Print this page
Saturday, 28 September 2013 13:20

ስልጣን - የነብር ጅራት!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

                       በየአራት አመቱ አንዴ የሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ቀናቶች ሲቃረቡ በሪፐብሊካንና በዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩዎች መካከል አንዱ ያንዱን ዋጋ ለማሳጣት የግል ምስጢር መውጣቱ፣ እርስ በርስ መዘላለፉ ወዘተ በእጅጉ ያይላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመታዘብ የቻለ ማንም ቢሆን ስነስርአትና የሰለጠነ ግብረገብ የጐደለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚካሄድበት እንደ አሜሪካ ያለ ሀገር ጨርሶ አይቶ አላውቅም ቢል ቂል ወይም ገሪባ ብሎ የሚያላግጥበት ብዙ ሰው አይኖር ይሆናል፡፡ ይህንን አስተሳሰቡን ለአንድ የአውስትራሊያ ዜጋ ቢያካፍለው ግን ኢትዮጵያውያን “አባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል” እንደሚሉት “የአውስትራሊያን ብሔራዊ ምርጫ ሳታይ እንዲህ የመሰለውን አቋም አትያዝ” ብሎ እንደሚመክረው ምንም አያጠራጥርም፡፡ በቅርቡ በሌበር ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድና በወግ አጥባቂ ፓርቲ ተቀናቃኛቸው ቶኒ አቦት መካከል በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ የታየውን ቦክስ ቀረሽ የእርስ በርስ መሰዳደብ አይተውና ሰምተው አጀብ ያላሉ ቢኖሩ ራሳቸው አውስትራሊያውን ብቻ ነበሩ፡፡

ለእነሱ እንዲህ ያለው የምርጫ ወቅት የተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ከገደብ ያለፈ የእርስ በርስ ስድብና ዘለፋ ቢሊ ሂውዝ የአውስትራሊያ ሰባተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ከ1920ዎቹ ጀምሮ ሲያዩትና ሲሰሙት የነበረ የአንድ ሰሞን ተራ ግርግር ነው፡፡ በዚህ ጠቅላላ ምርጫ የወግ አጥባቂው ፓርቲ እጩ ቶኒ አቦት የተዋጣላቸው ፖለቲከኛ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን አለብላቢት ምላስ፣ እሳት የላሱ ተሳዳቢ እንደሆኑም በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ላለፉት ስድስት አመታት በስልጣን ላይ የቆየው ሌበር ፓርቲ የሰራቸውን ስህተቶች አንድ ባንድ ልቅም አድርገው በማውጣት፣ ፓርቲውንና መሪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድን ተሸጠውም ሆነ ተለውጠው አሊያም ለምነው እንኳ እንዳይበሉ አድርገው አበሻቅጠው በመስደብና በመዝለፍ የመራጩን ህዝብ የምርጫ ድምጽ ለእርሳቸው እንዲሆን ማድረግ ችለዋል፡፡

