Saturday, 28 September 2013 13:35

በተጓዝክ ቁጥር ትሰፋለህ…

Written by  በዳዊት ንጉሡ ረታ dawitnegussu@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)
  • አባቶች የአክሱምን ሃውልት አቁመዋል፤ ልጆች ከሃውልቱ ስር የካርታ ቁማር ይጫወታሉ
  • አባቶች በቀረፁት ድንጋይ ዓለምን ያስደንቃሉ፤ ልጆች የጠጠር መንገድ መደልደል አቅቶአቸው መኪና አይገባም ይላሉ
  • ዝም ያለቺው አድዋ… ደማቋ ሽሬ… የተቆፋፈረችው አዲግራት…

        የዛላምበሳ - አሲምባ - አሊቴና ጉዞዬን ለማካፈል ከጥቂት ሳምንት በፊት በዚሁ ጋዜጣ የጀመርኩትን ወግ አልጨረስኩም፤ ወጌን ከዳር ለማድረስ፣ ለአፍታ ወደ ጎንደር የፋሲል ጉብኝት ጎራ ብዬ ወደ አክሱም እዘልቃለሁ።
የፋሲል ቤተመንግስትን ስጎበኝ የመጀመሪያዬ አይደለም። ነገር ግን ካሁን በፊት ያላስተዋልኩትን አስደናቂ ነገር በአስጎብኛችን አማካኝነት ተመለከትኩ። ከቤተመንግስቶቹ ድንቅ የሚያደርጋቸውና ድንጋዮቹ እርስ በርስ ተነባብረው እንዲህ እስከዛሬ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቆዩ የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ለማግኘት የበቁበትን ድንጋይ ማጣበቂያ ያደረጉት ኖራን ነበር። ታዲያ ኖራው ለረጅም ዓመታት በማጣበቂያነቱ ፀንቶ እንደሚቆይ ለማረጋገጥ በዚያው በፋሲል ቅጥር ጊቢ ውስጥ አንድ መለስተኛ ክፍል ያለው ቤት በድንጋይ ተሰርቶ ለዓመታት ከታየ በኋላ አለመፍረሱ ተረጋግጦና ኖራም ለዘመናት ጠንካራ ማጣበቂያ መሆኑ ታምኖበት ነው ታላላቆቹ ቤተመንግስቶች ተራ-በተራ የተገነቡት። አስደናቂ ነው። በዚህ ዘመን እንኳን የአንድን ነገር ዘላቂነትና አዋጪነት ለማወቅ ሙከራ ሳይደረግ፣ ስንቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ በላያችን ላይ ተሞከረብን? ከውሃ ማቆር ስትራቴጂ እስከ ትምህርት ፖሊሲ፤ ከንግድ ምዝገባ ህግ እስከ ብዙ ነው ዝርዝሩ፡፡
ያልተደሰትኩባቸው የአክሱም ወጣቶች
ለመጎብኘት እጅግ የጓጓንለት አክሱም ከተማ ደረስን። በእርግጥም ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ድንጋዮችን እንዲህ ባይነት ባይነታቸው ደርድሮና በላያቸው ላይ ደግሞ የቅርፅ ጥበብን በማኖር የዓለምን ዓይን ለመሳብ የበቃንበትን ተዓምራዊ ጥበብ ለሰሩ አባቶቻችንና እናቶቻችን የሚኖረን ክብር እጅግ ከፍ ያለ የሚሆነው ድንገት ከሃውልቶቹ ጋር ዓይን ለዓይን ስንገጣጠም ነው። ያን