Print this page
Saturday, 12 October 2013 12:32

ከአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(13 votes)

በቅርቡ ያወጡት በፖለቲካ ህይወትዎ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ወደ አማርኛና ኦሮምኛ እየተተረጐመ መሆኑን ቀደም ሲል ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን መጀመሪያውኑ መፅሃፉ ለምን በእንግሊዝኛ ታተመ የሚል ጥያቄ አላቸው ?
በእንግሊዝኛ እንዲታተም ያደረግሁት ለፖለቲካ ብዬ አይደለም፡፡ የምናገረው ውሸት የለም፣ በእንግሊዝኛ መፃፍ ስለሚቀለኝ ነው፡፡ አሜሪካን ሆኜ ነው የጀመርኩት፣ የጨረስኩትም እዛው ነው። በአማርኛ ማሳተም የምችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡
የመጽሐፉ ርዕስ “ህይወቴ - ለኦሮሞ ህዝብ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ያለኝ ራዕይ” የሚል ነው፡ለምን “በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝ ራዕይ” አላሉትም?
ገና ስጽፈው ጥያቄው እንደሚነሳ አውቅ ነበር። ፓርላማ ውስጥ ሆኜ በኦሮምኛ ነበር የምናገረው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ብዙ ህዝብ ነው፡፡ ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ሲሰቃይ ሲረገጥ፣ ሲናቅ ሲዘረፍ እያየሁ ነው ያደግሁት፡፡ በጣም የተበደለ ህዝብ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ የተበደሉ አሉ። ጐንደሬም ተበድሏል። ጐጃሜም ተበድሏል። ሆኖም የተበደሉት ተነጥለው እንደ ህዝብ አይደለም። ኦሮሞ ግን ቁጥሩ ብዙ ነው። ለስሙ ንብረቱም ብዙ ነው። ግን ንብረቱ ተዘረፈ፡፡ ነፃነቱን አጣ፡፡ ብዙ ህዝብ ነፃነት ባይኖረውም ከሁሉ የበለጠ ግን የኦሮሞ ህዝብ ነፃነቱን ተገፏል፡፡ ስለዚህ እኔ ሁልጊዜ እነሱን ነው የማስበው፡፡ የነሱ ችግር ልክ እንደ ቁጥራቸው ቦግ ብሎ ይታየኛል፡፡ በቅድሚያ ስማቸውን የጠራሁት ለዚህ ነው፡፡ ስለሌላው ህዝብ ግን አስባለሁ፡፡
በመፅሃፍዎ ውስጥ አዲስ አበባ መጥተው ትምህርት ቤት ለመግባት መቸገርዎን ገልፀዋል። “ስሜን ሳይቀር ለመቀየር ሞክሬያለሁ”ሲሉም ፅፈዋል፡፡ እስቲ በዝርዝሩን ይንገሩኝ---
የባላገር ልጅ ሁሉ ወደ አዲስ አበባ አይመጣም። ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በብዛት እድል ያገኙት የሸዋ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ከመንዝ፣ ከተጉለት፣ ከመራቤቴ የመጡ ሰዎች ናቸው ያን ዕድል ያገኙት። አዲስ አበባ መምጣት ማለት መሰልጠን ማለት ነው፡፡ ስልጣኔን ማየት፡፡ በዛን ጊዜ ለምሳሌ ከተወለድኩበት መንደር የመጣሁት እኔ ብቻ ነኝ። የኔም በአጋጣሚ ነው። አባቴን ጣሊያን አስሮት ለመጠየቅ ከዘመዶቼ ጋር እመላለስ ነበር፡፡ ያኔ ከተማ አየሁ፡፡ አባቴ በጣሊያን ወደ ማጂ ሲወሰድ፣ ለወንድሙ ልጄን አስተምርልኝ ብሎት ስለነበር፣ አጎቴ ያን ቃል ለመፈፀም ባደረገው ጥረት ነው አዲስ አበባ መምጣት የቻልኩት፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ የገጠመኝ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር በር ላይ አስር ወር ተቀምጠን ትምህርት ቤት ማግኘት አልቻልንም፤ ጠዋት ጠዋት