Saturday, 07 September 2013 11:13

ከጋዜጣ አዟሪነት እስከ ፊልም አከፋፋይነት

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(1 Vote)

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለዚህ ስላበቃኝ ልዩ ትዝታ አለኝ
*እነፕሮፌሰር መስፍንና ፕሮፌሰር አስራት ደንበኞቼ ነበሩ
*የጋዜጣ አዟሪነት ሥራዬ አንባቢ እንድሆን አድርጎኛል

ከሊስትሮነት አንስቶ ሲዲ እስከማዞር ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ተስፋዬ ፈጠነ፤ ለበርካታ ዓመታት ጋዜጣ ሲያዟር እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ደንበኞቹ እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ጋዜጣ አዟሪነቱ አንባቢ እንዳደረገው የሚገልፀው ወጣቱ፤አሁን ወደ ፊልም አከፋፋይነት ገብቷል፡፡
የአማርኛ ፊልሞችን እየገዛም በዲቪዲ እያወጣ ይሸጣል፡፡ በቅርቡ የራሱን ፊልም ለማውጣት እየሰራ መሆኑን ከሚናገረው ወጣት ተስፋዬ ፈጠነ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

እስቲ ራስህን አስተዋውቅ----
ተስፋዬ ፈጠነ እባላለሁ፡፡ ፊልም አሳታሚ ነኝ፡፡ ከጐጃም ሙዚቃ ቤት ጋር ነው የምሰራው። የራሴን ድርጅትም ከፍቻለሁ፤ “ፒያሳ ዘ አራዳ ኢንተርቴይመንት” ይባላል፡፡ ሲኒማ የማሳተም ፍቃድ ነው ያወጣሁት፡፡ መሸጥ የሚፈልጉ ባለፊልሞች ሲኖሩ እየገዛሁ አሳያለሁ፡፡ ብዙ ፊልሞች እኔ ጋ ይመጣሉ፡፡ መርጬ ከእነሲኒማ ቤቱ መግዛት ካለብኝ ከእነሲኒማ ቤቱ እገዛለሁ፡፡ የሲኒማ ቤት ጊዜውን ጨርሶ የመጣውን ደግሞ በቪሲዲ ወይም ዲቪዲ አሳትማለሁ፡፡
“አዲስ አድማስ”ን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጦችን ታዞር ነበር፡፡ እስቲ ስለእሱ ንገረኝ…
ሥራዬን በፍቅር ነበር የምወደው፡፡ በ1985 ዓ.ም ነው ማዞር የጀመርኩት፡፡ እነ ጦቢያ፣ እነ ሪፖርተር ሲጀመሩ ትዝ ይለኛል፡፡ ሊስትሮ እየሰራሁ ጋዜጣ አዞር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አድማስ መጣ፡፡ እነ እንዳልክ ሲያከፋፍሉ፣ ፒያሳ አካባቢ እኔና አንድ ልጅ ነበርን ጋዜጣ የምናዞረው፡፡ ከቲሩም ፒያሳ እኔ፣ ኤንሪኮ እና ቶሞካ አካባቢ ደግሞ እንግዳው የሚባል ልጅ ያዞር ነበር፡፡
አራት ኪሎ እነ ጥላሁን ያዞሩ ነበር፡፡ አዲስ አድማስ ተመስርቶ እስከ አስረኛው እትም ድረስ እኔ ነበርኩ እየዞርኩ ማስታወቂያ እለጥፍ የነበረው። ትንሽ ቤት በ60 ብር ተከራይተን ማስታወቂያውን እያባዛን በየቦታው እንለጥፍ ነበር፡፡
አዲስ አድማስ ሲጀመር ገበያው እንዴት ነበር?
እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ሸጬ እጨርስ ነበር፡፡ አንባቢዎች የት የት እንደሚገኙ አውቃለሁ፡፡ አራት መቶና አምስት መቶ ጋዜጣ እሸጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነፃ ነኝ፡፡
ከሰዓት በኋላ ወደ ሊስትሮዬ እመጣለሁ። ጀብሎ እሰራለሁ፡፡ አዲስ አድማስን በተመለከተ ግንኙነቴ ከእንዳልክ ጋር ነበር፡፡ ጋዜጣው አለቀ ተብለን አዟሪዎች የምንጣላበት ጊዜ ነበር፡፡
የተለዩ አንባቢዎች ነበሩህ?
