Monday, 16 September 2013 08:22

ድንቅ የአዲስ ዓመት ስጦታ! “የብርሃን ፈለጎች”

Written by  በቅዱስ ሰውነት
Rate this item
(9 votes)

“The Old Man and The Sea” የገናናው አሜሪካዊ ደራሲ ኸርነስት ሄሚንግዌይ ዝነኛ ስራ ነው፡፡ አንብበን ተደንቀን በልባችን የያዝነው እንዳለ ሆኖ፣ የዘመነኞቹን ሀያሲያን አንጀት አርስ ውዳሴም አድምጠናል፡፡
“ከጽሁፉ አንድ ቃል ቢወጣ ወይም ቢቀየር ኖሮ፣ ጠቅላላ ድርሰቱ ሌላ መልክ ይኖረው ነበር!”
በእኛ የቅርቡ የስነ-ጽሁፍ ዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከልቤ ይሄንን ያሰኘኝ የበዕውቀቱ ስዩም “እንቅልፍ እና ዕድሜ” ነበር፡፡ ብዙ ሃሳብ በተጫነባቸው ቃላት እና አረፍተ ነገሮች የተገነባ ህያው ልብ ወለድ!
ጊዜ አለፈ፡፡ ቀጥሎ በመጡት ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ስር ከሚወጡ ማለፍያ ሳምንታዊ ጽሁፎች መካከል “አለማየሁ ገላጋይ” በተሰኘ ስም የሚቀርቡ መጣጥፎች ልቤን ይገዙት ጀመር፡፡ ደፋር፣ ምሉዕ እና ጥልቅ ትንታኔዎች፡፡ ማነው ይህ ሰው? የዘወትር ጥያቄዬ ሆነ፡፡ በራሱ ምን ሰርቷል? ስራዎቹ ምን ያህል ናቸው? ምንስ አቅም አላቸው? …

እነሆ አለማየሁ!
ከዕለታት በአንዱ፣ እንዲሁ በአጋጣሚ፣ እኔ እና አለማየሁ ተገናኘን፡፡ ያገኘሁት ሰውየውን ሳይሆን የበኩር ስራውን “አጥቢያ”ን ነበር፡፡ አራት ኪሎ፣ ዩኒቨርሳል መጽሃፍት መደብር ውስጥ፡፡ አየሁ የቃላት ተዓምር በ”አጥቢያ”፡፡ ሰማሁ ክሱት ትንቢት ከ”አጥቢያ”፡፡ በቃ፣ አለማየሁ የቀን ተቀን የወሬ ርዕሳችን ሌላ ቀለም፣ ሌላ አጀንዳ ሆነ፤ ለእኔ እና ለጓደኞቼ፡፡ ይህ ሰው ማን ነው? ሌላ የተራ አንባቢ ጥያቄ፡፡ የት ተወለደ? ምን ተማረ? መቼ? እንዴት? እስከ ወዲያኛው መልስ አልባ ጥያቄዎች፡፡ በከፊልም ከሰውየው ጋራ ያስተዋወቀን የታሪክ ተመራማሪው ብርሃኑ ደቦጭ ነበር … ሊያውም በጣም በቅርብ፡፡
በግሌ የእርሱን ስራዎች ከሌሎች ከምወዳቸው ጸሃፊዎች ስራዎች ጋር የማነፍነፍ ያህል ማሰስ ተያያዝኩ፡፡ ከአዲሱ ሚሊኒየማችን ማግስት ጀምሮ ድንቃ ድንቅ የልቦለድ ስራዎቹን “ቅበላ”ን እና “ኩርቢት”ን፣ ጥልቅ ሂሳዊ ፍተሻውን “ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ህይወትና ክህሎት”ን፣ ፍልስፍና ነክ የትርጉም ስራውን “የፍልስፍና አጽናፍ”ን፣ እና ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ዳሰሳውን ያቀረበበትን “ኢህአዴግን እከስሳለሁ!” እንዲሁም በዚሁ ክረምት በአርትኦትና መለስተኛ ጽሁፍ በማዋጣት የተሳተፈበትን “መልክዓ ስብሃት”ን በተከታታይ አቀረበልን፡፡ አስገራሚ ትጋት ነው። በጠቅላላ ስራዎቹ እጅግ በጣም ድንቅ የሚሰኙ ናቸው፡፡ ሰውየው ሰፊ ንባብ እንዳለው ያስታውቃል።

