Monday, 16 September 2013 07:53

የዘንድሮን አዲስ ዓመት (2006) ተጭበርብረናል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(22 votes)

ባለፈው ዓመት ማተምያ ቤት የገባ ጋዜጣ ለአዲሱ ዓመት አልደረሰም!
አንድ ሚኒስትር ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር ሲያደርጉ ገለፃውን በጣም ያረዝሙትና ብዙ ሰዓት ይወስዳሉ፡፡ ታዳሚው እስኪታክተው ድረስም ያብራራሉ፡፡ ከፊሉ እያንቀላፋ ከፊሉ እየተንጠራራ ስብሰባውን እንደምንም ይካፈላል፡፡ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ሲጨርሱ በጣም ብዙ ሰዓት መፍጀታቸው ለራሳቸው ተሰማቸውና ይቅርታ ለመጠየቅ ፈልገው፣ ሰዓት አለማሰራቸውን እያሳዩ “ሳላውቅ ብዙ ጊዜያችሁን ወሰድኩባችሁ፣ ይቅርታ ሰዓቴን ስላልያዝኩኝ ነው” አሉ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ እጁን ያወጣና “ክቡር ሚኒስትር፤ ከጀርባዎ ካላንደር ተለጥፎልዎ ነበር እኮ!” አላቸው፡፡
እንግዲህ ሚኒስትሩ ይቅርታ እስከመጠየቅ ድረስ ከሄዱ አነሰም በዛም የህዝቡን ሰዓት በእንቶ ፈንቶ አባክነዋል ማለት ነው አሊያም ጊዜውን አጭበርብረውታል፡፡ እቺን ቀልድ ለመሸጋገርያ ያህል ጣል ካደረግሁላችሁ አሁን ወደ ዋናው ቁምነገር እንለፍ - ወደ ዋናው የዓመቱ መጭበርበር!
አባቶቻችን ሲተርቱ እድሜ የሰጠው ብዙ ነገር ያያል ይላሉ (ይሄም ተጭበርብሯል እንዴ?) እኔ ግን የፈለገ እድሜ ቢሰጠኝ አዲስ ዓመት እንዲህ እንደ ዘንድሮ ሲጭበረበር አያለሁ ብዬ በህልሜም በእውኔም አልሜም አስቤም አላውቅም፡፡ እውነቴን እኮ ነው--- እስከዛሬ የማውቀው ምርጫ (ያውም የሥልጣን ) ሲጭበረበር እንጂ አዲስ ዓመት?----በፍፁም ሲጭበረበር አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ ዘንድሮ ግን አዲሱ ዓመት (2006 ማለቴ ነው!) ዓይኔ እያየ በግላጭ ተጭበረበረ! (አዲስ ዓመታችንን መልሱልን!) ክፋቱ ግን እማኝ የሚሆኑ ታዛቢዎች አላስቀመጥንም (እንደምርጫ) ለነገሩ እኮ ምርጫውስ ቢሆን መች ከመጭበርበር ዳነ! (የተቃዋሚዎችን “መሰረተቢስ ወሬ” ሰምቼ እኮ ነው) እናላችሁ---- አረረም መረረም ከአሁን በኋላ አዲስ ዓመትን እንደወትሮው ለብቻችን ማክበር አንችልም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ምነው የተባለ እንደሆነ---- ተጭበርብረናላ! ስለዚህም በየዓመቱ የፈረደባቸውን የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች ልናስቸግር ነው ማለት ነው (የግድ አና ጎሜዝ መሆን እኮ የለባትም !)
