Saturday, 21 September 2013 10:15

“መኢአድ በእኔ ፍጥነት ሳይሆን በወጣት ጉልበት መስራት አለበት”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያዊነት ግትርነት ከሆነ፣ አዎ ግትር ነኝ ደህና ተቃዋሚን ለመፍጠር ከልብ ከሆነ ጊዜ አይፈጅም አልዘፍንም እንጂ ሰው ሲዘፍን ለማየት የትም እገባለሁ

በምርጫ 97 የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ሊቀመንበር የነሩትና ከመኢአድ ሊቀመንበርነታቸው በቅርቡ የለቀቁት ኢንጂኒየር ሃይሉ ሻውል “ህይወቴና የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚል ርዕስ የፃፉትን ክፍል አንድ መፃሐፋቸውን ከሰሞኑ ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል፡፡ የመጽሐፉ ቀጣይ ክፍል ለንባብ እንደሚበቃና ስላለፉባቸው የስራና የፖለቲካ ሃላፊነቶች በዝርዝር የሚያትት አዲስ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየፃፉ መሆናቸውን ከገለፁት ከኢንጂኒየር ሃይሉ ሻውል ጋር ኤልሳቤት እቁባይ ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው ዙሪያ ቆይታ አድርጋለች፡፡

እርስዎ ያለፉባቸውን ሶስቱን መንግስታት እንዴት ያነፃጽሯቸዋል? ሶስቱን መንግስታት ማነፃፀር ያስቸግራል። ምክንያቱም ብዙ ሰው የሚያየው ከራሱ ጥቅም አንፃር ብቻ ነው፡፡ እኔ የራሴን ጥቅም መለኪያ አድርጌ አላየውም። የማይበት መነጽር ህዝብ ምን ሁኔታ ላይ ነው የሚለውን ነው፡፡ ሶስቱም ላይ ችግር አለ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ ጥቂት ግለሰቦች ያለእኛ ሰው የለም እያሉ፣ ህዝቡን ሲያበሳጩ አይቻለሁ፤ እኔም ራሴ ደርሶብኛል፡፡ ምን ደረሰብዎት? ኩሊ ተብያለሁ፡፡ ምክንያቱም ካኪ ለብሼ ቆሜ ስለምሰራ፡፡ ሰው የሚባለው ክራባት አስሮ ቢሮ ውስጥ ሰርቶ፣ ከዛ ሲወጣ ደግሞ ኢትዮጵያ ሆቴል ሄዶ እየተንዘባረረ ሲጠጣ ነው፡፡ ለኔ ደግሞ ሰው ማለት የትም ገባ የት ውጤት ሲያመጣ ነው፡፡ እኔ መጀመሪያውኑ ከውጭ ተምሬ ስመጣ ቀጥታ ገጠር ነው የገባሁት፡፡

አዲስ አበባ ቤት አልነበረኝም፡፡ ያን ጊዜ እንደኔ አይነት ሰው ዋጋ አልነበረውም፡፡ የታወቁ ህዝብን የሚያጐሳቁሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሆን ብለው ችግር የሚፈጥሩ፡፡ ችግሮችን ሁሉ በስርዓቱ ላይ ማላከክ ተገቢ አይደለም፡፡ በእርግጥ ስርአቱ ለሀብታም ያደላል፡፡ ዞር ብለው ደግሞ ለደሀ ልጅ ነፃ የትምህርት እድል ይሰጣሉ፡፡ ከዜሮ ክፍል እስከ ማስተርስ ዲግሪ ያስተምራሉ፡፡ ለደሀ እድል ተሰጠ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ ልዩነት የለም። ልዩነቱ ያለው በምታገኘው ገቢ፣ በምትሰሪው ስራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሁሉም መደቦች ለማረፍ የተመቻቸ ያደርገዋል። ካንቺ የሚጠበቀው ለምትሰሪው ስራ ትኩረት መስጠት ነው፡፡ ሠራተኛ ከሆንሽ አለቃሽንም Go to hell ማለት ትችያለሽ፡፡ እኔ እንደዚያ እል ነበር፤ ማንም የነካኝ የለም። ደርግ የአፄ ኃይለስላሴን መንግስት ሌት ተቀን እንደወቀሰ ሄደ፡፡ ኃይለስላሴ እንዲህ አድርጐ፤ መሬት ነጥቆ ይል ነበር። እነሱ ምንድን ነው ያደረጉት? የነጠቁት እኮ እነሱ ናቸው፡፡

