Monday, 16 September 2013 08:21

ጥበብ (ዘ -ፍጥረት)

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ጥሩ የጥበብ ፈጠራ ምን አይነት ነው? መካሪ ነው፤ ዘካሪ፣ አስተማሪ፣ ህይወትን የሚያሳይ መነጽር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የዋህ አስተያየቶች ናቸው፡፡ ምንድነው የዳንስ ትርጉም?...ሰው ሲደንስ ተደስቶ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በለቅሶም ሙሾ ሲያወጣ ይጨፍራል፡፡ ደረቱን እየመታ፡፡ ለዚህ ነው ለውበት ሀሊዮት ልናገኝ የማንችለው፡፡ ታሪክ ለመዘከር ጥበብ ያስፈልገዋል፡፡ ጥበብ ላይ ነፍስ ለመዝራት ግን ታሪክ አያስፈልገውም፡፡
የፈረንሳይ ቋንቋ ትርጉሙ ምንድን ነው? እንደማለት ይሆንብናል፡፡ የፈረንሳይኛን ቋንቋ ወደ አማርኛ እናስተረጉማለን እንጂ…የፈረንሳይኛ እና የአማርኛ ቋንቋ ምንድነው ትርጉማቸው ልንል አንችልም፡፡ የሃሳብ ቁመት ስንት ነው ብሎ ከመጠየቅ የተለየ ስላልሆነ፡፡
                                                   * * *
ጥበብ ከራሱ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም። ብቸኛ ነው፡፡ ጥበብ የተለምዶውን የህይወት፣ የማህበረሰብ የቀድሞ ትርጉም አይቀበልም። ደራሲውን፣ ገጣሚውን፣ ሰአሊውን በማወቅ ከጠቢቡ አኗኗር በመነሳት፣ ጥበቡን መተርጐምም አይቻልም፡፡ የሰውየው ስነልቦና የጥበብን ስነልቦና ለማጥናት አይጠቅምም፡፡
ቫንጐ ያረጁ ጥንድ ጫማዎች ስሏል፡፡ ምንም አዲስ ነገር አልነበራቸውም አሮጌዎቹ ጫማዎች በስዕል ላይ እስኪቀርቡ ድረስ፡፡ Defamiliarization የጥበብ መንገድ ነው፡፡ (በብረት የተሰራ ሃውልት ከተሰራበት ጊዜ አንስቶ ብረት አይደለም፡፡ ከብረቱ ቀድሞ የሚጠራው “የብረት ምን?” የሚለው ነገር ነው፡፡) ከተለመደው ውስጥ ያልተለመደውን ማግኘት፡፡ ነገርዬው ከሚኖርበት አለም ነጥለን ስንገልፀው፣ በሱ ዙሪያ አዲስ ጥቅል የእውነታ ማስተሳሰሪያ በሰው ግንዛቤ ውስጥ ይፈጠራል፡፡
ከጐዶሎው ውስጥ ሙሉነት (holistic) በተሻጋሪ ከፍታ (transcendental aspect) ይወለዳል፡፡ የተወለደ ልጅ ምንድነው ትርጉሙ፣ ሲያድግ ምን ይሆናል፣ የተወለደበት አላማ ምንድነው? የወለደውን አባቱን ለምን አይመስልም? ለማለት አይቻልም፡፡ አባቱን ካልመሰለ “ውሸት ነው” ብላ ህልውና በራሷ እጅ አታጠፋውም፡፡ ተፈጥሮ ውበት ኖሯት ትርጉም ላይኖራት እንደሚችለው ፈጠራም ይሄንኑ ተከታይ ናት፡፡
ለጥበብ ፈጠራው ትልቅነት መሰረቱ ፈጠራው ራሱ እንጂ ፈጣሪው አይደለም፡፡ ግጥሙ ባይኖር ገጣሚው ገጣሚ ባልተባለ ነበር፡፡ በሆነ ምክንያት ጥበቡ ሳይፈጠር ቢቀር ኖሮ፣ ስለ ስራውም ሆነ ስለ ሰሪው መመራመር፣ መጠየቅ አይቻልም ነበር። ስሪቱ የሰሪው እና የስሪቱ ቅንጅት ቢሆንም…ውጤቱ ከድምሩ በፊት ከነበሩ ማንነቶች በላይ ነው፡፡ ስለመነሻው በማጥናት መድረሻውን ማወቅ ወይንም መስራት በውበት እውነታ አይቻልም፡፡ መነሻውም መድረሻውም ውበቱ ነው፡፡ Its an end in itself.
