Saturday, 19 October 2013 11:32

ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው አረብ አገር የጠፉባቸው ቤተሰቦች ኤጀንሲዎችንና መንግስትን አማረሩ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

“ኤጀንሲዎችና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እልባት ሊሰጡን አልቻሉም”
“የቤተሰቦቻችንን አድራሻ እና ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ተቸግረናል”

በተለያዩ ኤጀንሲዎች በኩል በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ህጋዊ ውል ፈፅመው ወደተለያዩ የአረብ አገራት ለስራ የሄዱ እህቶቻችን፣ ልጆቻችን እና ሚስቶቻችን በችግር ላይ ሆነው አቤት የምንልበት አጥተናል ሲሉ የተጓዥ ቤተሰቦች አማረሩ፡፡ ኤጀንሲዎቹን ስንጠይቅ ምላሽ አይሰጡም፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይም በቀጠሮ እያመላለስን ጉዳያችን እልባት ሳያገኝ ለመኝታ፣ ለቀለብ፣ ለጊዜና ለጉልበት ብክነት ተዳርገናል ይላሉ፤ የተጓዥ ቤተሰቦች፡፡
ከአምቦ ከተማ የ5 ወር ህፃን ልጇን አዝላ የእህቷን ጉዳይ እልባት ለማግኘት የምትመላለሰው ፋጤ ኑሬ ራህመት ኑሪ ሞሳ እህቷ “ይጠቅለን” በተባለው ኤጀንሲ በኩል ወደ ሳውዲ ሄዳ ጉልበቷ ያለ ደሞዝ እየተበዘበዘ እንደሆነ ደውላ እንደነገረቻች ገልፃለች፡፡ “ህፃን ልጄን ይዤ አንዴ ወደ ኤጀንሲው፣ አንዴ ወደ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ስመላለስ ብቆይም ምላሽ የሚሰጠኝ አጥቻለሁ” በማለት አማራለች፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ የተባለው ግለሰብ በበኩሉ፤ ከጋምቤላ ክልል መዠንገር ዞን እንደመጣ ገልፆ፣ እህቱ ጨረቃ ታደሰ ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሄደች ገና ሶስት ወር ቢሆናትም በሁለተኛው ወሯ ደውላ “ድረሱልኝ ከሞት አድኑኝ” የሚል ቃል ተናግራ ስልኩን መዝጋቷን ተናግሯል፡፡ “በራሴ ጥረት ደውዬ አገኘኋት፤ ወንድሜ ከሞት አድነኝ ሶስት ቦታ እያሰሩኝ በጣጥሰው ሊገድሉኝ ነው፡፡ ወደ ኤጀንሲ እሄዳለሁ ስል ጩቤ አውጥታ እቆራርጥሻለሁ ትለኛለች መሞቴ ነው” ብላ በጭንቀት ላይ ነን” በማለት ተናግሯል፡፡ አልጀዚር በተባለው ኤጀንሲ በኩል እንደሄደች የሚናገረው አቶ ቴዎድሮስ ኤጀንሲው ቦታ ይቀየርላታል ቢልም እስካሁን አለመየቀሯንና በስቃይ ውስጥ መሆኗን ኤጀንሲውም ሆነ የመንግስት መ/ቤት የሆነው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጉዳዩን ችላ እንዳሉበት ተናግሯል፡፡
ከትግራይ ክክል አዲግራት የመጡት አቶ መሰለ መሀሪ የ70 አመት አዛውንት ሲሆኑ ልጃቸው ፊዮሪ ሲሆኑ ልጃቸው ፊዮሪ መሰለ ቦሌ ሩዋንዳ በሚገኘው ናይል ኤጀንሲ በኩል ሪያድ መሄዷን ጠቁመው በሄደች በ4 ወሯ ደውላ ከዚያ በኋላ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች፣ ትኑር ትሙት የሚያውቁት እንደሌለ ጠቁመው ላለፉት 20 ወራት የልጃቸውን ሁኔታ ማወቅ እንዳልቻሉ በእንባ ገልፀዋል፡፡ “ለረጅም ጊዜ ወታደር ቤት ነበርኩኝ አካል ጉዳተኛም ነኝ ሰባት ልጆቼንና ባለቤቴን የማስተዳድረው በጡረታ ደሞዝ ነው” ያሉት አቶ መሰለ ልጃቸው ቤተሰቧን ለመርዳት ብላ ሄዳ ትሙት ትኑር አለማወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ “ናይል ኤጀንሲ ለበርካታ ጊዜ ከትግራይ ስደውል የተለያየ ምክንያት ሲሰጡኝ ቆይተው በመጨረሻም ሪያድ ካለው ኤጀንሲ ጋር ያለን ግንኙነት ስለተቋረጠ ለመገናኘት ተቸግረናል የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል” ሲሉ አማረዋል፡፡ ኤጀንሲው አክሎም ሪያድ ያለውን ኤጀንሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ክስ መስርተን እየተከራከርን ነው የሚል ምላሸ እንደሰጣቸውና በመጨረሻም ከትግራይ መጥተው ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አቤት ብለው ምላሽ እስካሁን አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አቶ ተሰማ ጉታ የተባለውና ከሰበታ ከተማ እንደመጣ የተናገረው ሌላው ባለ ጉዳይ ባለቤቱ ሞሚና አብደላ አራት ኪሎ በሚገኘው ተፈራ ኤጀንሲ በኩል ነሀሴ 2003 ዓ.ም ሳውዲ መሄዷንና በሄደች በዘጠኝ ወሯ እዛው በሚገኘው ቢሮ ደውላ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከቤት አውጥተው ጥለውኛል በማለቷ ተጨንቆ እንደነበር ገልፆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚስቱን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ ወደ ተፈራ ኤጀንሲና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሲመላለስ ቢቆይም መፍትሄ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡ “አንድ ቀን ደውላ ሁለት የሌላ አገር ዜጐች አብረውኝ ይሰሩ ነበር ምን እንዳጠፉ ባላውቅም ታስረው የሶስት ሰው ስራ ተከምሮብኛል ብላ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም ደውላ ነበር” ያለው አቶ ተሰማ የ10 ወር ደሞዝ ሳትቀበል ያንንሁሉ መከራ ስትቀበል ከርማ በመጨረሻም ለአሰሪዋ ስንደውል “ልጆች ት/ቤት ልታደርስ ወጥታ በዚያው ጠፍታለች” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውንና በጭንቀት ላይ መሆናቸውን አቶ ተሰማ ተናግሯል፡፡
ከምስራቅ ጐጃም የመጣውና የእህቱን መጥፋት ለኤጀንሲውና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አቤት ሲል ለአንድ አመት የቆየው አቶ ሱሌይማን ጋሹ ኤጀንሲና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሲመላለስ “ዛሬም አለህ እንዴ?” የሚል ምላሽ እንደሚያገኝ በምሬት ገልጿል፡፡ አሊማ ጋሻው የተባለችው የ29 አመት እህቱ ሰኔ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ ሳውዲ እንደሄደችና በሶስተኛው ወር ደውላ እስር ቤት መግባቷን እንደነገረችው ገልጿል፡፡ “ለምን እንደታሰረች ኤጀንሲውን ስጠይቅ አሰሪዋ ሪያድ ሄዷል ስራ ትገባለች እያለኝ ፉአድ ኤጀንሲ ሲያታልለኝ ቆይቷል” ያለው አቶ ሱሌይማን መጀመሪያም ደላላ 13 ሺህ ብር ወስዶባታል አሁን የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች አላውቅም በማለት ተናግሯል፡፡ “በወቅቱ ዶ/ር ዘሪሁን የተባሉ ባለስልጣን ጋር አቤት ብዬ ነበር” ያለው አቶ ሱሌይማን ዶ/ር ዘሪሁን