Monday, 16 September 2013 07:49

ኮራጁ ማርክስ!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(8 votes)

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በአዕምሮዬ እየተመላለሰ የሚበጠብጠኝ ነገር ቢኖር የማርክስ መንፈስ ነው፡፡ ከ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን ፖለቲካ ውሰጥ ወሳኝ እና ገናና ሆኖ የዘለቀ ፖለቲካዊ አስተምህሮ እና ርዕዮተ ዓለም ነው ማርክሳዊነት፡፡
በልጅነት የማስታውሰው ደርግ እንዲሁም ነፍስ ካወቅሁ የመጣውና እስከዛሬም ያለው ኢህአዴግ እንደ ኮሶ አንጀታቸውን የተጣባው የአመራር መርህ ማርክሳዊነት ነው፡፡ በእኔ ግምት በዚህ ዓለም ላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቀጥሎ ስሙ በሰዎች ዘንድ ተደጋግሞ የተነሳ ቢኖር ካርል ማርክስ ይመስለኛል። ከፍተኛ የሆነ የህዝብ መነቃቃትን በመፍጠር፤ የፖለቲካ ነውጦችን በማውጠንጠን፤ የተበዳይነት ስሜትን በማጦዝ ሰፊውን የአለም ክፍል ያዳረሰ ተጽእኖ ፈጣሪ ነበር፤ ካርል ማርክስ፡፡ ከዘመኑ በፊት በነበሩ አሳቢዎችና ፈላስፋዎች፤ እንዲሁም በራሱ ዘመንም በነበሩ አሳቢዎች እና ፈላስፋዎች ከፍተኛ ተጽእኖ የተደረገበትና ተጽእኖ ማድረግም የቻለ ሰው ነው፡፡
ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርጉ ይመራበት የነበረው አብዮታዊት ኢትዮጵያና አሁን እያበበ ነው የምንባለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ አፍአዊ ካልሆነ በስተቀር ብዙም ለውጥ ያላቸው አይመስለኝም፡፡
ያኛው ወጣቶችን በጉልበት እያፈሰ ያዘምታል፣ አባልም ያደርጋል፡፡ ይሄኛው ደግሞ በድህነትና ውጥረት በመፍጠር አማራጮችን እያመነመነ ወጣቱን ወደ እራሱ ያግዛል፡፡ ያኛው ስለ ሀገር አንድነትና ወንበዴን ስለ መደምሰስ ሲያወሩለት ቃታ ከመሳብ ጣቶቹን ይሰበስባል፡፡ ይሄኛው ደግሞ ስለብሔሮች እኩልነትና አሸባሪዎችን ስለመዋጋት ሲዘምሩለት የገንዘብ ካዝናውን ይከፍታል፡፡ ሁለቱም የኔ መንገድ የጽድቅ ናት፤ ሌላው መንገድ ግን ፍጻሜው ሲዖል ነው የሚል ጽኑ እምነት አላቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም መንግስታት በአባታቸው ማርክስ በመሆናቸው ነው፡፡
ካርል ፖፐር የተባለው የሳይንስ ፈላስፋ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሳይንስ ምርምር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በማሳደር ይታወቃል፡፡ ሳይንስን እና አስመሳይ ሳይንስን ለመመርመር በሰራው መጽሐፉ The logic of Scientific Discoveries ውስጥ የካርል ማርክስን ሃልዮት እልም ያለ አስመሳይ ሳይንስ ነው ይለናል፡፡ ምክንያቱም ትችትንና ሌሎች አማራጮችን ከመቀጠልና ከመመርመር ይልቅ ማውገዝና ማስወገድን ይመርጣልና ነው፡፡ በፓፐር ትንታኔ አንድ ሃልዮት የሳይንስነት ማዕረግ የሚጐናፀፈው እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል ራሱን እየተቸ አማራጮችን ያሳየ እንደሆነ ነው፡፡ ያለዚያ አስመሳይ ሳይንስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከጥንቆላ የማይሻል አይነት ማለት ነው፡፡ ማርክሳዊያን ርዕዮት ዓለማቸው ሲተችባቸው በምክንያት ከመወያየት ይልቅ አስቀድመው አፍቃሬ ቡርዥዋ የሚል ስያሜ ይሰጡና አፈሙዛቸውን ያመቻቻሉ፡፡ ልክ በኛ ዘመን “የድሮ ስርአት ናፋቂዎች” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡
ካርል ማርክስ የተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ዘመንና አውድ ውስጥ ሆነው የጻፏቸውን ቅቡልና ወርቃማ ሃሳቦችን ለቃቅሞ ልክ እንደራሱ ወጥ ሥራ አስመስሎ ማቅረብ ችሏል፡፡ በጣም ምርጥ ኮራጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሃሳቦችን መልክ መልክ አላሲያዛቸውም ብዬ ለመሞገት ሳይሆን በዚህ ጽሑፌ ውስጥ የማቀርባቸው ማስረጃዎች ካርል ማርክስን የምንረዳበት ዋናዎቹ የማርክሲስት ርዕዮት ዓለም ፍሬ ጉዳዮች ማርክስ አንጡራ እሳቤ የተገኙ አለመሆናቸውን ለመጠቆም ብቻ ነው፡፡
ኩረጃ አንድ - surplus value (የተትረፈረፈ የሰው ጉልበት):- አዳም ስሚዝ እና ዴቪድ ሪካርዶ የተባሉ በእንግሊዝና በስኮትላንድ ታዋቂ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ናቸው የሃሳቡ አመንጭዎች። እነዚህ ምሁራን ከሚታወቁባቸው ሃሳቦች መካከል የጉልበት ሃይል እሴት (labor value) አንዱ ነው፡፡ በምርት አጠቃላይ ወጪ ውስጥ የሰው ጉልበት ምን ያህሉን ገንዘብ እንደሚፈጀው ለማስላት የሚረዳ ዘዴ የቀመሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ ሰዎች ሃሳብ በመነሳት ማርክስ “አላግባብ የተትረፈረፈ የሰራተኛ ጉልበት ቡርዡዋው እያግበሰበሰ ነው” የሚል ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ሠራተኛው ለቀን ከሚከፈለው በላይ ጉልበቱ በቡርዡዋ እየተበዘበዘ፣ ቡርዡዋው አላግባብ ትርፍ ያግበሰብሳል ይለናል፡፡ ቡርዡዋው ለወዛደሩ በቀን የሚከፍለውን ገንዘብ የሚያገኘው በወዛደሩ የጥቂት ሰዓታት ምርት ነው፤ ቀሪው የወዛደሩ ድካም ለቡርዡዋው የተትረፈረፈ ትርፍ እንዲያጋብስ የሚያስችለው ነው ብሎ ያምናል ካርል፤ ማርክስ። ስለዚህም በቀን ውስጥ የሚከፈለውን ያህል ብቻ ማምረት ለወዛደሩ ፍትሃዊ አሰራር ይሆናል፡፡
