Print this page
Saturday, 21 September 2013 10:51

አየር ቢሸጥ እንደ ኢትዮጵያ ሀብታም የለም ነበር!

Written by  በሰለሞን ኃይለማርያም
Rate this item
(4 votes)

“የአገሬ ብርድ ግደለኝ፣ የአገሬ ፀሃይ ማረኝ፣ የአገሬ ዝናብ ደብድበኝ”

                    በአዲስ አበባም ሆነ ባብዛኛው የሀገራችን ክፍል ያለውን ያየር ፀባይ በዋዛ በማየት ተገቢውን ክብርና ዋጋ እንዳልሰጠነው ከተገነዘብኩ ቆየት ብያለሁ፡፡ ይህንን ግንዛቤዬን የበለጠ ያረጋገጠልኝ በቅርቡ ወደ አውሮፓ ያደረግሁት ጉዞ ነው፡፡ በየአመቱ በሚደረገው የፔን ዓለምአቀፍ ጉባዔ ተጋብዤ የአይስላንድ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ሬይኬቪክ መጓዜ የሀገሬ ብርድ ግደለኝ፤ የሀገሬ ፀሐይ ማረኝ፤ የሀገሬ ዝናብ ደብድበኝ ብዬ እንድመለስ አድርጐኛል፡፡ በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ የምትገኘው ትንሿ ደሴት በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ መሀል ተሸጉጣለች። አብዛኞቹ ነዋሪዎች እንግሊዝኛ የሚናገሩ ቢሆንም አይስላንዶች የራሳቸው አይስላንዲክ ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ ቋንቋቸውም ከእንግሊዝኛ ይልቅ ለስካንዲኒቪያን ቋንቋዎች የቀረበ ነው።

በሬይኬቪክ ዛፎች ለምልክት ካልሆነ በስተቀር የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ለዘመናት በብርድ የተገረፈው ይህ አገር፣ ድንጋያማ ነው - በአለት የተሞላ፡፡ ኮረብታውም ሆነ ተራራው የገረጣና የጠየመ አለት ድንጋይ ነው፡፡ ሁለት መቶ ያህል እሳተገሞራዎች የፈነዱባት አይስላንድ፤ ብዙ ከአለት ሥር የተኙ ፍልውሃዎች ባለቤት ናት፡፡ ግሪን ላጐን እየተባለ የሚጠራውን ታዋቂ የፍልውሃ መዋኛን ጨምሮ ብዙ የፍልውሃ መዝናኛዎች፤ ፏፏቴዎችና ለአይን የሚማርኩ ወንዞች አሏት፡፡ የአይስላንድ ዋና ከተማ ሬይኬቪክ ስፋቷ በጣም ትንሽ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ሰው ብርዱና ዝናቡ ካላወከው በቀር በ30 ደቂቃ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሊያካልላት ይችላል፡፡

በሬይኬቪክ ብዙዎቹ ህንፃዎች ከአምስት ፎቅ የማይበልጡ ሲሆን ከተማው ውስጥ ዓይን የሚስበው ብቸኛ ህንፃ ወደጠፈር ለመብረር እንደተዘረጋ የህዋ ሰረገላ ወይም ክንፉን እንደጣለ ግዙፍ የአሞራ ቅርጽ የተሰራው ቤተክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ ጠቅላላው የአይስላንድ ህዝብ ቁጥር ከሁለት መቶ ሃምሣ ሺህ አይበልጥም፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚም ከአሣ ማስገርና ወደ ውጭ መላክ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው። የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ደረጃ ከምዕራብ አውሮፓ ጋር የሚስተካከል ነው፡፡ ይሁንና አውሮፓዎችም ቢሆኑ ዘላቂ ህይወታቸውን በአይስላንድ ለመቀጠል የአየር ጠባዩ ስለሚፈታተናቸው የህዝቡ ቁጥር ከአመት አመት እጅግም ለማደግ አልተቻለውም፡፡

