Saturday, 19 October 2013 12:19

‹‹እግር ኳስ ከዝንባሌ ባሻገር ትልቅ ንግድ ነው››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ
አቶ ጁነዲን ባሻህ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለሚቀጥሉት አራት አመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ከማድረጋቸው ሶስት ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ነበር፡፡ የድሬደዋ ከተማ መስተዳድርን በመወከል በምርጫው ተወዳድረው ድምፅ ከሰጡት 106 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የ55ቱን ድምፅ በማግኘት አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡ አቶ ጁነዲን ላለፉት 20 ዓመታት ከስፖርቱ ጋር ትስስር ነበራቸው፡፡ በተለይም የሐረር ቢራ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው በሰሩበት ወቅት ክለቡን ለፕሪሚየር ሊግ አብቅተውታል፡፡ ስለዓላማቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳደር ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን እሰራለሁ ብለዋል፡፡

በመላው አገሪቱ እግር ኳስን በተሻለ ደረጃ ለማስፋፋት ተስፋ እንደሚያደርጉ በመግለፅ፤ ስፖርቱን በተረጋጋ የለውጥ ሂደትና በዘመናዊ መዋቅር ለመምራት እንደሚፈልጉና በወጣት ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ከፍተኛልምድ ያላቸው አቶ ጁነዲን ባሻህ እግር ኳስ ከዝንባሌ ባሻገር ትልቅ ንግድ እንደሚሆን በተግባር የማሳየት ፍላጎት እንዳላቸው ያስገነዝባሉ፡፡ ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን በማስፋት ሊለወጡ በሚችሉበት የእድገት አቅጣጫ ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ ናቸው፡፡ አቶ ጁነዲን ባሻህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙበት እለት ከዚህ በታች የቀረበውን አጭር ቃለምምልስ ከስፖርት አድማስ ጋር አድርገው ነበር፡፡
በሃላፊነት ሳምንት እንኳን ሳይሞላዎት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ የጥሎ ማለፍ ትንቅንቁን በሜዳው ይጀምራል፡፡ ሁኔታውን እንዴት ይመለከቱታል?
በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫ ባያልፍ ምን ይመጣ ይሆን የሚለው ያስጨንቀኛል። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ውጤት እንዲመጣ ከመጓጓት ነው። አሁን ደግሞ ሃላፊነት ላይ እንደተቀመጠ ሰው በዚህ ሽግግር የተጨናነቁ ነገሮች እንዳይመጡ ፍላጐቴ ነው፡፡ ቢቻል ከቀድሞው አመራር ጋር በቦታው ተገኝተን ቡድናችንን በጋራ ብናይ፣ በሰከነ ሁኔታ ተጨዋቾቻችን እንዲጫወቱ ፤ ተመልካቾችም ድጋፍ እንዲሰጡ አስባለሁ፡፡ በአጠቃላይ መልካም ነገር እመኛለሁ። ዋሊያዎቹ መልካም ነገር እያስመዘገቡ ነው የመጡት፡፡ አሁንም የምንጠበቀው ይህን ነው፡፡ የአመራር መለዋወጥ ከውጤቱ ጋር ብዙም የሚነካካ ነገር የለውም፡፡
ዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፉ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያመጣል፡፡ እርስዎ ምን ይጠብቃሉ?
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ተመልካች ስታድዬም እየገባ በእግር ኳስ ውጤት እያዘነ የወጣበት ዓመታት ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ተመልካችና ለዚህ ህዝብ ብሄራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፍ መቼም ለሁላችን የሚፈጠረው ደስታ መጠን ያለው አይመስለኝም። እንግዲህ ይህን የሚፈጽሙት ሜዳ የሚገቡት ተጫዋቾች እና የብሄራዊ ቡድኑ አጠቃላይ አባላት ናቸው፡፡ አደራውን ለተጨዋቾችና ለአሠልጣኝ ነው የምሰጠው፡፡ በአጠቃላይ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ በአፍሪካ እና ዓለም ደረጃ ጥሩ ገጽታ ይፈጥርልናል ብዬ ነው የማስበው፡፡
ድሮ ኳስ ስንት ቁጥር ለብሰው ነበር የሚጫወቱት?
በተማሪነቴ ስምንት ቁጥር ለብሼ ነበር የምጫወተው፡፡
ከውጭ ኳስ የማን ጨዋታ ደስ ይልዎታል?
የእንግሊዝ እና የስፔን ክለቦችን በብዛት እከታተላለሁ፡፡
የሚያደንቁት ተጫዋችስ?
በፊት ለአርሰናል ይጫወት የነበረው ሄነሪ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሮናልዶና የሜሲ አጨዋወት በጣም ይስበኛል፡፡
ዋልያ የሚለው ቅፅል ስም ተስማምትዎታል?
በአገራችን ያለ ብርቅዬ እንስሳ ስለሆነ አዎ ለአለም ላይ የቱሪዝም ሃብታችንን ማስተዋወቅ ነው፡፡
የድሬድዋ ሰው ኳስን የሚወደው በምን የተነሳ ነው?
ድሬዳዋ ሜዳው ለጥ ያለ ነው፡፡ አሸዋ ነው፡፡ ብትወድቅም ብትንከባለልም፡፡ የሚወስደን ጐርፉ ብቻ አይደለም፡፡ አሸዋውም ላይ ኳሱም አለ፡፡ ህዝቡ በተፈጥሮው ለፊልም፣ ለቲያትር በአጠቃላይ ለጥበብ የተሰጠ ነው፡፡ ባህሉ ሰውን የሚያቀራረብ ነው፡፡ ድሬደዋ ለጅቡቲ ካላት ቅርበት በብዙ መልኩ የአለምአቀፍ ዕሳቤ እና ስልጣኔ አላት፡፡ ስፖርት ደግሞ ስልጣኔ ነው፡፡ በስፖርቱ መስክ የሚመዘገብ እድገት እና ለውጥ የስልጣኔ መገለጫም ይሆናል፡፡
ወደ ስፖርት ከገቡ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያት ብዙ አመራሮች በፌደሬሽኑ አስተዳደር ተቀያይረዋል፡፡ እርስዎ የፌደሬሽን አመራር እሆናለሁ ብለው አስበውት ያውቃሉ?
ስፖርት ያረካኝ ነበር፡፡ ስፖርትን ኳስ በመምታት አይደለም የማስበው ከዛ በላይ ነው፡፡ ክለብ ስናቋቁምም ወጣቱ የሚያተኩርበት ነገር እንዲያገኝ ከሚል ነው፡፡ አንዳንዴ ያሰብክበት ብቻ አይደለም የምትውለው ፈጣሪ የትም አውሎ ያስገባኝ የምትልበት ጊዜ አለ፡፡

 

Read 3118 times