Saturday, 19 October 2013 12:08

ሕይወት በማህፀን ዓለም

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(17 votes)

            አንድ ልጅ ተፀንሶ እስኪወለድ ድረስ ያለው የሰው ልጅ ዕድገት ፍጥነት በጣም አስገራሚና የሚደንቅ ነው፡፡ በአንደኛው ወር ብቻ በጣም ኢምንቷ ኦርጋኒዝም (አንዱ ከሌላኛው አካል ጋር የሚደጋገፉ ጥቃቅን ኅዋሳት) በተፀነሰበት ወቅት ከነበረው ክብደት 10ሺህ ያህል ጊዜ ይጨምራል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት፣ ከኢምንት ውሃማ ነገር፣ ቁጥር ስፍር ወደሌለው ውስብስብና ጅምር የሰው ቅርፅ ይለወጣል፡፡ ቅርፁ ባይጠናቀቅም ልጅ እንደሚሆን ግን መገንዘብ ይቻላል፡፡
እያንዳንዱ ሂደት ይሆናል ብሎ ለማመን የሚከብድና ግምትን የሚፈታተን ረቂቅ የዕድገት ለውጥ ነው፡፡ አንደኛው የለውጥ ሂደት ለሚቀጥለውና ለዋነኛው ሁለንተናዊ ዕቅድ፣ በሚያስገርም ፍፁም ትክክለኛነት ያስተላለፋል። ይህ 267 ያህል የሚፈጀው የትራንስፎርሜሽን ወይም የለውጥ ሂደት፣ የራስና የማንኛውም ሰው የማይታመን የሕይወት ታሪክ የሚጀመርበት የዕድገት ሂደት ነው፡፡
ተቃራኒ ፆታ የሆኑ ሰዎች ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈፅሙበት ጊዜ፣ ያኮረተ ወይም ለመፀነስ ዝግጁ የሆነ የሴቷ እንቁላል፣ ከወንዱ የዘር ፍሬ (ስፐርም) ጋር ሲገናኝ ወዲያውኑ ከመቀፅበት፣ የሴቷን ባህርያት የያዙ 23፣ የወንዱን ባህርይት የተሸከሙ 23፣ እንዲሁም ሁለት ፆታ ወሳኝ ከሆኑ ክሮሞዞሞች (የዝርያ ሐረግ) ጋር በመሆን 48 ክሮሞዞሞች፣ የተሟላ የዘር ሐረግ ባቀፈው ሴል (ኅዋስ) እምብርት ሆነው የመጀመሪያውን የኅዋስ ክፍፍል (ሴል ዲቪዥን) ለመጀመር በከፍተኛ ፍጥነት በመሽከርከር ይዋሃዳሉ፡፡
የእናቱንና የአባቱን የዘር ውርስ ይዞ የተፀነሰው እንቁላል መጠን በጣም የሚገርም ነው፡፡ በእንግሊዝኛው ፊደል አይ (i) አናት ያለችውን ነጥብ የሚያክል ነው፡፡ ነገር ግን ይቺ ኢምንት ፅንስ፣ ከሁሉም ልጆች ልዩ የሆነውን ልጅና ከማንኛውም ወላጅ ልዩ የሆኑትን የእናቱንና የአባቱን የወ/ሮና የአቶ እገሌን የዘር ሐረግ አጠቃላ ይዛለች፡፡
ኅዋሳቱ መከፋፈል ሲጀምሩ (አንዱ ሴል ሁለት፤ ሁለቱ አራት፤ አራቱ ስምንት፣ … እያለ ይቀጥላሉ) ፅንሱ በሴቷ ግራና ቀኝ ጐን በሚገኙት የእንቁላል መተላለፊያና የፅንስ መፈጠሪያ (ፋሎፒያን ቲዩብ) በአንዱ ውስጥ እየተንሳፈፈ ወደ ማኅፀን ጉዞ ይጀምራል፡፡ ከቲዩቡ እስከ ማኅፀን ያለው ርቀት 5 ሳ.ሜ ያህል (2 ኢንች) ቢሆንም፣ ፅንሱ ማኅፀን ለመድረስ ሦስት ወይም አራት ቀናት ይፈጅበታል፡፡ ብዙ ጊዜ ፅንሱ ማኅፀን የሚደርሰው በ16ኛው የኅዋስ ክፍፍል ደረጃ ነው፡፡
በእነዚህ የመጀመሪያ ቀናት እንኳ አስገራሚ ለውጥና ዕድገት ስለሚካሄድ ሁለት የተለያዩ ሴሎች በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹትንና የልጁን የውጪኛ አካላት የሚፈጥሩትን፣ ዝርግና በፍጥነት ጠላቂ ኅዋሳትና የልጁን የውስጠኛ አካላት የሚፈጥሩ ክብና የሚያምሩት በዝግታ ጠላቂ ኅዋሶች ይፈጠራሉ፡፡
