Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 08:32

“ልጅነት ወርቁ፣ ልጅነት እንቁ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“መዝናናት መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት” ጓድ ሌኒን 
ልጅነት ስንል፣ ከምንጩ ከእናት መነሳት ደግ ነው፡፡ ከጥንት እንጀምር፡፡ በዚያ በደጉ ዘመን ከብዙ ማስተዋልና ማሰብ ማሰላሰል በኋላ ተረትና ምሳሌዎቹን እመው ዝግ ባለ ድምጽ ይናገሩዋቸው ነበር፡፡ ከዚያ አበው ይቀበሉና፣ እንደ ገደል ማሚቶ በጐላ ድምጽ ይደጋግሙዋቸዋል ለዘመናት፡፡
የሚከተለው ጽሑፍ አብዛኛው ያዲስ አበባችን እመው ስለ ልጆች ያስተዋሉትን ተቀብዬ በአበው አርአያ የማቀብላችሁ መሆኑ ነው፡፡
አንድ
ጥንት በሀገረ ግብጽ ለክርስቶስ ያደሩ ፃድቃን ባልና ምሽት ይኖሩ ነበር፡፡ ፍሬ ስላልሰጣቸው በእድሜ እጅግ ከገፉ በኋላ፣ በስለት አንድ ልጅ ወለዱ - በእለተ አርብ፡፡ እናት ከአዋላጅ ተቀብላ ጡት ወደ አፉ ብታስጠጋለት ህፃኑ “በስመአብ ወወልድ መመንፈስ ቅዱስ! በፆሙ?” አለ፡፡ ከዚያ ወድያም ቢሆን ያ ልጅ ጡትም አልጠባ፣ እህልም አልቀመሰ እድሜ ልኩን፡፡ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አሉት፡፡ ጊዜው ሲደርስ አባይን ተከትሎ ለታላቅ ተጋድሎ ወደ ቅድስታገር ዘመተ፣ ወርረዋት እንደ ንብረታቸው አድርገዋት የነበሩትን ርኩሳን መናፍስት ጌታ በሰጠው መብረቅ እያሳረረ ፈጃቸው፡፡ በኋላ ምእምናን “አቦዬ ጣዲቁ ገደል እንደ አክርማ የሚሰነጥቁ!” ሲሉ ዘመሩላቸው፡፡


ሁለት
ሱራፌል ይባላል፣ እድሜው ሁለት አመት ተኩል፡፡ አንዳንዴ ሲያወራ “ድሮ ልጅ ሳለሁ” ይላል፡፡ እናቱ የአንዲት ዘመዴ ሰራተኛ ናት፡፡
እዚያ ሳገኘው ቁርስ ምሳ ስበላ፣ ለሱ እንደ ነብሱ የሚወደውን ለውዝ እጋብዘዋለሁ፡፡ አንድ ቀን ቢጠብቅ ቢጠብቅ ለውዝ አልጋበዝኩትም (ዘንግቼ!)
ስለዚህ እሱ ጋበዘኝ “አባባ፣ ምሳ ብሉ” አለኝ (እጣ-ፈንታ የምትባለውን አድባር ባገኛት፣ ሱራፌል ሲያድግ ዲፕሎማት ሆኖ ይጀምርና በትጋት እየሰራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ “ያገሩን ስም ያስጠራና ወላጆቹን ያኮራቸዋል”
አንድ ቀን ስገባ ሱራፌል ግድግዳው ጋ የተንጠለጠለውን የኔን ስእል ይመለከታል፡፡ Picasso የምንለው ሰአሊ ጓደኛችን የሰራው ነው፡፡ ቀያይ ቀለማት ይበዛበታል፡፡
“ከዚህ እሳት እየሮጡ ወጥተው ነው አሁን የመጡት?” አለኝ
“አዎን” አልኩት፣ አመነኝ፡፡
ሶስት
የሚቀጥለው ልጅ ሶስት አመት ሊሆነው ይችላል፡፡ አገር ቤት ነን፡፡ መንደሩ ጭር ብሏል፡፡ ሰው ሁሉ ለሀምሌ እርሻና ጉልጓሎ ወደየማሳው ተሰማርቷል፡፡ የዚህ ልጅ እናት ለታቦትዋ አመት ጌሾ ትወቅጣለች፡፡
ከወድያ አንዱን ሰውዬ አየቻቸውና “አያ አማረ፣ ጌሾ አታዋቅጡንም?” ብለ ተጣራች
“ምን ከፋኝ?” አለና መውቀጥ ጀመሩ፡፡ “እህ-እህ! እህ-እህ!” እያሉ እያለከለኩ ሲወቅጡ ከቆዩ በኋላ አያ አማረ “እፎይ!” አሉ፡፡ “አሁንስ ደከመኝ፡፡ ገባ ብለን አናርፍም?”
