Saturday, 12 October 2013 12:36

የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ብሔራዊ ቡድናችን እና ሁለቱ ወይዛዝርት

Written by  ቴዲ
Rate this item
(3 votes)

ልጅ እያለሁ ከአባቴ የመጽሐፍ ስብስቦች ውስጥ፣ “one step forward two steps back ward” የሚል ርዕስ የያዘ አንድ መጽሐፍ ትዝ ይለኛል፡፡ (አንድ እርምጃ ወደፊት እና ሁለት እርምጃ ወደኋላ እንደማለት ነው) ከልጅነቴ ጀምሮ የሚገርመኝ ርዕስ ነው፡፡
ከአእምሮዬ አለመጥፋቱ አይገርምም? አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ እና ሁለት እርምጃ ወደኋላ መመለስ በአገራችን ውስጥ በጣም የተለመደ የሕይወት ዘይቤ ነው፡፡ መቼስ 2005 ዓ.ም ለእግር ኳሳችን ያማረ አንድ እርምጃ የተራመድንበት ዓመት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ (ቢያንስ ማክሰኞ እለት ከሰአት በኋላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አንድ ፕሮግራም እስከማይ ድረስ)
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ማክሰኞ እለት ስራዬን ጨርሼ በጊዜ ነበር ቤቴ የገባሁት፡፡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንደኛው ተከፍቶ በቤት ያሉ ሰዎች እየተከታተሉ ደረስኩ፡፡ በፕሮግራሙም የብሔራዊ ቡደን ተጫዋቾቻችን (ዋሊያዎቹ) በየተራ ይጠየቁ ነበር፡፡ ዝግጅቱም በሚሊኒየም አዳራሽ ነው፡፡ ታዲያ ተጫዋቾቹ በየተራ ሲጠየቁ፤ እጅግ የሚያማምሩ ሁለት ሴቶች፤ አንዷ ከተጫዋቹ በቀኝ፣ ሌላኛዋ ደግሞ በግራ ይቆማሉ፡፡ ኮሚክ ነገር ሆነብኝ፤ ግራ ገባኝ፡፡ የሚጠየቁት ኳስ ተጫዋቾቹ ናቸው፡፡ ታዲያ ከተጫዋቾቹ ጋ እየሄዱ የሚቆሙትና የሚለጠፉት ሁለቱ ቆነጃጅት ምንድን ናቸው? መልእክቱስ? በተለይ ኳስ ተጫዋቹን ለሚያፈቅሩት ታዳጊዎች መልእክቱ ምንድን ነው?
ሴት ተጫዋቾች ሲሸለሙ ወይም በቲቪ ሲቀርቡ፣ ግራና ቀኝ ምን ልንለጥፍባቸው እንችላለን ብዬ ለማሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ ሁለት ቆነጃጅትን ወይስ ሁለት ጐረምሶችን?
ለዚህ ነው እንግዲህ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወይም ስድስት እርምጃ ወደኋላ ማለቴ፡፡ ምንም እንኳን በኳሱ አንድ እርምጃ ወደፊት ብንሄድም፣ በስነምግባር እና በጾታዊ እኩልነት ዙሪያ ብዙ እርምጃ ወደ ኋላ ሊወስደን ሲታገል ማክሰኞ እለት በኢቴቪ አይቻለሁ፡፡ እናም እስቲ የዚህ ዝግጅት አስተባባሪ ከቻለ፣ የሴቶቹን ሚና በዚሁ ጋዜጣ ቢያስረዳን ወይም የጋዜጣው አዘጋጆች ጠይቃችሁ ብትነግሩን፡፡ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የኮረጁት ነገር ምን ማለት እንደሆነ ብንነጋገርበት ይበጃል፡፡

Read 2581 times