Saturday, 05 October 2013 10:01

ፓርላማ፣ ኢትዮጵያውያንን ሳያማክር አዲስ ፕሬዚዳንት ይመርጥላቸዋል

Written by 
Rate this item
(20 votes)
  • የፕሬዚዳንቱ ስልጣን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ፓርላማውን፣ እንዲሁም የፌደሬሽን ምክርቤትን ሁሉ ይነካል።
  • ፕሬዚዳንቱ ሳይፈቅድ፣ ጠ/ሚሩ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረጎችን መስጠትና አምባሳደሮችን መሾም አይችልም።
  • ብዙዎች ቢያናንቁትም የፕሬዚዳንቱ ስልጣን ቀላል አይደለም። “ስልጣኑ ተሠርቶበታል ወይ?” ነው ጥያቄው።

ኢህአዴግ በተለመደው የምስጢራዊነት ባሕርይው፣ ለፕሬዚዳንትነት ማንን በእጩነት እንደሚያቀርብ ሳይነግረን ይሄውና የምርጫው ቀን ደረሰ። ባዕድ መሰልነው እንዴ የሚደብቀን? ዜችን ከመናቅ ይሁን ከመፍራት፣ ሕግን ባለማክበር ይሁን በቸልተኝነት… ምንም ሆነ ምን፣ ዜጎች በሰኞው የፕሬዚዳንት ምርጫና በእጩዎች ላይ ሃሳባቸውን እንዳያቀርቡና እንዳይወያዩ እድል ተነፍጓቸዋል - በኢህአዴግና በፓርላማው። ታዲያ የዜጎች ድርሻ ምንድነው? … ያው እንደተለመደው፣ “ተመልካች” መሆን ብቻ! በቃ፤ ሰኞ እለት ቴሌቪዥን ከፍተው፣ አንድ ሰው ፕሬዚዳንት ሆኖ ሲሾም መመልከት ብቻ! ለነገሩ፣ የአገራችን ችግር የገዢው ፓርቲ ብቻ አይደለም። ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ያው ናቸው። አንዳንዶቹም የባሱ! “ለፕሬዚዳንትነት በእጩነት የሚቀርበው ሰው ማን እንደሆነ ለዜጎች ተገልጾ ውይይት መካሄድ አለበት” ብሎ የኢህአዴግንና የፓርላማውን ድብቅነት የተቸ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲና ፖለቲከኛ የለም። 
ኢህአዴግ ከዜጎች ጋር በአደባባይ ከመወያየት ይልቅ የጓዳ ምስጢራዊነትን፣ ፓርላማውም በግልፅነት ዜጎችን ከማገልገል ይልቅ የጓሮ ድብቅነትን መምረጣቸው ሳያንስ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች እንዲህ መሆናቸው አይገርምም? ድብቅነትን በመተቸት ግልፅነት እንዲሰፍንና የዜጎች የሃሳብ ነፃነት እንዲሰፍን ሲጠይቁ የማናያቸው፣ ኢህአዴግን ወይም መንግስትን በመፍራት አይደለም። በፕሬዚዳንቱ ምርጫ ዙሪያብዙ ትችቶችን ለመደርደር አልሰነፉም - በተለይ ደግሞ የፕሬዚዳንቱን ስልጣን በማናናቅ።
በአላዋቂነት ይሁን በደንታቢስነት… ምክንያቱ ባይታወቅም፣ የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ማጣጣል በኛ አገር በጣም የተለመደ ነገር ነው። ለነገሩ፣ በአገራችን ኋላ ቀር ባህል ውስጥ፣ የመንግስት ስልጣን… “ሕግ የማያግደው አድራጊ ፈጣሪና ፈላጭ ቆራጭ” ካልሆነ፤ ብዙዎቻችን ያን ያህል አናከብረውም፤ እውነተኛ ስልጣን ሆኖ አይታየንም። ለዚህ ይመስለኛል፣ የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ማናናቅ እንደ አዋቂነት የሚቆጠረው - በሕግ የተገደበ ስልጣን ስለሆነ!