ስንት የደሀ ልጅ ለፍቶ ያገኘውን ነጥቀው ባዶ እጁን አስቀሩት፡፡ በኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪነት ሞተ። ኢትዮጵያን ለውጭ ዜጐች ያመቻቸውም ይሄ ነው። ምክንያቱም ድሮ ቆጣቢ የነበረው እንደ ደርግ መጥቶ የሚወስድብኝ ከሆነ፣ ለምን አስቀምጣለሁ ማለት ጀመረ። ሶስተኛው መንግስት ደግሞ በዛው ላይ ገነባበት፡፡ ከህዝብ የተወሰደውን በራሱ እጅ አደረገ፡፡ ገጠር ብትሄጂ እያንዳንዷ ኩርማን መሬት የመንግስት ናት፡፡ ገበሬው እናገራለሁ ቢል ከመሬቱ ላይ ይባረራል፡፡ ከተማ ሰማያዊ ቁምጣ ለብሶ የሚመጣው ማን ነው? ባለስልጣን ከመሬቱ ያባረረው ገበሬ ነው፡፡ በሱ ቦታ ላይ እርሻ ምን እንደሆነ የማያውቅ፣ የፖለቲካ ወሬ ህዝብ መሀል ቆሞ የሚጮህ ተተካበት፡፡ ስለዚህ ረሀብ መጣ፤ ምርታማነት አሽቆለቆለ። ዛሬ ያን ለመመለስ እያሉ በቴሌቪዥን የሚያወሩት ነገር አያስኬድም፡፡ እነሱ የሚያወሩትን የዘር ጉዳይም እኔ የትም አላገኘሁትም፡፡ ምናልባት ያለው ህወሓት የተፈለፈለበት ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ትግራይንም አውቀዋለሁ። ትምህርት እንደጨረስኩ መጀመሪያ ሱፐርቫይዝ ለማድረግ የሄድኩት መቀሌ ነው፡፡ በህዝቡና በእኔ መሀል አንድም ልዩነት አልነበረም፡፡ ተከባብረን ተዋደን ነው ስንሰራ የነበርነው። በርግጥ በአማራ እና በትግሬ መካከል የስልጣን ሽሚያ ነበር፡፡ እነሱ --- በህዝብ መሀል ድንበር ሰሩ፡፡ አሁን ነገሮች እየተለወጡ ነው፡፡ የደቡብ ህዝብ ከማንኛውም ዘር ጋር ችግር የለበትም፡፡ በቅርቡ አማራ ከደቡብ ይውጣ ሲል በፅሁፍ ያዘዘው ባለሥልጣን፣ አሁን ትምህርት ሚ/ር ሆኗል፡፡

ምን እንዲያስተምረን አስበው እንደሾሙት አላውቅም፡፡ ህዝቡ ቢፈልግ ኖሮ አማራውን በሁለት ቀን ያስወጣው ነበር፡፡ ህዝቡ ግን ስላልፈለገ እግሩን እየጐተተ ሳለ ነው ካድሬዎቹ አስወጡ ተብለው የተላኩት፡፡ እኛ ህዝቡ ተጐዳ ብለን ጮኸናል፡፡ ጉዳቱ ለሚባረረው ብቻ አይደለም፡፡ ለቀሪውም ጭምር ነው፡፡ መንግስት እንዲህ ያሉትን ችግሮቹን በጊዜ ካላስተካከለ ከሁሉም የባሰ ነው የሚሆነው፡፡ በመጽሐፍዎ ላይ “ከአባይ ሸለቆ ጭቅጥቅ ስለማልፈልግ ለቀቅሁ” ብለው የፃፉት ነገር አለ፡፡ ጥቅጥቁ ምን ነበር? አባይ ሸለቆ በጣም የወደድኩት ስራ ነበር፡፡ በገደል ላይ ተንጠልጥዬ ነፍሴን ሸጬ የሰራሁበት መ/ቤት ነው፡፡ ሠራተኛው በሙሉ ጐበዝ ነበር፡፡ መንገድ በሌለበት መንገድ ቆፍረን ነበር የምናልፈው፡፡ ስለዚህ አባይ ሸለቆን መተው ማለት ትልቅ የራሴን አስተሳሰብና ሃይል ጥሎ እንደመሄድ ነው፡፡ ወጣም ወረደ ስራው ውጤታማ ሆኗል፡፡ እኛ ስራ ስንጀምር ቢሮክራሲ አልነበረም፡፡ የውጪ ዕርዳታ ነበር፡፡ ስራችንን በተፈለገው መሠረት እንሠራለን፡፡ እጅ መንሳት ምናምን ግን የለም፡፡ በኋላ አንድ ኢትዮጵያዊ ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ፡፡

በሙያ ደረጃ ከፍተኛ ምሁር ነበር፡፡ ነገር ግን ቢሮ አናየውም፡፡ እሱ ጋ የተጠጉትም ምንም የማይረቡ ነበሩ፡፡ የምንሰራውን መንካት ጀመሩ፡፡ ዳይሬክተሩ ስራውን ትቶ ጃንሆይ የሆነ ቦታ ይሄዳሉ ሲባል ምንጣፍ በትክክል ተነጠፈ አልተነጠፈም የሚለውን የሚያይ መሀንዲስ ሆነ፡፡ “ሰውየው ምህንድስናው የምንጣፍ ሳይሆን አይቀርም” እያልን እንሳሳቅ ነበር፡፡ ቢሮክራሲው በጣም ሲያስቸግር ለመልቀቅ ወሰንኩ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ወጥቻለሁ አልኳቸው፡፡ የእውነት አልመሰላቸውም፡፡ ወሩ ሲሞላ ቀረሁ፡፡ ከዛ ሼል ኩባንያ ያወጣውን ማስታወቂያ አንብቤ አመለከትኩ፡፡ ቃለመጠይቁን ከእንግሊዝ ከመጣ ሰው ጋር አደረግሁና፤ ከአንድ ወር በኋላ ስራ ጀመርኩ። ደቡብ የመን የአውሮፕላን ጣቢያ ግንባታ ሱፐርቫይዝ እንዳደርግ ተላኩ፡፡ ወር ሳይሞላኝ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አለበት ተባለና፣ ስመለስ የተሳፈርኩበት አውሮፕላን ውስጥ ለኢትዮጵያ ከተመደበ አዲስ የሼል ማኔጀር ጋር ተገናኝተን ስናወራ “ለምን ቶሎ ተመለስ አሉህ?” አለኝ፡፡ “እኔ አላውቅም፤ ምናልባት መንግስት ይሆናል” አልኩት፡፡ ልክ እንደደረስን ከመንግስት ፈቃድ ሳያገኝ የወጣ ስለሆነ አባሩት የሚል ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡፡ እኔም ብትፈልጉ ከስራ አስወጡኝ እንጂ አልመለስም አልኩ።

አዲሱ ማኔጀር ለደብዳቤው መልስ አልሰጥም ብሎ ዘጋቸው፡፡ የበፊቱ እንግሊዛዊ ግን ከመንግስት ጋር ያጣላናል ብሎ ነበር፡፡ ሼል አስራ ሶስት አመት የሰራሁት የኔን አመል ችለው ነው፤ አንድ መ/ቤት ውስጥ ብዙ መቀመጥ አልወድም በማለት መጽሐፍዎ ላይ ገልፀዋል። ለምንድነው በአንድ መ/ቤት ብዙ መቆየት የማይወዱት?… ሼል እኮ ብዙ ቆየሁ፡፡ እነሱ በየጊዜው ደሞዝ ይጨምራሉ፡፡ ለማቆየት ብዙ ነገር ያደርጋሉ፡፡ መጨረሻ ላይ አንድ ትልቅ ብድር ሰጡኝ፡፡ ቤት ሥራ ብለው። ቀደም ብሎም አንድ ትንሽ ቤት ስሰራ አበድረውኛል። ገንዘቡ ቶሎ የማይከፈል ስለሆነ መያዥያ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ስልጠና ሰጥተውኛል፡፡ እሺ አልኩና ብድሩ ስለተጫነኝ አስራ ሶስት አመት ቆየሁ፡፡ በዛን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አልነበረም፡፡ የፈለጉበት ሄዶ መስራት ይቻላል፡፡

ኮካኮላ ካምፓኒ፣ሊባኖስ ናና ለኛ ስራ አሉኝ፡፡ አበሻ ስለሆንኩ ይሉኝታ አስቸገረኝ፡፡ ቀረሁ፡፡ በኋላ ለውጥ ሲመጣ ለቀቅሁ፡፡ ልዩ ልዩ ስራ ላይ ስለሚያሰሩኝ አይሰለቸኝም ነበር፡፡ መሀንዲስ ሆኜ ገባሁ። ከዛ የትራንስፖርት ኤክስፐርት ሆንኩ፡፡ በመቀጠል ሊቢያ ሄጄ ሠራሁ፡፡ ከዛ ሽያጭ ክፍል ገባሁ፡፡ እድገት አግኝቼ ወደ ምክትልነት ስደርስ “አንተ ውጪ አገር ተልከህ ሼል ኩባንያ መስራት አለብህ” አሉኝ፡፡ ለምን ስል፣ የኩባንያ ሃሳብ እንዲኖርህ ሲሉኝ፣ ይህን ሁሉ አመት ሰርቼ አልኳቸው፡፡ በኋላ ሳስበው በአንድ ወቅት የእንግሊዝ ፓውንድ የመግዛት አቅሙ ወርዶ አተረፈና ሪዘርቭ ሊያደርጉ ሲሉ፣ “ትርፍ ስለሆነ ዲክሌር አድርጉ” ስላልኩ የኩባንያ ታማኝነት የለውም አሉ፡፡ ከዛ እንግሊዝ አገር ሂድ ተባልኩ፡፡ በደሞዝ ለመጣላት ሞከርኩ። እንግሊዞቹ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከደሞዛቸው ውጪ ብዙ ይከፈላቸዋል፡፡ እኔን ግን ልክ አንድ እንግሊዛዊ እንደሚከፈለው ሊከፍሉኝ ወሰኑ፡፡ አይ አልኩ፡፡

