Saturday, 19 October 2013 11:53

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

“የጠባቂነት መንፈስ አገርን ያሽመደምዳል፡፡ እንክርዳድ የበላ ሰው ነው እሚያረገው”
        የአዋሳ ዕድሮችን አመራር አባላት የተሰናበትኩት ሰብሳቢው ሻምበል አህመድ ሁሴን፤ “128 ዕድሮች በጋራ እንሩጥ የተባባልነው ተሳክቶልናል፡፡ ሰውን ማጨናነቅ አልፈለግንም፡፡ ዋናው አባላቱ የዚህ ህብረት አባል ነኝ እንዲሉ ነው የፈለግነው፡፡ ተጠቃሚ መሆናቸው ቀጣዩ ጉዳይ ነው፡፡ በተጨባጭ ተጠቅመዋል፡፡ ከፍተኛ ት/ቤት፣ ከፍተኛ ወፍጮ ቤት፣ ግሮሠሪ… ብዙ የሥራ ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡” ሲሉኝ “መንግሥት እንዴት ያምናችኋል?” ብዬ ጠየኩ፡፡ 

“ከሥራችን አንፃር ነዋ! በደንብ ይከታተላልኮ! ለምሳሌ ጄክዶ ሲዳ የቤት ጥገና በጀት ሲፈቅድልን፤ በሰባቱም ክፍለ ከተማ መንግሥት በሚያውቃው ሁኔታ፣ ቀበሌም በቅርብ እያገዘን ነው ሥራውን ያካሄድነው! መንግሥትማ ምንጊዜም ከጐናችን ነው፡፡ ቦታ እየሰጠንኮ ነው ለአረጋውያን ቤት የሰራነው” አሉኝ፡፡
ልበ - ሙሉነታቸው፣ ጥንካሬና ጽናታቸው እየገረመኝ ነው ወደሚቀጥለው ጉብኝቴ ያመራሁት፡፡ ምነው ድፍን ኢትዮጵያ እንደነዚህ በጐ - ፈቃደኞች ባሰበ? የት በደረስን?/አልኩኝ በሆዴ፡፡
የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት እየረዳቸው የተቋቋሙ ኋላም ራሳቸውን የቻሉ፣ እስካሁን ያየኋቸው ማህበራትና ዕድሮች አራት ዋና ዋና ባሕሪ እንዳላቸው አስተውያለሁ - 1ኛ/ ሁሉም በራስ መተማመን አላቸው 2ኛ/ ሁሉም የማህበረሰቡን የልብ ትርታ በቅርብ ዳስሰው አውቀውታል 3ኛ/ ሁሉም ከመንግሥት ጋር በቅርብ ቁርኝት ይሰራሉ 4ኛ) ሁሉም የሚታይና የተጨበጠ፣ መሬት ላይ ያለ ሥራ የሠሩ ሲሆን ለዘላቂነታቸው ማረጋገጫ የሆነ ግንዛቤ አላቸው፡፡
አሁን የምሄደው ወደ “እንብራ የራስ አገዝ ቡድኖች ሕብረት” ነው፡፡
በውቅሮ ቀበሌ ምሥራቅ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ይሄ ሕብረት፤ ህፃናትና ሴቶችን እንዲሁም ወጣቶችን የሚረዳና፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋሙ ቡድኖች ህብረት ነው፡፡ ቀጥሎ እምፅፍላቸው በራስ የመተማመን መልካም ምሳሌ ከምላቸው አንዱ ነው፡፡ የሕብረቱ ሰብሳቢ ታየች ብርሃኑ ናት፡፡ ከጥንካሬ ድርና ማግ የተሰራች የምትመስል ቆራጥ ሴት ናት፡፡ “ህብረቱን ‘እንብራ’ ያልነው መጀመሪያ ኑሯችን አስከፊ ነበር፡፡ እኔ ለምሳሌ ብትወስደኝ እንደመልኬ ባህሪዬም አስቀያሚ ነበር፡፡