ገቡ፡፡ ቆይተው ቆይተው ወጡና ወቀጣውን ቀጠሉት፡፡ (ልጅ ከሙቀጫው ፈንጠር ብሎ አፈር ላይ ምናምን እየጫረ ከብቻው ጋር ይነጋገራል)
እናቱና አያ አማረ በወቀጣና በእረፍት እየተመላለሱ ስራቸውን ፈፀሙ፣ አያ አማረ “ጠላውን ለመጠጣት ያብቃን” ብሎ ተሰናብቶ ሄደ፡፡
መሸ፡፡ ገበሬ በዝናብና በጭቃ ሲያርስ ውሎ ድክም ብሎታል፡፡ በሬዎቹን ፈታ፣ እርፍ ሞፈሩን፣ ቀምበር ድግሩን እና ሌላውን ቁሳቁስ ተሸከመ፣ ከብቱን እየነዳ ወደ ቤት ገሰገሰ፡፡ ሸክሙን አራግፎ ቤት ሲገባ ልጁ እሳት ዳር ተቀምጧል፣ ሚስቱ እራት ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ እያለች ነው፡፡
መደቡ ላይ ፈንደስ እያለ “እፎይ!” ብሎ ሲተነፍስ
“አያ አማረ መጡልህ!” አለው ህፃኑ፡፡
አራት
ቀጣዩ እንግዳችን አራት አመቱ ነው፡፡ አባቱ የራሱ የግል ስራ ስላለው፣ ከልጁ ጋር በሰፈር ለመዘዋወር ይመቻቸዋል፡፡ ሲሳደብ ድሮ ልጅ ሳለ “አይን አራም!” እያለ ነበር፣ ዛሬ “አይጥ!” ነው፡፡
ቄሱ በሀይል በሚጮህ ድምፅ ማጉያ እንደ ነብዩ ሙሴ ይሁን ወይስ እንደ እግዚአብሔር እንጃ፣ አላፊ አግዳሚው ህዝብ ላይ እርግማንና ቁጣ እያወረዱበት ነው፡፡
ልጁ አባቱን ጠየቀው “ቄሱ ለምን ተቆጡ?”
ሌላ ቀን ሁለት አዋቂዎች ሲጨቃጨቁ ቆይተው፣ አንዱ “ኧረ ተው ስሜን አታጥፋ!” አለ፡፡ ልጁ አባቱን ጠየቀ “ስም ይጠፋል ‘ንዴ” አሰበበትና ለራሱ “ደሞስ ጠፍቶ የት ይሄዳል?”
አሁንም ሌላ ቀን ሁለት ሌሎች አዋቂዎች ሲነዛነዙ “ኤድ! አልፈራህም” አለ አንዱ ልጁ “አባዬ፣ እኔ’ኮ ሰዎችን አልፈራቸውም” አለ፡፡ አሰበበትና ለራሱ “እነሱም አይፈሩኝም”
አሁን ደሞ ሌላ ቀን (ማለት ስድስት አመት ሆኗታል) በአስር አመት የምትበልጠው እህቱ “እኔ እነዘነበች ጠርተውኝ መሄዴ ነው፣ ለማዬ ንገራት” አለችው፡፡
“እሺ” አላትና፣ ለአባቱ “ውሸቷን’ኮ ነው፡፡ ቦይፍሬንዷ ጋ ነው ‘ምትሄደው”
አምስት
ሌላ የስድስት አመት ልጅ ነው፡፡ አንድ አጥር ግቢ ውስጥ ሁለት ቤት አለ፣ የልጁ አዲስ ጐረቤት ቅርፃ-ቅርፅ የሚፈጥር አርቲስት ነው፡፡ አንድ ቀን ሁለት ቁምሳጥን የሚያክል ግድንግድ እብነ በረድ አራት ሰዎች ተሸክመው አምጥተው አርቲስቱ ቤት አስገብተው አቁመውት ሄዱ፡፡
ገና ከመውጣታቸው አርቲስቱ መዶሻና መሮውን አንስቶ ይወቅር ጀመር፡፡ ቋ! ቋ! ቋ! በሚል ድምፅ የእብነ በረድ ጠጠር ዙርያውን ይወድቃል፡፡
