Saturday, 05 October 2013 09:37

የ“ላይፍ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ በአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ተከሰሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የ“ላይፍ” መፅሄት ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ሰለሞን፤ በአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት በአቶ ፀሀይ ሽፈራው ክስ ቀረበበት፡፡ ላይፍ መፅሄት በመስከረም ወር እትሙ “የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ኩብለላና ህገ ወጡ ብድር” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ነው አዘጋጁ የተከሰሰው፡፡ ከትናንት በስቲያ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርቶ ቃል የሰጠው ዋና አዘጋጁ፤ የባንኩ ፕሬዚዳንት “ስሜ ጠፍቷል” በሚል ክስ እንደመሰረቱበት እንደተነገረውና ቃል ከሰጠ በኋላ በአምስት ሺህ ብር ዋስ እንደወጣ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ አዘጋጁን ለክስ ያበቃው ዘገባ “አዋሽ ባንክ ሰራተኞቹ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ያዘጋጀውን ብድር አቶ ፀሀይ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለራሳቸው በመደበር እና ቤት ገዝተው አትርፈው በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነዋል” የሚል ይዘት እንዳለው ታውቋል፡፡

“መረጃውን ያገኘነው ከአዋሽ ባንክ ሰራተኞችና ከውስጥ አዋቂዎች ነው” ያለው ዋና አዘጋጁ፤ ከሰራተኞቹ በተጨማሪ ነሀሴ 28 እና 29 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣም የፕሬዚዳንቱን እና የብድሩን ጉዳይ አስመልክቶ ተከታታይ ዘገባ አቅርቧል ብሏል፡፡ “አቶ ፀሀይ መፅሄቱን ሳይሆን ዋና አዘጋጁን ነው የከሰሱት” ያለው አቶ ዳዊት፤ ሁለት የሚዲያ ተቋማት አንድ አይነት ይዘት ያለው ዘገባ ሰርተው አንዱ ሳይከሰስ ሌላው የሚከሰስበት ሁኔታ እንዳልገባው ገልጿል፡፡

Read 1578 times