Friday, 13 September 2013 12:40

የአዲስ ዓመት ምኞት

Written by  ቱዋ (ጋርጋንቱዋ)
Rate this item
(4 votes)

ለአዲስ ዓመት የሆነ ስጦታ ማበርከት ያምረኛል። ስጦታ መስጠት የምፈልገው ደግሞ ለሁሉም ሰው ነው፡፡ “አርፈህ መልካም አዲስ አመት ይሁንልዎ! አትልም ምን ጣጣ ታበዛለህ?” እንደምትሉኝ ቢገባኝም/ቢሰማኝም…ይህ ግን የገፀ በረከት (ገፅ የማበርከት) ጥሜን አይቆርጥልኝም፡፡
ስለዚህ እስቲ ላስብ፡፡ ምን ልስጣችሁ?...የሀምሳ ብር የሞባይል ካርድ በየስልኮቻችሁ ላይ ልላክላችሁ? የሁላችሁንም የሞባይል ስልክ አላቀውማ…ምን ያደርጋል!…
አንድ ባለ አስር ብር ካርድ ገዝቼ፣ ፍቄ ቁጥሩን በመጣጥፌ ላይ አስፍሬ…ጋዜጣው ታትሞ ሲወጣ መጀመሪያ ጋዜጣውን የገዛ ሰው ቁጥሩን እንዲሞላ ለማድረግም አሰብኩ፡፡ ግን ጋዜጣውን መጀመሪያ የገዛ ሰው ሳይሆን ጽሑፉን መጀመሪያ ያነበበ ቢሞላውስ?..ቁጥሩን በሞባይላችሁ ላይ ስትጠቀጥቁ ልትውሉብኝ ነው፡፡
ቤቴ አልጋብዛችሁ ነገር፤ ስጦታዬን በዶሮ ወጥ መልክ ወይንም በቅልጥም መልክ እንድትግጡ… ሁለቱም (ቅልጥም እና ወጡ) እኔ ቤት የሉም፤ በዛ ላይ ቤቴ በጣም እሩቅ ነው፡፡ ከእናንተ ቤት አቅጣጫ በተቃራኒ ነው፡፡
ስለዚህ ስጦታዬ ዞሮ ዞሮ ቁስ የሆነ ወይንም ወደ ቁስ የሚመነዘር ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ያው ምኞት ብቻ ነው አቅሜ፡፡ ግን ምኞትም ከሆነ አይቀር…ከእውነተኛ የምኞት ምንጭ የፈለቀ፣ ፈልቆ እንደ ሀይላንድ ውሃ በፕላስቲክ እቃ ያልታሸገ፣ በሊትር ያልተወሰነ ነው ለእናንተ የምመኘው፡፡ ምኞቱ እናንተን ሁሉ የሚመለከት እንዲሆን ተመኘሁ። ለእግዜር ጆሮ ቀለል ያለ ምኞት ራሱ ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ለምሳሌ ለሁላችሁም ስኬታማ አመት ብመኝ…ፈጣሪ ራሱ አይሰማኝም። ከልብ የመነጨ ምኞት አይደለም፡፡ ቅዥት ነው፡፡ የሚጨበጥበት ቦታ የለውም ምኞቱ፡፡
አሳዳጁ ጭራውን እንኳን አይዘውም፤ ምኞቱን ለማሳካት የሚያሳድደው መንግስት ሊሆን ይችላል። ወይንም ፈጣሪ፡፡ ወይንም እድል፡፡ ወይንም ግለሰብ፣ እድል እና ፈጣሪ፡፡
ስለዚህ ለሁላችሁም ስኬት ልመኝላችሁ ብችልም…አላደርገውም፡፡ ባደርገውም የተመኘሁት አይሳካም፡፡ እንደዚህ ብዬ ምኞቴን አሻሽዬ ልመኝ:- “ስኬት ለሚገባችሁ ይሳካላችሁ”
