Saturday, 26 October 2013 13:52

“…አይወጣኝም ክፉ ነገር”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰላም ነው? ያው እንግዲህ ሰላምታችን “እንዴት ነው፣ በጎ አደርሽ ወይ…” “ትክትኩ ሌሊቱን ቀለል አለህ ወይ…” ምናምን መሆኑ ቀርቶ “ሰላም ነው?” በሚለው ከተጠቃለለ ሰነበተ፡፡
“ሰላም ነው?” ሲባል መልሱ “ምን ሰላም አለ ብለህ ነው?” እየሆነ… አለ አይደል… ዘመናችን በሰላምታችን ውስጥ እየተገለጸላችሁ ነው፡፡
ስሙኝማ…እውነትም ወደ ሚድል ክላስ መቃረባችንን የምናውቀው ሰላም ነው ከመባባል ወጥተን “እንደምን አደርክ?” “እግዜሐር ይመስገን…” ምናምን መባባል ስንጀምር እንደሆነ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡
እኔ የምለው…
ወደ መጣሁባት ምድር
እስክመለስባት በፍቅር
ሰውን ከማስደሰት በቀር
አይወጣኝም ክፉ ነገር፡፡
አይነት መልእክቶች ያሏቸው ክፉን ነገር “ጦሳችንን ይዘህ ሂድ…” ብለን የምናሽቀነጥርበት፣ ደጋጉን ነገር “እሰይ ስለቴ ሰመረ…” እያልን የምንቀበልበት ሥራዎች በዚህ ዘመን ምነው በብዛት አይሰሙምሳ! ነው…ወይስ ለ‘ቢዙ’ አይመቹም!
የምር ግን.. እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ክፉ ነገር’ የበዛ አይመስላችሁም? ማለትማ…አለ አይደል… ሁላችንም ለምን በትንሽ ትልቁ፣ ነገር ነገር እንደሚለን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከተማዋን ዘወር፣ ዘወር ስትሉ’ኮ እዚህም፣ እዛም… ትንቅንቅ፣ ግርግር፣ ጭቅጭቅ ማየት እየተለመደ ነው፡፡
በቀደም የነበርንበት ሚኒባስ ወደ ኋላ ሲሄድ የሆነን ሰው ለትንሽ ይስተዋል፤ ሰውየውም ሾፌሩን “አይተህ አትሄድም እንዴ” ምናምን ይለዋል። በዚሀ ጊዜ ሾፌሩ… ምን አለፋችሁ… በሰውየው ላይ ያዘነበበት ውርዥብኝ… “አዲስ አበባ ገዳይ ጠፋ እንጂ ሟችስ ሞልቶ ነበር… ያለውን የገጠር ሰው የሚያስታውስ ነው፡፡ ደግነቱ ሰውየው ነገሩን ሳያባብስ መሄዱ፡፡
ደግሞ ምን አለላችሁ መሰላችሁ…አንድ የሆነ ነገር ሲከሰት ሰዋችን ደግሞ ሦስት፣ አራት እየሆነ ከበብ፣ ከበብ ማድረግ እየለመደ ነው፡፡ የምር እኮ…ትንሿ ነገር አንድ መለስተኛ ዕድር ሊያቋቁም የሚችል ሰው ትሰበስባለች፡፡ እናላችሁ…አንዳንዴም በቀላሉ “አንተም ተው፣ አንተም ተው…” በመባባል ሊያልቁ የሚችሉ ነገሮች ‘አዳናቂ’ ይበዛና…‘ጎመኑ ይጠነዛል’፡፡
(እኔ የምለው… በከተማችን መኪና አሽከርካሪዎች መካከል ባለ የቃልና የምልክት ስድድብ… እኛን የሚስተካካል አገር አለ? የሚሰቀጥጥ እኮ ነው! “ጎረምሳ፣ ጎረምሳ የሚል…” ምናምን የለ፣ “ሦስት ጸጉር አብቅሎ አራተኛው እየተጠበቀ ያለ…” ምናምን የለ፣ “ገዳም በመግቢያ ዘመኗ…” ምናምን የለ፣ “አጎጠጎጤ እንኳን የሌላት ጩጬ”… ምናምን የለ…አገር ሲሰዳደብላችሁ ነው የሚውለው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ የ‘ጅምላ’ ነገር (‘ሞብ ሜንታሊቲ’ የሚሉት) አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ የሆነ ግርግር ነገር ሲሆን ባለጉዳይና ‘እበላ ባይ’ ይቀላቀልና ነገርዬው ሁሉ ይደበላለቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በየቦታው የምናየው አለመግባባት የሚባባሰው በሚመለከታቸው ሰዎች ምክንያት ሳይሆን በከባቢው ‘ሞብ’ ምክንያት ነው፡፡
እናማ…
…መጨቃጨቅ ይወገድና
ሰላም ይሁን ለሁላችን
መሰል መልእክቶች ያሏቸው ሥራዎች የሚያስፈልጉን ጊዜ ላይ ነን፡፡
ደግሞላችሁ…
ጥፋት እንዳለብኝ ይቅርታ
ንገረኝ ምንድነው ዝምታ
መሰል መልእክት ያላቸው ግጥሞች ዘንድሮ…አለ አይደል…በጣም በሚያስፈልጉን ጊዜ፣ ምነው ብዙም የማንሰማቸውሳ! ዘንድሮ የሆነ ጥፋት አጥፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ‘ጎጂ ባህል’ አይነት ሆኗል። ልክ እኮ “ይቅርታ፣ አጥፍቻለሁ…” ማለት የራስን ‘ክብር’ ዝቅ እንደማድረግ አይነት ነው የሚመስለው፡፡ ከ‘ቦሶቻችን’ እስከ እኛ ተራዎቹ ድረስ…“ይቅርታ…” የሚለው ቃል ከመዝገበ ቃላታችን የጠፋ ይመስላል።
