Saturday, 12 October 2013 13:05

የሴትነት ቀዩ መስመር!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

             የአመታት ጥረቷና ልፋቷ ውጤት የሆነው ስኬቷ የብዙዎች ምኞትና ጉጉት ቢሆንም እሷ ይኖረኛል ወይም አገኘዋለሁ ብላ ያሰበችውን ያህል ደስታ ልታገኝበት አልቻለችም፡፡ ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ስለነበረች፣ በቤተሰቦቿም ሆነ በቅርብ በሚያውቋት ሰዎች ዘንድ የት ትደርስ ይሆን? የተባለላት ልጅ ነበረች፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በማኔጅመንት ካገኘች በኋላ ለሁለት ዓመታት በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ሰርታለች፡፡ ትምህርቷን ለማሻሻልና የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት ቀጥላ፣ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን ለመማር ተመልሳ ዩንቨርስቲ ገባች። ምኞቷና ህልሟን ከዳር ሳታደርስ ላለመቅረት ከፍተኛ ጥረት ታደርግ ነበር፡፡ ለዚህ ህልሟ እንቅፋት ይሆኑኛል ካለቻቸው ነገሮች ሁሉ ራሷን ጠብቃ ትምህርቷን ቀጠለች፡፡ በዚህ ውብ የወጣትነት ዕድሜዋ የሚቀርብላትን የፍቅርና የጓደኝነት ጥያቄዎች ሁሉ እየገፋች፣ የሁለተኛ ድግሪ ትምህርቷን በጥሩ ውጤት አጠናቃ ተመረቀች፡፡ ራሷን ቀና ማድረግ በምትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷ እጅግ ቢያስደስታትም የህልሟ መቋጫ እንዳልሆነ ግን እርግጠኛ ነበረች፡፡

በአንድ የእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ በሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በጥሩ ደመወዝ በሃላፊነት ደረጃ ተቀጥራ መስራት ስትጀምርም ትምህርቷን የመቀጠሉ ሃሳብ በውስጧ እንዳለ ነበር፡፡
ለስልጠናዎችና ለልምድ ልውውጦች ወደ ተለያዩ አገራት የምትሄድበት ዕድልም በተደጋጋሚ አገኘች፡፡ ተፈላጊነቷ እየጨመረ፣ የትምህርትና የስራ ልምዷ እየዳበረ መጣ፡፡ ቤተሰቦቿ በስኬቷ ቢረኩም ትዳር ይዛና ልጅ ወልዳ እንድታስማቸው ይፈልጉ ነበርና አግቢ እያሉ መጨቅጨቃቸው አልቀረም፡፡

“ምን አስቸኮለኝ? በባል እጅ ከገባሁ፤ ልጆች ከወለድኩ በኋላ እኮ እንደልቤ መማር እና መስራት አልችልም” ትላቸዋለች፤ እናት አባቷን። ታናናሽ እህቶቿ ትዳር እየያዙ ልጅ ሲወልዱ የእነሱን ችኮላ እንጂ የእሷን መዘግየት ፈፅማም አስባው አታውቅም፡፡ እድሜዋ በ30ዎቹ መጨረሻ ላይ ሲደርስ ግን ነገሩ እያሳሰባት መጣ፡፡ በህይወቷ ውስጥ እጅግ የዘነጋችውና ችላ ያለችው አንድ ጉዳይ እንዳለ ይሰማት ጀመር። የዕድሜዋ መግፋት ልጅ መውለድ እንዳትችል ሊያደርጋት ወይንም እንቅፋት ሊፈጥርባት እንደሚችል አንድ የቅርብ ጓደኛዋ ስትነግራት የበለጠ ሃሳብ ገባት፡፡ በስጋት ተወጠረች፡፡
ለጓደኝነት በተደጋጋሚ እየጠየቋት ፊት ከነሳቻቸውና ደጅ ጥናታቸውን ካላቋረጡት አንዱን መርጣ ለመቅረብ ወሰነች በተግባርም አደረገችው። ለመጠናናት የምታጠፋው ብዙ ጊዜ እንዲኖር አልፈለገችም፡፡ በአነስተኛ ዝግጅት ተጠቃለው ትዳር መሰረቱ፡፡ የትዳር ጊዜያቸው እድሜው እየጨመረ ሄደ፡፡ አንድ…ሁለት…ሶስት አመታት እንደዘበት አለፉ፡፡ አሁን ራሄል ግራ ገባት፡፡
ባሏ ሳያውቅ የተለያዩ የማህፀን ሀኪሞችን ጎበኘች፡፡ ሁሉም ጤናማ መሆኗንና ከወሊድ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር እንደሌለባት ነግረው አሰናበቷት፡፡ ባሏን ጠረጠረችው፡፡

