Print this page
Saturday, 21 September 2013 10:54

ጂኦቴል ለተማሪዎች ላፕቶፕ ሊያቀርብ ነው

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በ43 ሚሊየን ብር የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ሊሠራ ነው “የጉምሩክ አሰራር ቀልጣፋ አይደለም”

ለአገራችን እንግዳ ይሁን እንጂ በኤስያና በብዙ የአፍሪካ አገራት ታዋቂ ነው፡፡ በአፍሪካ፣ በናይጄሪያ፣ በታንዛንያ፣ በኮንጎ ኪንሳሻ፣ በሴኔጋልና በኬንያ፤ በኤስያ ደግሞ በሕንድ፣ በዱባይ፣ በሆንግኮንግ፣ በቪየትናም፣ … በአጠቃላይ በመላው ዓለም ከ20 አገሮች በላይ ቅርንጫፎች አሉት - ሞባይልና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አምራች የሆነው ጂኦቴል፡፡ መሠረቱ ቻይና ሸንዘን የሆነው ጂኦቴል፤ መካከለኛ ሞባይሎችን ዲዛይን እያደረገ የሚያመርት የኤሌክትሪክ ኩባንያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ሞባይሎች ለመገጣጠም ሥራ የጀመረው በቅርቡ ነው - ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር፡፡ “ተልዕኳችን፣ ለአጠቃቀም ቀላልና ምቹ፣ ከፍተኛ ጥራትና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ሞባይሎች በማቅረብ በዓለም ዙሪያ የሚደረጉ ግንኙነቶችን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ ነው” ይላሉ፤ በኢትዮጵያ የጂኦቴል ሴልስ ማናጀር ሚ/ር ኮቢ፡፡ “የእኛ መርህ፤ ለብቻ መበልፀግ ሳይሆን ከአጋሮቻችን ጋር ማደግና የተሻለ ሕይወት መፍጠር ነው፡፡ ዓላማችን በመተባበር፣ በጋራ እምነት ላይ ተመሥርቶ ሰጥቶ መቀበል (win-win) ነው፡፡

 

ለስኬታችንና ለተወዳዳሪነት መሠረት የሆነን፣ ከማንም በላይ ለሰዎች ፈጠራ ትኩረትና እውቅና መስጠታችንና የአገር ውስጥ ጥሬ ሀብት መጠቀማችን ነው” ብለዋል፡፡ ሚ/ር ኮቢን በዚች አገር ኢንቨስት ለማድረግ ምን እንዳነሳሳቸው ጠየቅኋቸው፡፡ “ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉና ነዳጅ አምራች ካልሆኑ 10 የዓለም አገራት አንዷ ናት። ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ማንኛውም ካፒታልና እውቀት ኢኮኖሚውን ከፍ ያደርጋል፡፡ በዚህ ላይ ካፒታልና እውቀት ወደ ውስጥ የሚገባው በሁለት አቅጣጫ ነው፡፡ አንዱ ቻይናውያን ኢንቨስት የሚያደርጉት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዘመዶቻቸው የሚልኩት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ዶላር ነው፡፡ በዓለም ባንክ ሪፖርት መሠረት ባለፉት 10 ዓመታት ቻይናውያን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርገዋል። በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የአገሪቷን አጠቃላይ ምርት 10 በመቶ ወይም 3.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወደ ኢኮኖሚው አስገብተዋል፡፡ “በኢትዮጵያ ከውጭ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባውን ኢንቨስትመንት (ፎሬይን ዳይሬክት ኢንቨስትመንት) ከምርታማ ዕድገት ጋር ለማቆራኘት ያለው ዕድል ጠባብ ቢሆንም፣ መንግሥት፣ ሕዝብና ኢኮኖሚው፣ ዝግ ከሆነ ባህላዊ ኢኮኖሚ ተላቅቆ ፈጣን የሆነውን የዓለም ገበያ ይቀላቀላል የሚል እምነት አለን፡፡ እነዚህንና ሌሎች የዕድገት አማራጮችን በማጥናት ነው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የወሰነው” በማለት አብራርተዋል፡፡ ጂኦቴል በኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ያስረዱን፣ የጂኦቴል ባለቤት የሚ/ር ዣዥዋ አማካሪ አቶ ሰይፈ ስዩምና የማርኬቲንግ ኃላፊው አቶ አብዱልዓሊም አብደላ ናቸው። ጂኦቴል በኢትዮጵያ ሲመሠረት ካፒታሉ ምን ያህል ነው? አልኳቸው፡፡ አንድ ሚሊዮን 600ሺህ ብር ነበር፡፡