ምኞት ወደ ተጨባጭነት ቀረብ ሲል “ስጦታ” ተብሎ መጠራት ይችላል ባይ ነኝ፡፡ “የመስራት አቅም እና ፍላጐት ያላችሁ…ስራ ያሰራችሁ፤ ስራ መስራት እየሰነፋችሁ ስራ የምታስሱም እንደፍጥርጥራችሁ!…ተቻችሎ መኖር የሚያምራችሁ የምትችሉት እና የሚችላችሁ ይስጣችሁ (ነገር ግን መቻቻል እያማራችሁም ከዚህ በፊት ሊሳካላችሁ ካልቻለ…አርፋችሁ ራሳችሁን እንድትችሉ ምኞቴ ነው)፡፡
ስጦታዬ ቀጥሏል፡፡ ርካሹ ስጦታ ምኞት ነው፡፡ ወደ ኪስ አይገባም…አይወጣምም፡፡
“የሚያታልሉ ሰዎች ያታለሉትን ያህል (እምነት፣ ገንዘብ፣ እውነት) ከቁመታቸው ላይ ይቀነስባቸው” ብዬ ልመኝ ነበር፡፡ ከአፌ መለስኩት፡፡ እቺን ስጦታ ማንም ሰው ስለማይቀበለኝ ተውኳት፡፡ ማንም አይቀበለኝም፤ ማንም በቁሙ ቁመት ይዞ አይገኛትማ፡፡ ምኞቴ ቢሳካ፡፡
ስለዚህ ምኞቴን አሁንም አሻሽለዋለሁ፡፡ “የሚያታልሉ ሰዎች የሚያታልሉበትን ምክንያት ይወቁት፡፡ በማታለል ምንም ትርፍ ላያገኙ የሚያጭበረብሩ ሰዎች “እግዜር ያይላቸው” ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ መፍትሔ ለሌለው ነገር “እግዜር እንዲያይ” መመኘት ብቻ ነው መፍትሔው፡፡
“በጐቹ እና ፍየሎቹ እንደዚሁም በሬዎቹ ለአመት በአል ለለውጥ (በነጋዴዎቹ ፋንታ) የራሳቸውን የስጋ ተመን አፍ አውጥተው እንዲመሰክሩ ምኞቴ ነው” ተገዝተው መታረዳቸው ካልቀረ ቢያንስ ቢያንስ ምናለ ዋጋቸውን ከመሞታቸው በፊት ራሳቸው ቢናገሩ? ግን ይሄም የማይመስል ምኞት ነው፡፡ “ምናለ ሳልወለድ በቀረሁ ኖሮ” ከሚል ምኞት የተለየ አይደለም፡፡ እሽ እንደፈረደብኝ ላሻሽለው “የበጐቹን ዋጋ መንግስት፣ ነጋዴ እና የበጉ የስጋ ክብደት (ከሚዛን ጋር ሆነው) ሶስቱ ተማክረው ቢነግሩዋችሁ እመኛለሁ”
“ይሄ ‘የኑሮ ውድነት’ የሚባለው ሰውዬ ቢሞት እመኛለሁ” ካሁኑ… እኔ እየተመኘሁ ኔትወርኩ ሲጨናነቅ ተሰማኝ፡፡ ኔትወርኩ የተጨናነቀው በእኔ እና በእናንተ ፀሎት ብቻ አይደለም፡፡ መንግስትም እንደኛው እየተመኘ ነው፡፡ ማድረግ የሚችለውም የማይችለውም የሚመኝ ከሆነ…ምን ዋጋ አለው፡፡ ዲያስፖራ ከእኔ እኩል ኮንዶሚኒየም ለማግኘት እየተመኘ እኮ ነው…የፀሎት ኔትወርኩ የተጨናነቀው፡፡
“ሁሉ ሰው ቤት እንዲኖረው እመኛለሁ”…ግን ለሁሉ ሰው ቤት መስሪያ የሚበቃ መሬት መኖሩን እርግጠኛ ባልሆንኩበት ደረጃ ይሄንን መመኘቴን እቃወማለሁ፡፡ “የማይሆኑ ምኞቶችን የሚቃወም የፖለቲካ ፓርቲም እንዲመሰረት እመኛለሁ”
ሁሉም ሰው መኪና እንዲኖረው አልመኝም፡፡ ሁሉም ሰው መንገድ ይሰጠኝ “ይሰየምልኝ” ማለቱ ስለሚያሰጋኝ ነው፡፡ በዛ ላይ መንገዶቹ ተሰርተው ሳያልቁ የትራፊክ ፖሊስን ስራ ጫና ከመጨመር ውጭ ሌላ ትርፍ አይታየኝም፡፡
