Saturday, 19 October 2013 11:49

“ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ” የመሆን ህልማችን ይሳካ ይሆን?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

              ፈረንሳይ ከሌላው ሀገር የተለየ ቅርስ ወይም የተፈጥሮ መስሕብ የላትም፡፡ ነገር ግን ከሕዝብ ቁጥሯ በሚሊዮኖች የላቀ ቱሪስት በየዓመቱ ይጎበኛታል፡፡ ጎረቤቷ ጣሊያን ከፈረንሳይ በቁጥር የበለጡ ዓለምአቀፍ ቅርሶች ብታስመዘግብም እንደ ፈረንሳይ አልጎረፈላትም፡፡
ኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ ቅርስ በማስመዝገብ ከአፍሪካ አንደኛ ናት - ዘጠኝ ቅርሶች በማስመዝገብ። ስምንት ስምንት ቅርሶች በማስመዝገብ የሚከተሏት ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ ናቸው። ጎረቤት ኬንያ ደግሞ አራት ቅርሶች ብቻ ነው ያስመዘገበችው፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 ይፋ የተደረገውን ሃምሳ ምርጥ የዓለማችን ቱሪስት መዳረሻ ሀገሮች ዝርዝርን ስንመለከት ከአፍሪካ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ነበሩ የተካተቱት፡፡ ግብፅ 8.6 ሚሊዮን ቱሪስቶች ስታስመዘግብ ቱኒዝያ 6.5 ሚሊዮን አስመዝግባለች፡፡ በእርግጥ ባለፉት ሦስት አመታት ከተከሰተው የአረብ አብዮት ጋር ተያይዞ የቱሪስቶች ቁጥር ማሽቆልቆሉ አልቀረም፡፡

አገራቱ ሲረጋጉ ግን እንደገና ቁጥሩ አድጓል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በ2002 ዓ.ም የተመዘገበው የቱሪስት ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን እንኳን አልደረሰም - 468,365 ነው፡፡ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከስድስት ዓመት በኋላ በ2012 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስት ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ሀገራት አንዷ ለማድረግ አቅዷል፡፡ ሆኖም እቅዱ ከእነቱኒዝያ፣ ታንዛንያ እና ኬንያ አንጻር ሲታይ ገና እጅግ በጣም ብዙ ይቀረዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት ተጨማሪ ሰባት ቅርሶች በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በእንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ከቅርሶቹም መካከል የመስቀል በአል እና ባሕረሐሳብ የተሰኘው የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ይገኙበታል፡፡ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በደን ምንጠራና በሌላ የሰዎች ተጽዕኖ ከዓለም ቅርስነት የመፋቅ አደጋ አንዣቦበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ፓርኩን የመከለል እንቅስቃሴ በመጀመሩ ነው ከመሰረዝ የዳነው፡፡
የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት መንግሥት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ አምስት ክፍሎች ያሉት ብሔራዊ የቱሪዝም ልማት ፖሊሲ አዘጋጅቷል፡፡ የፖሊሲው ክፍል ሦስት፣ ቁጥር አራት “በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ፉክክር ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን የማስተዋወቅ ሥራን በመሥራት ጠንካራ የገበያ ትሥሥር” መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያወሳል፡፡

