Print this page
Monday, 16 September 2013 07:46

“ከሠማይ ወረደ” ተብሎ በጳጳሳት የተጐበኘው መስቀል ለህዝብ ይታያል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(42 votes)

                   በአቃቂ ቃሊቲ፣ በቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ፣ ባለፈው ነሐሴ 23 ቀን በቀስተ ደመና፣ በመብረቅና በነጐድጓድ ታጅቦ ከሠማይ እንደወረደ የተነገረለት መስቀል፣ በጳጳሳት የተጐበኘ ሲሆን፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለህዝብ እይታ እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት ለማንሳት የሞከረ ወጣት ተስፈንጥሮ በወደቀበት ለ4 ቀን ራሱን እንደሳተ የሚናገሩ የቤተክርስትያኑ አገልጋይ፣ ከምሽቱ 9 ሰዓት ከፍንዳታ ጋር አካባቢው በብርሃን ተሞልቶ ስናይ የእሳት ቃጠሎ መስሎን ነበር ብለዋል፡፡ እያንፀባረቀ በሃይለኛ ግለት ያቃጥል ነበር የተባለው መስቀል፤ በማህበረ ቅዱሳን መሪዎችና በጳጳሳት የተጐበኘ ሲሆን የኢየሱስን ስቅለት የሚያሳይ ወርቃማ ቅርጽ ያለው ነው፡፡
ወደ አቃቂ ከተማ ከሚያስገባው ዋና የአስፓልት መንገድ በስተግራ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ገላን ጉራ በሚባለው ስፍራ የዛሬ 5 አመት የተቋቋመው የገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ነሐሴ 23 ቀን የክርስቶስ ሰምራ በአለ ንግስ እየተከበረ እያለ ከሌሊቱ 9 ሰዓት የተከሰተው ግርግር ነው የዚህ ሁሉ መነሻ፡፡ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ የሰሙ እና የቀስተ ደመና ቀለማትን የተላበሰ ብርሃን የተመለከቱ ነገሩን ከዝናባማው የአየሩ ሁኔታ ጋር በማያያዝ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር የሚሉት የቤ/ክርስትያኑ መጋቢ፤ በነጎድጓድና በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት የታጀበ መስቀል ከሠማይ ሲወርድ አይቻለሁ ብለዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት ቀናት መስቀሉን ለማየት ወደ ቤተክርስትያኗ የሚጐርፉ ምዕመናን በርክተዋል፡፡
ባለፈው ሃሙስ ከአቃቂ ከተማ በማለዳ ተነስተን ከ2 ሠአታት የእግር ጉዞ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ስንደርስ፣ በጥቂት ምዕመናን ተሣታፊነት የእለቱ ቅዳሴ እየተከናወነ ነበረ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግቢው ከየአቅጣጫው የመስቀሉን ታሪክ ሠምተው በመጡ ምዕመናን ተሞላ፤ መስቀሉ ከሰማይ ሲወርድ አይቻለሁ የሚሉት መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፣ ስለ መስቀሉ አወራረድ ገለፃ ማድረግ የጀመሩት ከቅዳሴው በኋላ ነው፡፡
ግቢው ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኑ ህንፃ አጠገብ መስቀሉ የወደቀበትን ስፍራ እያመለከቱ ይናገራሉ -ቦታው በቆርቆሮ ታጥሮ ድንኳን ተተክሎበታል። መስቀሉ አርፎበታል ከተባለው ስፍራ አፈር እየቆነጠረ የሚቀርብላቸው ምዕመናን አፈር እየተመለከቱ የመጋቢ ሃዲስን ገለፃ ያዳምጣሉ፡፡
ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በአል ነሐሴ 23 ቀን የፀሎት ስርአት ከምሽቱ አምስት ሠአት አካባቢ እንደተጀመረ የሚያስታውሱት መጋቢ ሃዲስ፣ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ አካባቢው በቀስተደመና ብርሃን ደምቆ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምዕመናን ለዚህ ልዩ ክስተት ብዙም ትኩረት አልሰጡትም፤ ከዝናባማው የአየር ፀባይ ጋር በማዛመድ አቅልለው ነው የተመለከቱት ብለዋል መጋቢ ሃዲስ፡፡ የቀስተ ደመናው ብርሃን አንዴ ሲደምቅ፣ አንዴ ሲደበዝዝ መቆየቱን መጋቢ ሃዲስ ጠቅሰው፣ ከሌሊቱ 9 ሠአት ንፋስ ለማግኘት በካህናት መውጫ በር በኩል ስወጣ ግን ደብዛዛ የነበረው ብርሃን የበለጠ ደምቆ፣ እንደቀን ብርሃን ወገግ ብሎ ታየኝ ብለዋል፡፡
“አሻቅቤ ስመለከት ሠማዩ በነጭ ደመና ተከቦ ተመለከትኩ፡፡ አፍታም አልቆምየ፤ በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት የተጠቀለለ አንዳች ነገር በዝግታ ከሠማይ እየተገለባበጠ ሲወርድ አየሁ” ይላሉ መጋቢ ሃዲስ፡፡
ከቤተክርስቲያኑ ቤተልሄም አጠገብ ያለውን የአገር አቋራጭ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ማማ እያመለከቱ፣ “ከሠማይ እየተጠቀለለ የሚወርደው ነገር ከማማው አካባቢ ሲደርስ ነጐድጓዳማ ድምፅ ማሠማት ጀመረ” የሚሉት መጋቢ ሀዲስ፤ “መሬት ላይ ሲያርፍ በከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ አካባቢውን የእሣት ንዳድ በመሰሉ ብርሃን ሞላው” ይላሉ፡፡ “ቤተልሄሙ ተቃጠለ እያልኩ ብጮህም ድምፄን የሰማ ሰው አልነበረም፤ ለደቂቃዎች ያህል ለሠዎች እንዳይሠማ ሆኖ ታፍኖ ነበር” የሚሉት መጋቢ ሀዲስ፤ “ድምፄ መሰማት ሲችል ግን ፣ ካህናቱ ጩኸቱን ሰምተው ተደናግጠው ወደ ውጭ መጡ” ብለዋል፡፡ አንዳች አደጋ ደርሶ እሳት ተቀጣጥሎ ሊሆን ይችላል በሚል ድንጋጤ ሁሉም እሣቱን ለማጥፋት እንደተሯሯጠ ጠቅሰው፣ ነገር ግን በአካባቢው ከብርሃን በቀር የእሣት ቃጠሎ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል - መጋቢው፡፡
“አንድ የቤተክርስቲያናችን ወጣት አገልጋይ ወደ ደመቀው ብርሃን ተጠግቶ ለማየት ሞከረ፡፡ አንዳች ነገር ወደ ላይ አስፈጥንሮ መሬት ላይ ጣለው፡፡ ምዕመናን ተደናገጡ፡፡ የኤሌትሪክ መስመር ተበጥሶ ኮንታክት ፈጥሮ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ነበር ያደረብን” ሲሉም ተርከዋል፡፡ “የወደቀው ወጣት ምላሱ ተጐልጉሎ በወደቀበት ራሱን ስቶ ተዘርግቷል” የሚሉት መጋቢ ፍሰሃ፤ ከወደቀበት በጥንቃቄ አንስተን ፀበልና ቅባ ቅዱስ ብናደርግበትም አልተሻለውም ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ካህናቱ እንደምንም ወደ ብርሃኑ አካባቢ ተጠግተው የተመለከቱት፡፡ እናም በብርሃን የታጀበ መስቀል መሬት ላይ ወድቆ አዩ ብለዋል መጋቢው፡፡ ካህናቱና ምዕመናኑ በአግራሞት ሲመለከቱ ቢቆዩም የእሣቱ ወላፈን ይፋጃል ያሉት መጋቢ ፍሰሃ፤ በርቀት መጐናፀፊያ ተወርውሮበት እንዲለብስ እንደተደረገ ይገልፃሉ፡፡ የተቋረጠው ስርዓተ ማህሌት ከ10 ሰዓት በኋላ እንደቀጠለ የተናገሩት መጋቢ ፍሰሃ፣ በካህናቱ ትዕዛዝ ጠዋት 12፡30 ላይ መስቀል በወረደበት ቦታ ላይ ድንኳን ተተከለ፤ ብፁዐን አባቶችም በስልክ እንዲያውቁ ተደረገ ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በማግስቱ የአቡነ ተክለሃይማኖት ክብረ በል ስለነበረ ብዙዎቹ ጻጳሳት ወደ ደብረሊባኖስ፣ ቀሪዎቹም ወደየአድባራቱ ሄደው ስለነበረ መምጣት አልቻሉም ብለዋል - መጋቢው፡፡ ከበላይ አካላት በተነገረን መሠረት ለወረዳው ፖሊስ ካሳወቅን በኋላ፣ የፖሊስ ሃይል አካባቢውን ተቆጣጠረ” የሚሉት መጋቢ ሃዲስ፤ ቅዳሜ እለት የማህበረ ቅዱሳን አባላት መጥተው መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚያው እለት ከሰአት በኋላ ለመምጣት ቀጠሮ የሰጡ ጳጳሳት ግን ከአንድ ሰአት በላይ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በመጣሉና ጭቃው የማያስገባ በመሆኑ ከመንገድ ተመልሰዋል። በማግስቱ እሁድም አክራሪነትን በመቃወም ሰልፍ የሚካሄድበት ቀን በመሆኑ መምጣት አልቻሉም፡፡ ሰኞ እለት ነሐሴ 27 ቀን ግን በርካታ ጳጳሳት በቦታው ተገኝተው በበርካታ ምዕመናን ታጅቦ መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነስቶ፣ ወደ መቅደሱ እንዲገባ መደረጉን መጋቢ ፍሰሃ ተናግረዋል፡፡ በደረሰበት አደጋ ራሱን ስቶ የቆየው ወጣት፤ በ4ኛው ቀን መንቃቱንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ መጋቢ ሃዲስ ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቱ ሲጠየቅም፣ መስቀሉን ተመልክቶ ሊያነሳው እጁን ሲሰነዝር ከኋላው አንዳች ህፃን ልጅ የመሰለ ነገር ጐትቶ መሬት ላይ እንደጣለውና ከዚያ በኋላ የሆነውን እንደማያውቅ መግለፁን እኚሁ መጋቢ ተናግረዋል፡፡
መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነስቶ ሲገባ ከፍተኛ ግለት እንደነበረውና የተሸከሙት አባት “እያቃጠለኝ ነው” ሲሉ እንደነበር መጋቢ ፍሰሃ ገልፀዋል፡፡ መስቀሉ የሰው ስራ እንዳይሆን የተጠራጠሩ ካህናት መኖራቸውን ያመኑት መጋቢ ፍሰሃ፣ መስቀሉ ከምን እንደመጣ የሚያውቀው ፈጣሪ ነው ብለዋል፡፡
አቶ እንግዳው የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፣ መስቀሉ ከሠማይ ሲወርድ እንዳልተመለከቱ ጠቅሰው፤ በጳጳሣቱ ተነስቶ ወደ መቅደሡ ሲገባ ወርቃማ ብርሃን ነበረው ብለዋል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ሠዎችም ሌሊቱን ነጐድጓዳማ ድምፅ መስማታቸውንና በማግስቱም ይህን ክስተት በቤተክርስቲያኑ ከነበሩ ሰዎች ታሪኩ እንደተነገራቸው ገልፀዋል፡፡ ለአካባቢው ፀጥታ በማሰብ መስቀሉ በየእለቱ ለምዕመናን እንዳይታይ ከቤተክህነት ትዕዛዝ እንደተላለፈ ጠቅሰው፤ መስከረም 19ቀን 2006 ዓ.ም በቤተክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ መስቀሉን በይፋ ለእይታ ለማብቃት ቀጠሮ መያዙን መጋቢ ሃዲስ ተናግረዋል፡፡

Read 52229 times