ልጁ ከእኩዮቹ ጋር መጫወት ረሳ ይህን ሲመለከት፡፡ እናቱ ስትጣራ አቤት አይልም (ግማሽ እንደ ህልም ነው ድምጿ፣ የልጁ ትኩረት አርቲስቱ እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ ነው)፡፡ እናቱ መጥታ በግድ ወስዳ ትመግበዋለች፣ እሱ እየሮጠ ወደ ቅርፅ ትርኢቱ ይመለሳል፡፡
እብነ በረዱ ቅርፅ እያወጣ በአራት እግር እየቆመ አንበሳ እየመሰለ ሄደና፣ ልክ አንበሳ ሲመስል ቀራፂ ስራውን አቆመ፡፡
ይህን ሁሉ ቀን በፀጥታ ሲመለከት የሰነበተው ልጅ ገና አሁን ተናገረ፡-
“አንተ ግን አንበሳው እዛ ውስጥ ሲደበቅ አይተኸው ነበር’ንዴ”
“አዎን”
“አይኑ ግን አያይም”
አርቲስቱ ሰአሊ ጓደኛው የነገረውን አስታወሰ፡ምናልባት የሶስት አመት ልጅ ይሆናል፤ ጐረቤቱ ነው፣ መጣና የማይቻል ትእዛዝ ሰጠው፡- “ደበረኝ’ን ሳልልኝ”
ስድስት
ሞት ይርሳኝ! የገዛ ራሴን ልጅነት ረስቼ፡፡ “ድሮ በልጅነቴ” ብዬ ልጀምር (ከዚህ በላይ እንዳያችኋቸው ገፀ-ባህሪያት)
እንበል ከሶስት እስከ አራት አመት ይሆነኛል፡ “ውጪ ተጫወቱ” ተብለን በጠጠር፣ በአፈር፣ በስንጥር፣ እየተጫወትን ነው፡፡
እሱ በአፈር እየተጫወተ እኔ በስንጥር መጫወት ስጀምር “ስጠኝ” ይለኛል፡፡ እምቢ ስለው “እማዬ” ብሎ ይጣራል “ወይ!” ስትለው “ከለከለኝ” ይላታል “ስጠው!” ትለኛለች፣ ምን እንደሆነ እንኳ ሳትጠይቅ፡፡
ትንሽ ትቆይና “ደሞ’ምትሰራውን እማላይ እንዳይመስልህ፣ ዋ!”
እንደምታየኝ እርግጠኛ ስለነበርኩ በጥንቃቄ አጫውተዋለሁ፣ እሷን ከነመኖርዋ ረስቼ በጭራሮ ቤት መስራት ስጀምር “ስጠኝ” ይለኛል፣ እከለክለዋለሁ፣ ይጣራል … እያልን እንቀጥላለን፡፡
ይሄ ደሞ ተራዬን ወላጅ ሆኜ ያጋጠመኝን አስታወሰኝ፡፡ ከሶስት አመት ሴት ልጄ ጋር ሽርሽር ልንሄድ ከቤት ቀድሜያት ወጥቼ በዝግታ ስራመድ “አንተ አባዬ፣ ሳይነግሩህ አትሰማም’ንዴ” ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ለካ ስታስብም የምሰማት ይመስላት ኖሯል!
አንድ ቀን (አራት አመት ይሆናታል) መንገድ ዳር የሚያምር ህብረ ቀለማት ያለው ጃንጥላ ዘርግተው፣ ከስሩ ሳንቲም መቀበያ ጨርቅ አንጥፈው፣ የጌታን ስቅለት የሚያሳይ ትልቅ ስእል ይዘው፣ ፀናፅል እያንቃጨሉ ላረጀ ቤተ ክርስትያን ጥገና መዋጮ ይጠይቃሉ፡፡ በአድናቆት ስታስተውል ቆይታ፡-
“አባዬ፣ ቄሶቹ እዝጊያቤርን ይገርፉታል?”
“ኧረ አይገርፉትም! እሱ’ኮ በጣም ሀይለኛ ነው፡፡ መብረቅና ነጐድጓድ አለው አይደለም ‘ንዴ?”
“አሀ! ረስቼ” አለች እየተረጋጋች፡፡ ለካ ፈርታለች ኖሯል!
ትንሽ ቆይታ “አባዬ፣ እዝጊያቤር ይታያል?” ጠየቀች
“አይታይም”
“እንሰማዋለን?”
“አንሰማውም”
“እንግድያው የለማ?!”