የአየር ፀባዩ አይስማማኝም፡፡ ርካሽ እቃ የሚገዛበትን አላውቅም። እናንተ እዚህ ቆንጆ የአየር ፀባይ ያለው አገር መጥታችሁ ልዩ ክፍያ ስለሚሰጣችሁ አልስማማም አልኩ፡፡ አፍሪካ ውስጥ አድርገን አናውቅም ሲሉ፤ አሁን ጀምሩ አልኳቸው፤ እሺ በሚስጥር ብለው ጀመሩ፡፡ እዚህ ሂደት ላይ ሳለን ለውጥ መጣ፡፡ እስከዛሬ የማማርረው ቢሮክራሲ አለ ብዬ ነው፡፡ አሁን ለምን ፈረንጅ አገር እንደገና እሄዳለሁ ብዬ ሳስብ፣ የስራ ሚኒስትር “አውራጐዳና ችግር ተፈጥሯል፤ አግዘን፤ ሠራተኛው በር ዘግቶ ማኔጀሮቹን፣ ኢንጀነሮቹን አባረረ አለኝ፡፡ ታድያ ምን ላድርግ ስለው፤ አግዘን አለኝ፡፡ በቋሚነት ሳይሆን በኮንትራት እሠራለሁ ብዬ ተስማምተን አውራ ጐዳና ገባሁ፡፡ ከደርግና ከተለያዩ የፖለቲካ ጐራዎች የግድያ ሙከራዎች ተርፈዋል፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ --- ያን ጊዜ ሁሉም ግራ ዘመም ፖለቲከኛ ነበር። እኔ ደግሞ አንዳቸውንም ማስጠጋት አልፈለግሁም፤ ምክንያቱም ጥፋት እንጂ ልማት የላቸውም፡፡

የገባሁባቸው መስሪያ ቤቶች ደግሞ ብዙ ወዛደር ያለባቸው፣ ብዙ ገንዘብ የሚዘዋወርባቸው ስለሆኑ ሁሉም በእጃቸው ማስገባት ይፈልጉ ነበር፡፡ ኢህአፓ እና ኦነግ አንዱ በወንጂ በኩል፣ ሌላው በመተሀራ ተጠናክረው እርስበርስ ሲፋጁ ነበር፡፡ እኔ ለሁለቱም እድል አልሰጠሁም፡፡ ስራ የምንሰራ ከሆነ እነዚህን ወደ ዳር ማውጣት አለብን አልኩ፡፡ ሠራተኛው አልገባውም፡፡ ደርግም መጥቶ እንደማያድነኝ አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም የግራ ክንፍ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ጊዜ የመውደድ፣ የመደገፍ ጉዳይ አለ፡፡ የወዛደር አምባገነንቱም አለ፡፡ የወንጂዎቹ ብዙም አስቸጋሪዎች አልነበሩም፡፡ ማታ ከማህበር መሪዎች ጋር ቁጭ ብዬ አወራለሁ፡፡ “ድርጅቱ ቢዘጋ ቤተሰባችሁ ምን ይሆናል? ችግር ሲኖር ለኔ ንገሩኝ እንጂ ድርጅቱን አትጉዱ” በሚል ተስማማን፡፡ የመተሀራዎቹ ግን አናዳምጥም አሉኝ፡፡ አንድ ቀን ስሄድ አንድ መሀንዲስ ሚኒስትር ሆኗል፡፡ ወዛደሩ ከቦ ይዞታል፡፡ ቀጥታ ገባሁና ልጁን እጁን ይዤ ወጣሁ፡፡ ከወጣሁ በኋላ ተጯጯሁ፤ ዝም አልኳቸው፡፡ በኋላ ሊገድሉኝ ሞከሩ፡፡ በሳር ቤት በኩል ነበር፡፡ አንዱ መሳሪያ ይዞ ሲሄድ አይቼዋለሁ፡፡

“ገልጃጃ ነው፤ እኔን ፍለጋ መጥቶ ከጀርባው ስሄድ የማያውቅ” ብዬ ጥዬው ሄድኩ፡፡ መተሀራ ያሉት ከቤትህ አትውጣ አሉኝ፡፡ እኔ ያኔ አልፈራም ነበር፡፡ ልጆች ከመጡ ወዲህ ነው ፍርሃት የሚባል ነገር የመጣብኝ፡፡ ስብሰባም ላይ Shut up ነው የምለው፡፡ ያኔ በዛ ባላቆም ኖሮ ተያይዘን ነበር ገደል የምንገባው፡፡ በወቅቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ “እኔ ነኝ አሸናፊ” ብሎ ደምድሟል፡፡ ደርግ ደግሞ “እስቲ ይሞክሩኝ” ይላል፡፡ በሽታው አዲስ አበባ መጣ፡፡ አንድ ሠራተኛ ለመያዝ ብለው ቤቱን ከበዋል፤ ቢሮአችን ፊሊፕስ ህንፃ ነበር፡፡ ምንድን ነው ይህ ሁሉ ሚሊሺያ ብዬ አልፌያቸው ገባሁ፡፡ ልጁን እንፈልጋለን አሉ፤ ውሸታቸውን ነው፤ ቀጥታ እኔ ቢሮ ነው የመጡት፡፡ ሁሉም መሳሪያ ደግነው መሳቢያዬን ከፈቱ፤ መሳሪያ ያለኝ መስሏቸው ሲያጡ “አንተ ሲአይኤ ነህ” አሉና ወሰዱኝ፤ አስፈራሩኝ፡፡ ከአውራ ጐዳና ያመጧቸውም ነበሩ፡፡ ለኔ ያ ትግል ፖለቲካ ውስጥ ከገባሁ በኋላ እንኳን ያላየሁት፣ ሠራተኞቼንና ድርጅቱን ለማዳን ያደረግሁት ትልቅ ትግል ነበር፡፡ የምሁራንን ተሳትፎ በገለፁበት የመፅሃፍዎ ክፍል ላይ ምሁራን ወደ መአህድ እንዲቀላቀሉ ስጠይቅ፣ “ሃይሉ ይዘልፈናል፣ ይንቀናል ይላሉ እንጂ ምንም የረባ ነገር ሲያደርጉ አላየሁም” ብለዋል፡፡