ኩረጃ ሁለት፡- utopian community:- በፈረንሳዊው ቻርልስ ፊዮረር ፍልስፍና መሠረት፤ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል የሆነባት፣ የሃብት ልዩነት የሌለባት፤ ማህበራዊ መደብ አልባ የሆነች አለም ማምጣት ይቻላል ብዬ ያስባል፡፡ ይህ በፈረንሳዮች አብዮት ዘመን ሲቀነቀን የነበረ ሃሳብ፣ ለማርክሳዊ መንግስት ሰማያት ግንባታ ታላቅ መሰረት ሆኖታል። እንደ ማርክስ አስተምህሮ ከሆነ ወዛደሮች ቡርዡዋውን ገልብጠው የሚፈጥሩቱ የወዛደሮች አምባገነንነት የተከማቸ የግል ሃብትን በማጥፋት፣ ቀስ በቀስ ወደ መደብ አልባ የእኩልነት ማህበረሰብ ይለወጣሉ ብሎ ያምናል፡፡ እናም አምሳለ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም የመሰለች ሃገር ገንብተው ሰዎች በእኩልነት ያለ ጭቆና ይኖራሉ፡፡
ኩረጃ ሦስት፡- “ከእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ” የተባለውን የማርክስን ዝነኛ ጥቅስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳቡን ያፈለቀውና የተነተነው ሉዊስ ብላክ የተባለ ጸሃፊ ነው፡፡ ሉዊስ ብላክ ማህበራዊ መርሆዎችን ሲተነትን ገቢን እና የሥራ ክብደት /መጠን/ እንዴት መሰራጨት እንዳለባቸው የጠቆመበት ጥቅስ ነበር፡፡ በካርል ማርክስ ስሌት መሰረት፣ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ መሃንዲስና ወዛደሩ ቢኖሩ፣ ገቢያቸውን የሚወስነው ፍላጎታቸው ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህም መሃንዲሱ ሁለት ቤተሰብ ቢኖረውና የወዛደሩ ቤተሰብ ቁጥር ደግሞ ስድስት ቢሆን የወዛደሩ ገቢ ከመሃንዲሱ ገቢ ሦስት እጥፍ ሊበልጥ ነው ማለት ነው፡፡ ይሰውረን! ነው መቸም፡፡
ኩረጃ አራት፡- (abolishing private property) የግል ንብረት ክልከላን በተመለከተ የፈረንሳይ ሶሻሊስት አንቀሳቃሽ ከነበሩት መካከል ዥን ጃኩስ ሩሶ እና ዮሴፍ ፑርዶኧ፤ የምጣኔ ሃብት ክምችት ከካፒታሊስቶች ወደ ሠራተኛው መዘዋወር እንዳለበትና የሃይል ዝውውሩን የተሳካ ለማድረግ ደግሞ የግል ንብረት ማፍራት ላይ ቁጥጥር እንዲኖር ይጠይቃሉ፡፡ ሰውን ክፉ ያደረገው ነገር የግል ንብረት የሚባለው ጉዳይ ነው ብለው ያስባሉ፤ እነዚህ ፈላስፎች፡፡ የግል ንብረት ለማፍራት በሚደረግ ግርግር ውስጥ ነው የሰዎች ጭቆና ስር የሚሰደው የሚል እምነት ይከተላሉ፡፡ ለካርል ማርክስ ታዲያ እንዲህ አይነት አስተምህሮ የተመቻቸና ከእራሱ ሃልዮት ጋር በቀላሉ የሚዋሃድ ሆኖለታል፡፡ በእኛም ሃገር አምስት መቶ ሺህ ብር የሃብት ጣሪያ ነበር። ዛሬ ዛሬ የአንዳንድ ልማታዊ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች ደሞዝ ሆኖ ሊያርፈው፡፡
ኩረጃ አምስት፡- (dialectical materialism) የጀርመኑ ፈላስፋ ሔግል ታሪክ ዲያሌክቲካል ነው ይላል፡፡ ዲያሌክቲካል የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ግጭት የሞላበት ተቃርኖ የሚያዋክበው ሁኔታን የሚገልጽ ነው በተለምዶ፡፡ አንድ የሆነ ቀዳማዊ ሃሳብ/ታሪክ ቢኖር ቀጣዩ የሚፈጸመው ነገር የቀዳማዊው ተቃራኒ የሆነ ሃሳብ/ታሪክ ነው ብሎ እንደማሰብ ነው (በግርድፉ)፡፡ የቁስ አካል ፍልስፍናን በመውሰድ ማህበራዊ ህይወትን ተነተነበት፡፡ በማህበራዊ ህይወታችን ስናመጣው የቡርዡዋ ስርአትን ለመገርሰስ መገዳደል ትክክለኛው መንገድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማመጽ እና መደምሰስ ጤናማና ዋነኞቹ መለወጫ መንገዶች ይሆናሉ፡፡
