Saturday, 21 September 2013 11:14

…Early loss… የጽንስ መቋረጥ ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(8 votes)

.የሰው ልጅ እራሱን በእራሱ ተካ የሚባለው ልጅ ወልዶ መሳም ሲችል ነው ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ አንድ የተፈጥሮ ሕግ የሚወሰድ መሆኑን ብዙዎች ያምናሉ። ነገር ግን እርግዝናው ከተፈጠረ በሁዋላ ባልታሰበ ጊዜ አደጋ ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ የተለያየ እንደመሆኑ በተቻለ መጠን ሁኔታውን በአትኩሮት መከታተል ይገባል ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡ በዚህ እትም ከአሁን ቀደም የእርግዝና መቋረጥን በደፈናው እስከመወለጃው ጊዜ ድረስ የተመ ለከትን ሲሆን የዛሬው ደግሞ የሚመለከተው በተለይም ቀደም ባሉት ወራት የሚከሰተውን ነው፡፡ ማብራሪያውን የሰጡን ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ ናቸው፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ የጽንስና ማህ ጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የክሊኒካል አገልግሎትና የጥራት ዳይሬክተር ናቸው፡፡

                                                ----------////---------

ጥ/ Early loss… ማለት ምን ማለት ነው? መ/ እርግዝና በሶስት ወቅት የተከፈለ ነው፡፡ እሱም የመጀመሪያው ሶስት ወር ፣ቀጥሎ ያለው ሶስት ወር እና በስተመጨረሻው ያለው ሶስት ወር ነው፡፡ ርእሱ የሚያመለክተው ሁለተኛው ሶስት ወር ከማለቁ በፊት ያለውን ጊዜ ማለትም የአለም ጤና ድርጅት እንደ ሚለው ከ20-22/ሳምንት ወይንም ጽንሱ ከ500/ ግራም በታች የሚመዝን ከሆነ...ሲሆን እንደኢትዮያ ከሆነ ደግሞ ከ28/ሳምንት በታች ወይንም ከአንድ ኪሎ ግራም በታች የሆነ ውን ጽንስ ነው፡፡ ነገር ግን ትክክለኛው ትርጉም የሚሆነው ከአምስት ወር በታች ወይ ንም ከ500/ግራም በታች የሚለው ይሆናል፡፡ ጽንሱ በዚህ ጊዜ የሚቋረጥ ከሆነ በእንግ ሊዝኛው Early loss ¾ሚባል ሲሆን ይኼውም ጽንስ ከተፈጠረ በሁዋላ እድገቱን መቀ ጠል ሳይ ችል ሲቀር ወይንም በውጫዊው አለም መኖር ከማይችልበት ደረጃ ደርሶ ተቋ ረጠ ማለት ነው፡፡ በአለም የጤና ድርጅት አተረጉዋጎም መሰረት ከ20-22/ ሳምንት የሚ ለው በዚህ እድሜ ያለው ጽንስ ምናልባት ሕይወት እያለው ከማህጸን ቢወጣ እንኩ ዋን እንዲዳብርና ሳንባው እንዲሰራ የሚደረግበት ምቹ ሁኔታ እና የተሟላ የህክምና ተቋም ካለ ጽንሱ እድገቱን ሊቀጥል ይችላል ከሚል ግምት የተወሰደ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግን ከሀያ ስምንት ሳምንት እና ከአንድ ኪሎ ግራም በታች የሆነውን ጽንስ ሕይወቱ እንዲ ቀጥል ለማድረግ የሚያስችል የህክምና ተቋም አደረጃጀት ስለሌለ በዚህ ደረጃ ያሉ ጽን ሶች እንደጠፉ ወይንም እንደተቋረጡ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮያ አለመኖሩን በሚመለከት ምንም እንኩዋን የህክምና ባለሙያዎች ቢኖሩ እና የህክምና ተቋማቱ ቢመሰረቱም አሰ ራራቸውን እንዲሟላ በማድረግ ረገድ የህክምና መሳሪያ በማ ሟላት ረገድ የሚቀር ነገር ስላለ ለጊዜው እንደየአለም ጤና ድርጅት የጊዜ መግለጫ ሳይሆን በአገሪቱ አሰራር አስፈላጊው ይፈጸማል፡፡ ጥ/ በመቋረጥ ላይ ያለውን ጽንስ ማዳን ይቻላልን? መ/ በእርግጥ በመቋረጥ ላይ ያለ ጽንስ ሲባል የሚከፋፈሉበት ደረጃ አለ፡፡ ያለምንም እገዛ በራሳቸው የሚቀጥሉ አሉ፡፡ በድንገተኛ የህክምና እገዛ ተደርጎላቸው የሚቀጥሉ ይኖራሉ፡፡ በምን ሁኔታ ሕይወታቸው ሊቀጥል ይችላል የሚለውን ለመለየት አስቀድሞውኑ ችግሩ የተከሰተው በምን ምክንያት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ጥ/ ጽንሱ የሚቋረጥበት ምክንያት ምንድነው? መ/ እርግዝና በሶስት እኩል ወራት እየተከፈለ ጊዜው የሚቆጠር ሲሆን እስከ 14 ሳምንት ከ14-28 ሳምንት ከ28- 42 ሳምንት በሚል ተከፍሎ ይታያል፡፡ በዚህም ስሌት መሰረት ከ14/ ሳምንት በፊት በራሳቸው ጊዜ የሚቋረጡ ጽንሶች በዛ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ15-20 % የሚሆኑ እናቶች እርጉዝ መሆናቸውን ካወቁ በሁዋላ ጽንሱ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ጽንስ ለምን ይቋረጣል የሚል ጥያቄ ሲነሳ፡- 1/ አብዛኛው ምክንያት የክሮሞዞም ችግር ነው። አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው የክሮሞዞም ሂደቱ 46XY ነው፡፡ ስለዚህ ከወንድ እስፐርም 23/ ከሴት ደግሞ 23/ ሲቀላቀል ወንድ ከሆነ XY ሴት ከሆነች XX ይሆናል፡፡ ነገር ግን በክሮሞዞም ሂደቱ የወንድና የሴት አኩል ተቀላቅሎ መሄድ ሲገባው አንዳንድ ጊዜ የወንዱ ብቻውን 46/ሆኖ ጽንሱ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ እና ሌሎችም ተፈጥሮአዊ ችግሮች የተነሳ የክሮሞዞም ችግር ከተከሰተ ጽንሱ ወጥቶም መኖር ስለማይችል በመጀ መሪያው ሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ይቋረጣል፡፡ ይህም 50% ድርሻ ይይዛል፡፡ 2/ ጽንሱ በራሱ በተፈጥሮአዊ አካሉ ላይ ያልተስተካከለ ነገር ሲኖር የሆርሞናል ሲስተሙ ችግር ሊኖርበት ስለሚችል ሊቋረጥ ይችላል፡፡ 3/ ከሴቶች ማህጸን ጋር በተያያዘ ለምሳሌ የአፈጣጠር ችግር ወይንም እጢ የሚኖር ከሆነ ወይንም ማህጸን ሲፈጠር ሁለት ክፍል ያለውና በሂደት ወደአንድ የሚጠቃለል ሲሆን ይህ አካሄዱ የተዛባ ከሆነ ጽንሱን እንዳያድግ ምክንያት ይሆነዋል፡፡ 4/ በስኩዋር ሕመም ወይንም በታይሮይድ እጢ ምክንያት ጽንስ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ 5/ እንግዴ ልጁ አካባቢ ኢንፌክሽን ሲኖር...ወዘተ በመሳሰሉት ችግሮች ጽንስ ሊቁዋረጥ ይችላል፡፡