ተገቢ የፕሮሞሽን ሥራዎችን መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማል - ፖሊሲው። በዚህም መሠረት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ ዓለም አቀፍ ዐውደርእዮችን እንደ ዋነኛ የቅስቀሳ ዘዴ እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሥራዬ ብሎ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቅርሶችንም ሆነ የተፈጥሮ መስህቦችን ሲያስተዋውቅ አይታይም፡፡ መገናኛ ብዙሃኑ በራሳቸው ጊዜ መጥተው ስለ ቅርሶቹና መስሕቦቹ ከሚዘግቡት በቀር በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ለምን መስህቦችን አታስተዋውቁም በሚል የተጠየቁት በሚኒስቴሩ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው፤ “በዚህ መልኩ አናስተዋውቅም፡፡ ከዚያ ይልቅ በምናተኩርባቸው ሀገራት ያሉ ታዋቂ ፀሐፍትንና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን በመጋበዝ ስለ ኢትዮጵያ ቅርሶችና መስሕቦች እንዲጽፉ፣ እንዲናገሩ እናደርጋለን፡፡ በዓለም አቀፍ ዐውደርእዮች በመሳተፍም ሀገራችንን ይበልጥ እናስተዋውቃለን” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፉ እንደ ድክመት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ በዘርፉ የሰለጠኑና የተካኑ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ነው፡፡ አቶ አወቀ በበኩላቸው፤ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በዘርፉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን መድቦ እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ አብዱ ከድር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስትሬት ዲግሪ ማሟያቸው እ.ኤ.አ በ2013 “Tourist Destination competitiveness of Ethiopia; The Tour operators perspective” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት ማጠቃለያ ላይ፤ “ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዐውደርእይ ላይ ስትሳተፍ ከፖለቲከኞች ይልቅ ገበያ ሊያመጡ በሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ብትወክል ይበጃታል” ብለዋል፡፡ መካከለኛው ምስራቅ በተለይም የዓረቡ ዓለም የተዘነጋ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ገበያ ክልል እንደሆነም በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስቴሩ አምና ባሳተመው መጽሔት ላይ ኢትዮጵያን ከሚጐበኙ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ውስጥ 51.2 በመቶ የሚሆኑት የአሜሪካ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ኬንያ፣ ጣሊያን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሕንድና ፊንላንድ ዜጐች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
ችግሩ ግን እነዚህ ቱሪስቶች በሚጎበኟቸው ስፍራዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚቀበሏቸው አስጐብኝዎች በቂ እውቀትና ልምድ የሌላቸው ከማስጎብኘት ይልቅ ከማገት የሚስተካከል ሚና የሚጫወቱ ወጣቶች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህም የተነሳ በዓመት ግማሽ ሚሊዮን እንኳን ያልደረሱት የኢትዮጵያ ጎብኚዎች በአገሪቱ ውስጥ ያላቸው ቆይታ በጣም ውሱን ነው፡፡ እስራኤል በቱሪስት ብዛት ቀዳሚ ከሆኑትን ፈረንሳይ እና አሜሪካ ጋር ልትወዳደር አትችልም፡፡ ነገር ግን የቆይታ ጊዜአቸውን በማራዘም ከቱሪዝም ዳጎስ ያለ ገቢ እንደምታገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንዲት ትንሽዬ የእስራኤል ከተማን በቅጡ ጐብኝቶ ለመጨረስ ቀናት እንደሚፈጅ ይነገራል። ኢትዮጵያም የእስራኤልን ፈለግ የመከተል ብርቱ ጥረት ልታደርግ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና መንገዶችን በስፋት በመገንባት የጉብኝት ስፍራዎችን ለማብዛት መትጋትን ይጠይቃል፡፡
ከዚሁ ጐን ለጐን የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በተለይ የቱሪዝም መስህብ በሆኑ ስፍራዎች ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግም የግድ ነው፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ፣ የኮንሶ አካባቢ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ የሆነበት አንደኛ ዓመት ሲከበር፣ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት አርባምንጭ ድረስ ለመጓዝ መገደዳቸውን ታዝቤአለሁ፡፡
በቂ የቱሪዝም እውቀትና ልምድ የሌላቸው አስጐብኝዎች፣ መስተንግዶአቸው እንደነገሩ የሆኑ ሆቴሎች፣ ደካማና ፈዛዛ እንቅስቃሴ ይዘን ከአፍሪካ ምርጥ አምስት የቱሪዝም መዳረሻ አገራት አንዱ ለመሆን ማሰብ ከህልምነት አያልፍም፡፡
የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በአንድ ወገን ጥረትና ትጋት የታሰበበት ደረጃ ላይ ሊደርስ አይችልም። ከግሉም ሆነ ከመንግሥት ዘርፍ የለያዩ ወገኖች ተዋናይ የሆኑበት ሰፊ ክፍለ ኢኮኖሚ በመሆኑ የተቀናጀ የጋራ ስራን ይፈልጋል፡፡ ከልብ መትጋትን ይጠይቃል፡፡ ያኔ የታቀደውም ሆነ የታለመው ሊሳካ ይችላል፡፡ በተለይ ደግሞ ራሳችንን በማስተዋወቁና በመሸጡ በኩል እጅግ ብዙ የቤት ሥራ እንዳለብን ማወቁ ተገቢ ነው፡፡

Read 2930 times