“ሁሉ ሰው ሶስቴ መብላት ሲችል ቢያንስ አንዴ እንዲጠግብ እና ሲጠግብ እርስ በራሱ እንዳይመቀኛኝ እመኛለሁ” ምቀኝነት ራሱ ለብዙ ዘመን በመሐላችን እየኖረ ማንም ሊይዘው ያልቻለ ሽፍታ ነው፡፡ የጥንት ሽፍታ ነው፡፡ ከትውልድ ትውልድ አቅሙ የማይደክም፡፡
አመት በአል የሚከበረው በልጆች ምክንያት እንደሆነ ማመን ጀምሬአለሁ፡፡ “የአመት በአል መንፈስ ለመፍጠር ስንል ወደ ቤተሰብ ምስረታ (baby farming) ያለ በቂ ዝግጅት እንዳንገባ እመኛለሁ” ትዳር በቀላሉ የኮንዶሚኒየም ቤትን ከማግኘት ጋር ሲመሰረት ተመልክቻለሁዋ፡፡ “አንድ ስቱዲዮ እና ሁለት ልጆች አሉኝ” የሚሉ ጐረምሳ አባቶች እየበዙ ነው፡፡ የህዝብ ቁጥር መጨመር ትርፍ ሰዎችን (እንደ ሰሞነኛ የታክሲ አጫጫን) እንዳይፈጥርብን እመኛለሁ”
“ቅንነት በሀገሬ ሰዎች ላይ እንዲሰፍን እመኛለሁ”…እንደዚህች አይነቷን ምኞት ሲናገሩ የምሰማቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቅንነት የጐደላቸው ወይንም ቅን ሆነው የማያውቁ ናቸው፡፡ እቺን የአሁኗን ምኞቴን ስቃችሁ እለፏት፡፡ ቅንነት በውስጥ ከሌለ ከውጭ አይመጣም፡፡ እንደ ኑሮ፤ ወይንም የሰውነት ውፍረት… ሀገር በመቀየር፣ ሃይማኖት በማጥበቅ ቅንነት አይገኝም፡፡
ሰላም ልመኝላችሁ?...ግን የትኛውን አይነት ሰላም? የራሳችሁ ህይወት ሲስተካከል ወይንም ከማዕበሉ ሲያመልጥ የምታገኙትን ሰላም? ሰላም ባላችሁበት? የትም የሌሉ ሰዎች ሰላም እንዲያገኙ ምኞቴ ሰፋ ማለት አለበት፡፡
በሌላ ሰው መሰበር የሚቃና አንገት፤ ሰላምን አግኝቻለሁ የሚለኝ ከሆነ ሰላምን እንዲሁ በደፈናው ለመመኘት እፈራለሁ። (በዚህ አመት) ከስራው የሚባረር/የሚታገድ ጓደኛውን ቦታ የወረሰ ሰው፣ “ሰላም አግኝቻለሁ” ካለኝ በእኔ ምኞት ምክንያት እንዳልሆነ ንገሩልኝ፡፡
“ሁሉም ህፃናት ይደጉ፤ ርሃብ ወይንም ሐዘን አይንካቸው፤ የፈለጉት ሁሉ ይሟላላቸው…ደስተኛ ይሁኑ” እቺ ምኞት ላይ ብቻ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ፈጣሪም፣ መንግስትም፣ እግዜርም፣ ወላጆችም ይሄን ምኞት ለመሙላት ጐን ለጐን የሚሰሩ ይመስለኛል፡፡
በእርግጥም ስጦታዬን ማበርከት የምወደው ለህፃናቱ ነው፡፡ የዘመን መለወጥም ሆነ አዲስ ሆኖ መምጣት ለአዋቂዎቹ ሳይሆን ትርጉም የሚሆነው ለህፃናቱ ነው፡፡ ለአበቦቹ፡፡ ለጐረምሳ እና አዋቂ ወላጆች ለህፃናቱ የተመኘሁት ምኞት በሚያሳድጓቸው አበቦች በኩል ይደርሳቸዋል። ይድረሳቸው፡፡
መልካም አዲስ አመት!

Read 7798 times