Print this page
Saturday, 21 September 2013 10:23

ዓለምን ያስደመሙ ተአምራት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(55 votes)
  • የሚያማምሩ አበቦች ከሰማይ መዝነብ የወርቃማዋ ፀሐይ ተአምር
  • በደመና የማርያም መገለጥ
  • ደም የምታነባው የማርያም ስዕል

የክርስትና ሃይማኖት መሠረት የሆነው መፅሃፍ ቅዱስ በየዘመናቱ የተለያዩ ተአምራቶች መደረጋቸውን ዘግቧል። ሠዎች በተፈጥሮ ካላቸው መረዳት ውጪ የሆኑ ተአምራቶች በዚሁ ቅዱስ መፅሃፍ የተለያዩ ክፍሎች ተካተው እናገኛለን፡፡ ለምሣሌ የቅዱስ ኤልያስ ወደ ሠማይ በደመና ታጅቦ በሠረገላ ማረግ፣ የበለአም አህያ አፍ አውጥታ መናገሯ፣ አብርሃም ልጁ ይስሃቅን ለመስዋዕት ሲያቀርብ በልጁ ፋንታ እግዚአብሔር ከሠማይ በግ ማውረዱ፣ እግዚአብሔር በእጁ የፃፈው አስርቱ ትዕዛዛት ያሉበት ፅላት በቁጥቋጦ መሃል በእሣት ለሙሴ መገለፁ፣ ኤልሣዕ የተባለው ነቢይ የሞተችን ህፃን ማስነሣቱ እንዲሁም ይኸው ነብይ ባዶ የነበረን የድሃዋን ሴት የዘይት ቋት በዘይት እንዲሞላ ማድረጉ እና የመሣሠሉት ብሉይ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሠው የምናገኛቸው ናቸው፡፡

የአይሁድ እምነትም እነዚህን ተአምራቶች ይጋራል፡፡ እነዚህን መሠል የተአምራት ዘገባዎች፣ ኢየሡስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣቱንና ተልዕኮውን ፈፅሞ ወደ ሠማይ ማረጉን በሚዘረዝረው አዲስ ኪዳን መፅሃፍ ውስጥም እናገኛለን፡፡ ኢየሡስ ክርስቶስ የሞቱ ሠዎችን ማስነሣቱ፣ በጥምቀቱ ወቅትም መንፈስ ቅዱስ በእርግብ ተመስሎ በአደባባይ ከሠማይ መውረዱ፣ ኢየሡስ ክርስቶስ ሲሠቀል ምድር በቀን ጨለማ መዋጧ፣ ከዋክብት መርገፋቸው፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃዎች መቀደዳቸው የመሣሠሉት በመፅሃፉ ክፍሎች ተአምራት ተብለው የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በቡዲህዝም የሃይማኖት መዛግብት ውስጥም አንዳንድ ተዓምራት ሠፍረው ይገኛሉ፡፡

645-527 ዓ.ዓለም የኖረው ኢቻይዶን የተባለው የቡዲህዝም ሃይማኖት ነቢይ፤ በወቅቱ በነበረው የኮርያ ንጉስ አንገቱ ተቀልቶ እንዲሞት ሲፈረድበት፣ በሞቱ እለት ብዙ ተአምራቶች እንደሚፈፀሙ ተናግሮ ነበር፡፡ የሞት ፍርድ ሲፈፀምበትና ነፍሡ ከስጋው ሲለይ የሚከተሉት ተአምራቶች መፈፀማቸው በሃይማኖቱ ድርሣናት ተዘግቧል፡፡ በእለቱ ምድር በሃይል ተንቀጥቅጣለች፣ ፀሃይ ጨልማለች፣ የሚያማምሩ አበቦች ከሠማይ ዘንበዋል፣ አንገቱ ሲቀላ ከአንገቱ በደም ፋንታ ነጭ ወተት ፈሷል፡፡ የወተቱ ፍንጣሪም እስከ 100 ጫማ ሽቅብ ወደ ላይ ተስፈንጥሯል፡፡ ይህን ተአምር የተመለከተው የወቅቱ ንጉስ ሄይንግ ኮሡንግ ጆን፤ “ቡዲህዝም እውነተኛ ሃይማኖት ነው” ብሎ በማመኑ መንግስታዊ ሃይማኖት እንዲሆን አውጇል፡፡