ጊዜ ድንገት ዞር ስንል ውብ የአርክቴክቸር ጥበብ ያረፈባትን የአክስም ፂዮን ቤተክርስቲያን ከጎናችን እንመለከትና እዚህ ቦታ ስለመገኘታችን ምስጋናችንን ዝቅ በማለት እናቀርባለን። ነቢይ ባገሩ ይሉ ዘንድ እኛ እዚያ በመገኘታችን ደስታ የሚያደርገንን አሳጥቶን ስንቅበዘበዝ፣ የአክሱም ወጣቶች ግን በሃውልቶቹና በቤተክርስቲያንዋ መሃል በሚገኝ ሜዳ ላይ በካርታ ቁማር ይጫወታሉ። የእኛን መምጣት ነገሬም ያሉት አይመስልም። ብዙ ከመኖር ተላምደውት፣ ሃውልቱም ያው ድንጋይ ሆኖባቸዋል፤ ጎብኚም ሲጨርስ ወደ መጣበት ይመለሳል።
ከካርታ ተጫዋቾቹ መሃል አንዱ የደደቢት እግር ካስ ቡድንን ማሊያ የለበሰ ወጣት፣ ወደ እኛ መጣና የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው የማስጎብኘቱን ስራ እያከናወኑ እንደሆነና ለእኛ ጉብኝት የተመደበው ሰው እርሱ እንደሆነ ነገረን። ለጉብኝታችን 250 ብር እንደሚያስከፍለንና ህጋዊ ደረሰኝ እንደሚያቀርብልን ገለፀ። ጉብኝቱ ተጀመረ። የአክሱም ሃውልቶችንና የታሪካዊትዋ አክሱም ፂዮን ቤተክርስቲያንን ካስጎበኘን በኋላ በግምት ከ5 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ የሚገኘውን የአፄ ካሌብን ቤተመንግስት ሊያስጎበኘን በመኪናችን ጉዞ ጀመርን። ከመድረሳችን በፊት ግን ቆምን፤ መንገዱ አልተስተካከለም። መኪና አያስኬድም። ከመኪና ውረዱ ተብለን በእግር ጉዞ ጀመርን። ግራና ቀኝ የድንጋይ ክምር እያለ፣ እነዚህ ወጣቶች ይችን መንገድ መስራት አቅቶአቸው ነው? አባቶቻቸው ያንን የአለም ድንቅ ቅርስ ሰርተው ሲያበቁ፣ እነዚህ ልጆች በግማሽ ቀን ሥራ የካሌብን መሄጃ መንገድ ማስተካከል ተስኖአቸው በካርታ ጨዋታ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ።
አስደናቂው የአክሱም ሃውልቶችና አካባቢውን ጎብኝተን ለምሳ ወደ ከተማ ሄድን። ምሳ ተበልቶ ካለቀ በኋላ አስጎብኛችን የጎበኘንበትን 250 ብር እንድንከፍል ጠየቀን። የቡድኑ ገንዘብ ያዥ እኔው ነበርኩና ደረሰኝ ስጠኝና ብርህን ልስጥህ ስለው ተቅለሰለሰ። ለካንስ ያችኑ የማህበር ገቢ ወደ ኪሱ ለማድረግ ማሰቡ ነበር። ደግሞ ሙስና በየት በኩል ተከትላን መጣች? የሆነው ሆኖ በአክሱምና አካባቢዋ በወላጆቻችን ጥንታዊ ስልጣኔ በእጅጉ ተደንቀን፣ በእኛው ዘመናዊ ኋላቀርነት ደግሞ ተሸማቀን ጉዟችንን ወደ አድዋ አደረግን።
ዝም ያለቺዋ አድዋ
እምዬ ምኒልክ ዛሬም ያንቱ ፈረስ
የቸኮለ ይመስላል አድዋ ለመድረስ።
ሐውልትዎን ባዩት ምኒልክ ቢነሱ
ልጓሙ አልችል ብሎት ሊሄድ ሲል ፈረሱ!