በ97 ምርጫ ቅንጅትን በተመለከተ ነገሮች የተበላሹት ኢንጂነር ግትር ስለሆኑ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ? እነሱ ምን እንደሚፈልጉ አላውቅም፡፡ በእነሱ ቋንቋ ግትርነት ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግትርነት ከሆነ፣ አዎ ግትር ነኝ፡፡ እነሱ በየኤምባሲው እጅ መንሳት፣እነሱን ተለማምጦ መኖር ትክክለኛ ፖለቲካ ነው ይላሉ፡፡ እነሱ በኛ ፖለቲካ ምን አገባቸው? የኢትዮጵያን ጉዳይ መወሰን ያለብን እኛው ነን፡፡ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በወልደሀና በምን የሚወሰን ሊሆን አይገባም፡፡ ችግር ሲኖር ሮጠው ለነሱ ይነግራሉ፡፡ መጨረሻ ላይ የኛን ምርጫ ዜሮ አድርጐ ድምፃችንን ለመንግስት የሰጠው ማን ሆኖ ነው? ለአገሩ የሚያስብ እንዲኖር አይፈልጉም። ግትርነት ኢትዮጵያዊነት ከሆነ ልክ ነው፡፡ በመጽሐፍዎ ላይ “ፕሮፌሰር መስፍን መኢአድ ላይ ይዶልታሉ” ብለዋል፡፡ ምን ለማለት ፈልገው ነው? አንዳንድ ሰው ተፈጥሮው ዶላች ነው፡፡ አንዲት አፓርትመንት ዛሬም አለች፤ ኤንሪኮ በታች፡፡ እዛ ቤት የሚዶለተው ዱለታ ዛሬም ብዙ ነው፡፡ ትናንትም በጣም ብዙ ነበር፡፡

ለምን እንደሚዶልት አይገባኝም፡፡ ፕሮፌሰር አስራትን ስለማይወደው ነው… ለምንድነው የማይወዷቸው? እሱን ሄደሽ ብትጠይቂው --- መአህድን ከዛ አውጥቶ ህብረ ብሔራዊ አድርጌያለሁ ብሎ ሌላ ፓርቲ እንዲመሠረት አደረገ፡፡ ከዛ እየደጋገመ ነው ይህን ስራ የሰራው፡፡ መአህድ ከበድ ሲልበት መኢአድን ማዳከም አለብኝ አለ፡፡ ይቅርታ አድርጊልኝና እሱ ለማን እንደሚሠራም አላውቅም፡፡ አንድ ጊዜ ከኢዴፓ ጋር ላስታርቅ አለ፡፡ እነ ልደቱን እናውቃቸዋለን፤ እነሱም ያውቁናል አልኩ፡፡ ግን ቅንጅት ምስረታ ላይ ለእነልደቱ የኃይሉን ቦታ እሰጣለሁ ብለው ማግባባታቸውን ልደቱ ራሱ ሲናገር፣ ፕሮፌሰር መስፍንና ዶ/ር ብርሃኑ፣ እምነት የለ ክህደት የለ ፈጠው ቁጭ አሉ፡፡ እኔ ነገሩን ድሮ አውቄዋለሁ፡፡ አበሻ ሰባቂ ነው፡፡ ሚስጥር አያውቅም፡፡ ሁሉንም ሰምቼ ነበር፡፡ መኢአድ እና ኢዴአፓ- መድህን ውህደት ለመፍጠር ሞክረው ሳይሳካ ወዲያው ሁለቱ ፓርቲዎች በቅንጅት ጥላ ስር በጥምረት ብሎም ለመዋሀድ ተስማምተው ነበር፡፡ ችኮላውን ምን አመጣው? አዎ ችኮላዋን ያመጣው ምርጫ ዘጠና ሰባት ነው።