ኩረጃ ስድስት፡- ሰው የአካባቢው ውጤት ነው፤ አስተሳሰቡ በአካባቢው ካለው ቁስ አካል በሚኖረው መስተጋብር ይወሰናል/ይቃኛል/፡፡ ሉድዊንግ ፊዮርባኧ የተባለው የጀርመን ፈላስፋ፤ የማህበራዊና ፖለቲካዊ እሳቤዎችን መሠረት ሲተነትን፣ በቁስ አካላት ላይ ያለን ፍላጎት ቁልፍ መለኪያ መሆኑን ያስረግጣል፡፡ ሃሳብ የሚባል ነገር የለም ይለናል ካርል ማርክስ፤ ከፊዮርባኧ በተኮረጀ ሃሳቡ፡፡ ያለ እውነታ ቢኖር ቁስ አካል ነው፡፡ የቁሳቁስ እንጂ የሃሳብ አለም የለም፡፡ አካባቢያችን በሙሉ በቁስ አካላት የተሞላ ስለሆነ እኛም የቁስ አካላት ውጤን ነን እንጂ መንፈስ ምናምን… ሃሳብ የሚባል ጉዳይ የለም፤ አይኖርምም ነው የሚለን ካርል ማርክስ፡፡
ሉድዊንግ ፊዮርባ “አምላክ የሰዎች ፈጠራ እንጂ አምላክ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሰዎች ለፈጣሪ የሰጡት ባህሪያት የራሳቸውን አምሳያ ነው፡፡” ካርል ማርክስ ይህንን ሃሳብ በመውሰድ ሰዎች የቁስ አለም ውስጥ ስለሚኖሩ ሃሳቦቻቸውም የቁስ አካላት ውጤቶች እንጂ፤ ሰው በሃሳቡ ብቻ ያለ ቁስ አካላት አጋዥነት ያመጣው አንዳች ነገር የለም ይላል፡፡ ይሄን የፊዮርባኧ ፍልስፍና በቀጥታ በመኮረጅ ካርል ማርክስ፤ ሰዎች በራሳቸው ዛቢያ ላይ መሽከርከር ሲሳናቸው የሚጠለሉበት አምላክ የሚባል ነገር ፈጠሩ ይለናል፡፡
“ሃይማኖት የድሆች መጽናኛ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት የሰዎች ማደንዘዣ ነው፤ መንፈስ አልባ ለሆነው ማህበረሰብ መንፈስ ነው፤ ልብ አልባ ለሆነው ዓለም ልብ ነው” ሲል ያብራራል፡፡ በታሪክ ሂደት እንዳየነው ግን እራሱ ካርል ማርክስ ነው ለወዛደሮች መጽናኛ የሚሆን ርዕዮት አለም የፈለሰፈ። ማርክሳዊነት ለብዙ ስራ ፈቶችም ማደንዘዣ ሆኖ አገልግሏል፤ እያገለገለም ነው፡፡ ማርክስ ሃይማኖትን አጠፋለሁ በሚለው ርእዮት አለሙ፤ ሌላ አዲስ ማህበረሰባዊነት የተባለ የጭቁኖች/የወዛደሮች ሃይማኖት የፈጠረ ሲሆን ይሄው እስከዛሬም ካህናተ ማርክስ ካልተጠመቃችሁ እያሉ ይበጠብጡናል፡፡
አዲሱ ዓመት፤ በማርክሳዊነት የተኮረጀ ርእዮት አለም ውስጥ ሆነው መንፈሳቸውን አውከው የኛንም መንፈስ ከሚያመሳቅሉ የአልባኒያ ደብተራዎች በኢትዮጵያ መንፈስ ሰውሮን፤ ፍቅር አንድነት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብና ሰው የመሆን ማእረግ እንድንጎናጸፍ እመኛለሁ፡፡ እኛን እኛን የሚሸት ፍልስፍና እና መንግስታዊ ስርአት የኢትዮጵያ አምላክ ያድለን! “ፊውዳሎች ይውደሙ!” ሲሉ የነበሩትን “ማርክሲስቶች ይውደሙ!” አንላቸውም። ይልቁንም “ኢትዮጵያዊያን እንደአደይ አበባ ይለምልሙ!!!”

Read 5838 times