(ገጣሚ አርቲስት ንጉሡ ረታ፤ ከአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ 1987 ዓ.ም በሞት የተለየን - ነፍስ ይማር ብያለሁ)
የአፍሪካ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ታሪክ የሚወሳባት አድዋ!... የምኒልክና የጣይቱ አድዋ!... ዛሬ ዝም ብላለች። ውብ የተራራ ሰንሰለቶችዋ በውስጣቸው አቅፈውና ቀብረው የያዙትን የጀግንነት ታሪክ በወጉ የሚያከብርላቸው አጥተው ያኮረፉ ይመስል ተኮፍሰው ይታያሉ። አድዋ ስምና ዝናዋ እንደ ተራሮችዋ ግዝፈት ከዳር ዳር ያስተጋባሉ። ከተማዋ ግን ዝም ጭጭ ያለች ሆነችብኝ። ቡና የሚጠጣበት ስፍራ ፍለጋ ከተማዋን አካልለናል። ይህቺ ከተማ የሟች ጠቅላይ ሚኒስትራችንና የጉምቱ ጉምቱ ባለስልጣኖቻችን የትውልድ ስፍራ አይደለችም እንዴ? በሚልም ሃሳብ ተነሳ። “እና ምን ይጠበስ!” ነው የአድዋ መልስ። ወይ ነዶ ይህ ታሪካዊ ቦታ ደቡብ አፍሪካ ወይንም ግብፅ ወይንም ደግሞ ሊቢያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ፣ አድዋን ለመርገጥ ዛሬ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር በተጠየቀ ነበር። ያም ሆኖ አድዋ አንቀላፍታለች።
ከዚህ ቀደም አንድ ግለሰብ በአድዋ ተራሮች ላይ ከተማዋን ለማስተዋወቅ አንድ የሆነ የጀመረው ፕሮጀክት እንደነበረ ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሰምቼ ነበር። እንዲያውም በትልቁ በብረት የተሰራ አድዋ የሚል ፅሁፍ ያለበት ማስታወቂያም ሳልመለከት አልቀረሁም። ዛሬ ግን ያ…ሁሉ በአድዋ የለም። እንግዲህ የማስታወቂያ ባለሙያው መሃመድ ካሳ፤ ባለፈው ዓመት የአድዋን በዓል በብሄራዊ ቴአትር ከህዝብ ጋር ሲያከብር ቃል በገባው መሰረት፣ በ2006 ዓ.ም የአድዋ በዓልን በዚያው በአድዋ ከተማ ውስጥ በማክበር ከተማዋን ከዝምታ እንደሚገላግላት፤ ከአንቀላፋችበትም እንደሚቀሰቅሳት ተስፋ አደርጋለሁ።
ደማቋ ሽሬ
ሽሬ ዕምደስላሴ ለአንድ ቀንና ሌሊት ጥሩ ጊዜ ካሳለፍንባቸውና እጅግ ከማረኩኝ ከተሞች ውስጥ አንዷ ሆናለች። በትግራይ ክልልም ትልቅ ከሚባሉት ከተሞች መሃል በስም እንደምትጠቀስም ሰምቻለሁ። ምሽት ላይ በሽሬ አንድ የምሽት ቤት በትግርኛና በኤርትራ እንደዚሁም ቆየት ባሉ የአማርኛ ሙዚቃዎች የጨፈርነው ጭፈራ እስካሁን በዓይኔ ላይ አለ። ሰሞኑን በቅርቡ በወጣ “ጊዜያችን” የተሰኘ መፅሄት ውስጥ በዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የቀረበ አንድ ፅሁፍ አንብቤያለሁ። ርዕሱ “በኤርትራ ሙዚቃ ስሜቱ የማይነካ ኢትዮጵያዊ፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ስሜቱ የማይረካ ኤርትራዊ ይገኛል?” ይላል። ማህመድ ሰልማን “ፒያሳ ማህሙድ ጋር ጠብቂኝ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሃፍ ላይም አንዲት በዚያው አካባቢ የምትገኝ ከተማን ሲገልፃት፣ በኤርትራ ሙዚቃ የምትደንስ ከተማ ብሏል። ፀጉራቸውን ፍሪዝ ያደረጉ፤ ቁመታቸው ዘለግ ያለ፤ አብዛኞቹ ጉርድ ቦዲ ቲሸርት ያደረጉ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች በፍቅር በያንዳንዱ ሙዚቃ ሳይታክቱ ሲጨፍሩ ተመለከትኩ።
ላፍታ መንፈሴ ወደ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሄደና አንድ ነገር አስታወስኩ። ይህቺ የትግራይ ምድር እኮ ዛሬ እንዲህ በሙዚቃ ደምቃ የምናያት ለዘመናት ወጣቶችዋን በጦርነት ያጣች፤ ርሃብ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ያጠቃት ክልል ናት። ህዝቦችዋ ስደትን ጠንቅቀው ያውቁታል። እናም ሁሉንም የሚረሱትና ተንፈስ የሚሉት በሙዚቃ ብቻ ነው። ገና ሙዚቃው ዝ..ዝ..ም ብሎ ሲጀምር ሁሉም ፈገግ ብለው በመነሳት ክባቸውን ሰርተው
አንቺ የትግራይ ምድር
የከበሮሽ ድምፅ ከሩቅ ይሰማ… የጦር መሳሪያን ድምፅ አሸንፎ
የስክስታሽ ውበት ይታይ…ደም ሳይደበቀው አኩርፎ
ልጆችሽ ልክ እንደዛሬው …ለጭፈራ ክብ እየሰሩ
የሰላም አየር በመማግ …ሳይሳቀቁ ይኑሩ!