ክፉኛ ደነገጥኩ፡፡ እዝጊያቤር ከሌለ ጮርቃ አእምሮዋ አይናወጥም? ደግነቱ፣ ውቃቤዬ ደረሰልኝና “እንዴ!” አልኳት “ምን መሆንሽ ነው?” ማለዳ ተነስተሽ ሄደሽ ቤቱን ጠርገሽለት ቡና ታፈይለት የለም’ንዴ?”
“እውነትም! ረስቼ፡፡ ጎበዝ አባዬ! አንተ ግን አስታወስክ”
ሰባት
ወደ ራሴ ልጅነት ልመለስና፣ ሶስት አመቴ ይሆናል፡ የሆነች ዘመዳችን ሞታ፣ እናቴ ለቅሶ ተቀምጣለች፡ የሟቿ ልጅ እኩያዬ ነው፡፡ የውጪው በር አጠገብ እንጫወታለን፡፡ አዋቂዎቹ ወንዶቹም ሴቶቹም እያወሩ እየተሳሳቁ ይመጡና፣ እኛ ጋ ሲደርሱ በድንገት ሌሎች ሰዎች ይሆኑና ጭንቅላታቸውን ይዘው አምርረው ያለቅሳሉ፡፡
ይሄ ድንገተኛ ለውጥ ቢደጋገምም ባየሁት ቁጥር ይገርመኝ ነበር፡፡ ሌላ ተደጋጋሚ ነገር ነበር፡፡ ሰዎች እኔን ከቁብ ሳይቆጥሩኝ፣ እሱን “ይሄ ነው ልጇ? እኔን! አይዞህ እሺ?” ይሉታል ከንፈራቸውን እየመጠጡ (እምጵፅ!)
ይህን ጊዜ እኔ በልቤ “እማዬ በሞተች! እኔንም እንደዚህ አዝነውልኝ ይስሙኝ ነበር!” እያልኩ ስመኝ ትዝ ይለኛል (ነገ ጧት እንደማገኛት እርግጠኛ ነኛ!)
አንድ ቀን ከጐረቤት እየሮጥኩ መጣሁና ሲናገሩ የሰማሁትን ልነግራት ስል፡-
“ዝም በል! የሴት ልጅ!” ብላ አካለበችኝ፡፡ ኩም አልኩ! “ወንድ ልጅ ወሬ አያመላልስም፡፡ አሳባቂ ይሉታል”
ዘፈን በጣም እወድ ነበር፡፡ አዲስ የሰማሁትን የድሮ ዘፈን “ሳንቆረቁርላት” ታመሰግነኛለች፣ እደጋግምላታለሁ፡፡
አንድ ቀን እየሮጥኩ ገባሁና እንግዶች ፊት “አዲስ” ዘፈን ዘፈንኩላት፡፡ እሷም እንግዶችዋም ድገምልን እያሉ ያመሰግኑኛል ብዬ ነበር፡-
“ዘውዲቱ ዓባዬ
አጥምዮም ነቦይ አባዬ፣ አጥምዮም!”
“ዝም በል! ውጣ ከዚህ! ባለጌ!” እያሉ አካለቡኝና አፍሬ ወጣሁ፡፡ እኔ ዘፈን መሆኑን እንጂ ባለጌ መሆኑን አላውቅ! “ዘውዲቱ ትልቋ ለአቦይ አባይ አቅምሺያቸው፣ አቅምሺያቸው” ብዬ ነበር የዘፈንኩት፡፡ ምኑ ላይ ነው ብልግናው? ያዋቂዎች ነገር ምኑም አይገባኝ!
ስምንት
“እንጫወት እንጂ እንጫወት በጣም
እንግዲህ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም” (ጓድ እውነቱ)
ልጅነቴ ልጅነቴ፣
ማርና ወተቴ” (ጓድ ሀሰቱ)
ኧረ አፍ አውጥተው ልጅነት ገነት ነው የሚሉ አሉ! ወይ ግብዞች ናቸው፣ ወይ ያሳለፉትን የልጅነት “ትንሽዬ ሲኦል” ረስተውታል፡፡ እኔ በበኩሌ እስከ መቼም የማልረሳቸዉን ገጠመኞች ልተርክላችሁ፡-
አራት አመቴ ነው፡፡ አንዲት መሬት ለመሬት የምትንፉዋቀቅ ሀረግ አለች፡፡ ታላቆቻችን እረኞች ያሳዩን “ጨዋታ” ነበረ፡፡ ከሀረጓ አንዱን ቅጠል ስንበጥስ፣ ወተት የሚመስል አንድ ጠብታ ብቅ ይላል፡፡ ያንን ወስደን የሽንታችንን መውጫ እንደፍነዋለን፣ እዚያው ይደርቃል፡፡
በነጋታው ጧት ስንሸና በአራት አምስት ቀዳዳ ይወጣል (ለዚያውም አልወጣ እያለን በሀይል እህ! እያልን ነው) አዋቂዎች ብንሆን ሀረጊቱን እርግፍ አርገን እንተዋት ነበር፡፡ ልጅ ግን ይበልጥ ማወቅ ይፈልጋል፣ ሳይንቲስት ነው፡፡ እኔም ገፋሁበት ይህን experiment.
