Saturday, 12 October 2013 13:28

ግዴለሹ የአሜሪካ ኮንግረስ!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

                የዲሞክራሲ ስርአትን በሚከተሉ ሀገራት ፓርላማ ከፍተኛው የህግ አውጭ አካል ነው፡፡ ፓርላማው በሚያወጣቸው ህግና ደንቦች መሠረት ሀገርና ህዝብ ይመራሉ፡፡ የፓርላማ አባላትም፣ በፓርላማው ውስጥ ተቀምጠው ህግ የሚያወጡበትን ወንበር የሚያገኙት በህዝብ ምርጫ መሠረት በመሆኑ፣ ውክልናቸው ወይም ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡
ህዝቡም፤ በነፃ ምርጫው አማካኝነት ወደ ፓርላማው የሚልካቸው ተመራጮች፣ ፓርላማው በሚያወጣቸው ህግና ደንቦች እሱን መስለው፣ እሱን ወክለው፣ ለሱ ጥቅም መጠበቅ እንዲከራከሩለት ወይም እንዲሰሩለት ማድረግ እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም፡፡
ካለፈው ሁለት ሳምንት ጀምሮ፤ የመገናኛ አውታሮችን ብቻ ሳይሆን የድፍን አለሙን ቀልብ ስቦ የሚገኝ አንድ ክስተት አለ፡፡ ይኸውም፤ የአሜሪካ የመንግስት መስሪያ ቤቶች (ከመላከያውና ደህንነት ክፍሉ በስተቀር) መዘጋት ጉዳይ ነው፡፡
ይህ የሆነው እንደሳበ የሚገኝ አንድ ክስተት የአሜሪካ የመንግስት መስሪያ ቤቶች (ከመከላከያውና ደህንነት ክፍሉ በስተቀር) መዘጋት ጉዳይ ነው፡፡
ጉዳዩ ተአምር በፈጠሩ ወይም በሸባሪዎች ጥቃት አሊያም በአስማት የተከሰተ ሳይሆን፤ የመንግስት በጀት እስካሁን ሊለቀቅ ባለመቻሉ ብቻ ነው፡፡ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ወይም እኔ በምፈልገው አይነት ቀመር ካልተዘጋጀ በቀር … ሁሉም ነገር እስከወዲያኛው ጥንቅር ብሎ ይከረቸማታል እንጂ እኔ በጀቱን አጽድቄ አለቅም” ያለው ደግሞ፤ ፕሬዚዳንቱ ባራክ ኦባማ፣ ወይም የገንዘብ ምኒስትሩ አሊያም የፌደራል ባንኩ ገዢ አይደሉም፡፡ ይህን ያደረገው በህገንግስቱ አማካኝነት የሀገሪቱን አመታዊ በጀት መርምሮ የማጽደቅ ስልጣን የተሰጠው የአሜሪካ ኮንግረስ ነው፡፡
ይህን የመሰለው የአሜሪካ ኮንግረስ ድርጊት፤ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ አሜካውያንን ስራ ፈት አድርጓቸዋል፡፡ ላልታሰበ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግርም ዳርጓቸዋል፡፡
ይህም ብቻም አይደለም፡፡ በስንት ፍዳ ተገንዞቦት የነበረውን የኢኮኖሚ አቡጀዲ ቀድዶ፣ አንገቱን ቀና ማድረግ የጀመረውን የአሜካንን ድውይ ኢኮኖሚ እንደገና ወደ ግንዝ አልጋው ሳይሆን ወደ ቀብር ሳጥኑ ሊከተው ይችላል የሚል ስጋት እንደ አዲስ ቀስቅሷል፡፡ ማርያም ማርያም እንዲባልለት አድርጐታል፡፡
ይህ ሁሉ ክስተት ግን ለአሜሪካ ኮንግረስ ግድ አልሰጠውም፡፡ ለስራ አጥነት የተዳረጉት አሜካውያንን እግዚኦታም ሆነ የፕሬዚዳንት ኦባማን ውትወታ ጉዳዬ ብሎ ከቁም ነገር አልጣፈውም፡፡
እንግዲህ፤ የአሜሪካ መንግስት ነገር እንዲህ ከሆነ መቸም … ማንም ሰው ቢሆን ሊጠይቀው የሚገባ አንድ ጥያቄ የሚከተለው ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ የአሜካንን ኮንግረስ (ለወከለው ህዝብና ለሀገሪቱ) እስከዚህ ድረስ ግዴለሽ ያደረገው ከቶ ምን አይነት አውሊያ ነው?” የሚለው ጥያቄ ነው መልስ የሚያሻው፡፡