በክርስትናው አለም ደግሞ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላም በርካታ ተአምራቶች መፈጠራቸው ተዘግቧል፡፡ እስካሁንም ሃገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የአለም ሃገራት የተአምራት ዘገባዎች ከአብያተ ክርስቲያናት ይቀርባሉ፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሠዎች ታይተዋል የተባሉና እውቅና የሠጠቻቸው ተአምራት በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረ እግር አልባ ስፔናዊ ወጣት፤ በፀሎት ሃይል ከጊዜያት በኋላ እግሩ እንደነበረ መመለሡ ተአምር ተብለው እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ይጠቀሳል። ሌላው እውቅና የተሠጠው ተአምር ኦክቶበር 13 ቀን 1917 ዓ.ም በፖርቹጋል የታየው የፀሃይ ተአምር ነው።

በዚህ ተአምር ፀሃይ ለደቂቃዎች ቀለሟ ወደ ደማቅ ወርቃማነት ተቀይሯል፣ ዳንስ በሚመስል እንቅስቃሴ ውስጥ ለ10 ደቂቃ ቆይታለች፣ ወደ መሬት በጣም በመጠጋቷም ከፍተኛ ሙቀት ተከስቷል እንዲሁም በዚህ ወቅት ቀደም ብሎ በዘነበው ሃይለኛ ዝናብ የረጠበው የሠዎች ልብስ እና ምድሪቱ ክው ብለው ደርቀዋል፡፡ ይህን ትዕይንትም ከ70ሺ እስከ 10ሺ ሠዎች ተመልክተውታል ተብሎ ተዘግቧል፡፡ በዚያው በፖርቹጋል በ16ኛው መቶ ክ.ዘመን ቅድስት ድንግል ማርያም ከነልጇ በሠማይ ላይ ምስሏ በሚያንፀባርቅ ወርቃማ ቀለም ታጅቦ በደመና መሃል መታየቱ ተዘግቧል፡፡ በካቶሊክ የአስተምህሮ መፅሃፎች ውስጥ ይህን የመሣሠሉ ተአምራቶች የተመለከቱና ተአምራቶቹን ራሣቸው የፈፀሙ 41 ያህል ቅዱሣን ሠዎች ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡

በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ተአምራቶች በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአድናቆት ተቀባይነት የማግኘታቸውን ያህል የሚቃወሟቸውም በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል የአሜሪካ የአብዮት ጠንሣሽ የሚባለው ቶማስ ፔይን በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን መፅሃፍቶች ውስጥ የምናገኛቸው ተአምራቶች በሙሉ ሠዎች እንዲያምኑ ተቀነባብረው የቀረቡና የሚያቄሉ ናቸው ሲል በአንድ ወቅት ፅፏል፡፡ አሜሪካዊው ቶማስ ጀፈርሠን በአዲስ ኪዳን የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ተፅፈው የሚገኙና በእሡ አመለካከት ከተፈጥሮ በላይ (Super natural) የሆኑ ተአምራቶችን የሚተርኩትን ቆርጦ በማውጣት የተሻሻለ መፅሃፍ ቅዱስ አሣትሞ ነበር፡፡ የአሜሪካ ሁለተኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን አዳምስ በበኩላቸው፤ “እግዚአብሔር አለምን የሚገዛው በራሱ ህግ ነው ወይስ በነገስታትና በቀሣውስት ልቦለዳዊ የተአምር ፈጠራ?” ሲሉ ጥያቄ አዘል ፅሁፍ አስነብበው ነበር፡፡ ርዕሠ ጉዳዩም ለዘመናት አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡

በቅርብ ጊዜም ለሠዎች ታይተዋል ተብለው በሃይማኖቶች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ፣ ነገር ግን ለሣይንስ ተመራማሪዎች ዛሬም ድረስ ግራ እንዳጋቡ የዘለቁ ተአምራቶች ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ተአምራቶችም በተለያዩ አለማአቀፍ ሚዲያዎች የተዘገቡ ናቸው፡፡ About.com ካሠፈራቸው የአለማችን ምርጥ 10 የሃይማኖታዊ ሚስጥሮች እና ተአምሮች መካከል የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የድንግል ማርያም መገለጥ ለዘመናት ድንግል ማርያም በዚህ ቦታ ተገለጠች የሚሉ ተአምሮች ተነግረዋል፡፡ ነገር ግን እውቅና አግኝተው በታሪክ ከተመዘገቡት መካከል በሜክሲኮ እ.ኤ.አ በ1531፣ በፖርቹጋል በ1917፣ በፈረንሣይ በ1858፣ በፖላንድ በ1877 ድንግል ማርያም በሠማይ ላይ በደመና መገለጧ ተዘግቧል፡፡

በክሮሽያ ደግሞ የድንግል ማርያም ምስል እስከዛሬ በተደጋጋሚ በሠማይ ላይ እንደሚገለፅ ይታመናል፡፡ በግብፅ ደግሞ በ1968 የማሪያም በደመና ታጅባ በሠማይ ላይ መገለጥ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሣይቀር እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ የመላዕክት መገለጥ በአያሌ ሠዎች የመላዕክቶች መገለጥ ተነግሯል። በርካታ ፅሁፎችም ይህንኑ ትንግርት አትተዋል። እስከዛሬም መላዕክቶችን በቀን አየኋቸው፣ በሌት ተገለጡልኝ የሚሉ ግለሠቦች ለሃይማኖት መሪዎቻቸው ሪፖርት እንደሚያደርጉ ይነገራል፡፡ የቅዱሣን ስዕላት ተአምር በሠው እጅ የተቀረፁ እና የተሣሉ የድንግል ማርያም እና የኢየሡስ ክርስቶስ ምስሎች ሲያለቅሡ፣ ደም ሲፈሳቸው ተመልክተናል የሚሉ እማኞች በአለም ዙሪያ በርካታ መሆናቸውን ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡ በእስራኤል ቤተልሄም በሚገኝ አንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁሌ ደም የምታነባ የማርያም ስዕል እንዳለች ተዘግቧል፡፡

በአሜሪካ ኤሊኖስ ግዛት በሚገኝ የኦርቶዶክሣውያን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንም የምታለቅስ የማርያም ምስል መኖሯ ከተዘገቡት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲህ መሠል ክስተቶች በካናዳ፣ በአውስትራሊያ እና በሌሎች በርካታ ሃገራት በድንቃድንቅ ሃይማኖታዊ ተአምራትነት ተመዝግበው እናገኛለን፡፡ ከነዚህ ድንቃድንቅ ሃይማኖታዊ ተአምራቶች ባሻገር የኢየሡስ ክርስቶስ ምስል በሠማይ ላይ መገለጥ በብራዚል፣ እንዲሁም የኢየሡስ ክርስቶስ መግነዘ ጨርቅ መገለጥ በጣሊያን መታየታቸውን የተለያዩ ዘገባዎች ያወሳሉ፡፡ ከክዋክብትና ከጨረቃ ጋር በተገናኘም ሃይማኖታዊ ትዕንግርት ናቸው ተብለው የሚታመኑ ተአምራቶች ተፈፅመዋል፡፡ የጨረቃ ደም መምሠል፣ የክዋክብት መርገፍ የመሣሠሉት በየጊዜው ይነገራሉ፡፡ በሃገራችንም መሠል ተአምራቶች ተከስተዋል የሚለው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በደንብ የተደራጀ መረጃ ባናገኝም በብዙ የገድልና የተአምራት ድርሣናት ውስጥ የተፃፉ የተአምር መገለጥ ዘገባዎች አሉ፡፡