ምናልባት መሃን ይሆን እንዴ? ብላ አሰበች፡፡ ስጋቷን ደብቃ መቆየቱ ሌላ ችግር መፍጠር መሆኑን አምና እንመርመር ስትል ጠየቀችው፡፡ ባለቤቷም እንደሷው ችግሩ አሳስቦት ኖሮ፣ ጥያቄዋን የተቀበለው በደስታ ነው፡፡ በቤተል ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ክፍል ምርመራ አድርገው፣ ሁለቱም መውለድ እንደሚችሉ ተነገራቸው፡፡
ዶክተሩ ለችግራቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚለውን ጉዳይ ግን አልደበቃቸውም፡፡ አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው የራሄል ዕድሜ ምናልባትም ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አረዳቸው፡፡ የአርባ ሁለተኛ ዓመት የልደት ሻማዋን ከወራት በፊት የለኮሰችው ራሄል፤ የሰማችውን መረጃ ማመን አቃታት፡፡ “እንዴ! ሴት ልጅ የምታርጠው ከ50ኛ ዓመቷ በኋላ አይደለም እንዴ?” ጥያቄዋን ለዶክተሩ አቀረበች፡፡
ህክምና ሙያ ውስጥ አመታትን ያስቆጠረው ዶክተር፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ ሴቶች በ30 ዎቹ ዕድሜያቸው ላይ መውለድ ማቆማቸው በስፋት እየታየ መሆኑን ለጥንዶቹ ነገራቸው፡፡ ሁኔታው ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ሆነባት፡፡ በአመታት ልፋትና እልህ አስጨራሽ ጥረት ያገኘችው ስኬት ሁሉ ከንቱ ሆነባት፡፡ ባዶነት ተሰማት፡፡ ስራ፣ ትምህርት፣ እድገት እያለች ያሳለፈችው ዕድሜዋና ጊዜዋ አንገበገባት፡፡ ግን ሁሉም ነገር “ጅብ ከሄደ…” ሆነና ምንም ማድረግ ሳትችል ቀረች፡፡ ሁኔታው የራሄልን ስሜትና ሞራል እጅግ ከመጉዳቱም በላይ ትዳሯን እየነቀነቀ ሊያፈርሰው ትግል ያዘ፡፡ “የቤት ምሰሶው ልጅ….” እንዲሉ ሆነና፡፡
ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ሩጫ ሴቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው ለታላቅ ስኬት መብቃታቸው ዛሬ ዛሬ የተለመደ ሆኗል። ቀደም ባሉት ዓመታት ለወንዶች ብቻ የተፈጠሩ በሚመስሉ የስራ መስኮች ውስጥ ሴቶች ገብተው የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡ ሂደቱ ግን ሴቶች ትዳር ይዘው ቤተሰብ የሚመሰርቱበትን ጊዜ እያራዘመው ነው፡፡ በአብዛኛው በትምህርት እና በተሰማሩበት ስራ ስኬታማ የሆኑ ሴቶች፤ ስለትዳርና ልጅ ስለመውለድ የሚያስቡት በ30ዎቹ ማጠናቀቂያና በአርባዎቹ መጀመሪያ ዕድሜያቸው ላይ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ልጅ የመውለድ እድላቸውን እያጠበበው መጥቷል፡፡
ሰሞኑን በአገረ አሜሪካ የሚኖሩ የዘርፉ ምሁራን ያደረጉት ጥናት እንዳመለከተው፤ ሴቶች ልጅ መውለድ የሚያቆሙበት ዕድሜ (menopause period) እያሽቆለቆለ ሄዶ 35ኛ ዓመት ዕድሜ ላይ እየደረሰ ነው፡፡
አንዲት በ35 ዓመት ዕድሜዋ ላይ የምትገኝ ሴት ልጅ የመውለድ ዕድሏ በአንድ በሀያ አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከምትገኝ ሴት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ነው፡፡ የሴቲቱ ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣና ወደ አርባዎቹ ውስጥ ሲጠጋ ልጅ የማግኘት ዕድሏ እያነሰ ሄዶ 25% ላይ እንደሚደርስም ይኸው ጥናት አመልክቷል፡፡
ከ35 ዓመት ዕድሜ በኋላ የሚከሰት እርግዝና ለተለያዩ ችግሮች ይዳርጋል ያለው ጥናቱ ከእነዚህ መካከል ውርጃ ዋነኛው እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው የማርገዝ ዕድል ካገኙ 10 ሴቶች መሀል አንዷ ዕንሱን በውርጃ ሳቢያ ማጣቷን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
ቀድሞ አንዲት ሴት ልጅ በአብዛኛው መውለድ የምታቆመው (menopause period) ከ49-55 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ እንደነበር ያመለከተው ጥናቱ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከ34-38 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ እየሆነ መምጣቱን ጠቁሟል፡፡
በዕድሜ እየገፉ መሄድ በሴትነት ተፈጥሯዊ ባህሪይ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የጠቆመው ጥናቱ፤ ከ35 ዓመት ዕድሜ በኋላ በሚከሰት እርግዝና የሚወለዱ ልጆች የአዕምሮ ዘገምተኞች የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ አርግዘው የሚወልዱ ሴቶች ምጥ እንደሚጠናባቸውና ቀኑ ያልደረሰ ልጅ ሊወልዱ እንደሚችሉም ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ዕድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር በልብ ድካም፣ በደም ግፊትና በስኳር በሽታዎች የመያዝ ዕድልም እየሰፋ እንደሚሄድ እሙን ነው ያለው ጥናቱ፤ ይህ ሁኔታ በሴቶች ላይ ከፍ ብሎ እንደሚታይ ጠቁሟል።