እንሄዳለን። ጉዳያችንን በመስኮት እንነግራለን፤ መልስ የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ረሀብ ያጠቃን ነበር፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በር ላይ ስንጫወት ከብዙ አካባቢዎች ከመጡ ልጆች ጋር እንገናኝ ነበር፡፡ የመጣንበትን ስንጠየቅ ከወለጋ ስንል እና ስማችንን ሲሰሙ ፊታቸው ይለወጣል፡፡ ጓደኛዬን “አንተ ተፈራ ትባላለህ፤ እኔ ደግሞ ከበደ ነኝ” አልኩት፡፡ ችግሩ ግን እኔ “ከበደ” ማለት አልችልም ነበር፡፡ ያኔ “ከበዴ” ነበር የምለው፤ ስለዚህ ስም ለውጠህ ነው ተብዬ ዞር በል ተባልኩ። ያኔ ደግሞ ትምህርት ቤት ማግኘት ብቻ ሳይሆን አዳሪ መሆኑ በጣም ያስፈልግ ነበር፤ ምክንያቱም አዳሪ ትምህርት ቤት ምግብ አለ፡፡
በነገርሽ ላይ አዲስ አበባ ስመጣ ሰው ሆቴል ቤት ተሰብስቦ ሲበላና ሲጠጣ ሳይ ሆቴል ሳይሆን ሠርግ ቤት ነበር የመሰለኝ፡፡ ምክንያቱም እኔ ከመጣሁበት አካባቢ ምግብ አይሸጥም፡፡ ሰው ተሰብስቦ የሚበላው ሠርግ ቤት ነው፡፡
በኦሮሞ ዙሪያ የሚቀለዱ ቀልዶች ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ እንዳለዎትም ጽፈዋል…
ለእኔ የልጅነት ቁስሌን ያስታውሰኛል፡፡ ይህ የስነልቦና ጫና ያሳድራል፡፡ ጥላቻን ይፈጥራል፡፡ እኔ ያን ጥላቻ በትምህርት አሸንፌዋለሁ፤ ማንንም ሰው አልጠላም፡፡ ሁሉም ሰው የአካባቢው ውጤት ነው።
በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በደል ሲገልፁ “ያኔ ስም መለወጥ ይበቃ ነበር፤ አሁን ስም መለወጥ ባያስፈልግም ችግሩ ግን እንዳለ ነው” ብለዋል፡፡ ማስረጃ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
ያኔ ለአማራ የገዢ መደብ ስም መለወጥ ብቻ ይበቃል፡፡ ስም ከለወጥሽ አድልዎ አይደርስብሽም። እንደአንዳቸው ነው የምትታይው፡፡ በችሎታም በእውቀትም በመልክም ምንም አይነት ልዩነት አይደረግም፡፡ በእርግጥ አሁን ባለው የትግራይ ገዢ መደብ፣ ኦሮሞዎች ቦታ አላቸው፡፡ ግን ዝቅ ያሉ፣ ታች የሚገኙ የስልጣን እርከኖች ላይ ብቻ ነው። እውነተኛ ክብርና እኩልነት የለም፡፡ አዝናለሁ፣ ወዳጆችም አሉኝ፤ እነሱም እዚህ ውስጥ ናቸው። እኔ ለኦሮሞ እውነተኛ ክብር አለ ብዬ አላምንም። ለምሳሌ ለኦሮሞ የሚሰጠው የፕሬዚዳንትነት ስልጣን በአገር ጉዳይ ውስጥ ብዙ ሚና ያለው አይደለም፡፡
እርስዎ ከፓርላሜንታዊ እና ከፕሬዚደንሻል የመንግስት አስተዳደር የቱን ይመርጣሉ?
እኔ የተማርኩትም አሜሪካ ስለሆነ ፕሬዚደንሻልን እመርጣለሁ፤ የእንግሊዝ ይሁን የአሜሪካ የሚባለው ጥያቄ የባህል ነው፡፡ እንግሊዞቹ ለአንድ ሺ አመት ንጉስ ወይ ንግስት አላቸው፡፡ በንጉስና በፓርላማ መካከል ጭቅጭቅ ነበር፡፡ የተዋጉበት ጊዜም አለ። አሜሪካን ደግሞ የሚሆናቸውን ራሳቸው በቀጥታ ይመርጣሉ፡፡ የማይሠክር፣ የማይጣላ፣ ጥሩ ስብዕና ያለው እያሉ…ይመርጣሉ፡፡ የአሜሪካና የእንግሊዝ ሥርዓት አንድ አይነት ነው፡፡ ከንግስቲቷ ውጪ እንግሊዞችም እንደ አሜሪካ ናቸው፡፡
የፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን የስልጣን ዘመን እንዴት ይገመግሙታል? አንዳንድ ተቃዋሚዎች “ውጤታማ አልነበሩም” ሲሉ ይተቻሉ…
በግሌ በዚህ ስራ ፕሬዚዳንት ግርማ ችሎታ አላቸው የላቸውም ማለት አይቻልም፡፡ እኔ በቅርበት አውቃቸዋለሁ፡፡ ሰውየው ደህና ናቸው፤ ቅን ሰው ናቸው፡፡ ነገር ግን የእሳቸው እውቀትና አዕምሮአዊ ችሎታ ለዘመኑ አይነት ስራ የሚበቃ አይደለም፡፡
አዲስ የተሾሙት ፕሬዚዳንትስ…?
