እንግዲህ በእኛና በሠራተኞቻችን መካከል ሰላም እንዲኖር የሚያደርጉት፡፡
40 ካፌዎች በአዲስ አበባ ከከፈታችሁ በኋላ ዕቅዳችሁ ምንድነው?
በአዲስ አበባ ከተማ 40 ካፌዎች ከከፈትን በኋላ ወደ አጐራባች ከተሞች እንወጣለን፡፡ ወደ ክልሎች የምንወጣው እዚህ 40 ካፌዎች ስለሞላን ብቻ ሳይሆን ለሥራችን ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን 50 በመቶ ራሳችን ማምረት ስንችል ነው፡፡ ከወተት የሚገኝ ብዙ ተዋጽኦ አለ፡፡ ቺዝ፣ ቅቤ፣ ክሬም፣… እነዚህ ለኬክ አስፈላጊ ግብአት ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ወደ እንቁላል ምርት (ፖልተሪ) እንገባለን፡፡
በመቀጠል ደግሞ አትክልቶችን ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተሟሉና በአዲስ አበባ 40 ካፌ ከሞላን በኋላ ወደ ክልል ለመውጣት ነው ዕቅዳችን፡፡ ፍራንቻይዝ የሚለውንም 40 ከሞላን በኋላ ቆሞ ብለን የምናየው ይሆናል፡፡ በመጨረሻም፤ አንባቢዎች ሥራ አስኪያጁን እንዲተዋወቁ አቶ ተስፋዬ ማናቸው? ትምህርትና የሥራ ልምዳቸውስ በማለት ጠየቅሁ፡፡
አቶ ተስፋዬ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ፣ ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ለ10 ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች በኦዲተርነትና በሂሳብ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡
በበደሌ ቢራ ፋብሪካ ለ8 ዓመታት ከአካውንታንት እስከ ፋይናንስ ሥራ አስኪያጅነት፣ በካልዲስ ለሁለት ዓመት በፋይናንስ ኃላፊነትና ለአራት ዓመት ድርጅቱን በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ነው፡፡
አቶ ተስፋዬ በካልዲስ ካፌ ኃ.የተ.የግል ማህበር ውስጥ ለ6 ዓመት ስለሰሩ በደንብ ያውቁታል፤ በአድናቆት የሚናገሩለትም ነገር አለ፡፡ “አንዱ፣ በትንሽ ካፒታል ጀምሮ ለ1,200 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ባለቤቶቹ በቅንነት የሚፈጽሟቸው ተግባራት ናቸው፡፡ አካለ ስንኩላንን፣ በሽተኞችን፤ ካንሰር ሶሳይቲን በገንዘብ ይረዳሉ፡፡
ጐበዝ ተማሪ ሆነው ችሎታው እያላቸው የሚረዳቸው በማጣት መማር የማይችሉትንም ይረዳሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ልጅ ከአምቦ አምጥተው እያስተማሩ ነው፡፡ ልጁ ከ1ኛ ክፍል እስከ 11ኛ ክፍል 1ኛ ነው የሚወጣው፡፡ እነዚህን ነገሮች አደንቅላቸዋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

Read 4134 times
Administrator

Latest from Administrator