የሆነ መስሪያ ቤት ጸሀፊ የሰውየውን ስም ስትጠራ በተወሰኑ ቃላት ለውጥ ‘እትብቱ የተቀበረበትን’ ቦታ ወደሌላ ስፍራ ትወስደዋለች። እናማ…“ይቅርታ…” እንደ ማለት ጭራሽ ሳቋን ታስነካዋለች፡፡ ሰውየው ለአለቃዋ ይነግርና ሰው በተሰበሰበበት “ይቅርታ…” እንድትል ተደረገች፡፡
የስም ነገር ካነሳን አይቀር…ስሙኝማ፡፡ አንድ ሰሞን በአንዳንድ የዚቹ አገር ክፍሎች አገልግሎት ለማግኘት ስም እስከ አያት ድረስ ይጠየቅ ነበር አሉ። (አሁን ቀረ…ወይስ ብሶበታል?) ድካም ይሆናል እንጂ እናውራ ከተባለ እኮ ስንት የሚወራ ጉድ አለን መሰላችሁ! ይሄ የዘመድ አዝማድ አመላከከት ብዙ ቦታ እያስቸገረን ስለሆነ ነው የምንደጋገመው፡፡
እናማ…በየትኛውም ስፍራ ስም ሲወጣ ዋናው ምክንያት ለመለያነት ነው፡፡ አለቀ! ደቀቀ! ዮሐንስም ተባል…ቢቂላም ተባለ…ደንቦባም ተባለ…ሰጥአርጋቸውም ተባለ…ስም የአንድ ሰው መለያ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ስም ከመጠሪያነት አልፎ… አለ አይደል… ‘በር ለማስከፈት’ና ‘በር ለማስጠርቀም’ ምክንያት ሲሆን “ኧረ ምን እየሆንን ነው?” ያሰኛል፡፡ ባለፉት ዘመናት እንዲሀ አይነት ስምን ‘በር ለመክፈትና ለመጠርቀም’ መጠቀም የነበረ ቢሆንም…ዘንድሮ ታች፣ መንደር ድረስ መውረዱ ሊያሳስበን ይገባል፡፡
የምር እኮ…ካነሳነው አይቀር…ዘንድሮ ስለ አንድ ሰው ባህርይና አመለካከት አስተያየት የሚሰጠው በስም ሆኗል፡፡ “እከሌ ይባላል…” “እከሊት ትባላለች…” ሲባል ወዲያውኑ የሰውየውን ስም በተዘጋጀ የሀሳብ ፎርማችን ላይ እንሞላዋለን፡፡ ከዚያ በኋላ ሃሳብ የሚያሰጠው፣ ሥራ የሚያሠራው፣ ትችት የሚያሰማው፣ ድጋፍ የሚያደርገው…ምን አለፋችሁ…ሁሉንም እንቅስቃሴ የሚያደርገው ‘ሰውየው’ ሳይሆን ‘ስሙ’ ይሆናል፡፡
ብዙም ሩቅ በማይባል አንድ ጊዜ፣ አንድ የምናውቀው ሰው የሆነች እንትናዬ ላይ ‘ጆፌ ጥሎ’ ሲያንዣብብ ይከርምና ጫፍ ላይ ያርፋል። ቂ…ቂ…ቂ…(አሁን ልክ እኛ ዓለም ዋንጫ ‘ጫፍ’ እንደ ደረስነው!) ታዲያላችሁ…ይሄን ሁሉ ጊዜ የሚያውቀው ዋናውን መጠሪያ ስሟን ሳይሆን ‘ባክአፕ’ ስሟን ነበር፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን እውነተኛ መጠሪያ ስሟን ከሌላ ይሰማል፡፡
እናማ… ምን ቢል ጥሩ ነው…“አንተ ያቺ እንትና ስሟ እንትና ነው እንዴ!” አለላችሁና…በቃ የፕሮጀክት ትግበራውን አቆመዋ! ስም…ለእንትንዬ ‘ነገራ ነገር’ እንኳ መመዘኛ ሲሆን አያሳዝንም!
ከዓመት ምናምን በፊት ለምሳ የሆነ ቦታ ገብተን አሳላፊ እስኪመጣ እንጠብቃለን፡፡ ያለማጋነን አምስት ደቂቃ ያህል ጠብቀናል፡፡ ወዲያው የሆኑ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያወሩ ገቡ፡፡ ገና ተቀምጠው ሳያበቁ ሁለት አሳላፊዎች አጠገባቸው ደርሰዋል፡፡
እናማ…እንደ ስም ሁሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋችን አገልግሎት ለማግኘትና ላለማግኘት ምክንያት ሲሆን በጣም፣ እጅግ በጣም ያሳዝናል። ለ‘አፋቸው ያህል’ እንኳን… “ይህ ጥሩ ምልክት አይደለም…” የሚሉ ‘ቦሶች’ በብዛት አለማየታችን ደግም…አለ አይደል…“አይ አንቺ አገር!” የማንልሳ!
እናማ…የከፉ የሚመስሉ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ክፉ ነገሮች ‘ጦስ ጥምቡሳሳችንን’ ይዘው የሚሄዱበትን፣ ደጋግ ነገሮች ልባችንንና ቤታችንን የሚሞሉበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!
ወደ መጣሁባት ምድር
እስክመለስባት በፍቅር
ሰውን ከማስደሰት በቀር
አይወጣኝም ክፉ ነገር፡፡
የሚለው ስንኝ የሁላችን ድምጽ የሚሆንበትን ጊዜም ያቅርብልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4167 times