ተበታትነን ከመቆየት ተባብሮ መሞከሩ ይሻላል ብለን ነው፡፡ የመጀመርያው ላይ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ሽማግሌ ነበሩ፡፡ የቅንጅቱ ጊዜ ግን የፓርቲ አባል ስለሆኑ የሚመጣውን መቀበል ይችላሉ በሚል ነበር፡፡ “ኢዴፓ ጥንካሬው አዲስ አበባ ነው፣ መኢአድ ደግሞ ገጠር እንጂ አዲስ አበባ ላይ ጠንካራ አልነበረም፤ ምክንያቱም እኛ አፈቅቤ አይደለንም” ሲሉ ምን ማለትዎ ነው ነው? እኛ ህዝብን አንዋሽም፤ አንዳንዶች ጥሩ ፖለቲካ አይደለም ይሉናል፡፡ መንግስት መሆን በጣም ከባድ ሃላፊነት ነው፡፡ እዳ ነው፤ ህዝብ የሰጠህን መልስ ይልሃል፡፡ ሰውን አስተባብሮ ማምጣት ከባድ ነው፤ አንዳንዱ ካድሬ ሆኖ መለፍለፍና ሚኒስትርነት አንድ ይመስለዋል፡፡ ይሄን ለመግለፅ ፈልጌ ነው፡፡ ተቃዋሚው ውስጥም ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ችግሩ አለ ማለት ነው? አለ፡፡ አሁንም ያሉ ሰዎች አሉ፤ አንድ ለውጥ ቢመጣ የኔ ቦታ የት ነው የሚሉ፡፡ ሰው በፖለቲካ ሲደራጅ ከታች ነው፤ አንድ ላይ የሚመራረጡት ይተዋወቃሉ፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ሲደረስ ያስቸግራል፡፡ እኔ ደቡብ ብዙ ቦታ ሄጃለሁ። ህዝቡ ላዕላይ መዋቅር የገባውን አይጠይቅም፡፡ ጊዶሌ በቋንቋ እንኳን አንግባባም፤ ግን እኛ ነን የተመረጥነው። አማራ ክልል ቀላል ይሆንላቸዋል ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡

እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ደቡብ ጐንደር ሄደን በዓይነ ቁራኛ ያዩናል፡፡ ይከታተሉናል። አርብ ቀን ስለሆነ ምን ይበላሉ፤ ምን ይጠጣሉ ብለው ነው፡፡ የከተማ ልጆችን አስጠነቀቅሁ፤ ማታ እራት ጠሩንና ሄድን፡፡ ምግብ ቀርቦ መፋጠጥ ሆነ፡፡ አይበሉም፣ አይናገሩም፤ ከዛ ገባኝ፤ አንድ ቄስ ነበሩና “አባ እባክዎት ይባርኩልን” ስል ሚስጥሩ ተፈታ፤ አለቀ፡፡ በኋላ ስሰማ አዲስ ሃይማኖት ይዘው መጥተዋል ተብሎ ተነግሯቸዋል፡፡ ከዛ ወዲህ ችግር ገጥሞን አያውቅም፡፡ ባህርዳርም ስብሰባ ልናደርግ ሄደን፣ ወያኔ ገበሬዎችን አዘጋጅቶ ጠበቀን፡፡ እኛ ስንገባ ሰው ሁሉ ሲያጨበጭብ፣ አንዱ ቡድን ጭጭ አለ፡፡ አንድ ችግር አለ ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ እኛ ጀመርን፣ ሲሰሙ ቆዩና፣ ማጨብጨብ ጀመሩ፡፡ ይሄኔ ካድሬው ጥሎ ሄደና ህዝቡ ራሱ ወሰነ፡፡ የቅንጅት ታሳሪዎች የይቅርታ ይደረግልን ሃሳብ የመጣው ከኛው ውስጥ ነው ብለዋል፡፡ እስቲ ስለእሱ ደግሞ ያጫውቱኝ --- ለምን እንደታሰሩ የረሱት መሰለኝ፤ ብዙ ሰዎች መውጣት ይፈልጉ ነበር፡፡ እኛ የገባነው ትክክል ነን ብለን ነው፡፡ እስር ቤት ሳንገባም በፊት በድብቅ ኤምባሲ ይሄዳሉ፡፡ እኔ አውቅ ነበር፡፡ ከገባን በኋላ የመጨረሻው ውሳኔ እስከዛሬ ይመረኛል፤ ፈረንጅ ምን ይላል - It leaves the bad taste in my mouth፡፡

