Saturday, 26 October 2013 14:22

አይስላንድ ድንቅ የስነጽሑፍ አገር!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ሁሉም አይስላንዳዊ መጽሐፍ ይወልዳል”
የሴቶች የፖለቲካ ፓርቲ ያላት ብቸኛ አገር ናት
በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ጥንካሬ ከዓለም ሁለተኛ
በአንድ ፓርቲ ተመርታ አታውቅም - በጥምር ፓርቲዎች እንጂ

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ “አይስላንድ የደራሲያን ሀገር” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሁፍ፣ ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ ከማስረዳቴ በፊት ሀገሪቱን በሚገባ ለማወቅም ሆነ ለጠቅላላ እውቀት ይረዳሉ ያልኳቸውን የተለያዩ ጉዳዮች አቅርቤአለሁ፡፡ ይህ የዛሬው ጽሁፍ ካለፈው ሳምንት የቀጠለና የማጠቃለያ ጽሁፍ ነው፡፡
አይስላንድን በተመለከተ አለም አቀፉ ሚዲያ ሊያወራው የሚችለው ክፉም ሆነ በጐ ዜና እምብዛም አግኝቶ አያውቅም፡፡ ለአለም አቀፉ ሚዲያም ሆነ ለአብዛኛው የአለም ህዝብ አይስላንድ በቅዝቅዜና በበረዶ ግግር መካከል የምታንቀላፋ አንዲት ለሰሜን ዋልታ የቀረበች አውሮፓዊት ሀገር ማለት ናት፡፡ ከተጫናት ቅዝቃዜ መካከል አውጥቶና ላዩዋ ላይ የተጋገረውን በረዶ አራግፎ፣ በጥሞና ላያት ግን አይስላንድ የበርካታ አስገራሚ ታሪኮች ባለቤት የሆነች ሀገር ናት፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚዎች፤ “የአለማችን የፖለቲካ መድረክ እስከዛሬም ድረስ እጅግ በአብዛኛው ወንዶች በመሪ ተዋናይነት የሚተውኑበት መድረክ ነው” ይላሉ፡፡ አይስላንዳውያንን ግን በዚህ ሀሳብ ጨርሶ አይስማሙም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አይስላንዳውያን ባይስማሙ አይፈረድባቸውም፡፡ ለምን ቢባል? በአለማችን ውስጥ በሴቶች የተመሠረቱና በሴቶች የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉዋት ብቸኛዋ ሀገር አይስላንድ ብቻ ናት፡፡ ዛሬ በምድረ አይስላንድ በማንኛውም አይነትና ሁኔታ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች፣ አርባ በመቶ የሚሆነውን ኮታቸውን ለሴቶች የመመደብ ግዴታ አለባቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም አይስላንዳውያን ባካሄዱት ብሔራዊ ምርጫ፣ ወይዘሮ ቪግዲስ ፊንቦጋዶቲርን ፕሬዚዳንታቸው አድርገው መርጠዋቸዋል፡፡ በዚህም በአለም በቀጥተኛ ህዝባዊ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት የመረጡ ዜጐችና ሀገር ተብለው በአለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለመመዝገብ በቅተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም ዮሀና ሲጐሮአርዶቲር፤ የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ጨበጡ፡፡ በዚህም አይስላንዳውያን ተጨማሪ የፖለቲካ ታሪክ ለመስራት በቁ፡፡ አይስላንድ ግብረ-ሠዶማዊነቷን በግልጽ ያወጀችን ፖለቲከኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጋ የሾመች በአለም የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች፡፡ በ2011 ዓ.ም የወጣ አለም አቀፍ ጥናት፤ በዲሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ አይስላንድን ከመላው አለም በሁለተኛ ደረጃ ሲያስቀምጣት፤ በመንግስቷ ግልጽነት ደግሞ ከአለም ሀገራት በአስራ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን መስክሮላታል፡፡
ምርጫን በተመለከተ ጨርሶ ቀልድ የማያውቁ ዜጐች በድፍን አለም ውስጥ አሉ ከተባሉ አይስላንዳውያን ብቻ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ሲደረግ የአይስላንዳውያን ዝቅተኛው ተሳትፎ በአማካይ 81.4 በመቶ ነው፡፡ በድፍን አለሙ እግር እስኪቀጥን ድረስ ሲያስሱ ቢኖሩ፤ እንደ አይስላንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ ከፍተኛ የህዝብ አመኔታ ያላቸው ፓርቲዎች ማግኘት ጨርሶ አይቻልም፡፡