ከአራተኛው እስከ ስድስተኛው ወይም ሰባተኛ ቀን ድረስ የፅንሱ መጠን ከነጥብ ከፍ ብሎ የስፒል (የወረቀት መርፌ) አናት ያህላል፡፡ በዚህ ጊዜ የኳስ (ኤግ ቦል) ቅርፅ የያዘው እንቁላል፣ በሙቅና በጥቁር ፈሳሽ በተሞላው ማኅፀን ውስጥ ይንሳፈፋል፡፡ ልስልሱ የማኅፀን ግድግዳ ከጥቃቅን የደም ስሮች ጋር ተጠላልፎ ይሰራል፡፡ ፅንሱ በዚህ ልስልስ ግድግዳና ስፖንጅ በመሰለ ነገር ላይ ይጣበቅና ራሱን በኃይል ይቀብራል፡፡ ከዚያም፣ በማቆጥቆጥ ላይ ካሉት ጥቃቅን ፀጉር መሰል ነገሮች (ካፒላሪስ) ጥቂቶቹን በመክፈት በውስጣቸው የያዙትን ደም ያስወጣል፡፡
ኳስ መሰሉ እንቁላል (ፅንስ) በመቶዎች የሚቆጠሩ በጣም ጥቃቅንና በፍጥነት አዳጊ ቪሊ (Villi) የተባሉ ፀጉር መሰል ነገሮች በመላ አካሉ ላይ ያበቅላል፡፡ ጥቃቅን ተክሎች ስራቸውን በጥልቀት ሰደው ምግብ እንደሚስቡት፣ ቪሊዎቹም፣ ስራቸውን እጅግ ጥቂት በሆነው ደም ውስጥ ተክለው ኦክስጂንና ምግብ ይመጣሉ፡፡ ምግቡም፣ ኳስ መሰሉን እንቁላል በፍጥነት ያሳድገዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ ለውጦች ሲከናወኑ እናቲቱ ማርገዟን እንኳ አታውቅም፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ ከ21ኛው ቀን በፊት ማርገዟን ማወቅ ስለማትችል ነው፡፡
በዚህ ጊዜ፣ ሞለል ያለው ማኅፀን ውስጥ የሚገኙት በርካታ ክብ ሴሎች፣ ራሳቸውን ወደ ትናንሽ አስኳልና አሚኒዮ (aminion) ከረጢትነት ይለውጣሉ፡፡ ከረጢቶቹ በሚነካኩበት (በሚገናኙበት) ስፍራ ደግሞ ሦስተኛ ከረጢት ይፈጥሩና ባለ ሦስት ደረጃ ሞላላ ንጣፍ ይፈጥራሉ። አሚንዮ ከረጢቱ ልጁ እስኪወለድ ድረስ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም የአስኳል ከረጢቱ ግን ወደፊት ምንም ጥቅም የለውም፡፡ አሁን ራሱን ወደ ሽል እስኪለውጥ ድረስ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወተው ቀለል ያለው ባለ ሦስት ደረጃ ኅዋስ (ሴል) ነው፡፡
እያንዳንዱ ንብርብር ንጣፍ ወደፊት ልጅ ለሚሆነው ሽል የተለያየ ኅዋስ መፍጠሪያ ይሆናል። አንደኛው ንጣፍ የነርቭ ሲስተም፣ ቆዳ፣ ፀጉር፣ የጣት ጥፍር፣ የጥርስ መስተዋት፣ የአፍንጫና የጉሮሮ ግድግዳ ሴሎች መፍጠሪያ ይሆናል፡፡ መካከለኛው ንጣፍ፤ የሽሉ ጡንቻ፣ አጥንትና ጅማት፣ ደምና የደም ስሮች፣ ኩላሊትና የድድ መፍጠሪያ ሴል ይሆናል። ሦስተኛው ንጣፍ ደግሞ አንጀትና ለአብዛኛው መተንፈሻ አካላት ሲስተም መስሪያነት ይውላል፡፡