እውነቴን ነው የምላችሁ ---- የኛ ነገር እኮ በጣም ይገርማል፡፡ ያለውጭ ጣልቃ ገብነት ራሳችንን ችለን የምንፈፅመው አንድ ነገር ቢኖረን በዓል ማክበር ነበር፡፡ እሱም ግን ይኸው ዘንድሮ ተጭበርብሮ አረፈው፡፡ ከአሁን በኋላ እኮ አዲስ ዓመትንም ያለ ውጭ አገር ታዛቢዎች አናከብርም ማለት ነው (አያምኑንማ!) የሚገርመው ደግሞ የኛ ሳያንስ የፈረንጆቹንም አዲስ አመት ማጭበርበራችን ነው። ምናልባት እናንተ አላስተዋላችሁት ይሆናል ---- ኢቴቪ ባለፈው ረቡዕ የአዲስ ዓመት ልዩ ዝግጅት ሲያስተላልፍ “እንኳን ለ2006 በሰላም አደረሳችሁ” ከሚለው የአማርኛ ፅሁፍ ቀጥሎ ፈረንጆቹም ለምን ይቅርባቸው ብሎ ነው መሰለኝ “Happy New Year 2014 ” የሚል ፅሁፍ አቅርቧል (አዲስ ዓመት ወደ እንግሊዝኛ ይተረጎማል እንዴ ?) ይታያችሁ-----የፈረንጆች አዲስ አመት እኮ ገና አራት ወር ይቀረዋል! (ቀላል ተጭበረበሩ!)
በነገራችሁ ላይ አዲሱን ዓመት ያጭበረበረን እንደ ምርጫ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እኮ አይደለም። ከተለያዩ አካላት ተውጣጥተው ነው፡፡ አዲስ ዓመታችንን በዋናነት ያጭበረበሩን ግን “ፒ ስኩዌር” የተባሉትን ታዋቂ የሙዚቃ ቡድን አባላት አስመጥተን በዋዜማው እናስቀውጣችኋለን በማለት ከ1ሺ ብር እስከ 2ሺ ብር የተቀበሉን ድርጅቶች ናቸው (የመሃሙድን “አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ---” ጋብዘናቸዋል!) እኛማ ምን እናድርግ --- ሰው እናምን የለ! ሲቪያቸውን ሳናይ ዝም ብለን ብራችንን መዘዝን (ኢቴቪ እኮ ነው የሰራልን) እናማ የበዓሉ ዋዜማ አንድ ቀን ሲቀረው ኮንሰርቱ ተሰርዟል ተባልን (አዲስ አመት ተሰርዟል እኮ ነው ያሉን!) ምክንያታቸው ደግሞ ግርም ይላል ---- አንዴ በውጭ ምንዛሪ እጥረት (ብሔራዊ ባንክ እንዳይሰማ ብቻ!) ----- አንዴ ደግሞ በትራንስፖርት ችግር (መቼም አየር መንገድ አልሰማም!) ወዘተ--- መምጣት አልቻሉም አሉንና አዲስ ዓመታችንን አጭበረበሩብን፡፡ እውነቴን ልንገራችሁ አይደል---- ህዝቡን ያበገነው እኮ የሙዚቀኞቹ መቅረት አይደለም---- የአዲሱ ዓመት መጭበርበር እንጂ! (ለማየት ለማየትማ እነ ቢዮንሴንም አይተናል እኮ!)
የባሰው ደግሞ የማን መሰላችሁ? የኢቴቪ! በዋዜማው ሌሊት ያደረገንን አይታችኋል? (ከተኛችሁ ተገላግላችኋል) “አይዟችሁ እኔ እያለሁ አዲስ ዓመትን አትጭበረበሩም” አለና ዋዜማውን አንዴ ቬላ ቨርዲ፣ አንዴ አዝማሪ ቤት፣ ሲቸግረው ደግሞ ያለፈ የዋዜማ ዝግጅት እያቀረበልን ሲያንከራትተን አደረ (ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ --- አሉ!) አንዳንዶች ደግሞ በሪችትም ተጭበርብረናል ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ (የመጭበርበር ዓመት ሆኖ አረፈው እኮ!) “ሪችት ይተኮሳል ተብለን እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት እንቅልፍ እያዳፋን ብንጠብቅም እንኳን ሪችት ጥይትም አልተተኮሰም” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል - አዲሱን ዓመት ተጭበርብረናል ባዮች። እኔ እንኳን ሪችቱ መቅረቱ ብዙም አላስቆጨኝም። ለምን መሰላችሁ? የእኛ ባህልና ወግ አይደለማ! ዋናው ነገር ማለዳ ላይ 21 ጊዜ የሚተኮሰው መድፍ እኮ ነው፡፡ እሱም አልተተኮሰም እንዳትሉኝ ? (በፍፁም አይደረግም!)
