Saturday, 28 September 2013 11:16

አዲሱ የሰላማዊ ሰልፍ ማስፈፀሚያ እያወዛገበ ነው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

“መመሪያን ማውጣት የፓርላማ ስልጣን ነው”

ከምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ የሰማነው፤ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና ቢያገኝም የመኪና ላይ ቅስቀሳ፣የበራሪ ወረቀት መበተን፣ ፖስተር መለጠፍና ፊርማ ማሰባሰብን በተመለከተ ከልዩ አካል ፍቃድ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ከልዩ አካል ይባል እንጂ ልዩ አካሉ ማን እንደሆነ ግን አልነገሩንም፡፡ ፍቃድ ሳይኖራችሁ የመኪና ቅስቀሳና የመሳሰሉትን ማድረግ ህገወጥ ስለሆነ እርምጃ እንወስዳለን ብለውናል፡፡ ግን በቃል ነው የነገሩን፤ ዶክመንቱን አሳይተውናል፤ ኮፒ አድርገው ሊሰጡን ግን አልቻሉም፡፡ መመሪያ ሲወጣ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ አለባቸው፡፡ መመሪያውን በማተም ፓርቲዎችንም ህብረተሰቡንም ማሳወቅ ይገባቸዋል፡፡ እነሱ የፈለጉት ግን የእኛን እንቅስቃሴና የምናደርገውን ዝግጅት ማነፍነፍ ነው፤ የሚሳተፉ ሰዎችን ማንነትና መፈክሮቻችንን ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ህጎች የአዋጅና የህገመንግስት ጉዳይ ስለሆኑ የአዲስ አበባ መስተዳደር ይቅርና መንግስትም ማውጣት አይችልም፤ ፓርላማ ቀርቦ መፅደቅ አለበት፡፡ አዲሱን መመሪያ በተመለከተ ምርጫ ቦርድም ሄደን “ ስለመመሪያው ታውቃላችሁ?” ብለን ጠይቀናቸው እንደማያውቁ ነግረውናል፡፡ እነሱም ተገርመዋል፤ “እኛም ትክክል እንዳልሆነ ተረድተናል።

ስለዚህ መመሪያ የአዲስ አበባ መስተዳደር ጠይቀን ያገኘነው መልስ፤ “የአዲስ አበባ ካቢኔ ወስኖ ከንቲባው ስላልፈረመበትና ማተሚያ ቤት ስላልገባ ኮፒ ልንሰጣችሁ አንችልም” የሚል ነው፡፡ በጎን ግን ለክፍለ ከተሞችና ለፖሊሶች ተሰጥቷል፡፡ የፅህፈት ቤት ሃላፊው መጀመሪያ ስንሄድ ይህንን ጉዳይ እየተነጋገርበት ነው አሉ ለሁለተኛ ጊዜ ስንሄድ ደግሞ መመሪያው የሚወጣው ለኩባንያዎችና ለንግድ ድርጅቶች እንጂ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም አሉን፡፡ ፖሊስ እንዲህ እያለን ነው ስንላቸው ደግሞ ሃላፊው፤ “ግዴለም እኔ ከከንቲባውም ሆነ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሃላፊዎች ጋር ተነጋግሬያለሁ” ብሎ ነበር፡፡ “ችግር ከተፈጠረ አስታውቁን” አለ፡፡ ችግሩ ግን ይህንን ፖሊሶች፣ ክፍለከተሞችና ደህንነቶች አላወቁም ነበር፤ ስለዚህ ሰሞኑን ቅስቀሳ ስናደርግ ሶስት መኪኖች ታስረዋል፡፡ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ ሰላሳ አባላቶቻችንም ታስረው ነው የተለቀቁት፡፡ ከ9 ሰዓት እስከ 11ሰዓት ታስረው ነበር፡፡ ይህ የህግ መፃረር ብቻ ሳይሆን ከህዝቡ ጋር እንዳንገናኝና ሃሳባችንን እንዳናሳውቅ እየተደረግን ነው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ይቁም እንደማለት ነው፡፡ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ለመስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም ለማድረግ አሳውቀን ነበር፤ ነገር ግን እኛ ሰልፉን ለማድረግ ያሰብነው በመስቀል አደባባይ ነበር፡፡ መስተዳደሩ ቅድሚያ የምንሰጠው ለልማት ነው በማለት መስቀል አደባባይን እንድንቀይርና ሌላ አማራጭ ቦታዎችን እንድንነግራቸው ጠየቁን፡፡ እኛም ኢትዮ - ኩባ ፓርክ፣አራት ኪሎ፣ስድስት ኪሎና ቴዎድሮስ አደባባይን እንደ አማራጭ አቀረብን፡፡ እነሱ ግን ይህንን አንፈቅድም በማለት በራሳቸው ፈቃድ ጃንሜዳ ብለው ወሰኑ፡፡ ይሄም ብቻ ሳይሆን ከቢሮአችሁ ተነሱና በዚህ መንገድ አድርጋችሁ ብለው ሰዓታችንን እና መነሻ ቦታችንን ወስነው ነገሩን፡፡ ጃንሜዳ አንደኛ ለትራንስፖርት አይመችም፤ ሜዳው ረግረግ ነው፡፡ ቦታው የንግድና የመኖሪያ ቤቶች በስፋት የሚገኙበት ነው፡፡ አዋጅ አንቀፅ 7 ንዑስ አንቀፅ 2፤ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከማህበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከት/ቤቶች፣ ከሆስፒታሎችና ከመኖሪያ አካባቢ 100 ሜትር መራቅ አለበት ይላል፡፡ ከወታደራዊ ካምፕ ደግሞ 500 ሜትር መራቅ እንዳለበት ህጉ ያዛል፡፡ ለእኛ የወሰኑልን ቦታ ግን በአጥር የሚገናኙ ሆስፒታል እና የጦር ካምፕ ያሉበት ነው፡፡ ያቀረብናቸውን አማራጮች ከልክለውን ይሄንን ቦታ ተጠቀሙ ብለውናል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር “አዲሱ መመሪያ በመውጣቱ ምንም አይመጣም” አዲስ መመሪያ መውጣቱን ሰምቻለሁ ግን ከቁም ነገር አልቆጥረውም፡፡ ምክንያቱም የህገመንግስቱ አንቀፅ 9/1፤ “ይህ ህገመንግስት የአገሪቷ የበላይ ነው፤ ከዚህ ውጪ የሆነ ልማዳዊ አሰራር አዋጅም ደንብም የባለስልጣን መመሪያም ተቀባይነት የለውም” ነው የሚለው፡፡ ይሄንን ቢያደርጉም ባያደርጉም ተቀባይነት ስለሌለው እኔ እንደ ቁም ነገር አልቆጥረውም፡፡ እየሰራ ያለው መመሪያው ሳይሆን ጉልበት ነው፡፡ እኛ ለእሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ስንዘጋጅ ቅዳሜ ይሄንን ቢሮ ገብተው ዘረፉ፡፡ አራት መቶ የምንሆን ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች ነበርን፡፡ ከየአቅጣጫው የሚመጡት ሰልፈኞች ከእኛ ጋር እንዳይገናኙ፡፡ በመኪናና በፖሊስ መንገዱን ዘጉት፡፡ እኛም ወደ መስቀል አደባባይ እንዳንሄድ አገዱን፡፡ እናም እዛው ጋ ትንሽ ንግግር አድርገን ሰላማዊ ሰልፉ ሳይካሄድ ተመለስን፡፡ የዚህ አይነት አገዛዝ ባህሪው ይሄ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ስለዚህ የእኛ ሰላማዊ ትግል ይቀጥላል፤ በበለጠ መልኩም ይጠናከራል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ስንዘጋጅ በህግ ያደረጉትና የከለከሉን ነገር የለም፤ በጉልበት ግን ቢሮአችን ገብተው የሚፈልጉትን ወስደውብናል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር “አዲስ የወጣ መመሪያ የለም” ያወጣነው መመሪያ የለም፤ ክልሎች አዋጆችን ለማስፈፀም የራሳቸውን ስነስርዓት ማስፈፀሚያ ያወጣሉ፡፡ እኛም በ1983 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባን ለማካሄድ የተደነገገውን አዋጅ መተግበር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ነው ያወጣነው፡፡ አዋጁ እንዴት ይተገበራል ለሚለው የሚያገለግል እንጂ ሌላ የወጣ ነገር የለም። ሰነዱ ገና ህትመት ላይ ያለ ነገር ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደማንኛውም ጊዜ ሰላማዊ ሰልፉን በየት አካባቢና እንዴት እንደሚያደርጉ ያሳውቃሉ። ይሄም