ኑሯችን ጨለማ ነበረ፡፡ ከዛ ስንወጣ ሕብረታችንን እንብራ አልነው፡፡ በመጀመሪያ የእየሩሳሌም ድርጅት ህፃናትን ይደግፍ ነበር፡፡ በቡድን በቡድን ተደራጀን - ሃያ ሃያ ሴት ያለበት፤ 6 ቡድን ተመሠረተ፡፡ ከየቡድኑ ሁለት ሁለት ተወካይ ተውጣጣና ወደ ሕብረቱ መጣን፡፡ ሕብረቱ ያስፈለገን ለቡድኖች የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ለመፈለግ፣ የገቢ ማግኛ አመራር ለመስጠት፣ ለማደራጀት፣ የቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ምን ዓይነት ፈጠራ ያልክ እንደሆን፤ ለምሳሌ የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት የምትነግድ ችሎታዋ የፈቀደውን ከሰልም፣ እንጨትም ነግዳ ራሷን እንድታቋቁም ነው፡፡ ወላጆች በተለያየ የንግድ ሙያ ሰልጥነው፣ የንግድን ትርጉም አውቀው፣ አትርፈው፣ ራሳቸውን ችለው፤ ነገ ልጆቻቸውን በራሳቸው ሙሉ አቅም እንዲያሳድጉ ነው፡፡
“ለምን ሴቶች በዙ ህብረታችሁ ውስጥ” አልኳት፤ ዙሪያዬን የከበቡኝን ከ8 ያላነሱ ሴቶች እየማተርኩ፡፡
“ሴቷ ናታ ዋንኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ! አሁን እኔ፣ መልክም ባይኖር፤ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የምታየኝ፡፡ ፊት ግን በጣም አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ነበር ያለሁት! ሁላችንም ችግር ውስጥ ነበርን፡፡ ባህሪያችንም እንደዚያው፡፡
ይሄ ባህሪ እንዲለወጥ መስዋዕትነትን ከፍሎ እየሩሣሌም መጀመሪያ ቤት ለቤት በመዞር የእኛ ባህሪ እንዲለወጥ ነው ያደረገው፡፡ የሥራ ባህል እንድናዳብር፣ የጠባቂነት መንፈስ ከእኛ እንዲርቅ ነው የሠራው፡፡ የእኛን ባህሪ መለወጥ አቅጣጫ ሲያይ፤ የፕሮጀክት ሥልጠና ሰጠን፡፡ የልምድ ልውውጥ እንድናደርግ አደረገን፡፡ ድልድያችን ሆነ! ከዚያ ፕሮጀክት ቀረጽን! ምን ትፈልጋለህ”
“ከዚያስ እንዳሰባችሁት ምላሽ ተገኘ?” አልኳት፤ ባላቋርጣት እየተመኘሁ፡፡
“ወይ ጉድ! ከፍትፍቱ ፊቱኮ ነው! ማንም ሰው የሚጠቅም ነገር ለማግኘት አበረታች መልክ ካገኘ ይለወጣል፡፡ ደብረማርቆስ ሄደን የልምድ ልውውጥ አድርገናል፡፡ ከዚያ ባገኘነው ዕውቀት አርባ የቡድን አባላትን ሰበሰብን፡፡ አባላቱ የገቢ ማስገኛ ሥልጠና ሠለጠኑና የፈጠራ ሥራ መሥራት ጀመሩ፡፡ ከዚያ የችግሩን ስፋት ጠልቆ እንዲያውቀው፣ መንግሥት የሴቷን ድምጽ እንዲሰማ ክለባት አቋቋምን፡፡ ከሃይማኖት ከሴት ከወጣት…ሁሉን አቀፍ ፕሮጄክት ቀረጽን፡፡ በጀት ፀደቀልን፡፡ ማገዶ ቆጣቢ ሠራን፡፡ አነስተኛ ምግብ ቤት ከፈትን፡፡ ራሳቸውን አሠልጣኝ ሆኑ - ሠልጣኞቹ፡፡ ሙዚቃ የሚማሩ እዚህ የምታያቸው ህፃናት አሉ፡፡
“ጄክዶን እንዴት ታዩታላችሁ?”
