Friday, 13 September 2013 12:39

ስብሐት፣ ድመትና አዲስ ዓመት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የዛሬ አሥር ዓመቱን ዘመን መለወጫ በዓል የማስታውሰው ከአንዲት ባተሌ ድመት ጋር አዳብዬ ነው፡፡ እዚህ ትውስታ ውስጥ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርም አለበት። ያኔ ድመቷና እሱ መካኒሳ አቦ አካባቢ ጉርብትና በማጠናከር ላይ ነበሩ፡፡ ስብሐት የተከራየው ሙሉ ግቢ ውስጥ ማን እንዳከራያት ያልታወቀች ባተሌ ድመት በአጥሩና በቤቱ ቦለኬት መካከል ተወሽቃ ትኖራለች፡፡ አውሬ ናት፤ ሰው ስታይ ከቻለች ከአካባቢው ትጠፋለች፣ ማምለጫ ካጣች ክፉኛ ትቆጣለች፡፡
“ተውዋት አርበኛ ናት” ይላል ስብሐት በቀልድ። አትንኩኝ ባይነቷ ብቻ ሳይሆን መጐሳቆሏም የአርበኛ ነው፡፡ ቢጫ ነብርማ መልክ ቢኖራትም አዘውትሮ ስለሚርባት ውበት ከእርሷ እርቋል፡፡ ቆዳዋ ከአጥንቷ ጋር ተጣብቆ ሙግግ ያለ አንገት አላት፡፡ ሲያይዋት የምትቀፍ ብትሆንም ስብሐት ስለእሷ አዘውትሮ ይጨነቃል፡፡
“አካባቢውን በሞኖፖል ከያዘው ፍጡር ጋር ተጣልታ፣ ህይወት እቅጯን መከራ ብቻ ሆነችባት” ይላል፡፡
“እንዴት?” ሲባል
“ምን እንዴት አለው? ከተማ ላይ እኮ ፈላጭ ቆራጩ፣ ሰው ነው፡፡ ቢሰጥም ቢነሳም የሚችል አምላክ ልትለው ትችላለህ፡፡
ታዲያ ይቺ አርበኛ ሰው አይንካኝ የምትል አውሬነት ውርሷ ሆኖ ተጫነባት፡፡ ጣሪያ ላይ ተወልዳ ጣሪያ ላይ አደገች፡፡ ሰውን ደግሞ እናውቀዋለን፤ የእኔ ነው ብሎ ካላሰበ እንኳን እንስሳ የገዛ ወገኑንም አያበላም፡፡”
ስብሐት ለእራሱ ከተቆረጠለት መቁነን ላይ ድመቷን ማጋራት ጀምሮ ነበር፡፡ እንደውም አንዳንድ ቀን ሁሉንም ለእሷ ሰጥቶ ጦሙን የሚውልበት ጊዜ አለ፡፡
“አንተስ?” ሲባል
“እኔ ለምኜ ሳይሆን ተለምኜም የሚያበላኝ አላጣም” ይላል፡፡
ድመቷን የሚመግብበት ሥርዓት ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር፡፡ ቁርሱን ወይ ምሳውን ይዞ ከቤቱ ይወጣና ድመቷን በአይኑ ሳያፈላልግ መኖሪያዋ የሆነው ወሻቃ ቦታ አካባቢ ያስቀምጠዋል። ከዚያ ቀጥ ብሎ ወደ ክፍሉ ገብቶ ማንበብ ይጀምራል። ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ቀስ ብሎ ምግቡን ወዳስቀመጠበት አቅጣጫ ገልመጥ ይላል፡፡ ከበላች ሰሐኑን ያነሳል። ካልበላች ሌላ ጥቂት ጊዜ ይጠብቃታል፡፡ ሰዎች አብረውት ካሉ ፀጥ ብለው መፅሐፍ ወይም ሌላ ነገር እንዲያነቡ ያዝዛል፡፡ ከበላች፡-
“አርበኛችን ከእነኩራታቸው ተመግበዋልና አሁን ጨዋታ እንቀጠል” ይላል፡፡
አንድ ጊዜ እያሳለው ስለተቸገረ ዜና፣ ሞርቶዴላ እንዲበላ አቀረበችለት፡፡
“እቺን የያዝናትን አጠናቀን እንመገባለን” ብሎ ወደ ክፍሏ ከሸኛት በኋላ፣ እንዳለ ለድመቷ አቀረበላት፡፡
“ለምን?” አልኩት
“እውነታውን ሳንሸፍጥ ለመቀበል ከደፈርን ሞርቶዴላው የሚያስፈልጋት ለአርበኛዋ ነው። እንደውም አማልክቱ እንዲያስለን ፈቃዳቸው የሆነው ለእሷ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም እንላለን፤ ባይመረመሩም፡፡ አሁን ፀጥታ ያስፈልጋል፣ አርበኛዋ ያለመሳቀቅ እንዲመገቡ፡፡”
በዚያ ዘመን መለወጫ እለት ወደ መካኒሳ ስሄድ የስብሐትና የድመቷ ግንኙነት ተሻሽሎ ተመለከትኩ፡፡ ስብሐት ለበአል የተሰጠውን ዶሮ ወጥ ከእነቅልጥሙ ለድመቷ አቅርቦ በረንዳ ላይ ያነባል፡፡ ድመቷ የእኔን መምጣት እስክትመለከት ድረስ ከጀርባው በመጠኑ ራቅ ያለውን ምግብ እየበላች ነበር፡፡ ተአምር የሆነብኝ፣ ስብሐት ወደ ክፍሉ ሳይገባ መብላቷ ብቻ ሳይሆን የሰውነቷ መለወጥ ጭምር ነው፡፡ ልጥልጥ ብላ ባትወፍርም መጠነኛ ሁኔታ ውስጥ መገኘቷ በራሱ ተአምር ሆኖብኛል፡፡ እኔን ስታይ ቱር ብላ ጠፋች፡፡
ስብሐት ቀልቡ ከእሷ ጋር እንደነበር በሚያስታውቅ ሁኔታ ቀና ብሎ አየኝ፡፡
“ለመደች?” ስል ጠየኩት
“በጥቂቱ”
“እንዴት?”