የኢህአዴግ የድብቅነት ባህል
ኢህአዴግና አጋሮቹ በ99.5% በላይ የተቆጣጠሩት ፓርላማ፣ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የሚኒስትሮች ሹም ሽርና ሽግሽግ እንዴት እንደተካሄደ ታስታውሱ ይሆናል። ባታስታውሱትም ችግር የለውም። እንደተለመደው ነው… አንድ የፓርላማ ስብሰባ ላይ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መጥተው፣ ለሹመት የታጩ ሰዎችን በስም ይዘረዝራሉ። “እገሌ፣ ይህንንና ያንን ተምሯል፤ እዚህና እዚያ ሰርቷል” የሚል፣ “የአጭር አጭር የመተዋወቂያ ገለፃ ይነበባል - ከሦስት ዓረፍተ ነገር ያልበለጠ። ከዚያ አንድ ሁለት ጥቅል አስተያየቶች በአጭሩ ይቀርቡና የፓርላማ አባላት ድምፅ ይሰጣሉ። የሚኒስትሮቹ ሹመት ይፀድቃል። እስከዚያች የስብሰባ ሰዓት ድረስ፣ ለሚኒስትርነት የታጩት ሰዎች እነማን እንደሆኑ አይታወቅም፤ በምስጢር ተደብቆ ይቆያል። የፓርላማ አባላት እንኳ፣ “ማን በእጩነት ይቀርባል?” ተብለው ቢጠየቁ፣ ከስብሰባው በፊት እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት።
ለሚኒስትሮች ሹመት የሚሰጠው አቅምና ብቃታቸው እየታየ መሆን እንዳለበት ሕገመንግስቱ በግልፅ ይደነግጋል። የእጩ ተሿሚዎችን አቅምና ብቃት የመመዘን ስልጣንና ሃላፊነት የፓርላማው የመሆኑን ያህል፤ በእጩዎቹ አቅምና ብቃት ላይ መረጃ መስጠትና ሃሳብ መግለፅ ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ነፃነትና መብት ነው። መንግስት፣ የግልፅነት አሰራርን በመከተል እቅዶቹን በይፋ የማስታወቅ ግዴታ በህግ የተጣለበት በሌላ ምክንያት አይደለም። በእቅዶቹ ላይ ዜጎች ሃሳባቸውን የመግለፅና የመወያየት ነፃነት ስላላቸው ነው። “መንግስት እና ፓርላማው የህግ የበላይነትን በማክበር ሃላፊነታቸውን ለማሟላት፣ የዜጎችንም መብትና ነፃነት ለማክበር ፈቃደኛ ቢሆኑ”… ብለን እናስብ። ያን ያህልም ውስብስብ አይደለም።
ለሚኒስትርነት ወይም ለፕሬዚዳንትነት የሚታጩ ሰዎች እነማን እንደሆኑ፣ ከሳምንታት አስቀድሞ የፓርላማ አባላት እንዲያውቁት ይደረግና፣ ለዜጎችም በይፋ ይገለፃል። ያኔ፣ የእጩዎቹን ማንነት በማጥናትና መረጃ በመሰብሰብ፣ ብቃታቸውንና የስነምግባር ደረጃቸውን የመመዘን እድል ይፈጠራል። ዜጎችና የፓርላማ አባላት፣ ሃሳብ ለመለዋወጥና ለመወያየት ጊዜ ያገኛሉ። በእጩዎቹ ብቃትና ድክመት ወይም የስነምግባር ፅናትና ብልሹነት ላይ፣ የሚያስመሰግን ወይም የሚያስወቅስ ተጨባጭ መረጃ ያላቸው ሰዎች፣ ማስረጃቸውን ለፓርላማ አባላት በማካፈል ይተባበራሉ - ሃሳባቸውን የመግለፅ ነፃነታቸውን በመጠቀም። እንዲህ፣ በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ እንደሚደረገው፣ ግልፅነትና ጨዋነትን የተላበሰ፣ የህግ የበላይነትና የዜጎች ነፃነትን ያከበረ አሰራር ቢፈጠር፣ በሙስናና በብቃት ጉድለት የሚፈጠሩ ግርግሮች በቀነሱ ነበር። ይሄ ግን አልሆነም።