ቀጣዩ ለውጥ ወይም ትራንስፎርሜሽን ደግሞ፣ ምናልባት ከሁለም የላቀው ተአምራዊ ሂደት ነው፡፡ በ19ኛው ወይም በ20ኛው ቀን፣ ሞለል ያለው ክብር ነገር፣ በአካሉ ላይ በሁለቱም በኩል ወደታች የሚሄድ ጐድጐድ ያለ ቦይ መሳይ ነገር ይፈጠራል፡፡ ቦዮቹ በአንድ ጫፍ ይገናኛሉ፤ ያ የልጁ ራስ መሆኑ ነው። ቦዮቹ ከፍና ዝቅ እያሉ በመተጣጠፍ ሲቀራረቡ ሞላላው ክብ ነገር የግማሽ ጨረቃ ወይም የደጋን ቅርፅ ይይዛል፡፡ የደጋኑ የውጪኛ እጥፋት (Curve) የልጁ ጀርባ ይሆናል፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ አከርካሪን የሚጠቁም ነገርና አዕምሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች፣ በራስ መጨረሻ የሚገኘውን ጐድጐድ ያለ ስፍራ ሙላት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅና እግር መሆኑን የሚጠቁሙ ትናንሽ ቡጥ መሰል ነገሮች ማቆጥቆጥ ይጀምራሉ፡፡ በ21ኛው ቀን፣ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ የሆነው ልብ ይፈጠራል፡፡ ከዚያም ያ ልብ ከ10 ቀናት በኋላ መምታት ይጀምራል፡፡
ፅንሱን የያዘው ሞለል ያለ ከረጢት (እንግዴ ልጅ) ከእናቲቱ ጋር የሚገናኘው፣ በእትብት ነው፡፡ እትብቱ የተሠራው ደግሞ እንደክር ወይም ገመድ በተጠላለፉ ኅብረ-ሴል (Tissues) ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእትብቱ ርዝመት እስከ 56 ሳ.ሜ (22 ኢንች) ሊደርስ ይችላል፡፡ በፕሮቲን ፈሳሽ (aminotic sac) በተሞላው ሞለል ያለ ከረጢት (እንግዴ ልጅ) ውስጥ የግማሽ ጨረቃ ወይም የደጋን ቅርፅ ያለው በጣም ትንሽ ሽል በኅብረ-ሴል ከረጢት ሁለቴ ተጠቅልሎና በሌላ የኅብረ-ሴል ኳስ ውስጥ ሆኖ፣ እንደስፖንጅ በሚለሰልሰውና በሚመቸው የማኅፀን ግድግዳ ራሱን ይቀብራል፡፡ 98 በመቶ ንፁህ ውሃ በሆነ ፈሳሽ የተሞላው ከረጢት (እንግዴ ልጅ) ተግባር፣ የሽሉ መቀመጫ ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ንቅናቄንም (Shock) በማርገብ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሽሉ በፍጥነት የልጅ ገጽታ እየያዘ ይሄዳል፡፡ በሁለተኛው ወር፣ ከራስ እስከ መቀመጫው (ቂጥ) ያለው ርዝመት 2ሳ.ሜ ተኩል (1 ኢንች) ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን አፍንጫ፣ አፍ፣ ጆሮና ዓይን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ጐድጐድ ያለ ነገር አለው፡፡ ከሦስተኛው ወር መጨረሻ ጀምሮ ሽሉ፣ ከ7ሳ.ሜ ተኩል በላይ (3 ኢንች) ሲረዝም፣ ክብደቱ ደግሞ ከ28 ግራም በላይ ይሆናል፡፡ የተለያዩ የአካል ሲስተሞቹም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በግልፅ ያሳያሉ ወይም ይለያሉ። በዚህ ጊዜ ዓይንና ሽፋሽፍቱ የተፈጠሩ ቢሆንም ዓይኑ ግን ለጊዜው እንደተከደነ ነው፡፡ ፆታም ይለያል፡፡ የእጅና የእግር መፈጠር ከመጠናቀቁም በላይ ሁለቱም ጣቶች ጥፍር አብቅለዋል፡፡ ሽሉ እጅ እግሩን ማንቀሳቀስ ቢጀምርም፣ እናቲቱ ግን ይህን የመጀመሪያ ጊዜ እንቅስቃሴ መገንዘብ አትችልም። ለሁለት ወራት ሲመታ የቆየው ልብ ጡንቻም ጠንክሯል፡፡