“እየሩሳሌም (ጄክዶ) እንዲሁ ልታይ ልታይ የሚል ድርጅት ቢሆን ኖሮ እኛም አናምንበትም፤ አንለወጥም ነበር፡፡ ሴቷ ላይ ትኩረት ስለሚያደርግና ክትትል ስለሚያደርግ ነው ውጤት ያመጣው፡፡ እኛ ባሁኑ ሰዓት ትልቅ ተደማጭነት የአለን ነን”
“መለወጥ ስትይ እንዴት ነው?” አልኩ አሁንም አቋርጪያት፡፡
“አየህ፤ ዱሮ ራሳችንን ገለን እርዳታ ጠባቂ ሆነን፤ ማዳበሪያና የዘይት ጀሪካን ይዘን ነበር የምንሮጠው፡፡ ዛሬ እንታገል፣ እንሻሻል፣ እንለወጥ፤ አልፈን ተርፈንም የተበደለችዋን ሴት፣ የተበደለችውን ሕፃን ፍትሕ እንድታገኝ እናድርግ እያልን ነው፡፡
“መንግሥት አይደግፍም የሚል ሃሳብ ያላቸው አንዳንድ ወገኖች አሉ፡፡ ለምን ይመስልሻል?”
“መንግሥት ያስፈልጋላ! አለመፍራት ተደጋግፈን እንሥራ ለማለት አለመፍራት ህብረተሰቡ ጋ ተደራሽ ለመሆን መንግሥት ያግዛል፡፡ እኛም የመንግሥትን ሥራኮ ነው የምንሠራው! ክፍተት ካለ እንሞላለን፡፡ አንዴ እዚህ ሥራ ውስጥ ከተገባ የነብር ጭራ እንደመያዝ ነው! ህፃናት ሲደፈሩምኮ እዚህ ድረስ መጥተው ውሰጂን ፖሊስ ጣቢያ ይላሉ፡፡ ማደሪያ እንደሰጣቸዋለን፡፡ ፍትሕ እንዲያገኙ እንከታላለን፡፡
ነገ መለወጥ አለበት፡፡ የጠባቂነት መንፈስ አገር ያሽመደምዳል፤ እንክርዳድ የበላ ሰው ነው የሚያደርገው”
እየገረመችኝ፤
ፊቴን ወደ ሌሎቹ የአመራሩ አባላት መለስኩ፡፡ ተራ በተራ ጠየኳቸው
“መመልመያ መስፈርታችሁ ምንድን ነው?” አልኩ፡፡
“አባት እናት የሞተበት፣ አባት ወይ እናት የሞተበት፣ እናት አባት እያላቸው መማር ያቃታቸው፣ ዋናው መስፈርታችን ዞሮ ዞሮ ችግር ነው” አለችኝ አንዷ፡፡
“25 ወጣቶች ወደኛ መጥተው ጄክዶ ሲዳ በለቀቀልን በጀት የሊስትሮ ዕቃ ገዝተን አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ቀጠለች ሌላዋ፡፡
“አንዱን ወጣት አባል አንተስ ምን ትለኛለህ?” አልኩት፡
“ብርሃንና ንጋት የእንጨትና የብረት ሥራ ማህበር ነው የእኛ” አለ፡፡ (ስማቸው ተስፋን ያዘለ መሆኑ በሆዴ አስገርሞኛል - ብርሃን ይወዳሉ) “በክፍለ ከተማው በጥቃቅንና አነስተኛ 10 ልጆች ተደራጀን፡፡ ትምህርት ጨርሰው ሥራ ያላገኙና ትምህርት አቋርጠው እቤት ቁጭ ያሉ ናቸው - ሙያ እያላቸው የመሥራት ዕድሉን ያጡ ናቸው፡፡ መሬት፣ ከነቤቱ፣ ከነማሽኑ ሰጠን ክፍለ ከተማው - ቀጠልን መንቀሳቀሻ ገንዘብ ፍለጋ ተሰማራን፡፡
አቶ ማስረሻ የእየሩሳሌም የአዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፤