የአይስላንድ መንግስት ይህንን ተግዳሮት በመገንዘብ በተለይ ቱሪስቶች ከቀረጥ ነፃ የሚሆኑበትን መንገድ አመቻችቷል፡፡ ዘመናዊ የየብስ፤ የባህርና የአየር መጓጓዣዎች በመኖራቸው ቱሪስቶች በምቾት ወደፈለጉበት ሥፍራ እንዲጓጓዙ ሆኗል፡፡ በሬይኬቪክ ከተማ በጣም የገረመኝ ብዙ ቱሪስት ማየቴ ነው፡፡ አስቸጋሪ በሆነው የከተማዋ የአየር ፀባይ ይህንን ያህል ቱሪስት እንዴት ተገኘ? በዚህ በቁር ከተማ ይህንን ያህል ቱሪስት መምጣት ነበረበት? እያልኩ ከራሴ ጋር ሙግት መግጠሜ አልቀረም፡፡ እኔ ባረፍኩበት ፎስ ሆቴል የነበሩ የጀርመን፣ የፊንላንድና የአሜሪካ እንዲሁም ፋሮ አይላንድ ከተባለ አስገራሚ ሀገር የመጡ ቱሪስቶችን አናግሬያቸው ነበር፡፡ በመጀመርያ ከፋሮ አይላንድ የመጡ ሶስት ሴትና ሶስት ወንዶችን ሳናግራቸው “ፋሮ አይላንድ” የሚባል ሰምቼ ስላማላውቅ የት ነው ፋሮ አይላንድ ብዬ ስጠይቃቸው፣ ካርታ አወጡና ማሳየት ጀመሩ፡፡ በአውሮፓም ሆነ በሌሎች የሰለጠኑ ሀገሮች ለትንሹም ለትልቁም ካርታ እየመዘዙ አቅጣጫ ማመላከት የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ አቅጣጫውን ሲያሳዩኝ ነጥብ የምታክል ደሴት ናት፡፡ በዙሪያዋ ዴንማርክ ስላለች “ከዴንማርክ ነው የመጣችሁት?” ስላቸው ፊታቸው ተቀያየረና “ከፋሮ ደሴት ነው የመጣነው” አሉ፡፡

ክሌር የተባለች መልኳ ከአውሮፓ ይልቅ ለአረቦች የቀረበ ሴት “ፌሮ ደሴት ከዴንማርክ ለመገንጠል የምትጥር ነች፡፡ ለጊዜው ግን በዴንማርክ አገዛዝ ስር ነን፡፡ የራሳችን ቋንቋና ባህል አለን” አለችኝ፤ ፈርጠም ብላ፡፡ እኔም ክሌርን አመስግኜ የፖለቲካ እሰጥ እገባ እንዳልፈለግሁ በመግለጽ እንዴት አይስላንድን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደመረጡ ጠየቅኋቸው፡፡ እነሱም ለሀገራቸው ቅርብ በመሆኗ፤ በቂ መረጃ በማግኘታቸውና ምቹ የአየር በረራ ስላላት እንደሆነ ገለፁልኝ፡፡ ከፌሮ ደሴት ቱሪስቶች ቀጥሎ ከጀርመን ሀምቡርግ የመጡትን ነበር የጠየቅኋቸው፡፡ ከሀምቡርግ የመጡትም ከበርሊን ወይም ፍራንክፈርት ይልቅ የኔዘርላንዷ አምስተርዳም እንደምትቀርባቸውና በ30 ደቂቃ ከሀምቡርግ ኔዘርላንድ እንደሚገቡ አጫወቱኝ፡፡ “ለምን አይስላንድን መረጣችሁ? ለምን ውቧን ኢትዮጵያ አትጐበኙም?” አልኳቸው፤ ትንሽ እያሳቅኋቸው፡፡ “ስለኢትዮጵያ ሰምተን አናውቅም፤ ስለ አይስላንድ በየመረጃ መረቡ፤ በቴሌቪዥኑ እናያለን፡፡ ሲመቸን መጣን፤ ሦስት አመት አጠራቅመን ነው የመጣነው፤ እስኪ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ እናጠናለን” አሉ፡፡ ከአሜሪካ የመጡት ቱሪስቶች ደግሞ “አይስላንድ የመጣነው ኪስ አውላቂ ሌባ እንኳ የሌለባት ፀጥተኛና ሰላማዊ ሀገር ስለሆነ ነው” ብለዋል፡፡

