Saturday, 26 October 2013 13:50

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(3 votes)

የጉዞዬ ማስታወሻ -አጄ!
በአባ ገዳ ሥርዓት ላይ የተመሰረተው የአጄ ማህበር!
“ወፍጮ ካለ ህይወት አለ!”
ድሮ ናዝሬት እያለን ከሻሸመኔ ለከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት የሚመጡ የሻሸመኔ ልጆች ነበሩ። በቀላሉ ከሰው ይግባባሉ፤ ናዝሬት በወሬ ደረጃው የምናውቀው ሻሸመኔ ከአዋሳ ወደ አ.አ ለሚመጣ ሰው ዋና የገበያ ቦታ መሆኗን፣ ኮረዶች የሴትኛ አዳሪነት ኑሮ ለመጀመር ከናዝሬት ወደ ሻሸመኔ ይጐርፉ እንደነበርና ሲያድጉ ወደ አዲሳባ እንደሚሄዱ ነው፡፡ አጄ የምትባለው ከተማ አለች፡፡ በቅሎ አላት… ጤፍ አላት፡፡ በተለይ ሻላ የምትባለው አካባቢ የተፈጥሮ ፀጋ አለው፡፡

የኡታ ዋዩ ማህበር ሰብሳቢው አቶ አማን አሊ -እንዲህ ይላሉ፡- አመሰራረቱ ፤ቀደም ሲል በነበረው የአባ ገዳ ስርዓትና ልምድ መሰረት ነው፡፡ በየ15 ቀን የኡታ ዋዩ ኮሚቴ አባላት ይሰበሰባሉ፡፡ የማህበረሰቡን ችግር እየጠየቁ ይፈታሉ፡፡ 2001 ዓ.ም ላይ በማህበር መልክ ማደራጀትና ማቋቋም አለብን፡፡
በተለይ ጎጂ ባህልን ማስወገድ ትኩረታችን ነበር። ከእየሩሳሌምና ሲዲአይ ጋር ተደራጀን፡፡ 40 ቀበሌ ማህበራት አሉን። የነዚህን ሁለት ሁለት ተወካዮች ጠርተን ፤ (ያኔ ሻላ ወረዳና ሲራሮ ወረዳ አንድ ላይ ነበሩ) 80 አባላት ያሉት ማህበር ሆነ-አባገዳዎች አሉት። ከእነመራሮቹ 93 ማለት ነው፡፡ ሃያ ሃያ ብር መዋጮና እስከ አንድ ሺህ ብር አክሲዮን ሂሳብ አደረግን፡፡ ሁሉም እንዳቅሙ!
በጎጂ ልምድ ማስወገድ ዙሪያ እናትና አባት የሌላቸው ህፃናትን እንርዳ የሚል መርህ ላይ ተመርኩዘን፣ ከ40 ቀበሌ ገበሬ ማህበር (ወደ 60 ኪ.ሜ የሚራራቁ) ትንሽ ቀረብ ቀረብ ከሚሉ 80 ህፃናትን መልምለን፤ወይ አባት ወይ እናት ወይም ሁለቱንም የሌላቸውን፤ የመጨረሻ ደካማ ቤተሰቦች (ከሁለቱ ወረዳዎች ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች (የወረዳው ቀበሌ ፤የከተማ አባላት፣ የሴቶች ጉዳይ ከአስተዳደር ከፖለቲካ ጋር በመስማማት) ተመልምለው እንዲመጡ አደረግን። (የወረዳው ቀበሌ፣ የከተማ አባላት፣ የሴቶች ጉዳይ፤ ከአስተዳደር፣ ከፖለቲካ ጉዳይ ወዘተ...) የተቀናጀ ስራ ነው፡፡
የእኛ ወረዳ ልዩ የሚያደርገው የፀጥታ ጉዳይ ነው። አጎራባች ቦታዎች ግጭት ነበራቸው፡፡ ይህን የሚፈቱ አባገዳዎች (የኮሚቴ አባላት ናቸው) ችግሩን ፈቱት፡፡
“ከነሱ ጋር ምን ሰራችሁ?”
“ብዙ የልማት ስራዎችን ! 60 ኪ.ሜ ርቀት ግሪሳ ላይ ት/ቤት ሰርተናል፡፡ 200 ተማሪዎች እስከ 3ኛ ክፍል አስተማሪ ቀጥረንላቸው በመማር ላይ ናቸው፡፡ (2002 ዓ.ም ነው)፡፡ ጥሪባ ቀበሌም እንደዚያው፡፡ ደጆ ቀርጠፋም እንደዚያው፡፡
“ሌላስ?”