አይስላንድ በሪፐብሊክነት ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት ህዝባዊ ምርጫዎች አንድም የፖለቲካ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ብቻውን መንግስት ለመመስረት አለመቻሉ ከአይስላንድ አስገራሚ የፖለቲካ ታሪኮች አንደኛው ነው፡፡ እስከዛሬም ድረስ አይስላንድ የምትገዛው ወይም የምትተዳደረው በተለያዩ ፓርቲዎች በሚቋቋሙ የጥምር መንግስት ነው፡፡
የአለምን የመከላከያ ሠራዊት ሁኔታ የሚከታተሉ ባለሙያዎች፤ ስለ አይስላንድ የመከላከያ ሰራዊት ሁኔታ የሚያወሩት በመገረም ነው፡፡ አይስላንድ ኔቶ እየተባለ በአጭር ስሙ የሚታወቀው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገር ናት፡፡ ይህ ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን ምንም የሚያስገርም ነገር የለውም፡፡ አስገራሚው ጉዳይ አይስላንድ የኔቶ አባል ሀገር የሆነችው አንድ መቶ እንኳ የማይሞሉ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያ የታጠቁ ጠረፍ ጠባቂዎች በስተቀር አንድም የመከላከያ ጦር ሰራዊት ሳይኖራት መሆኑ ነው፡፡
ይህን ወታደራዊ ሁኔታ በማጤን የአይስላንድ የአየር ክልል “ማርያም ትጠብቀው!” ተብሎ የተተወ ነው ብላችሁ ልትገምቱ ትችላላችሁ፡፡ እውነታው ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ የኔቶ አባል ሀገራት የጦር ሀይል የወራ ተራ እየገቡ የአይስላንድን የአየር ክልል ይጠብቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአይስላንድን የአየር ክልል የሚጠብቀው የጣሊያን የአየር ሀይል ነው፡፡
የአለም አቀፍ ፖለቲካ ነገር ሲነሳ አይስላንዳውያን በ1986 ዓ.ም በዋና ከተማቸው ሬይካቪክ ታላቅ ጉባኤ በማዘጋጀት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገንና የሶቪየት ህብረቱ መሪ ሚካይል ጐርቫቾቭ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ስምምነት እንዲፈራረሙ በማድረግ፣ ለአለም ሰላም የበኩላቸውን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በኩራት ይናገራሉ፡፡
የአለም ሰላምን በተመለከተ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች፤ አይስላንድ ከአለም ሀገራት መካከል እጅግ ዝቅተኛ ወንጀል የሚፈፀምባት፣ እጅግ ከፍተኛ የፖለቲካና ማህበራዊ መረጋጋት ያለባት ሰላማዊ ሀገር እንደሆነች ይጠቁማሉ፡፡
ኢኮኖሚዋን በተመለከተ ያላት ታሪክም ጉደኛ ነው፡፡ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት አይስላንድ ከአውሮፓ እጅግ ደሀ ሀገራት አንዷ ነበረች፡፡ አሁን ይሄ እንደ ተረት ወይም እንደ ጥንት ታሪክ የሚነገር ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ በአለም እጅግ ፍሬያማና ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ አመታዊ ገቢ አላቸው ከሚባሉት ሀገራት አንዷ አይስላንድ ናት፡፡ የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ከሁለት አመት በፊት ባወጣው ሪፖርት፤ የአይስላንድ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 54ሺ858 ዶላር መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡
እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ እስካሁን የቃኘነው አይስላንድ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊና፣ በአለም አቀፍ ግንኙነት ካሏት አሪፍ አሪፍ ታሪኮች በመጠኑ የተጨለፈ ነው፡፡ ከአገሪቱ ታሪኮች ከሁሉም የሚልቀውና አለምን ምንጊዜም አጀብ የሚያሰኘው ታሪኳ ግን በስነ ጽሁፍ ረገድ ያላት ታሪክ ነው፡፡ ይሄን ታሪኳን በአንድ አረፍተ ነገር መግለጽ ካስፈለገ “አይስላንድ ድንቅ የስነ ጽሁፍና የደራሲያን ሀገር!”