በዚህ የተነሳም ሌበር ፓርቲንና ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድን በዝረራ ለማሸነፍ የመሪነት ስልጣኑን ለመጨበጥ በቅተዋል፡፡ ምርጫውን ከ ሀ እስከ ፐ ነገሬ ብለው የተከታተሉ ባለሙያዎች፤ በዚህ ምርጫ ተሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ ጥይት ጨርሰው እንደነበር በጥሞና ያስረዳሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የባለሙያዎቹ አስተያየት አሳማኝነት አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ፤ መላ ሀይላቸውንና የምርጫ ቅስቀሳ ችሎታቸውን አሟጠው የተቀመጡት ለዚህኛው ምርጫ ሳይሆን ባለፈው ሰኔ ላይ ለሌበር ፓርቲው መሪነት በወቅቱ የሌበር ፓርቲው መሪና የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ወይዘሮ ጁሊያ ጂላርድ ጋር ላደረጉት ምርጫ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሊያ ጂላርድን አይሰየሙ ስያሜ በመስጠት፣ አያወጡ ስም በማውጣት አሸንፈው የሌበር ፓርቲውን መሪነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን መልሰው ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡ የዚህ ምርጫ ድል ለኬቪን ሩድ ቀዝቅዞ የቀረበ ጣፋጭ በቀል ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቆናጠጡትን የሌበር ፓርቲ መሪነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን በ2010 ዓ.ም በተደረገው የፓርቲ መሪነት ምርጫ አሸንፈው የነጠቋቸው እኒሁ ወይዘሮ ጂሊያን ጂላርድ ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ፤ ጠቅላላው ምርጫ ደርሶ የወግ አጥባቂ ፓርቲውን መሪ ቶኒ አቦትን የተጋፈጧቸው የፓርቲ መሪነት ድላቸው የፈጠረባቸውን ደስታ ገና በወጉ እንኳ አጣጥመው ሳይጨርሱና ለጠቅላላ ምርጫው በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ነበር፡፡ ከተገመተውና ራሳቸውም ካሰቡት ሳይሆን ከተመኙትም በላይ የሆነ ታላቅ ድል የተቀዳጁት ቶኒ አቦት፤ በምርጫው በለስ እንደቀናቸው እንዳወቁ “እነማን ናቸው እኔን የሚንቁ፣ ደረስኩባቸው ሳይታጠቁ!” የሚለውን ዘፈን በመዝፈን፣ በተሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ ላይ በአደባባይ አላግጠውባቸዋል፡፡ ኬቪን ሩድም ምርጫው ከተጠናቀቀና አይሆኑ አሸናነፍ መሸነፋቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ ከሌበር ፓርቲ መሪነታቸው በፈቃዳቸው አይነት ምርጫ ስወዳደር ብታዩኝ ሰው ብላችሁ አትጥሩኝ በማለት ራሳቸውን በራሳቸው የፖለቲካ ጡረታ አውጥተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ድል ባለ ድግስ ስልጣቸውን ለአዲሱ ተመራጭ ቶኒ አቦት ሲያስረክቡም ያሳዩት ስሜት በምርጫ ተሸንፎ ስልጣን የሚለቅ መሪ አይነት ሳይሆን ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለተተኪው የሚያስረክብ መሪ አይነት ነበር፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ባሁኑ ተሸናፊ ኬቪን ሩድ የሌበር ፓርቲ መሪነታቸውን በምርጫ ተሸንፈው በመነጠቃቸው የተነሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጠናቸውንም ላጡት ጁሊያ ጂላርድ ግን እስከአሁንም ድረስ ነገሮች ሁሉ በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡

ሳይወዱ በግድ በምርጫ ያጡት ስልጣን እጅግ ከፍተኛ ለሆነ የስነልቦና ቀውስ ዳርጓቸዋል። በአውስትራሊያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የሌበር ፓርቲ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ በስልጣን ላይ ለቆዩት ጁሊያ ጂላርድ ስልጣን ማለት የነብር ጅራት ማለት ነው፡፡ አስቀድመው የማይዙት፣ አንዴ ከያዙት ግን ጨርሰው የማይለቁት፡፡ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ አቦት፤ ቃለ መሀላ ፈጽመው ስልጣን ሲረከቡ የነበረውን ስነስርአት ጁሊያ ጂላርድ በቴሌቪዥን የተከታተሉት ብቻቸውን ሀይለኛ የምሬት ለቅሶአቸውን እያነቡ ነበር፡፡ እናም ይህንን ስሜታቸውን ዘ ጋርድያን ለተሰኘው ጋዜጣ የገለፁት “ስልጣንህን ማጣት ማለት ልክ ሳታስበው አፍንጫህን በቦክስ እንደ መመታት ማለት ነው” በማለት ነው፡፡ ይህንን የተናገሩት የቀድሞዋ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሊያን ጅላርድ፤ አፍሪካዊ ፖለቲከኛ ሆነው ቢሆን ኖሮ ማንም ይህን ያህል ነገሬ ባላላቸው ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ መጠየቅ የሚገባን ጉዳይ እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ለመሆኑ እኒህን ሴትዮ ስልጣንን የነብር ጅራት ነው እንዲሉ ያበቃቸው ምን ነገር ቢያገኛቸው ነው? ሳምንት በቀረው ጉዳይ እንገናኛለን፡፡

Read 3422 times