ከመድረሻው ውስጥ ሌላ መድረሻ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ጥበቡ ራሱን በራሱ አያበዛም፡፡ በተመልካቹ ስሜት ውስጥ ግን ሃሳብን ሊያበዛለት ይችል ይሆናል፡፡
The work is to be released the artist into pure self-subsistence. It is precisely in great art that the artist remains inconsequential as compared with the work, almost like a passage way that destroys itself in the creative process for the work to emerge.
ስራው (ጥበቡ) በራሱ የመናገር ነፃነት አቅም ካልተሰጠው ውበት ደረጃ አይደርስም፡፡ ምን ማለት እንዳለበት አስቀድሞ የሚያውቅ ገጣሚ ውበትን ሳይሆን ስብከትን ነው የሚያበረክተው፡፡ ስብከቱ ለህይወት እንጂ ለጥበብ እውነታ ምንም የሚፈጥረው አዲስ ነገር አይኖረውም፡፡
Inspiration ጥበብ በራሱ አንደበት ስንፈቅድለት የሚከሰት ነገር ነው፡፡ ምን እንደሚናገር አስቀድመን ልናውቀው አንችል፡፡ “How do I know what I think until I see what I say” እንዲል ደራሲው E.M Forester. አርቲስቱ የተገለፀለትን የሚከተል ነው፡፡ መገለጥ ከሌለ አርቲስቱም አርቱም የለም። ህይወት እና ሞት በሌሉበት ትንሳኤ” ሊታሰብ አይችልም፡፡ ጥበብ ከሰው ልጅ ህይወት እና ሞት ውስጥ የሚወለድ ትንሳኤ ነው፡፡
የመገለጥ ብርሃን የመግለጫ መንገዱን Style አብሮ ስለሚሠራ ይዘትና ቅርጽን በጥበቡ ላይ ለያይቶ መገንዘብ አይችልም፡፡
The power of disclosure itself is not our own it is not a human creation- the artist can compose only what of itself gathers together and composes itself.
የፈጠራ የጥበቡ ባለቤት በዚህ ረገድ ጥበበኛው አይደለም፡፡ የውሃው ባለቤት ምንጩም የፈሰሰበት ቧንቧም እንዳልሆኑት፡፡
የተፈጠረው ጥበብ ውበት የሚሆነው ብቸኛ (Singular) መሆኑ ላይ ነው፡፡ አርቲስቱንም፣ ተፈጥሮንም፣ ህይወትንም አለመምሰሉ ላይ፡፡ አለመምሰሉ፤ ልዩ እና ብቸኛ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ አካፋ፤ የፈለገ ልዩ እና በአዲስ መንገድ በአዲስ ፋብሪካ ወይንም ቅርጽ የተሰራ ቢሆን እንኳን ፍጡርነቱን ከግልጋሎቱ መነጣጠል አይቻልም፡፡ አካፋን አካፋ ወይንም ማንኪያ ብለን ብንጠራው የሆነ ነገር ከማፈስ ወይንም ከማማሰል ውጭ ጥቅም ሊኖረው አይችልም፡፡ የራሱ ለራሱ የሆነ ጥቅም ማለቴ ነው፡፡
“the work of art is similar rather to the more thing which has taken shape by itself and is self contained.