የሆኖ ሆኖ፤ ከስራ ውጪ ያደረጋቸው አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን ለሚያሰሙት የችግር ጩኸት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ማለቱ ብዙም አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ የአሜሪካንን ኮንግረስ ጓዳ - ጐድጓዳ ጠጋ ብሎ መመርመር የቻለ) ለዚህ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ማስረጃዎችን ማግኘት ይችላል፡፡
ለምሳሌ፤ አሁን ካሉት አምስት መቶ ሠላሳ አምስት የኮንግረስ አባላት ውስጥ፤ አስራ ሠባቱ፤ እያንዳንዳቸው በአማካይ ሀምሳ ሚሊዮን ዶላር ሀብት ባለቤት ናቸው፡፡ አሁን ካሉት የኮንግረስ አባላት መካከል ግንባር ቀደም ቱጃር የሆኑት፤ የቴክሳስ ግዛት የአስረኛው ወረዳ ተመራጭ የሆኑት፣ ሪፐብሊካኑ ማይክል ማካውል ናቸው፡፡ እኒህ የኮንግረስ አባል፤ በባንክ ያላቸው ተቀማጭ ሀብት ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ እኒህን የኮንግረስ አባል በሀብት ብዛት በቅርብ ርቀት የሚከተሏቸው የአራት መቶ ሰማኒያ ሚሊዮን ዶላር ባለቤት የሆኑት የካሊፎርኒያው ተመራጭ ዳረል ኢሳ ናቸው፡፡
የአስራት ሠባቱ ባለፀጋ የኮንግረስ አባላት ሀብት አንድ ላይ ሲሠላ፤ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ መቼም … ሁላችሁም እንደምታውቁት፤ የላይኛው የአሜሪካ ምክር ቤት ወይም “ሴኔት” የአባላቱ ቁጥር (ሳፊ) … አንድ መቶ ነው፡፡ ከነዚህ አንድ መቶ የአሜሪካ ሴናተሮች ውስጥ ታዲያ ስልሳ አንድ የሚሆኑት፤ የገንዘብ ካዝናቸው ባሻው ቀን ተከፍቶ ቢታይ ቢያንስ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ከውስጡ ይገኛል፡፡
ከአሜሪካ ሴናተሮች ውስጥ፤ የቁጥር አንድ ሀብታምነቱን ደረጃ ሁለት መቶ ሀያ ስምንት ሚሊዮን ዶላር በባለቤትነት በማስመዝገብ የሚመሩት የቨርጂኒያው ሴናተር (ዲሞክራቱ) ማርክ ዋርነር ናቸው፡፡ በሁለተኝነት የሚከተሏቸው፤ የምዕራብ ቨርጂኒያው ሴናተር ዲሞክራቱ ጄይ ሮክፌለር ናቸው፡፡ ሴናተር ጄይ ሮክፌለር የስታንዳርድ ኦይል ኩባንያ መስራች ሲሆኑ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ቢሊየነር የነበሩት የጆን ፎክፌለር የልጅ ልጅ ናቸው፡፡
የአሜሪካንን ኮንግረስ አብላጫውን መቀመጫ የያዙት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ ልክ የአሜሪካ የሴኔት ምክር ቤት አብላጫው መቀመጫ የተያዘው በዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት እንደሆነው …
እነዚህን የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የሆኑ ሴናተሮችን የሚመሩት ደግሞ፤ የኔቫዳ ግዛቱ ሴናተር ሀሪ ሪድ ናቸው፡፡ የአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ጌታ ናቸው፡፡ ሴናተር ሀሪ ሪድ ከሀብታም ሴናተሮች ተራ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ሰላሳኛው ተራ ቁጥር ላይ ነው፡፡
የሚገርመው ደግሞ፤ በፌደራል መንግስቱ ሥራ ማቆም ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያለ ደሞዝ ባዶ እጃቸውን ሲይጨበጭቡ፣ ሚሊዬነሮቹ የኮንግረስ አባላት ግን ደሞዝ ይከፈላቸዋል፡፡ ግዴለሽ ቢሆኑ ታዲያ ምን ይገርማል?!

 

 

Read 2661 times