============

ምን ዓይነት ሞባይሎች ነው የምታመርቱት? በአሁኑ ወቅት ስማርት ፎን (ታብሌት) ወይም ሚኒ ኮምፒዩተር እና ተች ስክሪን ጨምሮ 22 ዓይነት የተለያዩ ሞባይሎች እናመርታለን፡፡ በአገር ውስጥ ከእኛ በስተቀር ስማርት ፎን የሚያመርት የለም። ስማርት ፎናችን እነ ጋላክሲ፣ አፕል፣ ሳምሰንግ፣ የሚጠቀሙበት አንድሮይድ የተባለ ፈጣን ሶፍትዌር የተገጠመለት ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በጥራትና በዋጋም ደረጃ ቢሆን የደንበኞችን አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ ስማርት ታብሌታችን ኮምፒዩተር ማለት ነው፤ ማንኛውም ኮምፒዩተር የሚሠራውን (ዎርድ፣ ኤክሴል …) ይሠራል፡፡ ዋጋው ምን ያህል ነው? ከ2500 እስከ 3000 ብር ነው፡፡ ደንበኞቻችን “ስማርት ፎንስ ጂኦቴል ይሥራ” እያሉ ስለሚያሞካሹን እንኮራበታለን፡፡ ይህ ሞባይል በከተማ አካባቢ ላሉ ለቴክኖሎጂ ቅርበት ላላቸውና ብዙ አፕሊኬሽን መጠቀም ለሚችሉ ደንበኞች የቀረበ ነው፡፡ በገጠር አካባቢ ላለው ኀብረተሰብስ? የመብራት አቅርቦት ዝቅተኛ በሆነባቸው ከከተማ ውጭ ላሉ የገጠር ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ጥራትና ረዥም የባትሪ ዕድሜ ያለው ሞባይል በአማራጭነት ማቅረባችን ተመራጭ አድርጐናል፡፡ ደንበኞቻችንም በዚህ ደስተኞች ስለሆኑ የሚሰጡን አስተያየት ጥሩና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሞባይሎች ታመርታላችሁ? በዓመት 1.2 ሚሊዮን ሞባይሎችና 120ሺ ላፕቶፖች ለማምረት ነው ያቀድነው፡፡ ነገር ግን አሁን ጀማሪ ስለሆን ይህን ቁጥር አላሟላንም፤ የወደፊት ዕቅዳችን ነው፡፡

አሁን አንዳንድ ጊዜ በወር እስከ 5 ሺህ ሞባይሎች እናመርታለን፡፡ መገጣጣሚያዎቹን ከውጭ ስለምናስመጣ፣ የዶላር እጥረት፣ የዕቃዎቹ መዘግየት፣ … የመሳሰሉ ችግሮች አሉብን፡፡ በሙሉ አቅማችን ማምረት እስክንችል በዓመት እስከ 40ሺህ ሞባይሎች እናመርታለን፡፡ ላፕቶፕ ታመርታላችሁ እንዴ? አዎ! “አንድ ላፕ ቶፕ ለአንድ ተማሪ” በሚለው መርህ መሠረት፣ ወደ 43 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ በምንሠራው ማስፋፊያ፣ ላፕቶፖችን ለመሥራት ከኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ፈቃድ ወስደን እየተዘጋጀን ነው፡፡ መቼ ነው ላፕቶፖቹን መገጣጠም የምትጀምሩት? በመጪው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ወይም በእኛ በጥር ወር ገጣጥመን በርካሽ ዋጋ ለማቅረብ ነው ያቀድነው፡፡ ርካሽ ስትሉ በስንት ብር? ዕቃዎቹን ከውጭ ስለምናስገባ በአምስትና በስድስት ሺህ ብር ለማቅረብ ነው ያቀድነው፡፡ ታዲያ ይኼ ርካሽ ዋጋ ያሰኛል? የተማሪዎችንስ አቅም ያገናዘበ ነው ትላላችሁ? እኛ አትራፊ ድርጅት ነን፡፡

ብዙም ባይሆን መጠነኛ ትርፍ ማግኘት አለብን፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ የሚያደርጉልን ከሆነ ከዚህም በታች ዝቅ ባለ ዋጋ እናቀርባለን፡፡ በእርግጥ በመርህ ደረጃ አንድ ላፕ ቶፕ በ100 ዶላር ይቀርባል፡፡ በአሁን ወቅት የዶላር ምንዛሪ ደግሞ 2000 ብር ያህል ነው፡፡ ይህ በዕርዳታና በድጋፍ ሲሆን ነው፡፡ መገጣጠሚያ ዕቃዎቹ በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የሚመጡ ስለሆነ ውድ ናቸው፡፡ ድጋፍ ካላገኘን በስተቀር በዚህ ዋጋ ማቅረብ ይከብደናል፡፡ በጥር ወር ስማርት ፎንን ጨምሮ በወር አቅምን ያገናዘቡና ጥራት ያላቸው 100ሺ ሞባይሎችና በወር እስከ 30ሺ የሚደርሱ ላፕቶፖች ለማምረት አቅደናል፡፡ የአገር ውስጥ ፍላጐት ካረካን በኋላ ሞባይልና ላፕቶፖች ወደ ሱዳን፣ ላፕቶፕ ደግሞ ወደ ኬንያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ሚና ለመጫወት አቅደናል፡፡ አሁን በገበያ ውስጥ ያላችሁ ድርሻ ምን ያህል ነው? ጀማሪ እንደመሆናችን መጠን ከፍተኛ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን ገበያው ውስጥ መቆየት የሚያስችለን አቅም አለን፡፡ ከገበያው ውስጥ ምን ያህል ድርሻ ለመያዝ ነው ያቀዳችሁት? አዲስ በመሆናችን ያሰብነው ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ በቅርብ ዓመት ውስጥ የአገሪቱ ቁጥር አንድ የሞባይልና የቴክኖሎጂ አቅራቢ ግሩፕ እንሆናለን፡፡