አውቃቸዋለሁ፡፡ ችግሩ ምን መሰለሽ… ይሄን ስራ የሚቀበል ሰው መቶ በመቶ በራሱ እምነት የሌለው ሰው ነው፡፡ እንዴት ሰው ምንም ላለመስራት ሹመት ይቀበላል? በራስ መተማመን ካለ “ኧረ እኔ ከዚህ የተሻለ ዋጋ ያለኝ ሰው ነኝ፤ ቁጭ ብዬ ወንበር ከማሞቅ ሌላ ስራ እሠራለሁ” በማለት ሃላፊነቱን አይቀበልም፡፡
አባትዎ ዳኛ እንዲሆኑ ይፈልጉ ነበር፡፡ ህግ ተምረው ሲጨርሱ አባትዎን አስታወሱ?
አባቴ ዳኛ እንዲሆን ቢፈልጉም ያኔ በነበረው የትምህርት መስክ ምርጫ ውስጥ ህግ (Law) አልነበረም፡፡ ገንዘብ ሚ/ር እየሰራሁ ነበር ህግ ተምሬ ዲግሪ ያገኘሁት፡፡ የተመረቅሁ ዕለት አባቴን በጣም አስታወስኩት፡፡ ለአባቴ በቀበሌም ይሁን በአዲስ አበባ ትልቅ ስራ ዳኝነት ነው፡፡
በወጣትነትዎ ነው ቤተሰብ የመሰረቱት። ቤተሰብ እና ትምህርትን አጣጥሞ መምራት አልከበድዎትም?
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስገባ አራት ልጆች ነበሩኝ፡፡ አግብቼ ልጅ ስወልድ አስራ ስምንት አመቴ ነበር፡፡ አሁን የመጀመሪያ ልጄ 63 አመቱ ነው፡፡ በሙያው መሀንዲስ ነው፡፡ ልጅ ስለነበርኩ ስለማብላት እንጂ ስለማሳደግ አላውቅም ነበር፡፡ አራቱንም ያሳደግሁት በትግል ነው፤ እየተሯሯጥኩ፡፡
እርስዎ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ እንዳደጉና አዲስ አበባ ያገኟቸው ተማሪዎች ደግሞ ብዙ ልብወለድ የሚያነቡ፤ ሼክስፒርን በወሬ መሃል የሚያጣቅሱ ነበሩ ብለዋል፡፡ እስቲ ስለሱ ያብራሩልኝ----
እኔ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ነው ያደግሁት። ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት አለማዊ መጽሐፍም የጄን ኦስተንን ነው፡፡ ሙዚቃም ከመንፈሳዊ ሙዚቃ እና በአካባቢዬ ከሚዘፈኑ ዘፈኖች ውጪ አላውቅም ነበር፡፡ በኋላ ላይ እኔም ሙዚቃ ማዳመጥ ጀመርኩ። ያሳደጉኝ የሚሲዮን ሰዎች በየሳምንቱ እየመጡ “ድሮ ታነብ የነበረውን መጽሐፍ ማንበብ አታቁም” ይሉኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ከከተማ ልጆች ጋር ሲነፃፀር ባላገር ብሆንም ሰልጠን ብዬ ነበር፡፡ ዶርም ያሉት ልጆች ይዘፍናሉ፤ ይደንሳሉ፡፡ እነሱ የሚያደርጉት ነገር ያምረኝ ጀመር፡፡ አንድ ጓደኛዬ “ህይወት ማንበብ ብቻ ነው እንዴ?” ሲለኝ ሰው የሚያደርገውን ማድረግ ጀመርኩ፡፡ በሚሲዮን አባባል አለማዊነት አጠቃኝ፡፡ በህይወት ዘመኔ ከቤተክርስቲያን የራቅሁት ለአምስት አመት ያህል ነው፤ እሱም ይፀጽተኛል፡፡ ከዛ ውጪ ሁሌ ቤተክርስትያን እሄዳለሁ፡፡ እዛ ያለውን ነገር (ቤተክርስትያን ማለታቸው ነው) አምናለሁ፡፡ ልጆቼ ግን ከየትኛውም የሉበትም፡፡
በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን በደል ደረሰብኝ ቢሉም በዛ ዘመን የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር መሆንዎ ግራ የሚያገባ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እኔ ቡልቻ ተበድሏል አላልኩም፡፡ እኔ እንደ እድል ልዩ ቦታ አግኝቼ ነበር፡፡ የራስና የደጅ አዝማች ልጆች የሚያገኙትን ቦታ ነው ያገኘሁት። ይህ የሆነው በገንዘብ ሚ/ሩ በይልማ ደሬሳ ነው፡፡ እሳቸው ከጃንሆይ ሁለት አማካሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡
አቶ ይልማ ዴሬሳ ለኦሮሞዎች ያደላሉ ይባል ነበር…?
ለኦሮሞዎች ያደላሉ ይባሉ ነበር፡፡ ግን ስህተት ነው፤ የሌላ ተወላጅ ጐበዝ ቢያገኙ እንደሚረዱ አውቃለሁ፡፡ በወገን መከፋፈል የሚፀጽታቸው ሰው ነበሩ፡፡ የአዲስ አበባ ሰው ግን ቀልድ ሲፈበርክባቸው ነበር የሚውለው፡፡ “እሳቸው ያለ ኦሮሞ መቅጠር አይወዱም፤ በሳ የሚያልቅ ስም ያለው ሁሉ ይቀጥሩ ነበር፡፡ አንተ ስምህ ማነው ይሉና… መገርሳ፣ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ባይሳ፣ ነጋሳ ግቡ ይላሉ፤ አንዱ ግራ ገብቶት ካሳ ሲላቸው ግባ አሉት” ተብሎ ይቀለዳል። አሁን እሳቸው በካሳ እና በደመቅሳ መሀል ያለው ልዩነት ይጠፋቸዋል? እንዳልኩሽ ብዙ ይቀለድባቸው ስለነበር ነው፡፡
የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ አገር አልባ (Stateless) ሆንኩ ብለዋል፡፡ ስሜቱ እንዴት ነበር?
በቦታው ሆነሽ ካላየሽው ስሜቱ በቃላት አይገለጽም፤ በውስጡ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ደርግ ስልጣን ላይ እንደወጣ ዋሽንግተን አሜሪካን ኤምባሲ ሄድኩ፡፡ ዲፕሎማትነቱ ቢቀርም ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ፓስፖርቴን አድሱልኝ ስል አይሆንም ተባልኩ፡፡ በዛ ደቂቃ የተሰማኝን ስሜት በቃል ልገልፀው አልችልም፡፡ ያን ጊዜ ስራዬን አጣሁ፡፡ ፓስፖርት የለኝም፤ ከባድ ነበር፡፡
ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በተደረገው የሀምሌ ኮንፈረንስ ላይ ተሳትፈው ነበር። እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ…
እኔ በወቅቱ በታንዛኒያ የተባበሩት መንግስታት አምባሳደር ነበርኩ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር ደረጀ ነበር። እሱ ታመመ፡፡ ምክትሉ ደግሞ አቶ ክፍሌ ወዳጄ ነበሩ። ሁለቱ አይተማመኑም፡፡ መለስ እና ስዬ ማለት ናቸው። ለኮንፈረንሱ ምክትሉ ክፍሌ ተጋበዘ። ሁለቱ ስለማይተማመኑ ደረጀ ደውሎ፤ እባክህ አንተ ሂድ ሲለኝ በደስታ ተቀበልኩት፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለመመለስ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ተቀበለኝ፡፡ እኔ የድሮውን መንግስት (የንጉሱን ማለታቸው ነው) ስለማውቅ፣ ሲቀበሉኝ ነገሮች ወደኋላ መመለሳቸው አሳዘነኝ። በአቀባበልና በመረጃ አሰጣጥ ረገድ አሠራሩ ሁሉ የጥንት (ancient) ሆነብኝ፡፡ ሰኞ ስብሰባው ተከፈተ። ሁለት ልጅ እግር ጐፈሬዎች መጥተው ፊት ለፊት ተቀመጡ፡፡ አቶ መለስ እና ታምራት ናቸው፡፡ ወይ ጉድ! እኛ ያን ሁሉ ዘመን በትምህርት ቤት አጥፍተን፣ እነዚህ ልጆች ምን ሊመሩን ነው ብዬ ተገረምኩ። ነገር ግን አቶ መለስ በተናገረው የመጀመሪያ ቃል ተመሰጥኩ፡፡
ምን ነበር ያሉት?