ጥ/ አብዛኛውን ጊዜ የጽንስ መቋረጥ ሚገጥማቸው ሴቶች ምን አይነት ናቸው? መ/ ዋናው እድሜ ነው፡፡ እድሜ እየገፋ በመጣ ቁጥር ካለምንም ምክንያት ጽንስ ሊቋረጥ ይችላል። እድሜዋ ከ40/አመት በላይ የሆነች ሴት ጽንሱ ሳይቋረጥ የመውለድ እድሉዋ 30 % ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እድሜ በራሱ ካለምንም ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ጽንስ እንዲቋረጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው የተለያዩ የባህርይ ችግሮች...ለምሳሌ ሲጋራ ማጨስ...አደንዛዥ እጽ መጠቀም ...አልኮል በብዛት መውሰድ በመሳሰሉት ምክንያቶች ሴቶች የጽንስ መቋረጥ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከልክ ያለፈ የአካል ውፍረትና ቅጥነት ለጽንስ መቋረጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የውስጥ ሕመሞች ማለትም እንደስኩዋር እና ደምግፊት የመሳሰሉት ለችግሩ ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ የደም ግፊት ብዙውን ጊዜ ከ20/ሳምንት በፊት ባለው የእርግዝና ወቅት ባይከሰትም ነገር ግን አስቀድሞ ሕመሙ ካለ እና ምናልባትም እርግዝናው ቀኑን እየገፋ ከመጣ እንደአንድ ችግር የሚቆጠር ነው፡፡ ጥ/ ጽንሱ በመቋረጥ ላይ መሆኑን እናትየው በምን ልታውቅ ትችላለች? መ/ ጽንሱ በመቋረጥ ላይ መሆኑን ለመገመት ሰውነትን ማዳመጥ ይጠቅማል፡፡ አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ እያለች ደም ከፈሰሳት የደም መልኩ ንጹህ ቀይ ወይንም ቡና አይነት ሊሆን ይችላል፣ በሆድ እቃ ወይንም ፊኛ አካባቢ ሕመም ከተሰማት፣ የሚፈሰው ደም የረጋ ወይንም እንደስጋ መሰል ነገር ከሆነ እርግዝናው እየቀጠለ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ በእርግጥ የሆድ ሕመም ምልክት ወይንም ደም መፍሰስ የሚባለው ሁልጊዜ የጽንስ መቋረጥ ምልክት ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ የሌሎች ምክንያቶችም ምልክቶች ሊሆን ይችላል ፡፡ ለምሳሌ ከማህጸን ውጭ እርግዝና ሲከሰትም በቱቦ ውስጥ ስለሚቆይ በሚኖረው ምቹ ያልሆነ ስሜት የሆድ ሕመም ወይንም የደም መፍሰስ ሊያጋጥም ይችላል፡፡

ስለዚህም ወደህክምና ተቋም መሄድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ጥ/ ጽንስ ከተቋረጠ በሁዋላ ለቀጣዩ ጊዜ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል? መ/ ጽንስ ሲቋረጥ የህክምና ድጋፍ ከተደረገ በሁዋላ የደም መፍሰስ ስለሚኖር የደም መፍ ሰሱ እስኪቆም ድረስ ቢያንስ እስከሁለት ሳምንት ግንኙነት ማድረግ አያስፈልግም፡፡ በመጸዳዳት ወይንም በመታጠብ ጊዜ ከኢንፌክሽን ለመጠንቀቅ ሲባል እጅን ወደውስጥ አስገብቶ መታጠብ ትክክል አይሆንም፡፡ እንደ አንዳንድ ጥናቶች ጽንስ ከተቋረጥ በሁዋላ በአስረኛው ቀን ሴቶች የዘር ፍሬ እንደላኩ የሚያሳይ ሲሆን ነገር ግን በተቻለ መጠን ቀጣዩን እርግዝና ከ3-6ወር ድረስ ማዘግየት አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የህምና ድጋፍ ለማድረግ ፣የሚሰጥ መድሀኒት ካለ ለመውሰድ እንዲሁም የሰውነት መጠንከር እንዲኖር አስፈላጊውን ጊዜ ማግኘት አስፈላጊ ስለሚሆን ነው ፡፡ ጽንስ ከተቋረጠ በሁዋላ ማህበራዊና ስነልቡናዊ ችግርን ሊያስከትል ይችላል፡፡ አባትም እንደአባት የሐዘን ስሜት ሊኖረው ሲችል በተለይም እናትየው መደበት፣ መጨነቅ፣መበሳጨት ፣ማልቀስ የመሳሰለው ሁሉ ሊኖራት ይችላል፡፡ በዚህ ሰአት ከቤተሰብም ሆነ ከባለሙያ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡

Read 11592 times