Friday, 13 September 2013 13:00

ዋልያዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫ ወደ “ቻን” ከዚያም ወደ የዓለም ዋንጫ!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ወደ 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለመብቃት ለጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከደረሱ 10 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በእግር ኳስ ደረጃው፤ በፕሮፌሽናል ተጨዋቾቹ ብዛትና በዝውውር ገያው የዋጋ ተመኑ ዝቅተኛው መሆኑን ከትራንስፈርማርኬት ድረገፅ ያገኛናቸው አሃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ኢትዮጵያ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 102 በአፍሪካ 27
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 5
የዝውውር ገበያ ተመን -775ሺ ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 25.20
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 321
አልጄርያ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 34 በአፍሪካ
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 19
የዝውውር ገበያ ተመን -51.5 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.8
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 300
አይቬሪኮስት
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 18 በአፍሪካ 1
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 25
የዝውውር ገበያ ተመን -135 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.9
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 772
ናይጄርያ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 35 በአፍሪካ 5
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 18
የዝውውር ገበያ ተመን -56 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 24.10
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 362
ጋና
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 24 በአፍሪካ 2
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 34
የዝውውር ገበያ ተመን -77 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 25.20
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 725
ኬፕቨርዴ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 36 በአፍሪካ 6
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 25
የዝውውር ገበያ ተመን -16.5 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.5
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 244
ግብፅ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 61 በአፍሪካ 11
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 11
የዝውውር ገበያ ተመን -29 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.5
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 880
ቡርኪናፋሶ
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 48 በአፍሪካ 7
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 26
የዝውውር ገበያ ተመን -235 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26.7
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 535
ሴኔጋል
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 78 በአፍሪካ 17
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 26
የዝውውር ገበያ ተመን -97.5 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 25.5
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 247
ካሜሮን
የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ- በዓለም 51 በአፍሪካ 8
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት- 28
የዝውውር ገበያ ተመን -125 ሚሊዮን ፓውንድ
የቡድኑ አማካይ እድሜ- 26
የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዛት- 498

  ========

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ስኬት በማግኘት በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ዋልያዎቹ በሚል ስሙ የታወቀው ይህ የእግር ኳስ ትውልድ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ 180 ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡ ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቅተዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ “ቻን” ተሳታፊ ናቸው፡፡ በዋልያዎቹ አስደናቂ ጥረት 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቁ ስኬት እንዲመዘገብ ሆኗል፡፡ የዚህ ትውልድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የአገሪቱን የእግር ኳስ ደረጃ ብቻ አላሻሻሉም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፕሮፌሽናሊዝም ጉዞ ፈር ቀዳጅ ለውጦችን እየፈጠሩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የዋልያዎቹ አባላት ባገኙት ውጤት ልክ በገንዘብ ሽልማት ከ300 እስከ 450ሺ ብር በመሰብሰብ የላባቸውን ዋጋ እያገኙ ነው፡፡ በፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ወደ 6 የተለያዩ አገራት ወደ የሚገኙ ክለቦች በመሰማራት ከፍ ያለ ደሞዝና ጥቅም በማግኘትም በዝውውር ገበያው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ለመሆኑ ዋልያዎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፉት የእግር ኳስ ገድል ምን መልክ ነበረው? በአፍሪካ ዋንጫ እና የማጣርያ ውድድሮች ምን ታሪክ ሠሩ? በዓለም ዋንጫ በሁለት ዙር ማጣርያዎች 8 ብሔራዊ ቡድኖችን ጥለው ያለፉበት ጉዞ ምን ይመስላል?
ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ
ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ወደመሠረተችው አህጉራዊ ውድድር በመመለስ ደቡብ አፍሪካ ላስተናገደችው ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያለፉት በቀላሉ አልነበረም፡፡ በመጀመርያ የማጣሪያ ምዕራፍ ከቤኒን ጋር በጥሎ ማለፍ ተደልድለው በሜዳቸው 0ለ0 ሲለያዩ፣ በአበበ ቢቂላ ስታድየም የተደረገው ጨዋታ ጐል ማግባት ያልተቻለበት መሆኑ በወቅቱ የነበሩትን ቤልጅማዊ ዋና አሰልጣኝ ቆም ሴንትፌንት እና ምክትላቸውን ሰውነት ቢሻው ያስተቸ ነው፡፡ በመልሱ ቤኒን ላይ ሲጫወቱ 1ለ1 አቻ ሆኑ፡፡ ጐሏን ያስቆጠረው አዳነ ግርማ ነበር፡፡ ስለሆነም ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው የአሸናፊ መለያ ህግ ወደቀጣዩ ምእራፍ ተሸጋገሩ፡፡ወደ አፍሪካ ዋንጫ ወደየሚያሳልፈው የመጨረሻው ምእራፍ ማጣርያ የተገናኙት ከጐረቤት አገር ሱዳን ጋር ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ዋልያዎቹ በሜዳቸው ሱዳንን 2ለ0 ነበር ያሸነፉት፡፡ በመልሱ ጨዋታ ካርቱም ላይ ሲገናኙ እጅግ አስጨናቂ በነበረበት ጨዋታ 5ለ3 ተሸነፉ፡፡ በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ውጤት 5ለ5 እኩል ሆነ፡፡ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፈው ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጭ ብዙ ባገባ በሚለው ተለየ፡፡ በሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች በዋልያዎቹ የተሰበረ መጥፎ ሪከርድ ነበር፡፡ ከሜዳ ውጭ ወሳኝ ጐሎችን በማግባት ውጤታማ መሆን ስለተቻለ ነው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቃ፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከናይጀሪያ ከቡርኪናፋሶ እና ዛምቢያ ጋር ተመደበ፡፡ በመጀመርያ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር 1ለ1 አቻ ወጣ ከዚያም በሁለተኛ ጨዋታው በቡርኪናፋሶ 4ለ0 እንዲሁም በመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ በናይጀሪያ 2ለ0 ተሸነፈ፡፡ በዚህ ውጤቱ መሰረትም በምድብ 3 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባስመዘገበው 1 ነጥብና 6 የግብ እዳ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ ከአፍሪካ ዋንጫው በግዜ ተሰናበተ፡፡ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፋቸው ትልቅ ውጤት ነበረው፡፡ የመጀመርያው በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ለውድድሩ ከፍተኛ ድምቀት በማላበስ ለዋልያዎቹ ያስገኙት ትኩረት ነው፡፡ በሌላ በኩል ብሔራዊ ቡድኑ በምድቡ የመክፈቻ ጨዋታ ከዛምቢያ 1ለ1 አቻ ሲለያይ ለኢትዮጵያ የተመዘገበችው የአዳነ ግርማ ብቸኛ ጐል በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከ33 ዓመት በኋላ የተመዘገበች ነበረች፡፡ የዋልያዎቹ አባላት በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አፍሪካ፣ በምስራቅ አውሮፓ ክለቦች በመፈለግ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጉዟቸው የተሟሟቀው በአፍሪካ ዋንጫ በነበራቸው ተሳትፎ ነው፡፡
በሁለት ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች
ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ማጣርያ ሲገባ በመጀመሪያ ዙር ለጥሎ ማለፍ ጨዋታ የተደለደለው ከጐረቤት አገር ሶማሊያ ጋር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ በጅቡቲ ሲደረግ ውጤቱ 0ለ0 ነበር፡፡ ይህ ውጤት ስፖርት አፍቃሪውን ተስፋ ለማስቆረጥ የተፈታተነ ነበር፡፡ በመልሱ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 5ለ0 ሶማሊያን ያሸነፉን ዋልያዎች ወደ ሁለተኛው ዙር የምድብ ማጣርያ ምዕራፍ ተሸጋገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቦትስዋና እና ከመካከለኛው አፍሪካ ነበር የተደለደለው፡፡ በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በሩስተንበርግ ሮያል በፎኬንግ ስታድዬም ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 አቻ በመለያየት ጥሩ ጅማሬ አደረጉ፡፡ ከሜዳ ውጭ ደቡብ አፍሪካ ላይ ጐሉን ያስቆጠረው ሳላዲን ሰኢድ ነበር፡፡ በ2ኛው የምድብ ጨዋታ ዋልያዎቹ በአዲስ አበባ ስታድዬም መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊካን በማስተናገድ 2ለ0 አሸንፈው ምድቡን በአንደኛነት መምራት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይም ሁለቱንም ጐሎች ከመረብ ያዋሃደው ሳላዲን ሰኢድ ነው፡፡ ከዚያም በ3ኛው የምድብ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ቦትስዋናን ገጠሙ፡፡ በጌታነህ ከበደ ጐል 1ለ0 በማሸነፍ መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በ4ኛው የምድብ ጨዋታ ከቦትስዋና ጋር ዋልያዎቹ በዋና ከተማዋ ጋብሮኒ ሎባታሴ ስታድዬም ተገናኝተው 2ለ1 ከሜዳ ውጭ አሸንፈው ነበር፡፡ አንዱን ጐል ሳላዲን፣ ሌላኛው ጌታነህ አስቆጥረዋል፡፡ በዚሁ ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ቅጣቱ መሰለፍ ያልነበረበት ምን ያህል ተሾመ ተሰልፎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በፊፋ ህገ ደንብ ተቀጪ ሆና 3 ነጥብ 3 ነጥብ ተቀነሰባትና ሙሉ ሶስት ነጥብ እና የ3ለ0 ውጤት ለቦትስዋና እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ ከዚያ አሳዛኝ ጥፋትና ቅጣት በፊት የምድቡ 4ኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተደረገው ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በሜዳቸው ደቡብ አፍሪካን 2ለ1 አሸነፉ፡፡ 1 ጐል ጌታነህ ከበደ ሲያስቆጥር የማሸነፊያውን ጐል ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ተጫዋች መረብ ላይ ያገባው ነበር፡፡ ይሁንና ከምድቡ በመሪነት ማለፉን ለማረጋገጥ የምድቡ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በኮንጎ ብራዛቪል የምድብ 1 የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር ተደረገ፡፡ በሳላዲን ሰኢድ እና በምንያህል ተሾመ ጐሎች 2ለ1 በማሸነፍ ምድብ 1 ላይ በመሪነት ጨረሱ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 የደረጃ ሰንጠረዥ በ6 ጨዋታዎች ምንም ሳይሸነፍ በ1 ጨዋታ በቅጣት 3 ነጥብ ተቀንሶበት በ13 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ መሪ በመሆን ለቀጣዩ ምእራፍ በቅቷል፡፡ ዋልያዎቹ በምድብ ማጣርያውን ያለፉበት ሂደት አስደናቂ ልዩ የሚሆነው በተመሳሳይ የተሳትፎ ታሪክ ትልቁ ውጤት በመሆኑ ነው፡፡ ከቅድመ ማጣሪያው ከተነሱ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው 24 ብሔራዊ ቡድኖች ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ መሆኑ ደግሞ ሌላው ስኬት ነው፡፡ እስከ ምድብ ማጣርያው በአጠቃላይ 8 ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ 5 ጨዋታዎችን ድል አደረጉ፡፡ አራቱን በሜዳ አንዱን ከሜዳው ውጭ ነው፡፡ በ2 ጨዋታዎች አቻ ወጡ፡፡ ሁለቱንም ከሜዳ ውጭ ነበር፡፡ እንደ ሽንፈት የተቆጠረው ግጥሚያ ሁለት ቢጫ ካርድ ያየ ተጨዋች በመሰለፉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመርያ 2ለ0 አሸንፎ ለቦትስዋና በቅጣት በፎርፌ 3ለ0 እንዲሸነፍ የተደረገበት ነው፡፡ በስምንቱ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቹ ላይ 13 ጎሎች ያስመዘገበው ብሄራዊ ቡድኑ የተቆጠረበት ግብ 6 ሲሆን በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ 1.63 ጎሎች እንደሚያገባ እና 0.75 ጎል ሊገባበት እንደሚችል የፊፋ ስታስቲካዊ ስሌት ያመለክታል፡፡ ከስምንቱ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ግጥሚያዎች ሁሉንም በመሰለፍ ለ709 ደቂቃዎች የተጫወተው አበባው ቡጣቆ ነው፡፡ ስዩም ተስፋዬ በ7 ጨዋታዎች ለ575 ደቂቃዎች በመሰለፍ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሳላሃዲን ሰኢድ በ6 ጨዋታዎች ለ540 ደቂቃዎች በመሰለፍ አራት ጎሎች ያገባ ሲሆን ሌሎቹ በ6 ጨዋታዎች ያገለገሉት 446 ደቂቃዎች ተሰልፎ ሁለት ያገባው ሽመልስ በቀለ እና ለ540 ደቂቃዎች የተጫወተው አምበሉ ደጉ ደበበ ናቸው፡፡ አይናለም ሃይሉ፤ አስራት መገርሳ፤ አዲስ ህንፃ እና ምንያህል ተሾመ እያንዳንዳቸው በ5 ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ በመሰለፍ ከ425 እስከ 450 ደቂቃዎች ግልጋሎት የሰጡ የዋልያዎቹ አባላት ናቸው፡፡
ለዓለም ዋንጫ 180 ደቂቃዎች ጉዳይ
ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ በመብቃቷ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪክ ትልቅ ውጤት ሆኖ ተዘመግቧል፡፡ በታሪካዊው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ 10 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ሆኗል፡፡ የ3ኛው ዙር ወደ ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ድልድል ለ10ሩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚወጣው ከሳምንት በኋላ በካይሮ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከምዕራብና ከሰሜን አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሚገናኝበት እድል ያመዝናል፡፡ ብራዚል በ2014 እኤአ በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ 6 ኮንፌደሬሽኖች የተውጣጡ 203 አገራት መካከል በተለያዩ የማጣርያ ምእራፎች ሲደረግ የቆየው ፉክክር 34 ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ይሄው የማጣርያ ሂደት ሊጠናቀቅ 2 ወራት ቀርቶታል፡፡ በአዘጋጅነት ያለፈችውን ብራዚል ጨምሮ ጃፓን፤ አውስትራሊያ፤ ኢራንና ደቡብ ኮርያ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ናቸው፡፡ በቀረው የ27 ብሄራዊ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ኮታ በስድስቱ ኮንፌደሬሽኖች 67 አገራት የማለፍ እድል እንደያዙ ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ኮታ መሰረት ለአፍሪካ ዞን የተሰጠው እድል ለ5 ብሄራዊ ቡድኖች ነው፡፡ እነዚህን 5 ብሄራዊ ቡድኖች ለመለየት በአፍሪካ ዞን የሚደረገው የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ከ5 ሳምንት በኋላ በመጀመርያ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
በአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያ ከ10 ምድቦች በመሪነት ያለፉት 10 ቡድኖች ታውቀዋል፡፡ እነሱም ግብፅ፤ አልጄርያ፤ አይቬሪኮስት፤ ጋና፤ ኢትዮጵያ ፤ ኬፕቨርዴ፤ ጋና፤ ቡርኪናፋሶ፤ናይጄርያ፤ ሴኔጋል እና ካሜሮን ናቸው።
ከሳምንት በኋላ ለአስሩ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድልድል በካይሮ ከተማ ሲመጣ ከቀናት በኋላ በሚታወቀው የፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ መሠረት ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዥ ከፍተኛ እርከን ላይ የሚገኙ 5 ብሄራዊ ቡድኖች በአንድ የእጣ ማሰሮ ሌሎች ዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች በሁለተኛ ማሰሮ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ በማሰሮ 1 አይቬሪኮስት፤ ጋና፤ አልጄርያ፤ ናይጄርያና ኬፕቨርዴ አይስላንድ እንዲሁም በማሰሮ 2 ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሮን፤ ግብፅ፤ ሴኔጋል እና ኢትዮጵያ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ የዓለም ዋንጫ በሚያሳልፈው ጥሎ ማለፍ ከአይቬሪኮስት፤ ከጋና፤ ከአልጄርያ፤ ከናይጄርያ ውይም ከኬፕቨርዴ አይስላንድ ጋር የሚገናኝበት ሁኔታ የሚፈጠር ይመስላል፡፡ በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ የማሸነፍ እድል ቡድኖች እኩል 50 በመቶ ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፉ ‹አርኢቺ ስፖርት ሶከር ስታትስቲክስ ፋውንዴሽን› የመረጃ መዝገብ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ባለው ታሪክ መነሻነት የሚያገኘውን ውጤት ለመገመትም ይቻላል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጥሎ ማለፍ ሊገናኛቸው ከሚችላቸው 9 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ያለው የማሸነፍ ስኬት በመቶኛ ሲሰላ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በግምታዊ የጥሎ ማለፍ የጨዋታ ድልድል ላይ በማሰሮ 1 ሲደለደል ከአልጄርያ ጋር 50 በመቶ፤ ከአይቬሪኮስት ጋር 33.33 በመቶ፤ ከናይጄርያ ጋር 16.67 በመቶ፤ ከጋና ጋር 50 በመቶ የማሸነፍ እድል ሲኖረው ከኬፕቨርዴ ጋር በታሪክ ተገናኝቶ ስለማያውቅ ለመገመት ያስቸግራል፡፡ በተቀረ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አብሮ በማሰሮ 2 ለድልድል ከተመደበባቸው ቡድኖች ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ ከተፈጠረ ከቡርኪናፋሶ ጋር 50 በመቶ፤ ከሴኔጋል ጋር 0 በመቶ፤ ከግብፅ ጋር 16.6 በመቶ እንዲሁም ከካሜሮን ጋር 16.67 በመቶ የማሸነፍ እድል ይኖረዋል፡፡

Read 6246 times