እነ ፕሮፌሰር እኛ ጋ ይመጣሉ፤ የኛን ይወስዳሉ። ከነሱ ምንም የለም፤ ያው ከእኛም ከሽማግሌዎቹ ጋር የሚሄዱ መጡ፡፡ የኛ አቋም እየሞተ፣ እኛ በመደራደር ፈንታ ከእኛው የእንፈታ ጥያቄ መጣ፡፡ መቼም የማልረሳው ነው፡፡ እኛ እስር ቤት ሆነን መንግስት ፈረንጆቹን ከራሱ ጐን አሰልፏል፡፡ እኛ ተከፋፍለናል፡፡ ምናልባት በፖለቲካ የኔ አቋም የሞኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ከቅንጅት ፓርቲ ጋር በተያያዘ የኔ ስህተት ነው ብለው የሚያነሱት ነገር አለ? ቅንጅት በቅንጅትነቱ ቢቀጥል ጥሩ ነበር፤ የኔ ስህተት ምንድን ነው ውህደቱ ነው፡፡ በደንብ ሳንተዋወቅ ወደ ውህደት መግባታችን ነው ስህተቱ፡፡ ከእስር ቤት ከተፈታችሁ በኋላ በኛ ጋዜጣም ተዘግቦ ነበር፡፡ የአሜሪካን ኤምባሲ ቪዛ ከልክሎዎት ነበር፡፡ መጽሐፉ ላይ ያስከለከለኝ ዶ/ር ብርሃኑ ነው ብለዋል---- ተዶልቷል፡፡ እስር ቤት ሆነን ነው ውጪ ካሉት ጋር መነጋገር የጀመሩት፡፡ አንድ ቀን ስናወራ፣ “ስንወጣ ቅንጅትን በአለም አቀፍ ደረጃ እናቋቁማለን” አለኝ “መቼ ነው የምትወጡት?” ስል “እንወጣለን” አለኝ፡፡ ህዝቡስ? ስል ዝም፡፡ ለኔ ይህ አይዋጥልኝም፡፡ ሞትም ከመጣ አብረን እንሞታለን አልኩ፡፡ ይሄኔ በአቋም ተለያየን። በኋላም መኢአድ እንደአንጋፋነቱ ሳይሆን ተመልካች ሆነ፡፡ ቅንጅቱን ስንመሰርት እኮ ቀስተደመና ምንም አባል አልነበረውም፡፡ ኢድሊን እርሺው፤ ፈቃድ ብቻ እንጂ ከጀርባ ምንም የለም፡፡ ችግሩ የመጣው ትልቁ የቅንጅት ፖርቲ መኢአድ ስለሆነ የጠቅላይ ሚ/ርነቱን ቦታ ሊወስድ ነው በሚል ነው፡፡ መጀመሪያ አናሸንፍም በሚል ዝም ብለው ነበር፤ ስናሸንፍ ነው ችግሩ ፈጦ የወጣው፡፡ ኢዴፓ ከመኢአድ ስለወጣ የሌጂትሜሲ ጥያቄ ነበረነበት። ቀስተደመና ደግሞ መኢአድን ማመን አልቻለም፤ እኛ ማንም ቢመጣ ተስማምተን ነበር፡፡

ስልጣኑ ቢመጣም ለማስመሰል አንድ አመት እቆይ ይሆናል እንጂ እለቃለሁ ብያለሁ፤ ግን ያለመተማመን ነበር፡፡ አሁን መኢአድ በምን ሁኔታ ላይ ነው? 97 ላይ የነበረው ጥንካሬ አሁን የለውም፡፡ በጣም ተዘምቶባታል፡፡ ኢህአዴግ በውስጥ ሪፖርቱ መኢአድ አልጠፋ ብሎናል ብሏል፡፡ ቀስ በቀስ ለማገገም እየሰራን ነው፡፡ መኢአድ የደከመው ውጪ አገር የነበረው የገንዘብ ምንጫችን በተለያዩ ቅስቀሳዎች በመቋረጡ ነው፡፡ በተቃዋሚ ጐራ ያለውን ፖለቲካ እንዴት ይገመግሙታል? ይቅርታ፤ ምንም የጠለቀ ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱን ፓርቲ በደንብ ስታይው ምንም የለውም፡፡ ለሰው ለማሳየት ከሆነ እያንዳንዱ ፓርቲ ውስጥ ማን ነው ያደራጀው? መሪዎቹ ማን ናቸው? የት ነበሩ? የሚለው ጉዳይ ሳይመረመር ጥምረትና ህብረት የሚለው አይሰራም፡፡ ከዚህ በፊት የሠራነው ስህተት ይበቃል፡፡ ደህና ተቃዋሚን ለመፍጠር ከልብ ከሆነ ጊዜ አይፈጅም፡፡ መኢአድ ከድሮው የደከመ ቢሆንም አሁን ካሉት ጋር ሲታይ እንደሱ መሠረት ያለው የለም፤ እኔ አንገቴን እሰጣለሁ፡፡ እኛ መጮህ መፎከር ባህላችን አይደለም፡፡ በቅርቡ ጥንካሬውን ይመልሳል፤ እኔም የወጣሁት ፓርቲው መስራት ያለበት በኔ ፍጥነት አይደለም፤ በወጣት ጉልበት ነው በሚል ነው፡፡

ሙዚቃ እወዳለሁ፤ አንጐራጉር ነበር ብለዋል፡፡ ስለሙዚቃ ዝንባሌዎ ይንገሩኝ አንጐራጉር አትበይኝ እንጂ እነግርሻለሁ፡፡ ሙዚቃ ከድሮም በጣም እወዳለሁ፡፡ አሜሪካን አገር ምህንድስና ለመማር ሄጄ፣ የየዶርሚተሪው ቡድን አለ፡፡ እኔን ሀሪ ቤላፎንቴን ይሉኝ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ዴንቨር መንገድ ላይ ስሄድ አንድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት አየሁ፡፡ ለምን አልማርም ብዬ ገባሁ፡፡ ያነጋገረችኝ ሴት “ምን ያህል ጊዜ ትቆያለህ?” አለችኝ፡፡ ሶስት ሳምንት አልኳት፤“ብዙ ባይሆንም ናና ተማር” አለችኝ፤ ገባሁ፡፡ ቀን ቀን የግድብ ዲዛይን እሰራለሁ፤ ማታ ማታ ሙዚቃ (ፒያኖ) እማራለሁ፡፡ በኋላ ልሄድ ነው ስላት “እንዴት ታቆማለህ?” ብላ ዲትሮይት ፌላርሞኒክ ለሚባል ተቋም ደብዳቤ በመፃፍ “መማር አለብህ፤ተሰጥኦ አለህ” አለችኝ፤ እሷ መሀንዲስ እንደሆንኩ አላወቀችም፡፡ አገሬ ስመጣ ደግሞ ቤተሰቤን ላበሳጭ እንዴ ብዬ ዝም አልኳት፡፡ ከተቋሙ በየቀኑ እየደወሉ “አትመጣም?” ይሉኝ ነበር፤ በኋላ ሠለቻቸውና ተውኝ፡፡