በነገራችን ላይ አይስላንድ የጦር ሰራዊት የላትም፤ ሌላ ቀርቶ የኔቶ የጦር መርከብና አየር ሃይል በሀገራቸው እንዳይንቀሳቀስ እየታገሉ ነው፡፡ በርግጥ ይህቺን ሚጢጢ ደሴት መጐብኘት እንደጀብዱ እንደሚቆጥሩትም አሜሪካኖቹ አልሸሸጉኝም፡፡ ሆነም ቀረ ምቹ የአየር ፀባይ ያላት ሀገራችን፤ ማንም ሰው ሳይሳቅቅ የሚጐበኛት ኢትዮጵያ፣ ለምን የሚገባትን ያህል ቱሪስቶች ለመሣብ አልቻለችም? እያልኩ ማሰቤን አላቋረጥኩም፡፡ አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ያላትና ውድ የሆነችው ሬይኬቪክ ቱሪስት ከሳበች፣ ኢትዮጵያ የበለጠ ቱሪስት የማትስብበት ምክንያት አልታየኝም፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ የአየር ጠባይ ብዙ ሊወራለት የሚገባ ሀብታችን ነው፡፡ ያረፍኩበት ሆቴል በባህር ዳርቻ አጠገብ ያለ ፎስ ሆቴል የሚባል እንደሆነ ጠቅሻለሁ፡፡ የተሰበሰብንበት አዳራሽ ደግሞ በከተማው ሌላ አይን የሚገባ ከክሪስታል የተሰራ የአራት መዐዘን ቅርፅ ያለው ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን ከሩቅ ሲመለከቱት የጠርሙስ ስብስብ ይመስላል፡፡

ሀርፖ የተባለው የመሰበሰቢያ አዳራሽ፤ ላቅና መጠቅ ያለ ጥበብ ይታይበታል፡፡ ይህንን የሰራው አርክቴክት ብዙ ሌሊቶችንና ቀናቶችን ያለ እንቅልፍ እንዳሳለፈ ብዙ ምልክቶች ትቷል፡፡ ከውስብስቡ የመስታወት ስራ ባሻገር ከአመት አመት ዝናብና ብርድ የማያጣውን የሬይኬቪክ ከተማ ብሩህና ምቹ ለማድረግ ብዙ ተለፍቶበታል፡፡ ካረፍኩበት ሆቴል እስከ መሰብሰቢያው አዳራሽ ቢበዛ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ነው፡፡ ታክሲ በጣም ውድ በመሆኑ የማይሞከር ነው፡፡ ለአውቶቡስ ደግሞ አጭር መንገድ ሆነ፡፡ በዚህ የተነሣ በእግራችን ማቅጠን የግድ ነበር፡፡ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ምን ችግር አለው ትሉ ይሆናል? በርግጥ በሀገራችን የአየር ጠባይ፣ በሸጋው አዲስ አበባ እንኳን 10 ደቂቃ ሌላም ቢሆን ችግር የለውም፡፡ ብርዱና ውሽንፍሩ እያፏጨ ጆሮ የሚበጥሰው፣ ፊት የሚገርፈው የሬይኬቪክ አየር ባለበት አንድ ደቂቃ ቀጥ ብሎ መራመድ ግን ፈተና ነው፡፡ ወይ አዲስ አበባ! ኧረ አየርሽ ይግደለኝ የሚያስብል ነው፡፡ አየር እየታሸገ ወደ ውጭ ሀገር የሚላክ ቢሆን ኖሮ፣ እንደ ኢትዮጵያ ሀብታም ሀገር ይኖር ይሆን? እንጃ? በጐበኘኋቸው ሀገራት ባብዛኛው ወይ ሙቀቱ ልብስ ያስጥላል ያለበለዚያ ብርዱ የተወለዱበትን ቀን ያስቆጥራል፡፡ የአዲስ አበባ አየር በብዙ መልኩ ሲታይ የተመጣጠነና ለኑሮ የተመቸ ነው፡፡ እርግጥ ነው በአይስላንድ ያለውን ከባድ ቅዝቃዜ ለመቋቋም ሙቀት ሰጪ ምግቦችን መብላት፤ ሙቀት ሰጪ የሆኑ ዘመናዊ ልብሶችን መልበስ የግድ ነው፡፡ ዘመናዊ ልብስ ያልኩት ብርድን ለመቋቋም ተብለው በልዩ ሁኔታ የተመረቱ ልብሶች በመኖራቸው ነው፡፡ ይሁንና ልብሱም ሆነ ምግቡ ውድ ነው፡፡ ለምሣሌ በአራት ጉርሻ የሚያልቅ ጥሩ ፒዛ አራት ሺ አይስላንድ ክሮነር ነው፡፡