ቦታው ላይ ችግር እንዳይፈጠር፣ በነዋሪዎችና በትራፊክ እንቅስቃሴዎች ላይ መጨናነቅ እንዳይከሰትና ሰልፈኛው አስፈላጊው ጥበቃ ተደርጎለት በሰላማዊ ሁኔታ ወደመጣበት እንዲመለስ ለማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህን ጫናዎች ለማቅለል ነው ማሳወቅ የሚያስፈልገው። ከዚህ ቀደም ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድም ሁለት ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል። መጠቀም ያለመጠቀም የፓርቲው ጉዳይ ነው፡፡ ከዛ ውጪ እንደ ከተማ መስተዳደር፣ እንደ መንግስትም ሊደረግላቸው የሚገባውን ነገር ሁሉ እያደረግን ነው፡፡ ነገር ግን የደጋፊ ቁጥር ሲያንስና ደጋፊ ሲጠፋ፣ የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ጃንሜዳን የሚያክል ቦታ ተፈቅዶላቸው ሳይጠቀሙበት “መንግስት እገዛ አላደረገልንም፤ ከለከለን” የሚሉም አሉ፡፡ በጃንሜዳ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ፤ የጦር ካምፕ አለ ብለው እንደሰበብ አቅርበዋል፡፡ እነሱም በአማራጭነት ባቀረቡዋቸው ቦታዎች በሙሉ ትምህርት ቤትና የሃይማኖት ተቋማት አሉ፡፡ ጃንሜዳ ምናልባት ትንሽ ቅርበት ያለው ለጦር ካምፕ ነው፤ እሱም ቢሆን 500 ሜትር ርቀት አለው፡፡ ስለዚህ እነሱ ከመረጡት ቦታ የተሻለ ነው፡፡ አቶ አሰግድ ጌታቸው የአዲስ አበባ መስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት እና የካቢኔ ሃላፊ “ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ መፍቀድና መከልከል አይችልም” ሰላማዊ ሰልፍና ፖሊስ የሚገናኙት ከከተማችን ሰላምና ፀጥታ ጥበቃ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ዜጎችም ሆነ ማንኛውም ሰው ሰላሙንና ፀጥታውን ማስከበር አለበት፡፡ ይሄንን እንደተልዕኮ በዋነኛነት የተሸከመው የፖሊስ ሃይል ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ህጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ፣ በሰልፎኞች ላይ አደጋ እንዳይደርስና በመልካም ግንኙነት እንዲጠናቀቅ ፖሊስ የፀጥታ ሃይል ያስከብራል፡፡ አስቀድሞ በተቀመጠለት ቦታ ፣ጊዜና አቅጣጫ መከናወኑን ይከታተላል፡፡ ፖሊስ አዲስ ያወጣው መመሪያ የለም፡፡ መስተዳድሩ አዲስ ያወጣው የሰላማዊ ሰልፍ አፈፃፀም ስነስርዓት አለ፤ እኛም ደርሶናል፡፡ ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ መፍቀድና መከልከል አይችልም፡፡ ይሄ ጥያቄ የሚቀርብለት ለአስተዳደሩ ነው፡፡ አስተዳደሩ ሲፈቅድ ለፖሊስና ለሚመለከተው አካላት ያሳውቃል፡፡ ፖሊስ ፀጥታውን ያስከብራል፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች መብት ሲጠበቅ የሌላውም መጠበቅ አለበት፡፡ እኛ ፈቃጁ ክፍል ፈቅጃለው ካለን ጊዜ ጀምሮ ዝግጁ ሆነን ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር እንቀሳቀሳለን፡፡ የከተማችን መንገዶች በልማት ተይዘዋል። ዋናው የከተማው መንገድ ግንባታ ላይ ነው፤ በሙሉ አቅም እየሰራ አይደለም፤ ስለዚህ መጨናነቁ ይጨምራል። ሰላማዊ ሰልፍ ሲጨመርበት ደግሞ ይብሳል፡፡ የልማት ተግባር እንዳይስተጓጎል እንዴት ነው መሆን ያለበት የሚለውን አስተዳደሩ ነው የሚጨርሰው። እኛ ግን ፀጥታን እናስከብራለን፡፡ በዚህ ከተማ ማናቸውም ጉዳዮች ሲካሄዱ ፖሊስ ሰላማቸውን ይጠብቃል፡፡ ይሄ ማለት ጉዳዩ ወይም ባለቤቱ ፖሊስ ነው ማለት አይደለም፡፡ የአፍሪካ ህብረት ሲካሄድ ፖሊስ ፀጥታ ያስከብራል እንጂ ባለቤት ወይም ፈቃጅ አይደለም፡፡ ከሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተያያዘም ከተለያዩ አቅጣጫዎች መታየት ስላለባቸው ፍቃድ መስጠት የአስተዳደሩ ጉዳይ ነው፡፡ የፀጥታው ጉዳይ ነው የእኛ፡፡ በአስተዳደር እና በፖሊስ በኩል እስካሁን ችግር የለም፡፡ እስካሁን አስተዳደሩ የፈቀደውን ፖሊስ ከልክሎ አያውቅም፤ ባሳለፍነው ሳምንት ሰማያዊ ፓርቲ ጃንሜዳ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ተነገረን፡፡ እኛ በቂ ሃይል አዘጋጅተን ስንጠብቅ ጃንሜዳ ግን መምጣት አልቻሉም፤ እንደውም ባልተፈቀደላቸውና አሁን በልማት ላይ ወደሚገኘው መስቀል አደባባይ ባነራቸውን ይዘው ሄዱ፤ ይሄ የጠያቂው ስህተት እንጂ የፖሊስ ችግር አልነበረም። ፖሊስ እንደውም ከዚህም ወጣ ብሎ በተቻለ መጠን ሃላፊዎችን በማግኘት የተፈቀደላችሁ ደብዳቤ ደርሶናል፤ እናንተን የመጠበቅ ሃላፊነት አለብን፤ ይሄንን ደግሞ ማድረግ የምንችለው ተራርቀን ሳይሆን ተቀራርበን ነው፤ የሚያስተባብሩ አካላት ስጡን፤ እኛም ሰው እንስጣችሁ፤ እየተመካከርን የሚያስቸግሩ ነገሮችን እያስተካከልን በጋራ እንስራ ብለን ነበር፡፡ ይህንን እንደ ተራ ነገር ነው ያዩት። አንዳንዴ እንደ ዜጋ ማሰብ ጥሩ ነው፤ ልማት ይካሄዳል ሲባል “ለእኔ ሲባል ካልቆመ ወይም ካልተደናቀፈ” እንዴት ይባላል? ሰልፉ ሊካሄድ የነበረው ለአገር እድገት ይጠቅማል ተብሎ አይደለም እንዴ? በርካታዎቹ ሰልፎች በሰላም የሚጠናቀቁ ናቸው። ፖሊስ እነዚህን ያመሰግናል ከተወሰነ ወራት በፊት ሰማያዊ ፓርቲ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂድ፣ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን (ብዙ ጊዜ አንዋር መስጊድ ላይ ሲስተጋቡ የነበሩ) አንፀባርቋል፡፡ ያ መሆን ነበረበት ወይ? እኛ በመታገሳችን በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለጠናቀቅ ችሏል፡፡ አሁንም ቢሆን የተፈቀደላቸው ቦታ ጃንሜዳ ነውና እሱን ተጠቀሙ ብንልም ይሄንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ አንዋር መስጊድ እኮ ፖሊስ ጉዳት እየደረሰበት እንኳን ለአብዛኛው ህዝብ ስንል “ቻለው” ብለነው ብዙ ጊዜያቶችን አልፏል። ተቃዋሚዎች ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ችግራቸውን ይፍቱ፤ ፖሊስን አይመለከተውም፡፡ ፖሊስ የሚቆመው ዜጎች በሰላምና በነፃነት በአገራቸው ላይ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ንቃተ ህሊናውን የሚያሳድጉ ስልጠናዎች ይሰጣሉ። በፖሊስ ላይ የሚታዩ ችግሮች ዝም ብለው የሚመጡ አይደሉም፡፡ ከልምድና ከትምህርት ማነስ የሚመጡ ናቸው፡፡ ፖሊስ የህብረተሰቡ አካል እንጂ ልዩ ፍጡር አይደለም፡፡ ከሌላው ፈጠን ብሎ ቀድሞ መገኘት አለበት። ፖሊስ የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ ስህተት ሲሰራ ህዝቡ እያረመው ነው እዚህ የደረሰው፡፡ የሃይል እርምጃ እንዲወስድ ታዝዞ እንኳን፣ እርምጃውን ሳይወስድ ችግሩ የሚፈታበት ሁኔታ አለ፡፡ ዋና ኮሚሽነር ይደጐ ስዩም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር

Read 3351 times