መንግስት በህግ የተጣለበትን የግልፅነት አሰራርን ወደ ጎን ብሎ፣ ለፕሬዚዳንትም ሆነ ለሚኒስትር ሹመት በእጩነት የሚያቀርባቸውን ሰዎች በምስጢር ደብቆ ይይዛል። የተሿሚዎችን ብቃትና ስነምግባር ፈትሸው እየመመዘን ህገመንግስታዊ ሃላፊነት የተጣለባቸው የፓርላማ አባላትም፣ ሃላፊነታቸውን መወጣት ያቅታቸዋል። በአንድ ስብሰባ ላይ የእጩ ሚኒስትሮች ወይም የእጩ ፕሬዚዳንት ስም ዝርዝር የሚቀርብላቸው የፓርላማ አባላት፤ እዚያው ስብሰባ ላይ የእጩዎችን የቀድሞ የሥራ ትጋትና ስንፍና፣ ስኬትና ውድቀት መርምረው፣ የወደፊት አላማቸውንና ሃሳባቸውን ፈትሸው፣ ብቃትና አቅማቸውንም ሁሉ በአምስት ደቂቃ ውስጥ መዝነው፣ በአምስት ደቂቃ ውስጥ የሁሉንም ሹመት ማፅደቅ የሚችሉት እንዴት ነው? አንድ ሾፌር፣ አንድ ነርስ ወይም አንድ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ለመቅጠር እንኳ ከዚህ የበለጠ ጊዜ ያስፈልጋል። የብቃትና የስነምግባር ጉዳዮችን ለመመርመርና ለመመዘን ይቅርና፣ የሚኒስትሮችን ስም በወጉ ለማወቅ እንኳ በቂ ጊዜ አያገኙም። በብልሹ ምግባር ከስልጣን የሚባረሩ ባለሥልጣናትን፣ በብቃት ጉድለት ሳቢያ የሚሰናበቱ ተሿሚዎችን በየጊዜው የምናየው፣ ከመነሻው ያለበቂ ፍተሻና ምዘና ሹመት ስለሚሰጥ ሊሆን ይችላል።
መንግስትስ የዜጎችን ሃሳቦች ለማሰባሰብና ለመወያየት መሞከር የለበትም? የፓርላማ ተመራጮች፣ በየቀበሌውና በየወረዳው ከመራጮች ጋር መወያየት የለባቸውም? ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችስ?
ለዚህ የውስጥ ለውስጥ አሰራር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሦስት ምክንያቶች ይታዩኛል። አንደኛው ምክንያት፣ ሕጉ ምንም ይበል ምን፣ እስከ ዛሬ በተለመደው አሰራር በደመነፍስ የመጓዝ ልማድ ነው። ለመንግስት መሪዎችና ለፓርላማ አባላት፣ ለፓርቲዎችና ለፖለቲከኞች፣ ለምሁራንና ለዜጎች ሁሉ… ያን ያህልም ስህተት ሆኖ አይሰማቸውም። ድብቅነት፣ በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት የቆየ ባህልና የተለመደ አሰራር ነዋ። የጎጂ ልማድና የመጥፎ አመል ጉዳይ ነው።
ሁለተኛ፤ መንግስትን እንደ ቁጡ አባት፣ ዜጎችን እንደ ደካማ ሕፃን አድርገን የምናስብ መሆናችን ነው። እንዲህ መንግስትን እንደ ቁጡ አባት ወይም እንደ ጣኦት የማምለክ ኋላቀር ባህልና አስተሳሰብ ስለተጠናወተን፣ መንግስት ምንም ነገር ቢያደርግ፣ የዜጎችን ነፃነት ቢያፍን እንኳ፣ “መልካም ነገር አስቦ ይሆናል” እንላለን። ቁጡ አባት ምንም ቢያደርግ፣ “ለልጆቹ መልካም ነገር አስቦ ይሆናል” እንደምንለው አይነት ነው። ቁጡ አባት ምንም ነገር ሲያቅድ፣ ወደ ውሳኔ ከመሄዱ በፊት እቅዶቹን ለልጆቹ ማማከርና ሃሳባቸውን እንዲገልፁ የማድረግ ግዴታ አለበት? እሺ፣ ቢያማክራቸውና ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ቢፈቅድላቸው ጥሩ ነው እንበል። ግን፣ ይህንን ባያደርግ እንደ ወንጀል ወይም እንደ ክፋት