ምናልባትም ወደፊት ከነዚህ ተአምራቶች አንዱ ሆኖ ሊመዘገብ እንደሚችል የሚገመተው ከሠሞኑ “ከሰማይ መስቀል ወረደ” የሚለው ጉዳይም አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ አንዳንዶች ስለ ትዕንግርቱ ብዙ መመራመር ሳይፈቅዱ ከሠማይ መውረዱን አምነው የተቀበሉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ “እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ” በማለት እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ተመራማሪዎች መሠል ክስተቶችን ለበርካታ ጊዜያት በአንክሮ ያጤኗቸው ሲሆን አንዳንዶቹን ከአስማታዊ ምትሃት ጋር ሲያገናኟቸው የከዋክብት መርገፍ የመሣሠሉትን ከዩፎዎች ትዕንግርታዊ ስራ ጋር ያያይዟቸዋል። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ እስካሁንም ምላሽ አልተገኘላቸውም፡፡ ሌሎች ትዕንግርቶች ከሃይማኖታዊ ተአምራቶች ሌላ ከተፈጥሮ ሂደት ውጪ የሆኑ ትዕንግርቶች በተለያዩ ድርሣናት ተመዝግበውና እውቅና ተሠጥቷቸው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል የእንቁራሪቶች፣ የአሣዎች፣ እባቦች እንዲሁም የአዕዋፋት ከሠማይ መዝነብ ተጠቃሽ ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል በ1680 እ.ኤ.አ በሲንጋፖር እባቦች ከሠማይ መዝነባቸው ተዘግቧል። በፌብሩዋሪ 22 ቀን 1861 ዓ.ም በዚያችው በሲንጋፖር የአሣ ዝናብ መዝነቡ የተመዘገበ ሲሆን ሜይ 15 ቀን 1900 በሮድ ደሤት፣ ኦክቶበር 23 ቀን1947 በሉዚኒያ፣ ፌብሩዋሪ 12 ቀን 2008 በህንድ፣ ኦክቶበር 24 ቀን 2009 በድጋሚ በህንድ፣ ፌብሩዋሪ 25 እና 26 ቀን 2010 በአውስትራሊያ፣ ጃንዋሪ 13 ቀን 2012 በፊሊፒንስ አሣዎች ከሠማይ መዝነባቸው ተመልክቷል፡፡ የእንቁራሪቶች ከሠማይ መዝነብ ደግሞ በጁን 2009 በጃፓን፣ ከጁን 18-20 2010 ደግሞ በሃንጋሪ ተመዝግቧል፡፡ ሌሎች እስከዛሬ ምንነታቸው ያልታወቀ እንስሳትም በካሊፎርኒያ በኦገስት 1 ቀን 1869 እንዲሁም በኬንታኪ በ1876 መዝነባቸው ተመልክቷል፡፡

በ1894 ደግሞ በእንግሊዝ የጄሊፊሽ ዝናብ ተከስቷል ይባላል፡፡ በአርጀንቲናም ኤፕሪል 6 ቀን 2007 ዓ.ም ጊንጦች ከሠማይ ዘንበዋል፡፡ ተመሳሳይ ትዕንግርት በብራዚል ፌብሩዋሪ 3 ቀን 2013 ዓ.ም እንደተከሰተ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንዳንድ ሣይንቲስቶች የተለያዩ እንስሣትን ከሠማይ መዝነብ አስመልክተው ባሠፈሯቸው የምርምር ውጤቶች፤ ጉዳዩን ከሃይለኛ ንፋስ ጋር ያያይዙታል፡፡ በተለይ ቶርኔዶ የተሠኘው ሃይለኛ ነፋስ ሲነፍስ እነዚህ የውሃ ውስጥ እንስሣት እና ሌሎች የምድር ላይ እንስሣትን ወደ ሠማይ በማንሣፈፍ አርቆ እንደሚጥላቸው ይገልፃሉ። ቶርኔዶ የተሠኘው የንፋስ አይነት ከሃይለኝነቱ የተነሣ በሠከንዶች ውስጥ መጠነኛ የውሃ ይዘት ያለውን ሃይቅ ውሃ ጠራርጐ የመውሠድ አቅምም እንዳለው ተመራማሪዎች ያመለክታሉ፡፡

Read 23149 times