ጧት ልሽናህ ብለው ባንዲት ቀዳዳ እንኳ አልወጣም አለ፡፡ ብገፋ፣ እህ! ብል፣ ምንም! የምፈነዳ መስሎ ተሰማኝ፡፡ “ጋሽዬ!” ብዬ ሰማይ እስኪሰነጠቅ ጮህኩ፡፡
በአስር አመት የሚበልጠኝ ወንድሜ ደንግጦ ወደኔ ሮጦ፡፡ መሽኛዬን ይዤ ሲያየኝ ገባው (እሱም በዚህ ገጠመኝ አልፎ ነዋ እዚህ የደረሰው!) ሮጦ ተመልሶ ወረንጦ ይዞ መጣ፡፡
ያሸገኝን “ሰም” ሲነቅሰው ጊዜ እንደ መክደኛ ረገፈ፡ እፊቴ የተምበረከከውን ጋሼ ፉሽ ብሎ ሄዶ ፊቱን አጠበው፡፡
እኔም እፎይ አልኩ፣ እሱም እየሳቀ፣ ፊቱን እየጠረገ ገባ፡፡
ስድስት አመት ይሆነኛል፡፡ በአል ነው፡፡ ጋሼ እርሻ ስለሌለበት ሊያግዘኝ ሊያለማምደኝ አብሮኝ እረኝነት መጥቷል፡፡
የሩቅ መንደር እረኞች አጋጠሙን፡፡ የማይታለፍ ስነ ስርአት ነው መቼስ፣ ትግል እንግጠም ተባለ፡፡ (ትልልቆቹ “ድሮ እኛን ሲያክሉ” ታግለው ተዋጥቶላቸዋል፡፡ የምር ከተጋጩ ደሞ በዱላና በድንጋይ መፈናከት ነው እንጂ …)
ከነሱ አንዱ ተመረጠ፡፡ በኛ በኩል ሶስት እኩያሞች አለን፡፡ ጋሼ ባንድ በኩል ለወንድሙ አድልቶ ነው እንዳይሉት፣ በሌላ በኩል ደሞ ስለተማመነብኝ እኔን መረጠኝ፡፡ “አይዞህ! እርግጠኛ ነኝ ትጥለዋለህ” ብሎ በትከሻዬ ወደ ባላጋራዬ ገፋ አደረገኝ፡፡
ያችን ጥቂት እርምጃ ሄጄ እስክንያያዝ ድረስ አመት ያህል ረዘመብኝ፡፡ ሰዎች በፍርሀት ሽንት ያመልጣል ሲሉ፣ እኔ ለምን እንዳላመለጠኝ ይገርመኛል፡፡ በኋላ ደጋግሜ ሳስበበት ከዚያም የበለጠ የገረመኝ ምንድነው? ብትሉኝ፣ ያንን ጭራቅ ባላጋራዬን ጣልኩት! “ወይ መዓልቲ!”
እኛ መንገድ ሶስታችን ልጆች እኩያ ነን፡፡ እኔ፣ ፍስሀ እና ተክሉ፡፡ በትግል እኔ ፍስሀን እጥለዋለሁ፡ ፍስሀ ተክሉን ይጥላል፣ ተክሉ እኔን ይጥለኛል፡፡ “ፍስሀ ተክሉን ጣለ፣ እኔ ፍስሀን ጣልኩ፡፡ ስለዚህ እኔ ከፍስሀ እጐለብታለሁ፡፡ ስለዚህ እጥለዋለሁ” ይህን በእርግጥ አምናለሁ፡፡ ከዚያ በኩል በእርግጥ ደግሞ ተክሉ እንደሚጥለኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ መልስ የማይገኝለት “ምስጢረ እንቆቅልሽ!”

 

Read 5852 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:37