የኤጀንሲውን ባለቤት አስደውሎ ጠርቶ ስለ ጉዳዩ ሲያነጋግረው በጥሩ ሁኔታ ስራ ላይ እንደምትገኝ ነገረው ሲል ገልጿል፡፡ “እህቴን ለመላክ የሚያስፈልገውን ብር ከአማራ ብድርና ቁጠባ ወስደን ነበር ብድሩን ክፈል እያሉ ሲያስጨንቁኝ ወደ ኤጀንሲው መጥቼ ማልቀስ ጀመርኩ” ያለው አቶ ሱሌይማን አድራሻዋን ማግኘት እንደማይችል ነገር ግን በጥሩ ስራ ላይ እንደሆነች ኤጀንሲው ነግሮች የሶስት ወር ደሞዟ ነው በሚል ወደ ስምንት ሺህ ብር እንደሰጠውን ልጅቷን ማግኘት እንጂ ብር አልፈልግም በማለቱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊዎች ብሩን ፈርሞ መቀበል እንዳለበት ሲነግሩት መቀበሉን ተናግሯለ፡፡ ከዚያም አድራሻዋ ሳይገኝ በተጨማሪ የ1 ወር ደሞዟን ኤጀንሲው ቢሰጠኝም የእህቴን አድራሻ እስካሁን አላገኘሁም ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ ስመላለስ አንድ አመተ አለፈኝ፡፡ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ለምን እንደተቋቋመና ለምን እንደማይዘጋ አልገባኝም ሲል አማሯል፡፡
አቶ ቃሲም ይመር ከካራ ኮተቤ መምጣቱንና ሚስቱ ነኢማ ይመር ያሲን በሳውዲ አረቢያ በችግር ላይ መሆኗን ተናግሯል፡፡ ሰኔ 4 ቀን 2005 ዓ.ም በሁለት ወሯ ደውላ አሰሪዬ እናቱ ቤት ሊቀይረኝ ነው ከአሁን በኋላ እኔ ካልደወልኩ አታገኙኝም ማለቷን የተናገረው አቶ ኡመር፣ ከ20 ቀን በኋላ ደውላ ሰውየው እናቱ ጋር እንዳልወሰዳትና ወደ አንድ ጭለማ ቤት ወስዶ በየቀኑ ሁለት ወንዶች እየተቀያየሩ እየደፈሯት እንደሆነ የደወለችውም በአንድ አጋጣሚ ሲፈቷት ስልክ ሰርቃ መሆኑን ገልፃልኛለች” ብሏል፡፡ “ወይ ወደ አገሬ አሊያም ወደ ቀድሞው ቤት ሰውየው ካልመለሰኝ ራሴን አጠፋለሁ ብላ በጭንቀት ላይ ነኝ” ያለው አቶ ኡመር ነፍሷን ለማትረፍ ቢሯሯጥም በኤጀንሲውም ሆነ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በኩል ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ “ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ 15 ቀን ወደ ኤጀንሲው 14 ቀን ብመላለስም ምንም እልባት አላገኘሁም” ብሏል፡፡
አቶ ተመስጌን ወርቂቾ ከጉራጌ ዞን ማረቆ ወረዳ፣ አበበ አየለ ከወልቂጤ፣ ፈይሳ ቱሉ የተባሉ ከአርሲ የመጡ አባት፣ እና በርካታ ወላጆች የልጆቻቸውን አድራሻ እንደማያውቁና በኤጀንሲም በኩል ሆነ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መፍትሄ አጥተው እየተንገላቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ “አንድ ሰው አልጋ ከያዘ እየተደበቅን አምስትና ስድስት ሆነን ሲሚንቶ ላይ እያደርን እየተንገላታን ነው ብለዋል ባለጉዳዮቹ፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የኤጀንሲዎቻቸውን ስልኮች በሰጡን መሰረት ለአብዛኞቹ ደውለን ከአዲስ አድማስ መሆኑን ስንነግራቸው ስልካቸውን ያጠፉ ሲሆን ፊዮሪ መስላን ወደ ሪያድ የላከው ናይል ኤጀንሲ ደውለን ስለ ጉዳዩ ያነሳን ሲሆን ስማቸውን ሳይገልፁ ያናገሩን አንዲት ሴት “ቅሬታ ያለው ሰው ለሚመለከው የመንግስት አካል እንጂ ሚዲያ ምን አገባው? የሚል ምላሽ ሰጥተው ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡

Read 3026 times