አንቆጥርበትም። “ዞሮ ዞሮ ለልጆቹ መልካም ነገር ማሰቡ አይቀርም። ለልጆቹ ምን እንደሚበጃቸው እሱ ያውቃል” እንላለን። እንደ ቁጡ አባት የምንቆጥረው መንግስትም፣ እቅዱን ባያሳውቀን፣ ዜጎችም ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ባይፈቅድ፣ ህገመንግስቱን እየጣሰ ቢሆንም እንኳ ትልቅ ጥፋትና ወንጀል ሆኖ አይታየንም። መንግስትን እንደ ቁጡ አባት የመቁጠርና፣ “የሚበጀንን እሱ ያውቅልናል” የሚል ኋላቀር አስተሳሰብ አልለቀቀንማ።
ሦስተኛ፣ የመንግስት ባለስልጣናት እቅዳቸውን በማሳወቅ ከዜጎች አስተያየት ከጠየቁ፣ አላዋቂና ደካማ የሆኑ ይመስላቸዋል። እኛም፣ አላዋቂና ደካማ እንደሆኑ በመቁጠር፣ ከፍ ዝቅ እናደርጋቸዋለን። እንፈታተናቸዋለን። እነሱ ህጋዊውን መንገድ ጥሰው ያሰኛቸውን ነገር ከመፈፀም ይልቅ ዜጎችን ለማማከር ከሞከሩ፤ በእነሱ ፋንታ አዛዥ ናዛዥ ለመሆንና ዙፋን ላይ ቂብ ለማለት ይቃጣናል። እዚያ ድረስ ባንሄድ እንኳ፣ በንቀት መረን ለቀን፣ ጨዋነትን ጥሰን መሳደብ፣ ማንጓጠጥ፣ ሥም ማጉደፍ ያምረናል። ስድቡና ዘለፋው እየተግለበለበ ወደ ውግዘትና ውንጀላ ይሸጋገርና ምስቅልቅል ይፈጠራል። የማዘዝና የመታዘዝ፣ የመርገጥና የመረገጥ ባህል እንጂ፣ ተከባብሮ የመነጋገር ባህል የለማ። እናስ፣ መንግስትና ባለስልጣት ምን ያደርጋሉ? ስልጡን ባህል ለመፍጠር ከመጣጣር ይልቅ፣ አቋራጩን መንገድ ይመርጣሉ - በምስጢር ደብቆ ማቆየትና የእጩ ፕሬዚዳንቱን ወይም የእጩ ሚኒስትሮችን ስም በመዘርዘር በአምስት ደቂቃ ውስጥ ሹመታቸው እንዲፀድቅ ማድረግ! ይሄ ስንፍና ነው። መንግስት፣ በስልጣኔ እንደተራመዱት አገራት ባይሆን እንኳ፣ የእጩ ተሿሚዎችን ስም ከሁለት ከሦስት ቀን በፊት በማሳወቅ፣ የለውጥ ጅምር ማሳየት ይችላል። ለከርሞ ደግሞ የእጩ ተሿሚዎቹን ከሳምንት በፊት በይፋ ማሳወቅ… ቀስ በቀስ ስልጡን የግልፅነት አሰራርን መጀመር ይችላል። ከመርገጥና መረገጥ አባዜ የመላቀቅ ፍላጎት ካለው ማለቴ ነው።

የተቃዋሚዎች ዝርክርክነት
ከላይ እንደገለፅኩት፣ መንግስት በድብቅነት አባዜው፣ የዜጎች ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት መጣሱ ሳያንስ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ድብቅነት በዝምታ በማለፍ የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ለማናናቅ መረባረባቸው ያሳዝናል። ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም የሰጡትን አስተያየት ልጥቀስላችሁ።
“የፕሬዚዳንቱ ስራ ዝም ብሎ ቁጭ ማለት ነው፡፡ ወደ 12 ዓመት ገደማ ቁጭ ብሏል፤ ይወጣል፤ በቃ አለቀ፡፡ … ህጉ ራሱ ምንም ሀላፊነት እና ሥራ አይሰጠውም፡፡ በህጉ ላይ የተወሰኑ ነገሮች አሉ፡፡ ሰዎችን መቀበል፣ እንግዶችን ማስተናገድ፣ አምባሳደሮችን መቀበልና መሸኘት፣ ይቅርታ መስጠት… የመሳሰሉትን ያከናውናል”