ጥገና መስጫ ማዕከል አላችሁ? መርካቶ አካባቢ ከይርጋ ኃይሌ የገበያ ማዕከል አጠገብ በተሠራው ሕንፃ በቅርቡ የጥገና አገልግሎት እንጀምራለን፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች ደንበኞቻችን ወደ ዋናው የጥገና ማዕከል በመምጣት እንዳይጉላሉ፣ በአቅራቢያቸው ጥገና ቤቶች ከፍተን አገልግሎት ለመስጠት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በዚህ የሞባይል መገጣጠም ሂደት ምን ችግር ገጠማችሁ? ችግሩን አሁን ነው እየተረዳን የመጣነው። ጉምሩክ አካባቢ የሚገባው ቃልና በተግባር የሚገለፀው የተለያየ ነው፡፡ በጉምሩክ ለምንከፍላቸው ታሪፎች፤ “ይለቀቃል” በሚል ታሳቢነት በዲፖዚት (ተቀማጭ) ነው የምናኖረው፡፡ ጉምሩክ ከውጭ የምናስገባቸውን የመገጣጠሚያ ዕቃዎች፣ በውጭ አገር ተገጣጥመው አልቆላቸው እንደሚገቡ ሞባይሎች እንጂ እዚህ እኛ እሴት ጨምረንባቸው እንደሚቀርቡ አያስብም፡፡ ስለዚህ ለዲፖዚት የተቀመጠውን ገንዘብ በታክስ ይወስደዋል እንጂ ታስቦ ቀሪው ተመላሽ አይደረግልንም፡፡

እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ደግሞ ወጪያችንን በትክል እንዳናሰላ ችግር ይፈጥሩብናል። በዚህ አሠራር ላይ ቅሬታ በማቅረባችን “ከዚህ በኋላ እናስተካክላለን” ብለው ከቅርብ ቀን ወዲህ ከዲፖዚት ውጭ እንድናወጣ እየተደረገ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የጉምሩክ አሠራር ቀልጣፋ አይደለም። አሁን ጉምሩክ የሚያስከፍለው ቀረጥ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከውጭ ለመገጣጠም የምናስገባቸው ዕቃዎች፣ ያለቀላቸው ዕቃዎች በሚቀረጡበት ዋጋ ነው የሚቀረጡት፡፡ እኛ ብዙ ወጪዎች አሉብን፡፡ ለቤት ኪራይ ከፍለን፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረን፣ ገቢ ዕቃ አስቀርተን፣ … የምንከፍለው ቀረጥ በጣም ከፍተኛ ነው - ተወዳዳሪ የሚያደርግ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የምናስመጣቸው ዕቃዎች (ለምሳሌ ሶፍትዌር) ጥራት ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ዕቃዎቹን ወደመጡበት አገር ለመመለስ ችግር አለ፡፡ ጉምሩክ ለማስገባት እንጂ የገባውን ለማስወጣት ደንብ የለውም፡፡

እነዚህ ችግር ፈጣሪ ነገሮች ስለሆኑ መስተካከል አለባቸው፡፡ ምን ያህል ሠራተኞች አሏችሁ? ለጊዜው በአይቲ የሠለጠኑ 44 ሠራተኞች አሉን። ከተቀጠሩም በኋላ ሥልጠና እንሰጣቸዋለን። ከሌሎች ሞባይል መገጣጠሚያዎች የተሻለ ስለምንከፍል ከሌሎች ድርጅቶች ለቀው ወደ እኛ የሚመጡ ሠራተኞችም አሉ፡፡ በዚህም ሠራተኞቻችን ከእኛ ጋር ለመሥራት ደስተኞች ናቸው፡፡ ላፕቶፕ መገጣጠምና ሌሎች ማስፋፊያዎች ስንጀምር የሠራተኞቹ ቁጥር ከ80 እስከ 120 ይደርሳል፡፡ የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው? አሁን በኪራይ ቤት ነው የምንሠራው፡፡ በቅርብ ዓመት ውስጥ መሬት ወስደን የራሳችንን ፋብሪካ መገንባት ቀዳሚ ተግባራችን ነው፡፡ ከዚያም በሞባይልና በላፕቶፕ፣ በአጠቃላይ በኤሌክትሮኒክስ ምርት በአገሪቷ ቁጥር አንድ ተመራጭ ኩባንያ መሆን ነው፡፡ ከዚያም ምርቶቻችንን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ነው። የተለያዩ ብራንዶችን በመጠቀም ወደ ገበያው ለመግባትም እቅድ አለን፡፡

Read 5998 times
Administrator

Latest from Administrator