ይህ ማለት ወደ ብር ስንቀይረው ወደ 750ብር ገደማ መሆኑ ነው፡፡ የሀገሩ የደሞዝ መጠን በአውሮፓ ደረጃ በመሆኑ ይህንን ከፍሎ መመገብ ብዙ አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል ነገር ግን ምግቡም ሆነ መጠጡ ዋዛ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው፡፡ በዚህ ላይ የተበላው ምግብ መቼ ከሆድ እንደሚጠፋ አይታወቅም፤ አሁን በልቶ አሁን አምጡ ያሰኛል፡፡ ብርዱ ብዙ ወጪን ያስከትላል፡፡ እንደ አዲስ አበባ ቤቶች ማሞቂያም ማቀዝቀዣም የሌላቸው ቤቶች የሉም፡፡ በሬይኬቪክ እያንዳንዱ ቤት ገና ሲሰራ ጀምሮ ማሞቂያ ይገጠምላቸዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ከተማዋ ተጨማሪ የሀይል ፍላጐት ትጠይቃለች፡፡ ይህንን የሀይል (የሙቀት) ሂሣብ በመጨረሻ የሚከፍለው ነዋሪው ነው፡፡ በሀገራችን ያለው ሸጋው የአየር ፀባይ እንደ አሣማ ከመብላት እንዳዳነን የተገነዘብኩት እዚሁ ሬይኬቪክ ነው፡፡ ለጉባዔውና ለተሰብሳቢዎቹ ክብር የራት ግብዣ ተደርጐልን፣ ሆዳችን ቅሪላ እስኪያክል በልተን፤ አንዳንዶቻችንም ያለገደብ በቀረበው የወይን ጠጅ ሰክረን፣ ገና ከድግሱ አዳራሽ ወጥተን ጥቂት እንደተራመድን መብላት መጠጣታችን ተረስቶ ብርዱ ሆዳችን ገብቶ ያንሰፈስፈን ገባ፡፡ የበላነው ቡርንዶ አሣ፤ ሞቅ ያደረገን የወይን ጠጅን ብርዱ ይዞት ጠፋ!፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንኳን የሸመተ ያረሰስ ይችለዋል እንዴ? አወይ የአዲስ አበባ አየር መልካምነት! ውዱ የአዲስ አበባ አየርን እንደዋዛ እያየነው፣ እንደ እርጐ የሚገመጠውን የሸገር መዐዛ ያለውን የሀገራችንን ነፋስ መጠበቅ፤ መንከባከብ ችላ ያልነው ይመስለኛል፡፡ ልዩና ማራኪ የሆነው የሀገራችን የአየር ፀባይ፣ በተለይም የአዲስ አበባ አየር በምንም ሊለወጥ የማይችል ሀብታችን ነው፡፡ አሁን አሁን በእንጦጦ ተራራ ላይ ያለው የባህር ዛፍ እየሳሳ ነው፡፡ ከሩቅ ሲታይ ጥቅጥቅ ያለ ደን ይመስላል፤ ቀርበው ሲያዩት ግን መንምኗል፡፡ የአዲስ አበባ ምርጡ አየር ሚስጥሩ ይህ ደን በመሆኑ ተገቢ ጥበቃ ይሻል፡፡ በየአመቱ ሚሊዮን ዛፎች ቢተከሉም ዋናው መንከባከብ፤ ማሳደግ በመሆኑ የተተከሉት መፅደቃቸውንና ማደጋቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ግንባታዎችም ወደ ደኖቹ ዘልቀው ባይሄዱ መልካም ነው፡፡ በቸር ያቆየን፡፡

Read 2617 times