የፕ/ር መስፍን አስተያየት በጣም አስገራሚ ነው። አንደኛ ነገር፣ በህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩት የፕሬዚዳንቱ ዋና ዋና ሥራዎች፣ በፕ/ር መስፍን የተጠቀሱት ነገሮች አይደሉም። ሁለተኛ ነገር፣ የፕሬዚዳንቱ ስልጣን የውጭ አገራት አምባሳደሮችን መቀበልና መሸኘት እንዲሁም ለእስረኞች ይቅርታ መስጠት ቢሆን እንኳ፣ ትንሽ ስልጣን አይደለም። በሁለት አገራት ግንኙነት ውስጥ፣ ከውጭ የተላከ አምባሳደርን ወዲያወኑ አስተናግዶ የሹመት ደብዳቤውን በመቀበል ወዲያውኑ ሥራውን እንዲጀምር ማድረግ፣ ትልቅ የወዳጅነት ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል። ፕሬዚዳንቱ ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ የመጣውን አምባሳደር ባያስተናግዱትና ለረዥም ጊዜ የሹመት ደብዳቤውን ሳይቀበሉ ቢያጉላሉትስ? ይሄም የቅሬታና የጠላትነት ስሜት የሚገለፅበት የዲፕሎማሲ መሳሪያ እንደሆነ ይታሰባል። ፕሬዚዳንቱ ይህንን የመጠቀም ስልጣን አላቸው። የፕሬዚዳንቱ ዋና ዋና ስልጣኖች ግን፣ ከዚህም በእግጁ የገዘፉ ናቸው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣኖች መካከል ሁለቱን ልጥቀስ - የውጭ አገር ግንኙነት እና የመከላከያ ሃይል ፖሊሲዎችን መምራት! በእነዚህ ቁልፍ ስልጣኖች ውስጥ፣ ፕሬዚዳንቱም የማይናቅ ድርሻ አላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ተለያዩ አገራት አምባሳደሮችን ሳይልክ የውጭ ግንኙነቶችን መምራት አይችልም። ለከፍተኛ የጦር መኮንኖች የማዕረግ ሹመት ሳይሰጥም፣ የመከላከያ ሃይል ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ አይችልም። ነገር ግን፣ ያለ ፕሬዚዳንቱ ይሁንታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባሳደሮችን መሾም ወይም ለጦር መኮንኖች ከፍተኛ ማዕረግ መስጠት አይችልም። ፕሬዚዳንቱ የእጩ አምባሳደሮችን ሹመት ወይም የጦር መኮንኖቹን የማዕረግ እድገት፣ የማፅደቅ ወይም ውድቅ የማድረግ ስልጣን አላቸው። ይሄ ቀላል ስልጣን ነው? በውጭ ጉዳይ እና በመከላከያ ሃይል ፖሊሲዎች ላይ ተሰሚነትና ተፅእኖ እንዲኖረው የሚያደርግ ከፍተኛ ስልጣን ነው።
በእርግጥ፣ የእስካሁኖቹ ፕሬዚዳንቶች፣ ይህንን ከፍተኛ ስልጣን በአግባቡ አልሰሩበትም ይባል ይሆናል። ይሄ ግን ሌላ ጥያቄ ነው። በጣም ሰፊ ስልጣን በህገመንግስት የተሰጠው ፓርላማስ፣ ስልጣኑን በአግባቡ ሰርቶበታል እንዴ? ግን ስልጣኑ አለው፤ ሊሰራበትም ይችላል። ፓርላማው ካለፈው አመት ወዲህ፣ ሚኒስትሮችን የመቆጣጠር ስልጣኑን በመጠቀም ደህና እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይተን የለ? ልክ እንደዚያው፣ ፕሬዚዳንቱም፣ እስካሁን በጉልህ ተግባራዊ ሲደረጉ ያልታዩትን ስልጣኖች ስራ ላይ ማዋል ይችላል። የሆነ ሆኖ፣ የፕሬዚዳንቱ ስልጣን፣ ፕ/ር መስፍን እንዳሉት እንግዶችን መቀበልና በመሳሰሉ መለስተኛ ሃላፊነቶች የታጠረ አይደለም።
ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ ስለ ፕሬዚዳንቱ የስልጣን ቦታና ስለ ሥራ ሃላፊነቱ ወደሰጡት አስተያየት ልሻገር። “ቦታው ለምልክትነት ካልሆነ ብዙ የሚሰራበት አይደለም በሚለውም አልስማማም” የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ “ፕሬዚዳንቱ ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸው የተለያዩ ተግባራት አሉ” በማለት የሰጡት አስተያየት ከፕ/ር መስፍን አስተያየት የተለየ ይመስላል። ግን አይደለም። ዶ/ር ያዕቆብም ቢሆኑ፣ በሕግ የተቀመጠው የፕሬዚዳንቱ ስልጣን፣ እንግዳ ከመቀበልና በአመት አንዴ በፓርላማ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር ከማድረግ የዘለለ እንዳልሆነ ያምናሉ። “በግልፅ የተቀመጡትን እንግዳ መቀበል፣ ፓርላማ መክፈት እና የመሳሰሉትን ትተን፣ በርካታ ስራዎችን መከወን ይችሉ ነበር” ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፣ ፕሬዚዳንቱ የበጐ አድራጐት ስራዎችን መምራት፣ ማህበራትን ማጠናከር፣ ህዝቡን ለስራ ማደፋፈር፣ እስረኞችንና ህሙማንንን እየጎበኙ መከታተልና የመሳሰሉትን ሊሰሩ ይችሉ ነበር ብለዋል።
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ሙሼ ሰሙ የሰጡት አስተያየትም ተመሳሳይ ነው። “ፕሬዚዳንት ግርማን የማውቃቸው በአገር ምልክትነታቸውና መገለጫነታቸው ብቻ ነው” ያሉት አቶሙሼ ሰሙ፣ “ፕሬዚዳንቱ ህገመንግስቱ ሰፍሮ ከሰጣቸው ስልጣን ባለፈ ሊሰሯቸው የሚችሏቸው ሥራዎች ሞልተዋል፡፡ ለምሳሌ የፕሬዚዳንቱ ቦታ የዲፕሎማቲክ ስራዎችን እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ብዙ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችም አሉ” ብለዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዘለቀ፣ የፕሬዚዳንቱ ቦታ እዚህ ግባ የሚባል ስልጣን በህገመንግስቱ እንዳልተሰጠውና የፖለቲካ ቁምነገር የሌለው ቦታ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ህገመንግስቱ ላይ ባይቀመጥም ፕሬዚዳንቱ ብዙ ሊሰሯቸው የሚገቡ በጎና ማህበራዊ ነገሮች መኖራቸውን ገልፀዋል።
የአገላለፅ ልዩነት ቢኖራቸውም፣ ዶ/ር መስፍን፣ ዶ/ር ያዕቆብ፣ ኦቶ ሙሼ እና አቶ ዘለቀ የሰነዘሯቸው አስተያየቶች፣ ፕሬዚዳንቱ እንግዳ ከመቀበልና ከመሸኘት ያለፈ ስልጣን በህገመንግስት አልተሰጣቸውም፤ ነገር ግን ፖለቲካዊ ያልሆኑ ስራዎችን ማከናወን ይችላሉ የሚል ሃሳብ ያዘሉ ናቸው።