“ግምባታ! ከከተማ መስተዳደር ጋር በመተባበር 2000 ካ.ሜ ቦታ ጠይቀን አግኝተናል፡፡ 95 ቆርቆሮ ገዝተን፣ ቤት ሰርተን ሁለት ወፍጮ ተክለናል፡፡ ሆኖም ትራንስፎርመር ባለመገኘቱ ስራው አልተጀመረም!...
15 ስሪ አጦችን ራሳቸው ስራ ፈልገው እንዲይዙ አድርገናል- በስልጠና!
የዶሮ እርባታና ቁጠባ ለ15 ሰው ሰው ሰጥተናል
በሊስትሮነት 10 ልጆች ሰልጥነዋል!
10 ኮረዶች በግድ ሊዳሩ የነበሩ፣ ትምህርት ያቋረጡ፣ ለኛ ባመለከቱት መሰረት እንዲማሩ ት/ቤት አስገብተናል (ከ2ኛ -10ኛ ክፍል ደርሰዋል)
በሹፍርና ስራ 3 ልጆች ሰልጥነው አስተምረን ስራ አግኝተዋል!
የፋክስ ማሽን ኮምፒውተር፣ ካዝና አደራጅተናል። የቢሮ ዕቃ አሟልተናል! ዘመናዊ ሂሳብ እየተጠቀምን ነው!
ያለበትን ቦታ ይሄን ጊቢ የሰጠን መዘጋጃ ነው!
ወ/ሮ ማሚና ደቻሳ፤ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አስገራሚ አቅም ይታይበታል፡፡ ይህን ትላለች፡- “የኡታ ዋዩ ማህበር አባል ነኝ፡፡ ከተለያዩ ቀበሌዎች ተውጣጥተን ነው የመጣነው !ልናለማ! አባ ገዳዎች ስራ ሰርተዋል! የተመደብኩት ቀበሌ ሄጄ ልጆቹ እመለምላለሁ፡፡ በየቤቱ እየዞርኩ፤ በበጎ ፈቃደኝነት! ሁላችንም በጎ ፈቃደኞች ነን! ዘመዴ፣ወገኔ ሳንል እናት የሌላቸውን ህፃናት፤ በእኩል ዐይን፤ የዐርባ ቀበሌ ህፃናት። ትምህርት እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡
መኪና የሚገባበት በመኪና፣ በእግር በሚደረስበት በእግር እየሄድን እንሰራለን፡፡ በግል ኪሳችን፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡
“ኡታ ዋዩ ምን ማለት ነው?”
“ኡታና ዋዩ ሁለት ወንድማቾች ናቸው! ታላቅና ታናሽ! በትውልድ የዘር ግንድ ናቸው!”
“ሁላችሁም ኡታ ናችሁ?” አልኳቸው፡፡
“አዎ፡፡ ዋይዎችም አሉ”
ቡሽራ ኡኩሌ ናቸው የቁጥር ኮሚቴ ሰብሳቢ። “ከጄክዶ ሲዲአይ ጋር ሆነን ህፃናትን ረዳን፤ የደከሙ አረጋዊያንን አግዘናል፡፡ ወላጅ ልጆች ያጣ ቤተተሰብ ፍየል እየሰጠን ፍየል እንዲገዙ፣ እንዲጠቀሙ አመቻቸን።
ዋናው ነገር ትምህርት ነው- ልጆቹ የሚማሩት በላስቲክ ቤት ነው! ዳስ ውስጥ ናቸው! ት/ቤት አልተሰራም - ት/ቤት ለላጆ አስረክበናል!
ችግሩን ህዝቡ ለእኛ ያለቅሳል-ልጆቹን ማየታችሁ ጥሩ! ግን እኛ አንታያችሁም? ረዳን፡፡ እኛ ራሳችን፤ ራሳችንን መርዳት አለብን!
ወፍጮ ካለ ህይወት አለ! ትራንስፎርመር ካገኘን አገር ይለወጣል! (ከ2002 ጀምሮ - ብር ይዞ ወፍጯችን ተቀምጧል) ጄክዶ እንኳን ቢሄድ መንግሥትንም ባለሃብቶችንም አማክረን - ከአላህ ጋር ብዙ እንሠራለን… መጋዘን እንገነባለን፤ የእህል ግዢ አካሂደን ብዙ እናተርፋለን/ህብረተሰቡን እናግዛለን፡፡ ራሳችን ኤን.ጂ.ኦ (NGO) እንሆናለን ነገ!
በስብሰባችን ውስጥ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊው ተገኙ፡፡ ትልቅ ምሥራች ነው! ተጋግዘው እንደሚሠሩ አይቻለሁ፡፡ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊው፤ በቅርብ ተባብረው እንደሚሠሩና አብረው ለውጥ እያመጡ መሆኑን አረጋግጠዋል! “ኡታ ዋዩ ከተቋቋመ በኋላ ጐጂ ባህልን በማስቀረት ረገድ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ግርዛት፣ ጥልፊያና ውርስ ላይ ድንቅ ሠርተዋል፡፡ Remote (ሩቅ) ቦታ በመሆኑ ሥራ-አጥ ይበዛል! ኃይልም የለም፡፡ የማህበሩ ጠቀሜታ እዚህ ጋ ነው!”
“ገበሬውስ እንዴት ያየችኋል?”
“ገበሬው፤ የሚያስፈልገውን አወያዩን ጐናችሁ ነን!” ነው የሚለን፡፡
“ህዝቡ እናንተ ላይ እምነት አለው?”
“ልክ እንደ መንግሥት ነን እኛ!! መንግሥት እኛን ይዞ ነው ያለው-ወረድ ብሎ!”
አንዷን የሥራ አመራር ኮሚቴ አባል፤ “እናንተ ናችሁ ለመንግሥት የምትሠሩት፣ ወይስ መንግሥት ነው እየሠራላችሁ ያለው?” ብዬ ጠየኳት፡፡
“በእኩል ነው ያለነው … በመተባበር እየሠራን ነው”
የቱሪዝምና ባህሉ ኃላፊ፤ ሥራ አጦችን እንድናደራጅ ታስቧል የሚለውን አፅንዖት ሰጥተውታል - እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ ይቻላል ማለት ነው! አሉኝና ቢሮ ውስጥ ያሉትን የባህል ዕቃዎች አሳዩኝ- ሾሌ፣ ጭኮ እሚበላበት፣ ጡንጦ-ጮጮ ነው፣ ሞንቃ - የቀንድ ማንኪያ ነው፡፡
ጉራቲ-ትራስ ነው-200 ነው በጉራጊኛ፤ የሙሽራና ሙሽሪት መተሻሻ የቅቤ ቅመም፣ አልባሳትና ጌጣጌጥ … በመገረም አየሁ፡፡
በመጨረሻ፤ “አባት አንድ ነገር ከሠራ ልጁ ያባቱን ፈለግ መከተል አለበት፡፡ በጎ-ፈቃደኝነትን በተማሩት ልጆች መተካት እንፈልጋለን! በዚህ ሥራ አመራር ኮሚቴ እንዲገቡ እንሻለን-እንዲረከቡን!” ያሉኝ ሰብሳቢው ናቸው፡፡ በዚያው ተሰነባበትን፡፡
ቀጣዩ ጉዞዬ ወደ ደብረ ብርሃን ነው!
                                              * * *
የደብረ ብርሃን ጉዞዬ ማስታወሻ
የደብረ ብርሃን ጉዞዬን ልዩ እሚያደርገው ከሌሎች ለእየሩሣሌም ድርጅት ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉ ሁለት ሰዎች ጋር መሄዴ ነው - ሆኖም የሚያስገርም አጋጣሚ በመከሰቱ ሁለተኛው ልዩ የሚያደርገው ነገር ፊቴ ድንቅ አለ! እነሆ፡-
የላፍቶው አቶ መንግሥቴ የዘመኔ (የ60ዎቹ ሰው ነው)
የዱሮው የዕድገት በህብረት የዕድገትና የሥራ ዘመቻ ጓዴ፣ አብሮ ዘማቼ፤ ተድላ ነው፡፡
ወደ ደብረ ብርሃን ስገባ የተቀበለኝ የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ ደግሞ አቶ ዓለማየሁ ኃይሌ-የናዝሬት አፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት ዩኒት-ሊደሬ!
እንዴት ያለ ጊዜ እንዳሳለፍኩ እንደምትገምቱ ባውቅም፤ አሳምሬ እተርክላችኋለሁ!! ደሞ ወደ ደብረ ብርሃን ዞሬ ልተኛ!!
(ጉዞዬ ይቀጥላል)

Read 2701 times