በጣም ታዋቂ ደንበኞች ነበሩኝ፡፡ ይረሱት ይሆናል እንጂ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ደንበኛዬ ነበሩ፡፡ ሟቹ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስም ደንበኛዬ ነበሩ፣ ሊሴ ጀርባ ወደነበረው ቢሮአቸው እወስድላቸው ነበር፡፡ ታላላቅ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ቶሞካ ይመጣሉ፡፡ ቶሞካ ጋዜጣ በጣም ይሸጣል፡፡ ፖሊስ ጋዜጣ የሚነጥቅበት ጊዜም ገጥሞናል፡፡ አሁን የተባረረ አንድ ፖሊስ ነጥቆኝ ያለቀስኩበት ጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡
በአራት ሰዓት ከ400 በላይ ጋዜጣ ሸጫለሁ ብለሃል፡፡ አልተጋነነም?
የተጋነነ አይደለም፡፡ በወቅቱ ሸጬአለሁ፡፡ ያኔ ብዙ አዟሪ አልነበረም፡፡ አሁን ሃምሳ ስልሳ አዟሪ ሊኖር ይችላል፡፡ አዟሪ ብዙ ቢሆን እኮ መቼም አንጨርስም፤ በዛ ላይ አምስት ስድስት አይነት ጋዜጦች በቀን ይወጣሉ፤ ከያንዳንዱ አርባ ሃምሳ ጋዜጣ ወስደን እንሸጥ ነበር፡፡ እንግዳው የተባለው አዟሪ ከኔ የበለጠ ጐበዝ ስለነበር በቀን ሰባት መቶ ጋዜጣ ሁሉ ሸጧል፡፡ ከአንድ ጋዜጣ ያኔ ትርፋችን 15 ሳንቲም እኮ ነው፡፡ አሁንም ድረስ “አዲስ ዘመን”ን በየመስርያ ቤቱ ለደንበኞች እሰጣለሁ፡፡
በጋዜጣ ማዞር ሥራህ ምን አተረፍክ?
አንባቢ ያደረገኝ ጋዜጣ መሸጤ ነው፡፡ ጋዜጣ አዟሪ ሁሉ የተቃዋሚ ደጋፊ የሚመስላቸው አሉ፡፡ እኔ ግን ጋዜጣ ማንበብ በጣም እወዳለሁ፡፡ በጋዜጣ አዟሪነቴ አንባቢ ሆኛለሁ፡፡ ማንበብ ስለሚወዱ ብቻ ጋዜጣ እያዞሩ ጋዜጠኛ ሆነው የተቀጠሩ የማውቃቸው ልጆች አሉ፡፡
በቀን 400 ጋዜጣ በምትሸጥ ጊዜ ስንት ብር ታገኝ ነበር?
120 ብር ያህል አገኛለሁ፡፡ ቀይወጥ ያኔ በሦስት ወይ በአራት ብር እንበላለን፡፡ በ1997 ዓ.ም በሸጥኩት ጋዜጣ ብቻ ቤት ገዝቻለሁ፡፡ ያኔ ሳር ቅጠሉ ጋዜጣ ይሸጥ ነበር፡፡ ስራው ብዙ ታዋቂ ሰዎች እና አሳታሚዎችም አስተዋውቆኛል፡፡
አዲስ ጋዜጣ እንዴት ነበር የምታለማምዱት?
ዋናው አርእስት ነው፡፡ የካርቱን ሥዕሎችም ድርሻ አላቸው፡፡ ርዕሱ የጮኸ ጋዜጣ በጣም ይሸጥ ነበር፡፡ እነ “ጦቢያ” በነበሩበት ጊዜ ጋዜጣ በጣም የሚሸጠው ሐሙስ ሐሙስ ነበር፡፡ አዲስ ጋዜጣ አርእስቱ ጐላ ብሎ ይውጣ እንጂ በጣም ነበር የሚሸጠው፡፡ ጋዜጣን የሚያሸጠው ርእስ እንጂ የጋዜጣው አዲስነት ወይም መቆየት አይደለም፡፡
ጋዜጣ አዟሪነቱን ለምንድነው የተውከው?
የሆነ ሰዓት ላይ አላዋጣኝም፡፡ አዟሪም በዛ። አንዳንዶቹ ጋዜጦችም ከህትመት ራቁ፡፡ ጊዜው የፍቅር መፅሔቶች ሆነ፡፡ መፅሔቱንም ሞክሬአለሁ ግን የሚበልጥብኝ ሥራ ሳገኝ ወደዚያ ዞርኩኝ፡፡
የኢንተርኔት መስፋፋት ለጋዜጣ ፈተና ሆኗል ብለህ ታስባለህ?