ሁልጊዜም ሳቅ ይሁን ሁሌም ይሁን ፍቅር
እንዲህ ነው የሚያምርብሽ አንቺ የትግራይ ምድር!
የአዲግራት ጋንታ
አዲግራትም በክልሉ ስማቸው ከሚጠቀስ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ አንዷ ናት። እኛ አዲግራትን ስናቋርጥ ከተማዋ ልክ እንደ አዲስ አበባ እዚህና እዚያ ተቆፋፍራ ልማቱን እያሳለጠችው አገኘናት። ድንገት በአንድ መንደር ውስጥ ውስጥ ከ25 በላይ የሆኑ ህፃናት በአንዲት አሮጌ ኳስ ባንድ ላይ ሆነው ሲጫወቱ ስለተመለከትናቸው ለእነዚህ ልጆች ቢያንስ የአንዲት አዲስ ኳስ ስጦታ ስለምን ሳናበረክትላቸው እናልፋለን በማለት በቀና ሃሳብ ተነሳስተን ወደ ልጆቹ አመራን። የቋንቋ ችግር አለብንና አስተርጓሚ ተጠርቶ ስለስጦታው ሃሳብ ተነገራቸው። በዚህ ጊዜ እንዲያ በፍቅር ሲጫወቱ የነበሩ ልጆች ምክኒያቱ ባልገባን ሁኔታ እርስ በርስ ዱላ ቀር ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። አስተርጓሚያችንን ምን እንደተፈጠረ ጠየቅነው። ለካንስ እነዚህ ልጆች ምንም እንኳን በዚያች አንድ ኳስ በህብረት ቢጫወቱም የተለያየ ሰፈር ነዋሪዎች ናቸው። ስለዚህ ስጦታው እዚህ ሰፈር ከተገዛ ባለቤትነቱ የዚህ ሰፈር ህፃናት ብቻ እንደሚሆን ተተረጎመልን። እና ምን ይሻላል ብለን ብንጠይቅ የ 4 ጋንታ ልጆች ስለሆንን በየጋንታችን እንሰለፍና ስጦታውን አከፋፍሉን አሉን። ወቸው ጉድ! እጅግ ተገረምንና እስቲ በየጋንታችሁ ተሰለፉ አልናቸው።
እውነትም አራት ከፍ ከፍ ያሉ ህፃናት ከመካከል ወጥተው የየራሳቸውን ጋንታ በ4 በመክፈል አሰለፉ። ሁኔታውን ስናይ አስገረሙንና ስጦታውን ጨመር አድርገን ልናከፋፍላቸው ስንል ሌላ ጉርምርምታ ተነሳብን። ደግሞ ምን ተፈጠረ? ብለን ወደ አስተርጓሚያችን አፈጠጥን። እንደ ህፃናቱ ገለፃ ብዙ የጋንታ አባል ያለው በዛ ያለውን ስጦታ፣ አነስተኛ አባል ያለው ጋንታ ደግሞ አነስ ያለ ስጦታ ሊደርሰው እንደሚገባና ክፍፍሉም ይህንኑ መሰረት ያደረገ መሆን እንደሚጠበቅበት ተረዳን። በተባለው ፍትሃዊ ጥያቄ (ብዙሃን ያሸንፋሉ የሚለውን) እኛም አምነንበት እንደየጋንታቸው ስፋት ስጦታውን አከፋፍለን በገንዘብ ኃይል ፍቅራቸውን ያደፈረስንባቸውን የአዲግራት ህፃናት ተሰናብተን ጉዞአችንን ቀጠልን።
የህፃናቱ የፍትህ ጥያቄ ተገቢነት እንደነበረው መኪናችን ውስጥ በድጋሚ ተስማማን። ለብዙሃን ሰፊ ዕድል የማይሰጠው ፖለቲካችን ብቻ ነው እያልን በመቀለድ ከተማዋን በሚያውቅ አንድ ጓደኛችን አማካኝነት ወደ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፅ/ቤት ዘንድ አመራን። ይህ ድርጅት ከኦርቶዶክስ፣ ከሙስሊምና ከካቶሊክ ዕምነቶች በተወጣጡ የሃይማኖት መሪዎች የተመሰረተ ሲሆን መሰረታዊ ዓላማውም ነዋሪውን ስለ ሰላም፤ ፍቅር፤ አንድነትና ተቻችሎ ስለመኖር ወዘተ ማስተማርና ማሳወቅ ነው። ድርጅቱ ዕምነት ሳይለይ ለተቸገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕርዳታ የሚያደርግ ሲሆን በተለይ በሰላም ዙሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከሃላፊው እንደሰማነው አስደንቆናል። ዛሬ የሰላምና የመቻቻል እንደዚሁም አብሮ የመኖር ምሳሌ ናት የምንላት ደሴ ከተማ እንዲህ በሃይማኖት ልዩነት ስትናጥ፣ በአዲግራት ከተማ እንዲህ መሰሉ ጠንካራ ድርጅት መኖሩ ሳይቃጠል በቅጠል የሚያሰኝ ነው ብለን፣ አዲግራትን ተሰናበትንና ጉዞአችንን በመቀጠል በዛላምበሳ በኩል አድርገን አዲ ኢሮብ ገባን።
በባለፈው ፅሁፌ ስለ ኢሮብ ማህበረሰብ ብዙ ስላልኩ ዛሬ ደግሜ አልመለስበትም። በማሳረጊያዬ ደግሜ የምለው ግን ጉዞ መልካም ነው። በተጓዝንም ቁጥር እንዲህ ልምድና ተመክሮአችን እየሰፋ ይሄዳል። አገሪቱን ዞረን ሳናያት ስለ ዕድገትዋ ወይም ስለ ኋላ-ቀርነትዋ መነጋገር ይከብዳል። በአራቱም አቅጣጫዎች ብንሄድ ኢትዮጵያችን ሰፊ፣ ህዝቦችዋም ልዩ መሆናቸውን በእርግጥም እንረዳለንና ሰፊ አስተሳሰብን ለማዳበር የጉዞ ልምዳችን ይዳብር ብዬ ብሰናበትስ?...
ከመሰናበታችን በፊት…
ሰሞኑን ሞባይሌ አቃጨለና የአሜሪካ ኮድ በሆነ የስልክ ቁጥር አንድ ሰው እንደደወለልኝ ነገረኝ። የስራ ፀባዬ ሆኖ አልፎ-አልፎ ከውጪ አገራት ስልክ ስለምቀበል ማን ይሆን በማለት ስልኬን በማንሳት አቤት አልኩኝ። ፈላጊዬ ከወዲያኛው ማዶ ሆኖ “አቶ ዳዊት ንጉሡ ረታ?” አለኝ። “አቤት” አልኩኝ ቆፍጠን ብዬ። “ካህሣይ አብርሃ” እባላለሁ። የአሲምባ ፍቅር መፅሃፍ ደራሲ። የአሲምባው አማኑኤል ሲልም አከለልኝ። ባለፈው 15 ቀን ፅሁፌ የአሲንባ ፍቅር የሚለው መፅሃፉን በአስረጂነት የጠቀስኩ ስለነበረ ይህንኑ ፅሁፌን ከመታተሙ በፊት እንዲያነበውና አስተያየቱን እንዲልክልኝ አስቀድሜ መፅሃፉ ላይ ባገኘሁት የኢሜል አድራሻ ልኬለት ነበር። ሆኖም ፅሁፉ በአማርኛ ስለነበረና በእርሱ ኮምፒውተር ላይ አልከፍትለት ስላለ ፅሁፉን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አንብቦት እንደደወለልኝ ነገረኝ። እጅግ በጣምም ተደሰትኩ። አቶ ካህሳይ የእኔና የጓደኞቼን የጉዞ ትዝታ ሲያነብ የራሱን የወጣትነት ጊዜ እንዳስታወሰና በድጋሚ በፅሁፉ አማካኝነት የዚያ አካባቢ ሁናቴ በዓይነ ህሊናው እንደተመላለሰበት ገለፀልኝ። በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም ተገኛኝተን ይበልጡኑ የወጣትነት የአሲንባ ታሪኩን ሊተርክልኝ ቃል-ተገባብተን፣ እስከዚያው ዘመን ባመጣው ኢሜል ግንኙነታችንን እንድናጠናክር ተስማምተን ተለያየን። አቶ ካህሳይ አብርሃ እጅግ ትህትና ያለውና ተግባቢ፣ ለሰው ልጅም ልዩ ክብር ያለው ሰው መሆኑን ከነበረን የስልክ ጨዋታ ለመገመት ችያለሁ። በተጓዝክ ቁጥር ትሰፋለህ ማለት ይሄ አይደለ? መልካም ቅዳሴ!

Read 2672 times Last modified on Saturday, 28 September 2013 13:44