የዘንድሮ የአዲስ ዓመት መጭበርበር በየዘርፉና በየአቅጣጫው ይመስላል፡፡ እስቲ በግሉ ፕሬሱ ላይ የተፈፀመውን የአዲስ ዓመት መጭበርበር ደግሞ እንመልከት፡፡ ለምሳሌ አዲስ አድማስ ጋዜጣ አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ጳጉሜ 5 ቀን 2005 ዓ.ም የሚወጣ ልዩ እትም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ መቼ ቢወጣ ጥሩ ነው? መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም! ባለፈው ዓመት ማተምያ ቤት የገባ ጋዜጣ እኮ ለአዲሱ ዓመት አልደረሰም (ይሄስ--- ከመጭበርበርም ይብሳል!) የዚህ አስደናቂ ገድል ባለቤት ደግሞ ማን መሰላችሁ? በአገሪቱ የህትመት ታሪክ ብዙ ብዙ ድንቅ ገድሎችን የሰራውና በንጉሱ የተቋቋመው ብርሐንና ሰላም ማተምያ ቤት ነው። (“አልቻልኩምና አግዙኝ” ማንን ገደለ?) እስቲ ይታያችሁ---- “በኢኮኖሚ በፍጥነት እየተመነደጉ ካሉ አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ---” እያሉ መዘገብ የጀመሩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ ይሄን አሉታዊ መረጃ ቢሰሙ ምን ሊሉ ነው? (“አፋችንን በቆረጠው!”ማለታቸው እኮ አይቀርም!)
እኔ የምለው ግን --- ሰፊው ህዝብ ህገመንግስቱ ያጎናፀፈውን መረጃ በወቅቱ የማግኘት መብት ሲነፈግ ኢህአዴግ ዝም ብሎ ያያል ማለት ነው? (“መረጃ እየተጭበረበረ” እኮ ነው!) እውነት ግን ለዚህ ተጠያቂው ማነው? (ብቻ የኢኮኖሚ እድገታችን ያመጣው ጣጣ ነው እንዳትሉኝ!) እግረ መንገዴን ለመንግስት ወይም ለአውራው ፓርቲ አንድ ቀላል ግን ወሳኝ የሆነች ጥያቄ ጣል አድርጌ ልለፍ። ለምንድነው መንግስት ትላልቅ የግል ማተምያ ቤቶች እንዲቋቋሙ የማያበረታታው? ማተምያ ቤትም እንደ ቴሌ ገንዘብ ማተምያ ማሽን ከሆነ በግልፅ ይነገረንና አርፈን እንቀመጥ! (“ፖለቲካዊ ውሳኔ” ይሆን እንዴ ?) የሚገርማችሁ ግን በ93 ዓ.ም የታተመ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ወይም መግለጫ አንብቤአለሁ “በኢንተርኔት ግንኙነት መስተጓጎል ምክንያት የዚህ ሳምንት ሳምንቱ በታሪክ ውስጥ አልተዘጋጀም። ዕድሜ ለቴሌ!” ይኸው ከ13 ዓመት በኋላ ደግሞ ቴሌ ብቻ ሳይሆን ለሶስት- ማተምያ ቤት፣ መብራት ኃይልና ቴሌ ተባብረው የህዝቡን መረጃ የማግኘት ህገመንግስታዊ መብት እየነፈጉ ነው፡፡ (ድብቅ አጀንዳ ካላቸው ይንገሩን !)