በድንጋይ የታነፀ ቤት፣ ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ጠቅልሎ የያዘ ነው፡፡ ድንጋይ እና ቤት ነው፡፡ ድንጋዩ ከተራራ ተፈንቅሎ የመጣ ሊሆን ይችላል። ተራራው፤ የተፈጥሮ መወኪያ (representation) መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቤት ግን፤ ተፈጥሮ ውስጥ የምናገኘው ነገር አይደለም፡፡ በተጨባጩ ውጫዊ እውነታ ላይ ቤትን የሆነ ወይንም የሚመስል ነገር የለም፡፡
በ“World” እና “earth” መሀል ያለ ግንኙነት በሰው አማካኝነት የተቋጠረ ነው፡፡ በተጨባጭ የሚዳሰሰው፣ የሚታየው፣ የሚለካው እና የሚመዘነው ነገር “Earth” ነው (“አፈር” ማለት ነው ሀሌታ ትርጉሙ)፡፡ አፈሩ በሰው ምክንያት “አለም” ይሆናል፡፡ ድንጋዩ በሰው ምክንያት “ቤት” ወይንም ህንፃ እንደሆነው፡፡ የአካፋ እና የማንኪያ ግልጋሎትም ሆነ ትርጉም ሰው እስካለ ድረስ ብቻ እውነት ይሆናል፡፡ ለራሳቸው እንደራሳቸው ምንም ትርጉም የላቸውም፡፡
ጥበብ ግን ከዚህም ደረጃ በጥቂቱም ቢሆን ከፍ ያለ ነው፡፡ ለራሱ እንደራሱ…በሰው ልጅ አሊያም ከተፈጥሮ ምክንያትም ሆነ ትርጉም ሳይቀዳ ህልውና አለው፡፡ ከድንጋዩ የታነፀው ቤት በሰው አማካኝነት ሲፈጠር…በመፈጠሩ ድንጋዩን እንዲጠፋ ወይንም ህልውናውን እንዲያጣ አያደርገውም፡፡
እንዲያውም፤ በአፈር ቋንቋ ይመዘን፣ ይሰፈር፣ ይገለጽ የነበረውን objectivityወደ ሌላ ባለ (subjective) እውነት ከአፈሩ ውስጥ ይፈጥረዋል፡፡ ይህም ፈጠራ ትርጉም ካለው ለሰው እንጂ ለተፈጥሮ/እግዜር አይደለም፡፡ (አዳም መጀመሪያ አፈር ነበር/በመጨረሻ ወደ አፈር ቢመለስም አይገርምም፡፡ ነገር ግን በፈጣሪው አማካኝነት በተሰጠው ትንፋሽ ፍጡር ወይንም ሰው ሆነ፡፡ ወደ ቀድሞው መሰረቱ ቢመለስ እንኳን ከቅድመ ሞቱ በፊት የነበረው ማንነቱ፣ ከሞቱ በኋላ ያለውን አይመስልም፡፡ ድሮ አፈር ከነበረ ወደ አፈር ተመልሶ ከመግባቱ በፊት ግን ሰው ነበር፡፡ የተፈጠረ ነገር ቢጠፋ እንኳን ተከውኖ እንደነበር ግን መካድ አይቻልም፡፡ የደራሲው ፈጠራ ከመዛግብት ላይ ቢፋቅ እንኳን ፈጠራው መወለዱ ሊፋቅ አይችልም፡፡
“እኔ ጨረቃን ሳሳየው እሱ ጣቴን ያያል” እንደሚለው ብሂል፤ ቤቱን ሳሳየው ቤቱ የተገነባበትን ድንጋይ የሚያይ ሰው፤ ውበትን ወደ ተራ ማንነቱ (አፈር) ለመቀየር ስለፈለገ ነው፡፡ ቤቱን ሳሳየው የቤቱን የፈጠራ ውበት እንደመነሻና መድረሻው (an end in itself) መገንዘብ ያልቻለ መስተሀልይ፣ ለውበት እውቀት ዝግጁ አይደለም፡፡
የግጥሙ፣ የድርሰቱ፣ የስዕሉ ትርጉም ግጥሙ፣ ድርሰቱ፣ ስዕሉ ራሱ ነው፡፡ ሰለሞን ደሬሳ እንደሚለው፤ ግጥሙ እንደአጋጣሚ የተለያዩ የህይወት ትርጉሞችን ተንተርሶ ሊገኝ ይችላል። ሰባኪ፣ አስተማሪ፣ አራሚ ሊሆን ይችላል። በድንጋይ የተሰራ ቤት የድንጋይ ባህሪዎችን ተላብሶ እንደሚገኘው፡፡ በብረት የተሰራ ሀውልት የብረት ባህሪዎችን በተጨባጩ (ሳይንሳዊ) ልኬት እንደሚንተራሰው፡፡ ሰው እንደ እንስሳት አለም ስጋን ይለብሳል፡፡ ግን ከለበሰው ስጋ በላይ የሚያስብ ፍጡር ነው፡፡ ሃሳቡን በንግግር መግለጽ ይችላል፡፡

Read 3080 times