በጣም የሚገርመኝ ኢንተርኔት ላይ ያነበብነውን መፅሔት ላይ እናየዋለን፡፡ እንደ በፊቱ መረጃ ፈልፍሎ የሚሰራ ብዙ ጋዜጠኛ የለም፡፡ ቢሮ ቁጭ ብሎ ኢንተርኔቱን እየበረበረ ይፅፋል፡፡ እንደበፊቱ ሄዶ የችግሩን ስፋት አይቶ አይደለም የሚፅፈው። ዘመኑ ኢንተርኔት በመፅሔት እየሆነ መጣ፡፡ የኢንተርኔት መኖር በራሱ ችግር የለውም። ሕዝቡ የሚፈልገውን አለማወቅ እንጂ፡፡ አስበው… ጋዜጣ እየቀነሰ መፅሔት እየበዛ ነው፡፡ በዚህ መልኩ መፅሔት ለመስራት ቀላል ነው፤ ኮምፒዩተር ገዝተህ ብሮድባንድ ማስገጠም ነው፡፡
የጋዜጣ ደንበኞችህን እንዴት ነበር የምትይዘው?
ጧት በየቤታቸውና ቢሮአቸው እየወሰድኩ አድዬ፣ ከሰዓት ሂሳቡን ሰብስቤ ወደ ሊስትሮዬ እሄዳለሁ፡፡ አብዛኞቹ ሲከፍሉ መልሱን ያዘው ይሉኛል፡፡ ከዚያ ስመለስ ሲዲ አዞራለሁ፡፡ ቶሞካ ጋዜጣ ጧት እንደወጣ መግባት አለበት፡፡ አንድ ሰዓት ላይ ከሄድክ አይቀበሉህም፡፡ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ከወሰድኩ ግን ቁርስ ሁሉ ይገዛልኛል። ውባየሁና ባለቤቷ አቶ ዘውዱ ናቸው ባለቤቶቹ። ቢሮ ሳይገቡ በጠዋት በበር ሥር አኖርላቸዋለሁ፡፡ ቢሮ ሲከፍቱ ያገኙታል፡፡ ከዚያ በኋላ ዞሬ ሂሳቤን መሰብሰብ ነው።
ፊልም ማሳተምና ማከፋፈል የጀመርከው እንዴት ነው?
ፒያሳ ካሪቢያን በረንዳ ላይ እሰራ ነበር፡፡ አንድ የማውቀው ሰው ከውጭ አምጥቶልኝ የውጭ ሀገር ዘፈን ሲዲ ማዞር ጀመርኩ፡፡ በዚያው የአማርኛ ፊልም ጥያቄዎች በረከቱና እነሱንም ማዞር ያዝኩ። ጐጃም ሙዚቃ ቤት እየሄድኩ ተመላልሼ አወጣ ነበር፡፡ የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት ንፁህ አስቻለው እና ወንድሟ ገበያው አስቻለው ቅን ናቸው፡፡ እሷና ወንድሟ “እንዳንተ ካሴት የሚያዞሩት እኮ ፊልም እያሳተሙ ነው፤ ለምን አትሞክረውም፤ እኔ አከፋፍልልሀለሁ” አለችኝ፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ከደቡብ “ካያሞ” የሚል ቪሲዲ አውጥቼ ክልል ድረስ ሄጄ ሸጥኩኝ፡፡ አተረፈኝ። ከዚያ ከመቸርቸር ወደ ማሳተም ተሸጋገርኩ። በመቀጠል “ወይ አዲስ አበባ” የሚል ፊልም ገዛሁ። እንዲህ እንዲያ እያልኩ አሁን ፊልም በስፋት ማሳተም ጀምሬአለሁ፡፡
የትምህርት ደረጃህ እንዴት ነው ?
የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት የጋዜጣ ደንበኛዬ አባ ተክሌ፣ አንድ ቀን ጋዜጣ ሳደርስላቸው “ትማራለህ?” ሲሉ ጠየቁኝ “አልማርም፤ ከሰባተኛ ክፍል ነው ያቋረጥኩት” አልኳቸው፡፡ ከዚያ በካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት በነፃ እንድማር ፈቀዱልኝ፡፡ ትምህርቴን እዚያ ጨርሴ ነው ኤዲቲንግ የተማርኩት፡፡ የሴቶች ፀጉር ሥራም ተምሬአለሁ፡፡ አሁን እንግዲህ አስር ያህል ፊልሞች አሳትሜአለሁ፤ ገና ያልወጡም አሉ፡፡ “ኦ ያበሻ ሴት”፣ “ሌዲስ ፈርስት” “ሀረግ”፣ “ሜድ ኢን ቻይና”፣ “የዜግነት ክብር” እና ሌሎችን አሳትሜአለሁ፡፡
በተለያየ ምክንያት በተለይ በሕገወጥ ቅጂ የከሰሩትን ፊልሞች ጭምር ሃላፊነት ወስደህ አከፋፍለሃል ይባላል፡፡ እንዴት አላከሰረህም?
