Friday, 13 September 2013 12:29

“ቆመን ጠበቅናቸው፤ ጥለውን አለፉ” - ይድነቃቸው ተሰማ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

“ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው!
አምሣ ጥገቶች አሥረው…!”
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አሳማ፤ በጐች በብዛት ወደተሰማሩበት የግጦሽ መስክ ጐራ ይላል፡፡ እረኛው “ምን ሊያደርግ መጣ” በሚል ጥርጣሬ ያስተውለዋል፡፡ አሳማው ወደ በጐቹ ለመቀላቀል ይሞክራል፡፡ እኛው ያደፍጥ ያደፍጥና ፈጥኖ ተጠግቶ አሳማውን ይይዘዋል፡፡ ከዚያም፤
“ለምን መጣህ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
አሳማውም፤
“ከበጐች ልመሳሰል ጀ.ቨ” ሲል ይመልሳል፡፡
“ተመሳስለህስ?”
“እንደበጐች ልኖር”
“ኖረህስ?”
“እንደበጐች እንድታኖረኝ!?”
“አንተን እንኳን ለዚህ አልፈልግህም አያ አሳማ”
“እንግዲያ እንዴት እንድኖር ትፈልጋለህ?”
“አይ፤ ኑሮው ይቅርብህና ወደገቢው ቦታ ብወስድህ ነው የሚሻለው፡፡” ብሎ፤ እየጐተተ ወደ እንስሳ ማረጃው ቦታ ይዞት ሊሄድ ይጐትተዋል፡፡
አሳማው፤ መወራጨት፣ መንፈራገጥ፣ ማጓራት መጮህ ይጀምራል፡፡
ይሄኔ ከበጐቹ መካከል አንዱ ብቅ ይልና፤
“አያ አሳማ?” አለ በለጋስ ጥያቄ ቅላፄ፡፡
“አቤት” አለ አያ አሳማ፡፡
“ምንድነው እንደዚህ የሚያስጮህህ? እኛ ሁላችንምኮ በጌታችን እየተጐተትን ወደሌላ ቦታ እንወሰዳለን፡፡”
“ነው፡፡ ግን የእኔ ይለያል” አለ አሳማ፡፡
“እንዴት?” አለ በጉ፡፡
“አይ አያ በግ የሁለታችን ለየቅል ነው!”
“እኮ እንዴት?”
“ጌታህ አንተን የሚፈልግህ ከቆዳህ ሱፍ ለመሥራት ነው፡፡ እኔን የሚፈልገኝ ግን ለሥጋዬ ነው - ጠብሶ ሊበላኝ”
አያ አሳማ፤ እንደፈራው እየተጐተተ ሄደ፡፡
* * *
በአዲሱ ዓመት ከእንዲህ ያለ ምርጫ ይሰውረን፡፡ ለጥብስ ይሁን ለሱፍ፣ ዞሮ ዞሮ መታረድ ላይቀር ምርጫውን በቅናት መልክ ከማሰብ ይሰውረን፡፡ አራጁንም መሆን ታራጁንም መሆን በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አሰቃቂ ነው፡፡
“አውራ ዶሮ ጮኾ መንጋቱን ነገረኝ
ዛሬ ማታ ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ”
እንዳለው አንዱ የእኛ ገጣሚ፤ የታራጅና አራጅ ምፀት የምንነጋገርበት እንዳይሆን አዲሱ ዓመት ልቡን ይስጠን፡፡
አዲሱን ዓመት የእኩልነት ያድርግልን!
ይገብር ካላችሁ ዝንጀሮም ይገብር
የንጉሥ አይደለም ወይ የሚጭረው ምድር”
የምንልበት ዘመን ይሁንልን!
እንደ ዱሮው ሳይሆን እንደዛሬው ተስፋችን፣ ምኞታችንና ርዕያችን አይሞትምና
“ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው
አምሣ ጥገቶች ወልደው…
በኳስ በድል ታጅበው…”
ስንባል ሞቅ የሚለን፣ ከጭንቅ የሚገላግለን የአዎንታዊነት ምርቃት እንዲሆንልን እንጽና፣ እንጽናና፡