እነዚህ በሽታዎች ለእርግዝናና ለወሊድ እጅግ አደገኛ ከሚባሉት ዋነኞቹ እንደሆኑ ጥናቱ ገልጿል፡፡ በዚህ ሳቢያም ከ35 ዓመት ዕድሜ በኋላ የሚከሰት እርግዝና አደጋው ከፍ ያለ ነው ብሏል፡፡
የማህፀንና የፅንስ ሐኪሙ ዶክተር አሳየኸኝ ታምሩ እንደሚገልፁትም፤ ዕድሜ ከገፋ በኋላ የሚከሰት እርግዝና ለእናቲቱም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት እጅግ አደገኛ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በሰላሳዎቹ እና አርባዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች አካላቸው በሃያዎቹ ውስጥ እንዳሉ ሴቶች እርግዝናን የመቋቋምና ወሊድን የማስተናገድ አቅም አይኖረውም፡፡ በአጠቃላይ ከ35ኛ ዓመት ዕድሜ በኋላ የሚከሰት እርግዝና መጥፎ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡ ስለዚህም ሴቶች ተፈጥሮ ባደላቸው ፀጋ ተጠቅመው ወልደው መሳም የሚችሉበትን ዕድሜ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የሴቶች የወሊድ ማቆሚያ እድሜ (menopause period) ቀደም ባሉት ዓመታት ከነበረው መጠን እየቀነሰ የመጣበትን ምክንያት አስመልክተው ዶክተር አሳየኸኝ ሲናገሩ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሴቶች የወር አበባ የሚያዩበት ዕድሜ ከ14-15ኛ ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ ሲሆን የወር አበባቸው የሚቆምበት ዕድሜ ደግሞ ከ49-55 ዓመት ዕድሜ ድረስ ነበር፡፡ ሁኔታው በጊዜ ሂደት ለውጥ አምጥቶ አሁን ባለንበት ዘመን ሴቶች በዘጠኝና አስር ዓመት ዕድሜያቸው የወር አበባቸውን ማየት እንደሚጀምሩና ከ35-40 ዓመት ዕድሜያቸውም የወር አበባቸውን ማየት ማቆማቸው እየተለመደ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አኗኗሯችን፣ አመጋገባችንና ለተለያዩ የእርግዝና መከላከያነት የሚወሰዱ መድሃኒቶች እንደሆኑ ዶክተሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ እንግዲህ ጐበዝ “ዕድሜና ጅረት ሲፈስ አይታወቅም” እንዲሉ… ቀዩ መስመር ላይ ከመድረሳችን በፊት ሁሉንም ነገር በጊዜ ብናስብበት ይሻላል፡፡

Read 6080 times