በነገራችሁ ላይ በዛሬው የፖለቲካ ወግ ስለመጭበርበር በስፋት ያወጋነው “አዲስ ዓመት ተጭበረበረ” ብለን ነው እንጂ መጭበርበርማ ለሃበሻ ልጅና ለጦቢያ አዲስ ነገር ሆኖ እኮ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ሳንጭበረበር ውለን አድረን እናውቃለን እንዴ!?
እስቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ስሟቸው ---- የዘወትር እሮሮአቸው ምንድነው? “ህገመንግስቱ ያጎናፀፈንን በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ራሱን አውራ ፓርቲ እያለ የሚጠራው ኢህአዴግ አጭበረበረን” የሚል እኮ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም እኮ በተቃዋሚዎች ተጭበረበርኩ እንዳለ ነው (መንግስትም ይጭበረበራል እንዴ?) አዎ ኢህአዴግም “ለሰፊው ህዝብ ለማስፈን ያቀድኩት ሰላምና ልማት በተቃዋሚዎች እየተጭበረበረብኝ ነው” ሳይል ቀርቶ አያውቅም፡፡ ይሄ ዓይነቱ የተጭበረበርኩ አቤቱታ እንግዲህ በአዘቦት ቀን ብቻ የሚሰማ ነው፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር የምንሰማው የመጭበርበር ስሞታ ደግሞ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ስላልሆነ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይዘንለት እንለፈው፡፡
ሰፊው ህዝብ (እኛ ማለት ነን!) ደግሞ የራሱ በርካታ የተጭበረበርኩ አቤቱታዎች አሉት (ጆሮ የሚሰጠው አጣ እንጂ!) ለምሳሌ በእያንዳንዷ ሻማ እያበራን ባደርንባት ምሽት ሁሉ መብራት ተጭበረበረናል፡፡ ብጫ ጀሪካን እየያዝን በምንዞርባትና ውሃን እስከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በምንጠብቅባት ውድቅት ሌሊት ሁሉ ደግሞ ውሃ ተጭበርብረናል፡፡
በሞባይል ስልካችን ደውለን የምንፈልገውን ሰው ማግኘት ሲያቅተንም በኔትዎርክ እየተጭበረበርን መሆኑን ካወቅንም ቆየት ብለናል፡፡ በታክሲ እጥረት ሳቢያ በወረፋ ስንገላታ ደግሞ በትራንስፖርት መጭበርበራችንን እናውቀዋለን፡፡ (እድሜ ለቀጣና ስምሪት!) እኒህ ሁሉ ጠቅለል ሲደረጉ አውራው ፓርቲ በምርጫ ሰሞን አሰፍነዋለሁ እያለ ምሎ በሚገዘትለት የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በሚገባ መጭበርበራችንን እንገነዘባለን (ኢህአዴግም እኮ አልካደውም!) አሁን ትንሽ ያሳሰበን ለምን መሰላችሁ? ማጭበርበሩ የተጀመረው ገና በአዲሱ ዓመት መጀመርያ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ (እስቲ አንድዬ ይሁነና!)
ሴትየዋ አንድ አዋቂ ዘንድ ትሄድና “እጣ ፈንታዬን ንገሩኝ!” ትለዋለች፡፡ አዋቂው የሥነፈለክ እውቀት ያለው ነውና ኮከቧን አየላት፡፡ መዳፏንም አነበበላት፡፡ ከዚያም “የእኔ እህት 30 ዓመት እስኪሞላሽ ድረስ መከራና ጉስቁልና እንደ ጉድ ይፈራረቁብሻል!!” አላት፡፡ ሴትዮይቱም በጣም በመጣደፍ “ከዚያስ--- ከ30 ዓመት በኋላስ እንዴት እሆናለሁ?”
አዋቂውም “ከዚያ በኋላ እንኳን ምንም ችግር የለም - ትለምጂዋለሽ!” (መጭበርበርን ከመልመድ ያውጣን!) መልካም አዲስ አመት ለሁላችንም!! (በተለይ ደግሞ ለብርሐንና ሰላም ማተምያ ቤት!)

Read 4567 times