ስም ያላቸው ስለነበሩ ተሸጠዋል፡፡ ግን ስገባበትም አልፈራሁም፡፡ ሥራውን በጣም ነው የማውቀው፡፡ ፊልሞቹ የተሰረቁም እንኳ ቢሆኑ የመታየት አቅም እንደነበራቸው አውቃለሁ፡፡ እስካሁን ፊልሞች ለመግዛት የከፈልኩት ከፍተኛው 140 ሺህ ብር ሲሆን ዝቅተኛው ዘጠኝ ሺህ ብር ነው፡፡ የቅጂ መብት እንዲከበር የሕዝቡ ግንዛቤ መጨመር አለበት፡፡
በዚህ ረገድ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር ሃላፊዎች እነ ኃይላይ እና እቁባይ እንዲሁም ሌሎቹም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አሁን ደግሞ ሕገወጥ ቅጂ በሲዲ መሆኑ ቀርቶ በፍላሽ እና በሚሞሪ ሆኗል። ይኼን ለማስቀረት ብዙ ጥረት ያስፈልጋል፡፡
የሚሸጥና የማይሸጥ አልበም ዘፈኑን ሰምተህ እንድትለይ ያመጡልሃል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
በነገራችን ላይ ውሎዬ ከታዋቂው ሙዚቀኛ መስፍን ታምሬ ጋር ነው፡፡ እሱ ብዙ ነገር አስተምሮኛል፡፡ ዘፋኞች አስተያየት ለመጠየቅ ወደኔ ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱን አርቲስት “ፖስተር” አሳምር እንጂ ይሸጥልሃል ብዬው እንዳልኩት ተሸጦለታል፡፡ ሙዚቀኛ አይደለሁም፡፡ በሙዚቃው ቢዝነስ እንደመቆየቴ ግን በደንብ ታሽቻለሁ፡፡ “የትዝታ ትዝታ” ሲወጣ ይኼ ሲዲ ሁለት አመት ይነግሳል ብዬ ነበር፡፡ ሌላው ሲፈራ እኔ በርካታ ኮፒዎች ወስጄ ሸጫለሁ፡፡ ሲዲው አሁንም እየተሸጠ ነው፡፡
ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በግምገማ ብቁ አይደሉም ያላቸው ፊልሞች አንዳንዴ በዲቪዲ ይመጣሉ፡፡ እነዚህንስ ገዝተሃል?
በጭራሽ አልገዛም፡፡ መስፈርቴ ፊልሙ በዓለም ሲኒማ መታየቱ እና ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ብቁ ነው ማለቱ ነው … ብቃት የሌላቸው ፊልሞች አልገዛም። ዓለም ሲኒማ ቤት ካልታየ አልገዛም፡፡ ቢኒያም ወርቁ “ሰባተኛ ሰው” የተባለ ፊልሙን እምነት ጥሎብኝ ሸጫለሁ፤ በጣም አከብረዋለሁ፡፡ ይኼው ፊልም ወደ ዲቪዲ ሲመጣ ርእሱንና ፖስተሩን ለውጩ ነው ለገበያ ያበቃሁት፡፡ በጣም ሲሸጥ፣ ገረመኝ፡፡ አሜሪካ ውስጥ ያለ አከፋፋይም በጣም እንደተሸጠለት ነግሮኛል፡፡
የወደፊት እቅድህ ምንድነው?
ከታዋቂ ተዋንያን ጋር በመሆን ፊቸር ፊልም ለመስራት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ ቀረፃ በቅርቡ ይጀመራል፡፡ “ያንቺው ሌባ” የሚለውን ፊልም ደግሞ ሰሞኑን አወጣለሁ፡፡
በመጨረሻ የምትለው ነገር ካለ---
እዚህ ሥራ እንድገባ ለረዱኝ ለንፁህ፣ ለገበያው፣ ለመስፍን ታምሬና ለአስተማሪው አባ ተክሌ፤ እንዲሁም ቤተሰቦቼንና አዲስ አድማስን አመሰግናለሁ፡፡ እዚህ ስላደረሰኝ ለጋዜጣው ልዩ ትዝታ አለኝ፡፡ የጋዜጣው ባለቤቶች ባያውቁኝም እኔ አውቃቸዋለሁ፡፡

Read 2027 times