የማንን ሙዚቃ ነው የሚወዱት? ሁሉንም እወዳለሁ፡፡ ግድየለሽም--- በኋላ ስም ጠርቼ ልኮራረፍ ነው፡፡ የእነቻኮቭስኪን ሙዚቃ፣ የጣሊያን ዘፈኖች እወድ ነበር፡፡ በኋላ አማርኛ እየጣፈጠኝ መጣ። በእንግሊዝኛ መልክ የሚዘፈነው ብዙ አይመስጠኝም። It does not send me ይላል ፈረንጅ፡፡ እነ ቴዲ፣ መሐሙድ፣ ነፍሱን ይማርና ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽን እወድ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን አልዘፍንም እንጂ ሰው ሲዘፍን ለማየት የትም እገባለሁ፡፡ ኮሌጅ እያሉ እግር ኳስ ይጫወቱ ነበር፡፡ ስንት ቁጥር ነበር የሚጫወቱት? አምስት ቁጥር፡፡ ቁመቴ ረጅም ስለሆነ ስዊዲናዊው አሰልጣኛችን ሩጫና ረጅም ዝላይ ያሠራኝ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ፉክክርም አልነበረም፡፡ ሌላ ደግሞ በእግር መሄድ እወዳለሁ፡፡ የዛሬን አያድርገውና ጀሞ ሄጄ ብረት አነሳ ነበር፡፡ ኢኒጂነር ሃይሉ የሚወዱት ምግብና መጠጥ ምንድነው? ሰው ጠጅ ይላል አይደል፤ እኔ ጠላ ነው የምወደው። አሁን ዳያቤቲክ ስለሆንኩ ሳላውቀው ጥሩ ነገር ነው የመረጥኩት፡፡ ከምግብ የጣሊያንና የፈረንሳይ ምግብ እወዳለሁ፡፡ ከእኛ ደግሞ ገጠር ስሄድ ጥብስ እና ሚጥሚጣ ነው የምወደው፡፡ ልጆቼ በአገራቸው ባህል ባለማደጋቸው ቅሬታ አለኝ ብለዋል--- ሶስቱ ልጆቼ በጣም ትንሽ ሆነው ነው ወደ ውጪ የሄዱት፡፡ የኔ ትኩረት እነሱ ላይ አልነበረም፡፡ አንድ አባት ለልጆቹ ያን ትኩረት ካልሰጠ ቅር ይለዋል፡፡ የኔ አባት እስከሚሞት ድረስ ትኩረት ሰጥቶኛል፡፡

እኔ ያን ለልጆቼ አልሰጠሁም፤ በዚህ ይቆጨኛል፡፡ ትልቅ ለውጥ አመጣለሁ ብዬ አይደለም፡፡ ወጣት በወጣትነት መንገዱ ይሄዳል፡፡ አማራጮች እንዳሉ የማሳየት፣ እኔ ምን አይነት ዲሲፕሊን ኖሮኝ እንዳደግሁ እንዲያውቁ የማድረግ ነገር ነው፡፡ ወንዶቹን ደርግ ወታደር ውስጥ ይከታቸዋል በሚል ስጋት ያለጊዜያቸው ከኢትዮጵያ አስወጣኋቸው። ጓደኞቻቸው ተገድለዋል፤ ብዙዎች ታስረዋል፤ በኋላ ሳስበው ቀውጢ ጊዜ ባይሆን ኖሮ ልጆቼ ምን አይነት ልጆች ይሆኑ ነበር እላለሁ፡፡ አባቴ ትምህርት ሳይሆን ፍቅር ሰጥቶኛል፡፡ የኔ ልጅ ከኔ መማር ነበረባቸው ብዬ ይቆጨኛል፡፡ ሌላ መጽሐፍ እየፃፉ ነው፡፡ ከአሁኑ በምን ይለያል? አሁን የወጣው ተከታይ ክፍል አለው፡፡ በእንግሊዝኛ ዝርዝሮች የተካተቱበት መጽሐፍ አወጣለሁ፡፡ ያው እንደምታይው ከእስር ቤት ቅርስ አንዱ ህመም ነው፡፡ ቀጥ ብዬ መሄድ አልችልም፤ ህክምናዬን ጨርሼ ስመጣ መጽሐፉ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ፡፡

Read 1738 times