በዚህ ጊዜ ሽሉ መዋጥ ብቻ ሳይሆን መተንፈስን ለመለማመድ ይመስላል፣ ዙሪያውን ከከበበው የፕሮቲን ፈሳሽ ጥቂት ይጐነጫል፡፡ ፈሳሹ ወደ ሳንባው ሲገባ፣ ሽሉ የመተንፈሻ ጡንቻዎቹን በመጠቀም ያስወጣዋል፡፡ ይህ ሁሉ ልምምድ ሲሆን፣ ሽሉ እስኪወለድ ድረስ ኦክሲጅንና ምግቡን የሚያገኘው ከእናቱ ነው - በእትብት አማካኝነት። እነዚህ ሁሉ አስገራሚ ለውጦችና ዕድገቶች የሚከናወኑት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ነው፡፡ አሁን የእናቲቱ ማኅፀን ማደግ ቢጀምርም ምናልባት በራሷ ዓይነ ካልሆነ በስተቀር የሆዷን ማደግ ሌሎች አይገነዘቡትም፡፡ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ሽሉ ወደ ልጅ መጠን የሚያድግ ሲሆን አዲስ ልጅ ሆኖ ሲወለድ የሚያደርገው ነገር ችሎታም ቀስ በቀስ ያድጋል፡፡
እናትና ሽሉ የሚገናኙት በእትብት ብቻ ነው። እትብቱ ነርቭ ስለሌለው፣ የእናትና የሽል ነርቭ ሲስተሞች በጭራሽ አይገናኙም፡፡ ስለዚህ፣ እናቲቱ የምታስበው ወይም የምታየው ነገር ሽሉን በፍፁም አያውከውም፡፡ ስለዚህ፣ ሰው አካል ላይ ጠቆር ወይም ነጣ ያለ ነገር ሲኖር፣ “እናቱ እሷን ወይም እሱን እርጉዝ ሆና የሆነ ነገር ሲያምራት የዳበሰችው ወይም የነካችው ቦታ “ሽታ” ነው” የሚለው ብዙ ዘመናት ያስቆጠረው አፈ-ታሪክ ውሸት ነው ማለት ነው። የሽሉ የነርቭ ሲስተም፣ በእናትየው ጋር በፍፁም እንደማይገናኘው ሁሉ፣ የደም ዝውውር ሲስተሙም ከእናቱ ጋር ፈፅሞ የተለያየ ነው። ሽሉ፣ ከእናቱ ጋር በጭራሽ የማይገናኝና የራሱ የሆነ ደም ነው የሚያመርተው፡፡ ሁለቱ የደም ዝውውሮች (እናትና ሽሉ) ኦክስጅንም ሆነ ምግብ የሚለዋወጡት፣ በእርግዝና ወቅት በማኅፀን ውስጥ በሚፈጠርና እንደተወለደ በሚበጠሰው እትብት ነው፡፡ በሽሉ እንብርት ላይ ተጣብቆ የሚገኘው እትብት ከ12 እስከ 15 ሳ.ሜ ርዝመት ሲኖረው፣ ቪሊ በተባሉ ጥቃቅን የደም ስሮች የተሠራ ነው፡፡ የሽሉ መተንፈሻና ምግብ መፍጫ ሲስተሞች ዕድገት ዘገምተኛ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ወደፊት የሚወለደውን ልጅ ወክሎ የሚተነፍሰውና ምግብ የሚፈጨው እትብት ስለሆነ ለ ሽሉ የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛና በዋጋ ሊተመን የማይችል ነው፡፡
እናቲቱ የሽሉ እንቅስቅሴ የሚሰማት በአራተኛው ወር መጨረሻ ገደማ ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ እንቅስቅሴው በጣም ደካማ በመሆኑ የሽሉ እጅና እግር እንቅስቃሴ ጠንከር ለማለት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡ አሁን በእርግዝናው አጋማሽ ነን እንበል፡፡ በዚህ ጊዜ ሽሉ 15 ሳ.ሜ ርዝመትና 170 ግራም ክብደት ይኖረዋል፡፡ ቅንድብና ሽፋሽፍቱ መታየት ይጀምራሉ፡፡ የልብ ምቱ ጠንከር በማለቱ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በልብ ምት ማዳመጫ (ስቴትስኮፕ) ሊሰማ ይችላል፡፡ ልቡ በአንድ ደቂቃ 136 ጊዜ ይመታል፡፡ ይህም የእናቱን ልብ ምት እጥፍ ያህል ማለት ነው፡፡
