Saturday, 19 October 2013 12:01

አይስላንድ - የደራሲያንና የአንባብያን ሀገር

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

            ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ ጋዜጣ “ፔን” በተባለ ከደራሲያን ጋር በሚሰራ ድርጅት ጋባዥነት አይስላንድ የተባለችውን አውሮፓዊት ሀገር ጐብኝቶ የመጣ አንድ ወዳጃችን በዋና ከተማዋ ሬይካቪክ በቆየባቸው ቀናት ከተመለከታቸው ነገሮች ውስጥ ይበልጥ ትኩረቱን የሳቡትን ለይቶ በመፃፍ አስነብቦን ነበር፡፡ 

በአይሁዶች ሚሽናህ “ካለው ላይ የጨመረ እርሱ የአባቱን ምርቃት፣ የእናቱንም እቅፋት ያገኛል” የሚል የቅድስና ቃል ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ የዛሬው የእኔ ጽሑፍም አይስላንድ ስለተባለችውና በለምአቀፉ ሚዲያ በክፉም ሆነ በበጐ አዘውትሮ ስሟ ሲነሳ ስለማንሠማት አውሮፓዊት ሀገር በርካታ ነገረ ስራዎች ውስጥ የእኔን ትኩረት ይበልጥ የሳቡትን ጉዳዮች በማንሳት ከሳምንታት በፊት ወዳጃችን ከሰጠን ላይ ለመጨመር ነው፡፡ አይስላንድ ከአለማችን ሰሜናዊ ጫፍ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ቅርበቷ በቅዝቃዜና በበረዶ የተሞላች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ይህ በረዶና ቅዝቃዜዋ እነሆ የስሟ መጠሪያ ለመሆንም በቅቷል፡፡ እንዲህ ያለው የአይስላንድ መልክአምድራዊ አፈጣጠሯ አብዛኛውን ጊዜ በደንብ ለማያውቋት ወይም ላይ ላዩን ብቻ የሚያውቋት ሰዎች ልክ ወዳጃችን ባለፈው ጊዜ ጽፎ እንዳስነበበን ዋነኛ ትኩረታቸውን በአየር ንብረቷና ከአየር ንብረቷ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ዋነኛ ምክንያት ሆኖአቸዋል፡፡
ይህ ግን አሳሳች ነገር ነው፡፡ በርካቶች አይስላንድን በአንድ ጐን ወይም በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያዩዋት አድርጓቸዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ ነዋሪዎች “ከሁሉም ምርጥ የሆነው ዛፍ ጭው ካለው ገደል አፋፍ ላይ ይበቅላል፡፡” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ይህ አባባል አይስላንድን ምናልባት ከሌላው በተሻለ ሊገልፃት ይችላል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አይስላንድ ጥልቅ ከሆነው ገደል አፋፍ ላይ የበቀለች ምርጥ ዛፍ ናት፡፡ በበርካታ ዘርፍ ያሉት ነገረ ስራዎቿ ይህንን እውነታ በሚገባ ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡
አንድ መቶ ሶስት ሺ ስኩዌር ኪሎሜትር በሚሆነው ጠቅላላ መሬቷ ላይ ሶስት መቶ ሃያ አንድ ሺ ስምንት መቶ ሃምሳ ሰባት የሆነው ጠቅላላ ህዝቧ ሰፋ ሰፋ ብሎ በመስፈር ይኖራል፡፡ ይህም ዘርዛራ የህዝብ አሰፋፈር ካላቸው የአውሮፓ ሀገራት መካከል ቀዳሚ እንድትሆን አስችሏታል፡፡