በእርግጥም፣ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ውስጥ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በርካታ በጎ ነገሮችን ማበረታታት ይችላሉ። ነገር ግን፣ በህገመንግስት የተዘረዘረው የፕሬዚዳንቱ ስልጣን፣ እንግዳ መቀበል፣ አመታዊ የፓርላማ ስብሰባ መክፈትና የመሳሰሉት ብቻ አይደለም። በተለይ ዶ/ር ያዕቆብ፣ የሕግ ባለሙያ እንደመሆናቸው፣ እንዲህ አይነቱን ስህተት መስራታቸው ያስገርማል። ለነገሩ፣ ፕሬዚዳንቱን በማሞገስ አስተያየት የሰጡት የፓርላማ አባል ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ እና የፕሬዚዳንቱ ረዳትና የሕግ ባለሙያው አቶ አሰፋ ከሲቶም፣ ተመሳሳይ የተሳሳተ አስተሳሰብ አስተጋብተዋል።
የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ለማናናቅ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ አንድ አንቀፅ አለ። በፓርላማ የፀደቀ አዋጅ፣ ስራ ላይ የሚውለው ፕሬዚዳንቱ በፊርማ ሲያሳልፉት እንደሆነ የሚገልፀው የአገሪቱ ሕገመንግስት፣ ፕሬዚዳንቱ ፈቃደኛ ባይሆኑ እንኳ ህጉ ስራ ላይ እንዳይወል ማድረግ የሚችሉት ለ15 ቀን ያህል ብቻ ነው። በእርግጥ፣ አንድን ህግ ወዲያውኑ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ወይም ለ15 ቀን ማዘግየት፣ ሰፊ ስልጣን አይደለም። እንዲያም ሆኖ፣ በተለይ አጣዳፊና አወዛጋቢ በሆኑ ህጎች ላይ፣ ለምሳሌ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የጦርነት አዋጅ በመሳሰሉ ውሳኔዎች ላይ፣ ለ15 ቀናት አዋጁ ታግዶ እንዲቆይ የማድረግ ስልጣን ቀላል ስልጣን አይደለም።
ፕሬዚዳንቱ፣ በፓርላማ የሚወጡ ህጎችም ሆኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጡ ደንቦች ላይ ተጨማሪ ተፅእኖ የማሳረፍ እድል አላቸው። ህጎችና ደንቦች፣ ከህገመንግስት ጋር የሚጋጩ መሆን አለመሆናቸውን በመመርመር የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ ስልጣን በተሰጠው ለህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እንደሆነ ይታወቃል። 11 አባላትን ባካተተው አጣሪ ጉባኤ ውስጥ፣ የስድስቱ አባላት ሹመት የሚፀድቀው በፕሬዚዳንቱ ይሁንታ ነው። በቀነ ገደብ የታጠረ ስልጣንም አይደለም። በቃ! ፕሬዚዳንቱ ካልተስማሙበት ሹመቱ አይፀድቅም። የአምባሳደሮች ሹመትና የጦር መኮንኖች ማዕረግም፣ ያለ ፕሬዚዳንቱ ይሁንታ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።
ይሄ፣ ቀላል ስልጣን ነው? በጭራሽ አይደለም። ይልቅስ፣ ይሄ የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ስልጣን በአግባቡ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል ከተባለ፣ አዎ አልተደረገም። ለምሳሌ፣ ፕሬዚዳንቱ የተሿሚ አምባሳደሮችንና ከፍተኛ ማዕረግ የሚሰጣቸው የጦር መኮንኖችን ጉዳይ የሚመረምር፣ መረጃ የሚያሰባስብ የባለሙያዎች ቡድን የላቸው።

Read 3331 times