ሽሉ ፣ በ6ኛው ወር መጨረሻ አንድ ማስመርያ ያህል ርዝመትና ግማሽ ኪ.ግ ያህል ክብደት ይኖረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ፣ ሲታፈን ድምፅ ማሰማት፣ የፊት ጡንቻዎቹን ማንቀሳቀስና ማስነጠስ ይችላል። ዓይኖቹ የተሟላ ዕድገት ላይ ቢደርሱም፣ ብርሃን ብቻ ነው የሚለዩት፡፡ አሁን ሽሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ጥንካሬ በማምጣት፣ አካሉን መዘረጋጋትና እራሱን ማገላበጥ ይችላል፡፡ የደረት ጡንቻዎቹ በየዕለቱ ለመተንፈስ በሚያደርጉት ዝግጅት ይበልጥ እየጠነከሩ ነው፡፡ ኩላሊቶቹ ለማጣራት፣ አንጀቱ ምግብ ለመፍጨት ዝግጁ ቢሆኑም፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ስለሌለ መደበኛ ሥራቸውን የሚጀምሩት ልጁ ሲወለድ ነው፡፡ ሽሉ ከተወለደ በኋላ የተፈጥሮ ግዴታ የሆነውን አበላል ለመለማመድ (ያለ ማቋረጥ ማለት ይቻላል) የመጥባት እንቅስቅሴ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ልጆች ከመወለዳቸው በፊት እንደሚያደርጉት አውራ ጣቱን ሊጠባ ይችላል፡፡
በዘጠነኛው ወር መጨረሻ አካባቢ ወይም በ252ኛው ቀን ገደማ ሽሉ የሆድ ውስጥ ዕድገቱን ጨርሶ ለመወለድ ዝግጁ ይሆናል፡፡ ፅንስ ተፈጥሮ ለመወለድ 267 ቀናት ይፈጃል የሚባለው አማካይ ስሌት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ልጁ “ይወለዳል” ተብሎ ከሚጠበቅበት ቀን፣ 15 ቀናት ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሊወለድ ይችላል፡፡
ሊወለድ የደረሰ ሽሉ ብዙውን ጊዜ ከ2 ተኩል እስከ 3 ኪ.ግ ሲመዝን፣ 48 ሳ.ሜ ወይም አንድ ማስመሪያ ያህል ቁመት ይኖረዋል፡፡ በማኅፀን ውስጥ ያለው ቦታ እንዲበቃው፣ የእጁን ክንዶች ደረቱ ላይ አጥፎ ሲያስቀምጥ፣ ጭኖቹን ደግሞ ኩርምት ብሎ ሆዱ ላይ ያኖራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንቅልፍ ላይ የሆነ ይመስል ፀጥተኛ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን፣ እጅና እግሮቹን ሲያንቀሳቅስ እናቲቱ የሚሰማት ግፊት ኃይለኛ ነው፡፡ እርግዝናውን የሚከታተለው ሐኪም ሽሉ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ፣ የእጁን መዳፍ እናቲቱ ማህፀን ላይ ቢያሳርፍ ሽሉ ዝም የሚል እንዳይመስላችሁ፤ እጁን በማወራጨት የቦክስ ምላሽ በመስጠት ተቃውሞውን ይገልፃል፡፡
በዚህ ጊዜ ሽሉ ትንሽ፣ ነገር ግን የተሟላ የሰው ልጅ ፍጡር ነው፡፡ አሁን፣ በማንኛውም ቀን ለመወለድ ወይም ወደዚች ዓለም ለመምጣት፣ ማንነቱን የሚፈታተን የመጀመሪያውን ፈታኝ ሁኔታ ይጋፈጣል፡፡ አሁን የሚጠበቀው የእሱ መምጣት ወይም መወለድ ነው፡፡ እናቱ ማኅፀን ውስጥ ሆኖ ያካበተውን የሚደንቁ ተግባራዊ ልምዶች ከተወለደም በኋላ ይቀጥላል፡፡ በአጭሩ፣ የማንኛውም ሰው ሕይወት፣ ከመወለዱ በፊት ይህን ነው የሚመስለው፡፡

Read 9624 times