የብርሃን ፈለጎች
ይህ የአለማየሁ ገላጋይ ሌላው ትንግርታዊ ልብወለድ ነው፡፡ እንደ አዲስ ዓመት ውድ ስጦታ የቆጠርንለት፡፡ ያው ያ ምትሃታዊ የስነ ጽሁፍ ክህሎቱ እንዳለ ነው፡፡ ወትሮም የምናውቅለት አስደናቂ ቃላት አጠቃቀሙ፣ ውብ ገለጻዎች፣ ማራኪ የገጸ-ባህሪ አሳሳሉ እመርታ ታይቶባቸዋል፡፡ ጭብጡም እግዚኦ! የሚያሰኝ ምጥቀት ይዟል፡፡
በሁለት ክፍል የተሰደሩት ውብ ታሪኮች ልጅነት እና ጉርምስናን ጠልቀው ገብተው ይመረምራሉ፡፡ ልጅነት፣ በክፍል አንድ “የግንፍሌ ማለዶች” ስር፣ ጉርምስና፣ በክፍል ሁለት “የሞጆ ቀትሮች” ስር ቀርበዋል፡፡ አሁን አሁን እየተለመዱ እንደመጡት፣ በበርካታ ጸሃፊያን እንደሚቀርቡት፣ የልጅነት ወጎች እዚያው ልጅነት ላይ ተቀንብቦ አለመቅረቱ፣ በተራኪው “መክብብ” ህይወት ውስጥ የጉርምስናን ምስቅልቅል የሽግግር ወቅቶች ለማሳየት መጣሩ፣ ለነባራዊ ደቃቅ መሳይ ክስተቶች ጭምር ስውር ምክንያትና ውጤት ለማቅረብ መትጋቱ፣ በተለይ ባብዛኛው ጸሃፊያን ዘንድ እንደመዘንጋት በተባሉት ከ13 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ (የጉርምስና ዓመታት) ራስን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ለመቅረፅ ከቤተሰብ-ማህበረሰብ አንስቶ እስከ እግዜር ድረስ የሚዘልቅ ውስጣዊም ውጪያዊም ግጭት፣ በትናንት እና በነገ መሃል (በልጅነትና በአዋቂነት መንታ መንገድ) መሰፋት እና መወጠር እና የመሳሰሉት ቁምነገሮች ልቦለዱ የመረመራቸው የተዘነጉ እውነታዎች ናቸው፡፡
የመጀመሪያው ክፍል ሌጣ አጫጭር 14፣ ሁለተኛው 22 ባለ ርእስ ምዕራፎችን አካተዋል፡፡ የልቦለዱ ማሰሪያ ቁልፍ ድህረ ታሪኩ ነው፡፡ በዋዛ እንዳይታለፍ!!!