የአይስላንድ ባህል ከሀገሪቱ የኖርስ ቅርስ የተወረሰ ነው፡፡ አብዛኛዎቹን አይስላንዳውያን ስለዘር ሀረጋቸው ብትጠይቋቸው ከኖስና ጋይሊክ (ሴልቲክና ሻይኪንግ) ሰፋሪዎች የመጡ ወይም የሚመዘዝ መሆኑን አስረግጠው ይነግሯችኋል፡፡
የማንነታቸውን ስረ መሠረት ጥንቅቅ አድርገው የሚያውቁት አይስላንዳውያን ደግሞ የመጀመያው የኖርስ ሰፋሪ ኢንጐልፈር አርናርሰን እንደሚሰኝና የሰፈራ ዛኒጋባውንም በስምንት መቶ ሰባ አራት አመተ ምህረት ዛሬ የአይስላንድ ዋና ከተማ በሆነችው በሬይካቪክ ቀልሶ መኖር እንጀመረ በሚገባ ያብራሩላችኋል፡፡ ይህንን ታሪክ የሚነግሯችሁ ደግሞ እንዲሁ በወሬ ብቻ ሳይሆን በቁፋሮ የተገኙ ታሪካዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ነው፡፡
የአየር ንብረት ተመራማሪዎች በቀደሙት የኖርስና ጋይሊክ (የሴልቲክና ቫይኪንግ) ሰፋሪዎች ጊዜ የአይስላንድ የአየር ንብረት አሁን ካለው እጅግ በተሻለ ሞቃት እንደነበረ፤ አሁን ያለው አንድ በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ያኔ ሃያ አምስት በመቶ እንደነበረ በማስረጃ አስደግፈው ይናገራሉ፡፡
አይስላንዳውያን በዘጠኝ መቶ ሰላሳ አመተ ምሕረት የአይስላንዲክ ኮመንዌልዝን እንዲቆጣጠር ያቋቋሙት የህግ አውጭና፣ የህግ አስፈፃሚ ምክር ቤት ወይም ፓርላማ ህልውናውን እንደጠበቀ እስከ አስራ ሶስተኛው ክፍለዘመን ድረስ መዝለቅ ችሎ ነበር፡፡
በስተርላንግ ዘመን የተፈጠረው የውስጥ ትግልና የእርስ በርስ ግጭት በ1262 ዓ.ም ዛሬ “የድሮው ስምምነት” እየተባለ ለሚጠራው ውል መፈረም ዋነኛ ምክንያት ሆነ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ውል ተራ ውል አልነበረም፡፡ ራሷን ችላ ትኖር የነበረችው አይስላንድ በኖርዌይ የዘውድ መንግስት ስር እየገበረች እንድታድር የሆነችው በዚህ ስምምነት አማካኝነት ነበር፡፡
ከዚህ ክስተት በሁዋላ የተከተሉት አመታት ለአይስላንድና ለህዝቦቿ መልካም አመታት አልነበሩም፡፡ የአየር ንብረቷ ቀስ በቀስ ግን ባልተቋረጠ ፍጥነት እየቀዘቀዘና እየከፋ ሄደ፡፡ በተከታታይ የደረሱበት የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታዎች፣ከግግሩ በረዶ ጋር ተዳምሮ ቀላል የማይባል መጠን ያለውን መሬት ለእርሻ አገልግሎት እንዳይውል አደረገው፡፡ ሰፊ ይባል የነበረው የደን ሀብትም በከፍተኛ ፍጥነት እየተመናመነ ሄደ፡፡
ይህ ሁኔታ የአይስላንዳውያንን የእለት ተዕለት ህይወት እጅግ መራራና ሸክሙ የማይቻል ከባድ እዳ አደረገባቸው፡፡ በዚህ የተነሳም አይስላንዳውያንም ሆኑ ሀገራቸው ከአውሮፓ እጅግ ደሀ ከሆኑት ሀገራት ተርታ መሰለፍ ግድ ሆነባቸው፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በ1402 አ.ም እና በ1494 አ.ም የተከሰተውና “ጥቁሩ ሞት” እየተባለ የሚጠራው ወረርሽኝ እንዳይሞቱ እንዳይሸሩ አድርጎ ክፉኛ ደቆሳቸው፡፡ በተለይ በ1402 አ.ም የተከሰተውና ለሶስት አመት ያህል የዘለቀው የመጀመሪያው ወረርሽኝ ከጠቅላላው ህዝባቸው ከሀምሳ እስከ ስልሳ በመቶ የሚሆነውን በመፍጀት አይስላንዳውያንን ከምድረ ገፅ ነቅሎ ሊያጠፋው ክፉኛ ተገዳድሮአቸው ነበር፡፡
