Print this page
Saturday, 28 September 2013 10:55

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአህጉራዊ የንግድ ስራ ፈጠራ ይወዳደራሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

1.5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሽልማት ተዘጋጅቷል ዋና ጽ/ቤቱን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው አፍሪካ ሊደርሺፕ አካዳሚ፤ በንግድ ሥራ ፈጠራ ውድድር ለሚሳተፉ አፍሪካውያን ወጣቶች 1.5 ሚ.ብር የሚጠጋ ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም በውድድሩ መሳተፍ እንደሚችሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ፡፡ በውድድሩ መሳተፍ የሚችሉት ከ15 እስከ 22 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች እንደሆኑ የጠቀሰው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት መድሃኔ መለሰ፤ የላቀ የንግድ ስራ ፈጠራ ያላቸው ወጣቶች፣ ከመላው አፍሪካ አገራት ከተውጣጡ የፈጠራ ባለቤት ወጣቶች ጋር እንደሚፎካከሩና የመጨረሻዎቹ 12 ተወዳዳሪዎች 1.5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሽልማት ለሚያስገኘው የአንዚሻ ሽልማት (The Anzisha Prize) እንደሚፋለሙ ተናግሯል፡፡

የመጨረሻዎቹ ምርጥ 12 ተወዳዳሪ ወጣቶች ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ፣ ለሥራቸው አጋዥ የሆኑ የሙያ ሥልጠና እንደሚሰጣቸውና ከአፍሪካ የተሻለ የፈጠራ ሥራ ናቸው ተብለው የሚመረጡ ፈጠራዎች በተለያየ መንገድ እንደሚደገፉም ተገልጿል፡፡ የውድድሩ ዓላማ አፍሪካውያን ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች፣ የአፍሪካንና የዓለም ሕዝቦችን ሕይወት በሚለውጡ ፈጠራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ለማበረታታት መሆኑን የገለፀው ፕሬዚዳንቱ፤ ባለፈው ዓመት ውድድር ከ32 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የንግድ ሥራ ፈጠራ ችሎታ ያላቸው 400 ወጣቶች ተሳትፈው የዩጋንዳ፣ የታንዛንያና የሩዋንዳ ተወዳዳሪዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት 75ሺህ ዶላር (1.5ሚ.ብር ገደማ) መካፈላቸውን አብራርቷል፡፡ የፈጠራ ውድድሩ መመዝገቢያ ጊዜ በመጪው ጥር ወር ቢሆንም ትክክለኛው ቀን ወደፊት እንደሚገለፅና ምዝገባውም በኢንተርኔት አማካይነት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ አፍሪካን ሊደርሺፕ አካዳሚ ላለፉት 12 ዓመታት ተመሳሳይ ውድድሮችን ሲያዘጋጅ እንደቆየ ታውቋል፡፡

Read 7434 times