Saturday, 05 October 2013 09:47

ንግድ ባንክ በአስር ወር ውስጥ 1.8 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች አገኘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ይቆጥቡ ይሸለሙ” በሚል መሪ ቃል ላለፉት 10 ወራት በተካሄደው የቁጠባ ፕሮግራሙ 4.2 ሚሊዮን የነበረውን የደንበኞቹ ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ማሳደጉን ገለፀ፡፡
ባንኩ የዜጐችን የቁጠባ ባህል ለማሣደግ በጀመረው የቁጠባ ፕሮግራሙ፤ የደንበኞቹና ቁጥር ከማሣደጉም በላይ ተደራሽነቱን የበለጠ ለማስፋትና ትርፋማነቱን ለማሳደግ እንደቻለ የባንኩ የቢዝነስና ዴቨሎፕመንት ተጠባባቂ ዋና ሃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛ ዙር “ይቆጥቡ ይሸለሙ” ፕሮግራሙም ሽልማት የሚያስገኙ 4 ሚሊዮን ኩፖኖችን ማሠራጨቱን የጠቆሙት ሃላፊው፤ አብዛኞቹ ለደንበኞች መድረሣቸውን ገልፀዋል፡፡

ከአንድ ሺህ ብር በላይ ለሚቆጥቡ ደንበኞቹ በሚሠጠው የሽልማት ኩፖን አሸናፊ ለሆኑ ከ40 በላይ ደንበኞቹ ባለፈው ሰኞ የመኪና፣ የትራክተሮች፣ የወፍጮዎችና ሌሎች የተለያዩ በርካታ ሽልማቶች አበርክቷል፡፡
በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዳራሽ በተካሄደው የእጣ አወጣጥ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሊካ በድሪ፤ አውቶሞቢሎችን የሚያሸልሙትን የመጀመሪያዎቹን 15 እጣዎች አውጥተዋል፡፡
ዕጣዎቹም በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ጐንደር፣ ነቀምት፣ ሻሸመኔ፣ መቀሌ፣ ወላይታ፣ ድሬዳዋ እና ሃዋሳ ላሉ የባንኩ ደንበኞች ደርሠዋል፡፡
ለሁለተኛ ዙር ባዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም በ10 ወራት ውስጥ ብቻ ተጨማሪ 1.8 ሚሊዮን ደንበኞችን ማግኘቱን ያመለከተው ባንኩ፤ በቅርቡም ይበልጥ ሠፋ ባለ መልኩ ሶስተኛውን “ይቆጥቡ ይሸለሙ” ፕሮግራም ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

Read 2104 times