በመጪው ዓመት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፤ “የኢትዮጵያ ሬዲዮ መብራት በመጥፋቱ ከሚሴ አካባቢ የሥርጭት ችግር ገጠመኝ፤ አለ” የሚል ዜና የሚያሰማበት ዓመት እንዳይሆን እንመኝ!!
የአቦ - ሰጡኝ ሳይሆን የትግል ዓመት እንዲሆንልን ልብና ልቡናውን ይስጠን!
የችግር ማውሪያ ሳይሆን የመፍትሔ መፈለጊያ ዘመን እንዲሆንልን አንጐሉን ይስጠን!
የመለያያ ሳይሆን የመዋሃጃ፣ የመተሳሰቢያ ዘመን እንዲሆን በጐ አመለካከቱን አያጨልምብን!
ዕድሜ የጊዜ ሳይሆን፤ የመጠንከር፣ አቅም - የመገንባት፣ እርምጃችንን የማትባት ይሆንልን ዘንድ እርዳታው አይለየን፡፡
ሽቅብ እየተመነደግን እንጂ ቁልቁል እያደግን እንዳንሄድ፣ ድላችንን አስተማማኝ ያድርግልን፡፡
ፀሐፊዎቹ እንዳሉን፤
“አንድ ግዙፍ የብርቱካን ዛፍ እናስብ፡፡ በስሎ የተንዠረገገ ብዙ ብርቱካን አለው፡፡ ወደታች፣ በሰው ቁመት ያሉትን ብርቱካኖች በብዛት ለቀምኳቸው፡፡ ከዚያ በላይ ያሉትን ለመቅጠፍ ቁመት አጠረኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የብርቱካን እጥረት አለ ልል ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንድ አዋቂ ሰው አንድ ቴክኖሎጂ ፈጠረ፤ መሰላል የሚባል፡፡
ወደ ማይደረሱት ብርቱካኖች መድረሻዬን አበጀልኝ፡፡ ችግሬ ተቃለለ፡፡ ቴክኖሎጂ ወደኃይል ምንጭ መዳረሻ/ ማግኛ ስርዓት ነው፡፡ ያኔ እጥረት ያልነውን ነገር፣ አሁን በሽ - በሽ፤ ነው ያሰኘናል፡፡ (“አበንዳንስ”፤ በፒተር ዲያማንዲስ እና ስቲቨን ኮትለር)
ስለ ዕጥረትና ስለ ዕጦት የምናስብበት ዓመት እንዳይሆን መሰላሉን የሚሰጠን አዋቂ ይዘዝልን፡፡
የኳስ ድል ይለምልም፡፡ ሩጫውም ይቅናን፡፡
የዕውነት ለውጡም ይቅናን፡፡ ኑሮም ይታደገን!
በጐ እንድንመኝ፣ በጐ እንድናገኝ፤ በጐ እጅ ይስጠን!
“አይቀጭ ትልማችን፣ አይራብ ህልማችን!
አይመት ሐሞታችን፣ አይቃዥ ርዕያችን!
አይንጠፍ ጓዳችን፣ አትምከን ላማችን!
አይክሳ ቀናችን፣ አይላም ጉልበታችን!!
ከሁሉም ከሁሉም አይጥፋ ሻማችን!”
ብለን የምንመኝበትን የህይወት ፀጋ አይንሳን!!
ታዋቂው የእስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማ ሱዳን ከእግር ኳሱ አምባ ጠፍታ ከርማ ወደሜዳ ስትመለስ ያሳየችውን ድንቅ እርምጃ በተመለከተ የሰጡት አስተያየት፤ ማስገንዘቢያ፣ ማስጠንቀቂያና የእግር ኳሱን ሂደት ማሳያ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ ዋና ማሳሰቢያ ነው!
“ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ!” ነበር ያሉት፡፡ ነብሳቸውን ይማርና ዛሬ፤ ቆመን አልጠበቅናቸውም!
እየሄድን ነው!” እንላቸው ነበር፡፡ እንዴት ደስ ባላቸው!
እንደ አዲስ ዓመት ምላሽ “ከብረው ይቆዩን ከብረው” የምንባባልበት እንዲሆን እንመኛለን”
መልካም አዲስ ዓመት!!

Read 4178 times