አዳም እና አለማየሁ
ሃያሲ አብደላ እዝራ “ስለ መጽሐፉ” አስተያየት ሲሰጥ “የአዳም ረታ በጐ መንፈስ ያረፈበት አብይ ልብ ወለድ” ይለዋል፡፡ እውነትም ታዲያ “ኩርቢት” እና ይሄ “የብርሃን ፈለጐች” በአዳም ረታ ስም እንኳ ቢታተሙ ያለማወላወል የምንቀበላቸው አይነት ናቸው፡፡ ልጅነት ላይ ማተኮራቸው፣ የተቡ ቃላት መጠቀማቸው፣ ስውርነታቸው እና እጅግ ጥልቅ እይታዎቻቸው መሳ ለመሳ የሚያቆማቸው የወል ገንዘባቸው ነው፡፡ በ”ግራጫ ቃጭሎች”፣ በ”ትርንጐና ገብረ ጉንዳን” ያስተዋልነው የአዳም ሃይል ከላይ በጠቀስናቸው የአለማየሁ ስራዎች ውስጥ ተደግመዋል፡፡ በእርግጥ ለእኔ አለማየሁ ጉልበቱ የተገራ አዳም ሆኖብኛል፡፡ በአዳም “ትንቢተ ቁራ” ውስጥ እንደምናየው ያለ በቅንፍ ውስጥ ገብቶ ሶስት እና አራት ገጾች ገለጻ መስጠትን የመሰለ የጉልበት ብክነት በ “የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ከቶም የለም። እዚህ የተሻለ ፍጥነት አለ፡፡ “የብርሃን ፈለጐች”ን አንድ አንቀጽ ሳያነቡ ማለፍ “የጠፋውን እግዜር” እንደሚያስሰው ባካኝ “ቱሪስት” መነሻ እና መድረሻ የማጣት ያህል ነው፡፡ ያለነገር የተደነቆለ ቃል እና ሃረግ የለም፡፡ ብርሃማነቱ ሳይጐድልበት፡፡ “ፀኸየች” የሚል ውብ ቃል ያነበብነው እዚህ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኸርነስት ሄሚንግዌይት ቀድመን ያነሳነው፡፡

