Saturday, 26 October 2013 14:15

“በድንጋይ አትመኩ…” ማለት ምንድን ነው!?

Written by  ገዛኸኝ ፀ.(ፀጋው)
Rate this item
(4 votes)


ሁሉም ድንጋይ ድንጋይ አይደለም
በሰዋዊነት ሲመነዘር፣
ከሰው የሚሻል ድንጋይ አለ፤ ከድንጋይ
እንደሚሻለው የሰው ዘር …
አዋላጅ ሲገኝ… ድንጋይ እትብት አለው
ሶስት ሺ ዘመንን የሚያስር፣
ብልህ ሲጠርበው… ድንጋይ ፍትሕ አለው
የሀገርን እውነት የሚያበጥር፡-
ወላይታን ከትግራይ የሚያዋቅር፣
አማራን ከኦሮሞ የሚያፋቅር፣
ጠያቂ ሲኖር ድንጋይ እውቀት ነው፤ በመላው
ሀገር የሚስተጋባ፣
አዋቂ ካየው ድንጋይ እምነት ነው፤ ሁሉንም
አማኝ የሚያተባ!
እስላም ከክርስቲያን የሚያጋባ፣
በቅዱስ ሳይንስ የሚያግባባ…!
ጠቢብ ሲያየው ድንጋይ ብርሃን ነው፤ የሀገርን
ጨለማ የሚያበራ፣
መራሄ ሲገኝ ድንጋይ ሀር አለው፤ የሀገርን
ድር የሚያደራ፣
አፋርን ከቤልሻንጉል የሚያጋራ፣
ሶማሌን ከሀረሬ የሚያዋራ፣
ደቡብን ከጋንቤላ የሚያዳራ…!
ትርጁማን ሲገኝ፣ ድንጋይ ቋንቋ አለው
አፍሪካን በአንድ የሚያናግር፣
እንኳንስ ለአቢሲኒያው ውላጅ፣ ኩሽን
ከሴማዊው ለሚማግር፣
የትውልድ ሁሉ ልሳን ነው፤ እንደ
አማርኛችን ቅይጥ እግር!
ካልክማ ድንጋዩ እንጀራ ነው፤ ሀገርን
አስምቶ ለሚጋግር…!
(ስለዚህ ወዳጄ…)
በድንጋይ የሚመካ ሰው ነው፣ ያውም
ብልህ አእምሮን የታደለ፣
ግዑዙን አለትን ጠርቦ፣ ‹‹ድንጋይነት››ን
የገደለ!
ከ‹‹ሙት›› ድንጋይ ላይ፣ ሕይወት የዘራ
ህያው ቅሪቱን ያኖረ፣
እንደ አክሱማዊው ምንጅላቴ ፣አለት
በጥበብ ያነጠረ፣
ሀገርን ከአለት የፈጠረ፡፡
ሀገርም በድንጋይ ባይመካ፣ ከድንጋይ
ህላዌን ያስቆጠረ፣
የንጉስ ረምሀይ ሀውልት ሳለ
የተሟሸ ታሪኩን ያኖረ፣
ሰዋዊነትን ከድንጋይ ውስጥ፣ በጥበብ ጨምቆ
የቀመረ…!
የባዜን መቃብር ዕየታየ፤ የዘመን መንፈስ
እንዳረገዘ፣
ካሌብ የቀረጸው የድንጋይ ጣሪያ፣ ዛሬም እኛን
እያፈዘዘ…!
“በድንጋይ አትመኩ!” ማለት ምንድን ነው?
በውቀትና በውነት ለሚዳኝ ሰው፣
የሀገርን መቅን ከማድረቅ ውጭ፣ ጥበብን
በነገር ሳናድሰው…!
ያልገባን ታሪክ ሁሉ፣ ከንቱ ወንጅለን
ከምንገረጣ፣
የሀገርን ሰንደቅ አርማ፣ ከሀውልቱ አናት ላይ
ሳናወጣ፣
የጦቢያን ድንበር የምንኩልበት፣ ቁራጭ
ድንጋይ እንዳናጣ፣
የዕይታ አድማሳችንን አስፍተን፣ ከጠባቧ ኩሬ
እንውጣ!
የመርገም ዶሴያችን ይቀበር፣ ሥልጣኔያችንም
ይምጣ ...

ለጌታው፣ ጅምሩ ‹‹ሊቅ›› ማስታወሻ
(ጥቅምት 1፣ 1999፤ አክሱም፣ የሐ ሆቴል)

Read 3739 times