…ለብዙ ጊዜ የጠበቅነው ስብሰባ እነሆ ዛሬ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ለስብሰባው መሪ እንፈልጋለን፤ ምረጡ አለ፡፡ ያንን ማለቱ ትክክል ነበር፡፡ በኋላ ሰው ሁሉ ዝም ሲል፣ እኔ እሱ እንዲመራ ጠቆምኩ። የምትደግፉ ሲባል ሁሉም ደገፈ፡፡ በኋላ ላይ አንተ ነህ መሪ ያደረግኸው ያሉ ቢኖሩም ያኔ እሱ አገሪቱን ከአንድ ወር በላይ ሲመራ ቆይቷል፡፡ እኔ ግን ለዛ ስብሰባ ነበር የመረጥኩት፡፡ በወቅቱ ለአገር መሪነት የሚበቃ እጩ በአዳራሹ አልነበረም፡፡ ምናልባት እዚያ ከተገኙት ውስጥ ፕሮፌሰር አስራት ወይም ሱልጣን አሊሚራህ ለመሪነት ይታሰቡ ይሆናል፤ ከዕድሜም ከአንጋፋነትም አንፃር ማለቴ ነው፡፡ መለስን ግን በፍፁም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትም ሆነ ጠቅላይ ሚ/ር ይሆናል ብዬ አላሰብኩም፡፡
ፌደራሊዝም ላይ ያለዎት አቋም ምንድን ነው?
በፖለቲካ ፍልስፍና ከመጣሽ፣ ለኢትዮጵያ ከፌደራሊዝም ውጪ መፍትሔ የለም፡፡ እኛ እንግሊዝን መሆን አንችልም፤ ሲስተሙን ብንወደውም እንደአሜሪካንም መሆን አንችልም። ምናልባት ያን ጊዜ ሰው እንዲህ ቢባል አይደነግጥም?፡፡ የትግሬ ንጉስ፣ የኦሮሞ ንጉስ፣ የአማራ ንጉስ ቢሉ ኖሮ--መደንገጣችን አይቀርም።
መጽሐፍዎ ላይ አዲስ አበባን አይጠቅሱም፤ ፊንፊኔ ነው የሚሉት…
እኔ ኦሮሞ ከኢትዮጵያ እንዲገነጠል አልፈልግም፤ የኢትዮጵያ አካል ሆኖ እንዲኖር እፈልጋለሁ፤ ግን እንደብዛትና እንደ ሀብቱ ክብር ማግኘት አለበት፤ ክብር ማለት ጉቦ አይደለም። በዲሞክራሲ፣ በድምጽ ብዛት፣ በምርጫ --- የጠቅላይ ሚ/ር ቦታ ለኦሮሞ መሆን አለበት፡፡ ፕሬዚዳንታዊ አሰራር የምንከተል ከሆነም ኦሮሞ ፕሬዚዳንት መሆን አለበት፡፡ ሁልጊዜ እንዲሆን አልደግፍም፡፡ በዲሞክራሲ የሄድን እንደሆነ ግን ሁልጊዜ ይሆናል፡፡ እኔ ግን እሱን አልደግፍም። በየሁለትና ሶስት ዓመቱ በምርጫ የሚለወጥ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ያለንበት ግን ከዚህ በጣም ሩቅ ነው፡፡ አዲስ አበባን ፊንፊኔ የምለው የኦሮሞ ቋንቋው፣ ባህሉ መመለስ ስላለበት ነው። ደግሞ ይመለሳል አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ህዝብ ብዛት አለዋ!!

Read 4265 times