ፍሩድ እና አለማየሁ
ይሄ አለማየሁ የስነ ልቦና ሊቅ መሆን አለበት። ልቦለዶቹ ባብዛኛው የግለሰብ እና የማህበረሰብ ስብእናን በግል እና በጋራ በርትተው የሚፈትሹ ድንቅ የስነ ልቦና ምርምር ውጤቶች ናቸው፡፡ ከ“አጥቢያ” አንስቶ፣ “ቅበላ”ን ጨምሮ የታየው ይኸው እውነት በ”የብርሃን ፈለጐች” አድጐ፣ ጐልብቶ እና ተራቅቆ ቀርቦልናል፡፡
ቤተሰባዊ የአስተዳደግ ባህላችን፣ የልጅነት ገጠመኞቻችን፣ የወዳጅ ዘመድና ማህበረሰባዊ ጉድኝቶቻችን በስብዕና ግንባታ አንጻር የሚያበረክቱልንን በጐም ሆነ እኩይ አስተዋጽኦ ብቻም ሳይሆን በምናየው እና በማናየው ዓለም መካከል ያለውን ጽኑ ትስስር፣ በምንረዳው እና በማንረዳው የአእምሮአችን አሰራር እና ውጤት፣ በህልም እና በእውን አለም መካከል በተዘረጋው ስስ ድንበር ላይ የሚያጠነጥኑ ጠንካራ ታሪኮችን ከለስላሳው “የብርሃን ፈለጐች” ፈልቅቆ ማውጣት ይቻላል፡፡ ጠጣሩ የሲግመንድ ፍሩድ የPsychoanalysis (በማናዘዝ የአእምሮ እረፍት የማምጣት) ልምምድ ሁላ በልቦለዱ ቃለ ምልልሶች ውስጥ ይስተዋላል፡፡
እግዜር እና አለማየሁ
ከArts for Arts Sake በተጻራሪው እንደ እንግሊዛዊው በርናንድ ሾው፤ ማህበረሰብ ለማነጽ የሚታትሩ ፀሐፊያን በየአገሩ በብዛት አሉ፡፡ በዚሁ በእኛው አገር በዚሁ በእኛው ዘመን እንኳ በልብ ወለዶቻቸው ብቻም ሳይሆን በተለያዩ የመጣጥፍ ስራዎቻቸው ሞራልን የሚሰባብኩ አያሌ ናቸው፡፡ ዘነበ ወላን፣ ዳንኤል ክብረትን፣ ኤፍሬም ስዩምን፣ እንዳለ ጌታ ከበደን እና በግልጽ “ገጣሚ ለዘመዶቹ/ለሰው ልጆች” እንደሚቆረቆር የነገረንን ተወዳጁ በዕውቀቱ ስዩምን ጨምሮ ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ስብከቱ አይጩህ እንጂ አስተሳሰቡ የሚያስማማ ነው፡፡
ለእኔ አለማየሁ ገላጋይ በእዚህ በ “የብርሃን ፈለጐች” ልብወለዱ እኔን መሰል በጐና ክፉ እግዜር አልባዎችን ተዋግቷል፣ ፈንክቷል፡፡ “እግዜር ጠፍቷል” በሚል ቁንጽል እና ወላዋይ “የፍልስፍና እውቀት” ሰበብ ስርዓት አልበኝነት ሲያቆጠቁጥ፣ ፈሪአ እግዚአብሔር ጠፍቶ ማን አለብኝነት ሲያገነግን ውስጥ ውስጡን ሰብኳል፡፡ በፍትሃዊ ዳኛ፣ በአገናዛቢ ታዛቢ አልባነት ሰው የራሱን ፍርድ ለመስጠት ሲነሳ፣ በልብ ወለዱ የተፈጠረችው መጠነኛ ዓለም ወደ መፍረስ ስታዘነብል አሳይቷል። “ቱሪስት” እንደመጣባት እንግዳ ምድር ከጨረቃ ባሻገር በሌለ ቀጣይ ህይወት አልባነት ሃሳብ ንውዘት ለእብደት ሲያቆበቁብ፣ እንደ “መክብብነቱ” የህይወት ዘበትነት ሲገዳደረው፣ የህልም እና የእውን አለም ድንበር ሲደረመስበት ተስተውሏል፡፡ ስነ ጽሑፋዊ ይዘቱ ስለገነነ፣ ስብከቱ ፈጽሞ ስለተሰወረ፣ ጣዕምናው በጣም ሆነ፡፡ እኒህን መሰል የእጅ አዙር ምስክርነቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የቅዱስ መጽሐፋት ታዋቂ ህግጋት በሰው ልጅ ተሽረው የሚያስከትሉት ቀውስ ያው እንደዝምዝማት በስውር ስፌት ቀርበዋል፡፡ “ባል የሚስቱ ራስ ነው” የሚል ቃል ታጥፎ ቤት ሲናድ፣ “አታመንዝር” ቸል ተብሎ የፍልሚያ እና የሞት ሰበብ ሲሆን ተተርኳል፡፡ እጅግ ያምራል!
ሌላም በጉልህ ያስደነቀኝ የስነ ጥበብን ግብ የማጉላት ስራ አሽትቼአለሁ፡፡ ቀደም ብለን የጠቃቀስናቸው ዘላለማዊ እሴቶች በጽሑፍ ኪን መቅረባቸው እንዳለ ሆኖ፣ የተሰወረን እግዜር (በአባት ተመስሎ የጠፋን) በስነ ስዕል ሃይል የማግኘት ተአምር! ለስዕሉም መነሻ ሙዚቃ መሆኑ! ብራቮ አለማየሁ!

