Saturday, 21 September 2013 10:07

ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንት ግርማ ውጤታማ አልነበሩም አሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

                በሁለት ዙር ምርጫ ለ12 አመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሚገባቸውን ያህል አልሰሩም በማለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተናገሩ ሲሆን አማካሪያቸው አቶ አሰፋ ከሲቶ እና የፓርላማ የግል ተመራጭ ዶ/ር አሸብር በበኩላቸው፤ ፕሬዚዳንቱ ውጤታማና እድለኛ እንደሆኑ ገለፁ፡፡ “ፕሬዚዳንቱ ይህን ሰሩ የምለው ነገር የለም፣ ቦታው በራሱ የሚሰጠው የስራ ሃላፊነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም፤ “ፕሬዚዳንቱ በግላቸው መስራት የሚችሉት በርካታ ስራ ቢኖርም አንዱንም አላየንም” ብለዋል፡፡ የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ “ፕሬዚዳንት ግርማ በተለይ ለሁለተኛ ጊዜ መመረጣቸው ፈጽሞ ስህተት ነበር” ይላሉ።

በመጀመሪያዎቹ አመታት፣ ፕ/ር ግርማ ህገ-መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ስልጣንና ተግባር በተጨማሪ በርካታ በጐ ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ነበር የሚሉት አቶ ሙሼ፤ እየቆየ ግን የሰውየው እድሜና የጤና ሁኔታ ከመስራት አግዷቸዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ በበርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ አገር እንደሆነች አቶ ሙሼ ጠቅሰው፤ ፕሬዚዳንቱ ርዕሰ ብሔርነታቸውንና የአገር ምልክትነታቸውን ተጠቅመው መስራት ነበረባቸው ብለዋል፡፡ በፕሬዚዳንቱ የ12 ዓመት የስልጣን ቆይታ አገሪቱን ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ያራመድ ጠንካራም ሆነ ደካማም ነገር አላየሁም ብለዋል - አቶ ሙሼ፡፡ በፕሬዚዳንትነታቸው እንኳን አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ምንም አልሰሩም በማለት አስተያየት የሰጡት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ ቦታውም እንዲሁ በስም ብቻ እንዲቆይ በህገመንግስቱ የታጠረ ስለሆነ የፕሬዚዳንቱ ተግባር ቤተመንግስት ውስጥ ተቀምጦ ኖሮ ጊዜው ሲደርስ መውጣት ነው ብለዋል፡፡

በፓርላማ ብቸኛ የግል ተመራጭ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ግን፣ ፕሬዚዳንቱ ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ ተወጥተዋል ብለው ያምናሉ፡፡ ዶ/ር አሸብር፣ የእኛ አገር መንግስታዊ ስርዓት ፓርላሜንታዊ ስለሆነ ብዙውን የአፈስፃሚነት ስራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጥ ነው ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ ፕሬዚዳንት ግርማ ባልተሰጣቸው ሃላፊነት አልሰሩም ተብለው ሊወቀሱ አይገባም ብለዋል፡፡ “ፕሬዚዳንቱ በህገ-መንግስት የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር ከመወጣት በተጨማሪ አካባቢንና ተፈጥሮን በመንከባከብም ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል” ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ ፕ/ት ግርማ ባሳለፏቸው 12 ዓመታት ውጤታማ መሪ ነበሩ ብለዋል፡፡

ፕ/ት ግርማ በግላቸው በተፈጥሮ ሳይንስና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ፍላጐት እንዳላቸው ቢናገሩም በተግባር ያመጡት ውጤት አላየሁም የሚሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ መስራት ይችሉ ነበር፤ ግን አላደረጉም” ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ግርማ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ በበኩላቸው፤ ፕ/ት ግርማ በስልጣን ዘመናቸው ውጤታማና እድለኛ መሪ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፤ በእውቀታቸው፣ በቋንቋ ችሎታቸው፣ በአንባቢነታቸውና በስራ ሰአት አክባሪነታቸው ወደር የሌላቸውና ለሌሎች አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ መሪ ናቸው ሲሉ አድንቀዋቸዋል፡፡

ፕ/ት ግርማ እድለኛ ናቸው ያሉበትንም ምክንያት ሲያስረዱ፤ በእርሳቸው ዘመን ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጀመርና የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውጤታማ ጅምር ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡ የወደፊቱ ፕሬዚዳንት ማን ይሁን በሚለው ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች እከሌ ይሁን በሚል ስም ከመጥቀስ የተቆጠቡ ሲሆን ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማሪያም ብቻ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ቢመረጡ ምኞታቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

Read 24537 times