የናፖሊወንን ጦርነት ተከትሎ በ1814 አ.ም የተፈረመው የ“ኪየል ውል” የዴንማርክ - ኖርዌይ ግዛት ለሁለት እንዲከፈልና ራሳቸውን የቻሉ የንጉሱ ነገስት መንግስት እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡ በኖርዌይ አገዛዝ ስር የነበረችው አይስላንድም ዴንማርክን በአዲስ ገዢነት ተቀብላ ማደር ጀመረች፡፡
ከኖርዌይ ጋር ሲወዳደር ዴንማርክ አይስላንድን የገዛቻት ከብረት በጠነከረ ክንድ ነበር። ለአይስላንዳዊያን ግን ይህ በወቅቱ የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳያቸው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ከዴንማርክ የጭቆና አገዛዝ ይልቅ ከግራና ከቀኝ ጎናቸውን ሰቅዞ ይዞ አላፈናፍን ያላቸውና ህልውናቸውን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተናቸው ያለ ትልቅ ጉዳይ ከፊትለፊታቸው ተደቅኖባቸው ነበርና ነው፡፡ ይህ ትልቅ አደጋ ሌላ ነገር ሳይሆን በየእለቱ ቅዝቃዜውና የበረዶው ግግር እየከፋ የመጣው የሀገራቸው የአየር ንብረት ጉዳይ ነበር፡፡እየከፋ የሄደው የአየር ንብረት በተለይ በአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አካባበቢ በርካታ አይስላንዳዊያን ወደ አዲሱ አለም በዋናነት ደግሞ ወደ ካናዳ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ በ1820 አ.ም ሰባ ሺ ከሚሆኑት አይስላንዳዊያን መካከል አስራ አምስት ሺ የሚሆኑት ወደ ማኒቶባ ካናዳ ተሰደዋል፡፡ ይህ ቁጥር በሌላ አነጋገር ሲገለጽ በወቅቱ ከነበረው የአይስላንድ ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር ከሃያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በአንድ አመት ውስጥ ብቻ ሀገሩን ጥሎ ተሰዷል ማለት ነው፡፡
በ1943 አ.ም የሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ ለሀያ አምስት አመታት የዘለቀው የዴንማርክና አይስላንድ ህብረት ስምምነት ፈረሰ፡፡ በቀጣዩ አመት ግንቦት ሀያ ቀን ደግሞ አይስላንዳዊያን ከዴንማርክ አገዛዝ በመላቀቅ የራሳቸውን ነፃ ግዛት ለመመስረት ድምፃቸውን ሰጡ፡፡ ሰኔ አስራ ሰባት ቀን 1944አ.ም ላይ ደግሞ ነፃ የአይስላንድ ሪፐብሊክን በሟቋቋም ስቪን ቢዬንሰንን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንታቸው አድርገው መረጡ፡፡
ይህ የአይስላንድ የቀድሞው ታሪኳ ነው፡፡ ከነፃነት በሁዋላ ያለው የአይስላንድ የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ፣ማህበራዊና የአለም አቀፍ ግንኙነት ታሪኳበጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ይህቺ ድምጿም ሆነ ወሬዋ እምብዛም የማይሰማው አውሮፓዊት ሀገር በስነ ፅሁፍ ረገድ ያላት ታሪክና ለአለም ስለፅሁፍ እድገት ያበረከተችው አስተዋፅኦ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ እነዚህን የሳምንት ሰው ይበለንና ሳምንት እንመለስበታለን፡፡

Read 2574 times