ድንቅ ገለጻዎች
“ማናሉን በፍርሃት አየኋት፡፡…የእናቷ አይነት ደቃቅ አበባ የተበተነበት ቀሚስ ለብሳለች፡፡ በቆዳ ጫማ ሞድ የተሰራ አጭበርባሪ ኮንጐ አድርጋለች።…” (ገጽ 44)
“ወሬ ተሸሽቶ የትም አይደረስ፤ … ወሬ ታግሎ የሚጥልህ መኖሩን በሙሉ ትኩረት ስታረጋግጥለት ብቻ ነው” (ገጽ 68)
“ይሄን አስቀያሚ ዓለም የማሻሻል ፍላጎቴን በህልሜ ለማሟላት ወደ እንቅልፍ አለም የገባሁ ይመስለኛል … (ገጽ 70)
“አባቴ በእምምታ “ናፍቆቴ”ን እየተጫወተ ጊታሩን ማጀብ ጀመረ፡፡ … ጨርሶ ለመጥለቅ አፍታ የቀራት ጀንበር ይኽ ነው የማይባል ደስ የሚል ቀለም አንሰራፍታለች፡፡ እነ ጋሙዳው አመል ሆኖባቸው እንደኩርሲው ሁሉ በመስኩም ይጋፋሉ፡፡ ንጹህ ፊት ላይ የሚታየው ተመስጦ እንደ ጀምበሯ ቀለም ይህ ነው የማይባል አይነት ነው፡፡ ሀዘን ቅልቅል ደስታ፡፡ እግሮቿን ወደ ጎን ሸርመም አድርጋ ጉልበቷን በማነባበር ያለችበትን ልብ ሳትል ተቀመጠች፡፡ እኔ አጠገቧ ሆኜ ቀረሁ፡፡ ይህ ሁኔታና ምስል የረጅም ዘመን ቅርሴ ሆኖ በህልምና በእውን ቅልቅልነት አብሮኝ ኖሯል፡፡ የልጅነት ጊዜዎቼ ሁሉ በእዚች ዕለት ሁኔታ ተተክቶ የግሩም ዘመን ናፍቆትና ተነጥሎ የመቅረት ብሶት ተቀላቅሎ አሁንም ልቤን ይጎበኘዋል። … ነገሮች ሁሉ እዚች ቦታና ዕለት ላይ መቋጫ አጥተው እንደተገተሩ ወደ ዘላለማዊ ምስልነት ቢቀየሩ ኖሮ እያልኩ ብዙ ጊዜ ተመኝቻለሁ። … (ገጽ 72)
“ከድብድቤ ውጤት ጋር በተለየ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋወቅሁ ማለት እችላለሁ፡፡ በጥቃት፣ በእልህ፣ በቁጭት፣ በበቀል የምናካሂደው ድብድብ ውጤቱን ክብር ስንለው በወዲያ በኩል ውርደት ሊሆን እንደሚችል ተገለጸልኝ፡፡ ከንዳዴ ጋር የገጠምኩት አንሼ መታየትን በመጥላት ቢሆንም አሸንፌም ከትንሽነት እንዳልወጣሁ እዚህ ቆሜ ገባኝ፡፡ … (ገጽ 117)
“ከንግግር ውጭ ያለ መግባቢያ ሁሉ መጠፋፊያ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡” (ገጽ 124)
“ፍርድ ሁሉ የሰው እንጂ የእግዚአብሔር እንዳልሆነ እንዴት ሳላውቅ ቆየሁ? …” (ገጽ 176)
“የቴክኒክ መቋረጦች”
ትየባ ላይ የተፈጠሩ እዚህ ግቡ የማይባሉ ህጸጾችም ሳይኖሩት አልቀሩም መጽሃፉ፡፡ እስካሁንም እንደተስተዋሉ እናምናለን በደራሲው። ሁለተኛው እትም ላይ የሚታረሙ የቃላት ድግግሞሾች፣ የተዛነፉ ስርዓተ ነጥቦች፣ የተገደፉ ሆሄያት፣ የተዘባረቁ ፊደላት አሉ፡፡
ሌላም በገጽ 213 ከሌሎች ጋር መምጣቷ የተገለጸው “ምዕራፍ” በገጽ 216 “ዛሬ መጥታ አለመጠየቋ ሌላ ምልክት ሆነኝ፡፡” ተብሏል፡፡
በመጨረሻም
ይሄ ጽሁፍ የተሰናዳው በዚህ ዘመን በሰበብ አስባቡ ያጣነውን፣ “የብርሃን ፈለጎች” ከብርሃን ጋር የለገሰንን፣ እንደአደይ አበባ የሚያፈካ ደስታ፣ አንብባችሁ ታጣጥሙ ዘንድ ለመጋበዝ ነው። እግረ መንገዳችንን መልካም አዲስ ዓመት እንመኛለን፡፡
ረዥም ዕድሜ ለአለማየሁ!!

Read 3619 times