“አርበኝነታቸውን ባለመጋፋት፣ ከነፃነታቸው ምንም ጉዳይ እንደሌለን፣ ግዴለሽነትን እየተወንን፣ ተመግበው እንዲሄዱ እየፈቀድን… ወዘተ” አለ፡፡
ስብሐት ይቺን ድመት የሚያበላት እሩህሩኋ ብቻ አልነበረም፡፡ ረሃቧን የተካፈላት፣ አንዳንዴም ፋንታዋን የተራበላት ወዳጇ እንጂ፡፡
አፉን እየተመተመ ወደ አሱ ክፍል እንድገባ ጋበዘኝ፡፡ ሹክክ ብዬ አለፍኩ፡፡ ለጥቂት ደቂቃ መፅሔትና ጋዜጣ አገላበጥኩ፡፡ እሱ በረሃብ ጭምር የታደጋትን ድመት እኔ በፀጥታ ለማገዝ መሞከሬ እንደከበደኝ ታውቆኝ እራሴን ታዘብኩት፡፡
“አሁን መቀጠል እንችላለን” አለኝ፡፡
በራሴ ላይ አኩርፎ መቀጠል ተሳነኝ መሰል፡-
“ነፃነት የሚያስከፍለው ዋጋ ባሪያ በመሆንህ ከሚደርስብህ መከራ ጋር መነፃፀሩ የሰዎች እጣ ፈንታ ብቻ አለመሆኑን በዚች ድመት አውቀናል፡፡ አለማወቋ በጀ እንጂ፣ ብታውቅም ጉራ መንፋቱን ናቀችው እንጂ ወይም ስለ ነፃነት ከማውራት ነፃነቷን መኖር መረጠች እንጂ… አሜሪካኖችን ባስናቀች ነበር፡፡”
ወገቡን ይዞ ተነስቶ ቆመ፡፡ ብዙ ሲቀመጥ የሚያደርገው ሰውነት ማፍታቻ ስልቱ ነው፡፡ ወገቡን እንደያዘ ወደ ውስጥ እያየ ንግግሩን ቀጠለ፡፡
“የተወዳጃችን የማርክ ትዌይን እናት፤ በዚያ የሰዎች ገበያ ሥርዓት በተደናበረበትና የኑሮ ስልቱ በተወለጋገደበት ዘመን፤ (Great depression) የድመቶች ከየቤቱ መባረር ሐዘን ስለፈጠረባቸው እየሰበሰቡ ሰላሳ ያህሉን ማስጠጋት ችለው አስደንቀዋል፡፡ ያውም ከልጃቸው ጀምሮ የሚደርስባቸውን ተቃውሞ ተቋቁመው፡፡ ሌላው አንድ ድመት ከብዶት እኮ ነበር ወደ ጐዳና የሚያባርረው፤ እንኳን ሰላሳ አንዲቷ እንዴት እንዳሽቆጠቆጠችን በማሰብ መንፈሳቸው በሰላም እንዲያርፍ እንመኛለን፡፡”
ከሦስት ወር በኋላ ይመስለኛል፤ ተመልሼ ስሄድ ድመቷ ስብሐት ክፍል ድረስ መጥታ የመጮህ ወግ ደርሷት አየሁ፡፡
ምንም እንኳን እኔን ስታይ በርግጋ ብትጠፋም ሰውነቷ፣ ፍጥነቷና ንቃቷ በደንብ የተያዘች የቤት ድመት አስመስሏታል፡፡ ገረመኝ፡፡
“ያቺ ድመት ነች?” ባለማመን ጠየቅሁት
“እ…” አለኝ፡፡ “ነፃነቷን ጨርሳ ባለመተው፣ መጠነኛ ድጋፋችንን በመሻት፣ ፈር ያልለቀቀ ጥያቄዎችን ታቀርብልናለች፡፡ ደግሞም’ኮ እውነቷን እንደሆነ ተቀብለንላታል፡፡ የተፈጥሮ ባርነት መች አነሳትና የሰዎችን ትደርብ? እራሳቸው የተፈጥሮ ባሮች እንደሆኑ አጣነውና? ድንቄም ጌታ! ልትለን ትችል ነበር ያውም በመፀየፍ፡፡ አድርባይ ምሁሮች ስለበርን ለማዳ ድመትነትን ከእነጭራ አቆላሏ አጥርተን ስለምናውቅ ለአርበኛችን አንመኝላቸውም - ምን ቦጣቸውና…”
ከሁለት ወይም ከሦስት ወር በኋላ ስብሐት ያንን ቤት ለቀቀ፡፡ የነፃነት አርበኝቷ ያለስብሐት፣ ኑሮ እንዴት ተገፍቶላት ይሆን? ለብዙ ዘመን አብሮኝ የኖረ ጥያቄ፡፡

Read 3751 times