“ገንዘብ መለመን የለባችሁም፡፡ በራሳችሁ ተፍጨርጭራችሁ መንቀሳቀስ አለባችሁ” ብለው የመከሩንን መቼም አንረሳውም፡፡ ከኪሣችን መቶ መቶ ብር አዋጥተን በ1000 ብር ዝም ብለን ሥራ ጀመርን፡፡ አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው…ከእንብራ መጠናከሪያ አግኝተናል - እንደማህበራችን ነው እምናየው፡፡ ወጣት ፈጣን ነው፡፡ ብዙ ኢንፎርሜሽን ያገኛል ያንን እንጋራለን፡፡ ወደፊት ብሎኬት ሥራ፣ ሻይ ቡና፣ ዶሮ እርባታ ወዘተ እቅድ አለን፡፡
ባንዱ ብንከስር ባንዱ እንካሳለን፡፡ እንጠነክራለን ምክንያቱም እንብራም፣ የእየሩሳሌም ድርጅትም፤ ከጐናችን አሉ” አለኝ፡፡
አዛለች ንዳ የህብረቱ ፀሐፊ ስለራሷ ስትነግረኝ እንባ እየተናነቃት ነው - “ማንም ሰው አያቀኝም ነበረ፡፡ ልጆቼ አጉል ቦታ ነበሩ፡፡ ባሌ ሞቷል፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበርኩም (አለቀሰች) እንዴት ሆኖ እንዳገኙኝ እግዜር ነው የሚያውቀው፡፡ ተደብቄ የነበርኩትን ሴትዮ ጐትቶ አወጣኝ…መልምለው ያወጡኝ እህቶቼ ነይ አሉኝ… የምክር አገልግሎት ሰጡኝ፤ ሰው አረጉኝ! አደለም በትርፍ ሰዓት በሥራ ሰዓቴም እየመጣሁ ማህበሩን አገለግላለሁ፡፡ ራዕያችን ሩቅ ነው” አለች፤ በጣም ሆድ ታባባለች፡፡
“አባቴ ሞቷል” ታላቅ ወንድማችን እኛን ለማሳደግ ትምህርት ትቶ የቀን ሥራ ገብቷል ጄክዶ መጥቶ ቤት ለቤት መለመለን፡፡ ት/ቤት ገባሁ፡፡ አሁን ተመርቄ ሥራ ይዣለሁ፡፡ እናቴም በራስ ገዝ ተደራጅታ ተዘዋዋሪ ብድር ወስዳ ትነግድም ነበር፡፡ አሁን ጥሩ ሆነናል፡፡ ለማህበሩ በበጐ ፈቃድ እያገለገልኩ እገኛለሁ” አለኝ ሌላው ወጣት፡፡
ወደ አንዷ ዞር ብዬ “ምን አገኘሁበት ትያለሽ ይሄን ህብረት?” አልኳት፡፡ በአጭሩና በሚገርም ዓረፍተነገር ነው የመለሰችልኝ - “በራስ መተማመንና ተስፋ” አለችኝ፡፡ አጨብጭቡላት ልል ምንም አልቀረኝ፡፡
“እነጄክዶ ሲሄዱ ምን ይውጣችኋል?” አልኩ፤ ሁሉንም አንዴ ቃኝቼ፡፡
አንዷ ተሻምታ መለሰችልኝ
“ትቀልዳለህ? ጄክዶ ባመቻቸው መንገድ ላይ የገቢ ማስገኛዎችን ፈጥረናል፡፡ እየተጠናከርንኮ ነው! እንብራ 3 ባጃጅ አለው፡፡ ሸማች አለው፡፡ የዳቦ ቤት ሊጀምር ነው፤ በዛ ላይ ህብረተሰቡ እርስ በርሱ እንዲደጋገፍ፣ የጠባቂነት መንፈስ እንዲጠፋ፤ ብዙ ሥራ ሠርተናል፡፡ ያ የዘላቂነት ሀብታችን ነው፡፡ ምንም አንጨነቅም - ራሳችንን ችለናል፡፡”
በመጨረሻ ምንም ወዳልተናገረችው ሴት ዞሬ፤
“ለመሆኑ በሥራው ላይ ትጣላላችሁ” አልኳት፡፡ ሁሉም ፈገግ አሉ፡፡
“ለምን እንጣላለን” አለችና፤ ቆየት ብላ “አሃ ብንጣላም እዛው እንታረቃለን” አለችና ሁላችንንም አሳቀችን፡፡
ይሄ ሁሉ ውይይት ደጅ ሣሩ ላይ ክብ ሠርተን ያወራነው ነበር፡፡ ቢሮ ገብቼ ፎቶዎቹንና ቻርቶቹን አይቼ ተሰናበትኳቸው፡፡
ነገ ወደ ሻሸመኔ - አጄ መሄዴ ነው፡፡
ፊቴን ወደ አጄ አዙሬ ተኛሁ!!
* * *
(ጉዞዬ ይቀጥላል)

Read 3108 times