በየትኛውም አይነት አጋጣሚም ሆነ ምክንያት ወደ አይስላንድ እግሩ የጣለውና በጣት ከሚቆጠሩ አይስላንዳውያን ጋር “እንዴት ነህ? እንዴት ነሽ?” መባባል የቻለ ማንኛውም ሰው፤ በምንም ተአምር ቢሆን ሊያጋጥመው የማይችለው ሰው ቢኖር ደራሲ አይስላንዳዊ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከቶ እንዴት ይሆናል፣ ብትሉ ነገሩ ቀላል ነው፡፡ ከአስር አይስላንዳውያን ውስጥ ቢያንስ አንዱ ወይም አንዷ መጽሐፍ ጽፎ ወይም ጽፋ ያሳተመ ወይም ያሳተመች ስለሆነ ነው፡፡
በዋና ከተማዋ ሬዳካቪክም ሆነ በሌሎች የአይስላንድ ከተሞች ዞር ዞር ብትሉ ቆጥራችሁ የማትዘልቁት የመጽሀፍት መሸጫ ሱቆችና አሳታሚ ኩባንያዎችን ታገኛላችሁ፡፡ በእነዚህ የመጽሀፍት መሸጫ ሱቆችና አሳታሚ ኩባንያዎች ግድግዳ ላይ ለአፍታ ያህል አይናችሁን ጣል ካደረጋችሁ ደግሞ በአይስላንዲክ ቋንቋ “አድ ጋንጋ ሜድ ቡክ አይ ማጋነም!” የሚል ጥቅስ በብዛት ተጽፎ ታገኛላችሁ፡፡ ትርጉሙ “ሁሉም አይስላንዳዊ መጽሀፍ ይወልዳል፡፡” ወይም በሁሉም አይስላንዳዊ ሆድ ውስጥ መጽሀፍ አለ፡፡” ማለት ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን የአይስላንዳውያን ጥቅስ ማንም አሌ ብሎ ሊሞግተው የማይችለው ሀቅ ነው፡፡ ከጠቅላላው የአይስላንድ ዜጐች ውስጥ አስር በመቶ የሚሆኑት በዘመናቸው ቢያንስ አንድ መጽሀፍ ጽፈው ያሳተሙ ናቸው፡፡ በነፍስ ወከፍ ሲሠላ ከአይስላንዳውያን በስተቀር በርካታ መጽሀፎችን መፃፍና ማሳተም የቻሉ የሌላ ሀገር ዜጐችን ለሞት መድሀኒት ብላችሁ እንኳ በድፍን አለሙ ዞራችሁ ብትፈልጉ እስከወዲያኛው አታገኙም፡፡ መጽሀፎችን ገዝቶ በማንበብ ረገድም አይስላንዳውያን በመላው አለም አቻ የላቸውም፡፡ የስነ ጽሁፍ ህትመቶችን ወደ ሀገራቸው በማስመጣትም አይስላንዳውያን የአለም ቁንጮ ናቸው፡፡
አይስላንዳውያን ደራሲያን ብቻ አይደሉም። የሌሎች ሀገራት ደራሲያንን የስነጽሁፍ ስራዎች በመተርጐም በኩልም የሚስተካከላቸው አንድ ሀገር እንኳ አለማችን ማግኘት አልቻለችም። በነፍስ ወከፍ ሲሰላ እጅግ ከፍተኛ የመጽሀፍ መሸጫ መደብር በመያዝ አይስላንድን በልጦ የአለም ቁንጮ መሆን የቻለ አንድም ሌላ ሀገር እስከዛሬ ድረስ ሊገኝ አልቻለም፡፡
በሬይካቪክ ከተሞች ባሉ የህዝብ መናፈሻ ቦታዎች ውስጥ ያሉ ሁሉም መቀመጫዎች ስማርት ፎን ያላቸው ሰዎች የተለያዩ የመጽሀፍት ትረካዎችን ማዳመጥ እንዲችሉ ተደርገው በእውቅ የተሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ዩኔስኮ ከተማዋን ሬይካቪክን “የስነጽሁፍ ከተማ” ብሎ ለመሰየም በእጩነት መዝግቦ ይዟታል፡፡
በአይስላንድ እንግዳ የሆነና ፀጉሩን ለመቆረጥ ወደ ፀጉር ቤት ጐራ ያለ ማንኛውም ሰው በመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻ የሚቀረብለት ጥያቄ፣ እንደኛ ሀገር ፀጉር ቤቶች የአርሴናል ወይም የማንቸስተር ጉዳይ ሳይሆን ስለ አነበባቸው መጽሀፍቶችና በሀገሩ ስለታተሙ አዳዲስ መጽሀፍቶች ብቻ ነው፡፡
አይስላንድ በአለም ደረጃ የታወቁ ደራሲያንን ማፍራት ችላለች፡፡ ከእነዚህ እውቅ አይስላንዳዊ ደራሲዎች ውስጥ በ1955 ዓ.ም በስነጽሁፍ የኖቤል ሽልማት ያገኘው ደራሲ ሀልዶር ላክስነስ ይገኝበታል፡፡ ሲቲን ስቲይናር የተባለው አይስላንዳዊ ደግሞ የሀያኛው ክፍለ ዘመንን መቆጣጠር የቻለ የዘመናዊ ቅኔ ባላባት ነበር፡፡
በመጨረሻ ጉዳያችንን ለማጠቃለል አንድ ጥያቄ እናቅርብ:- “አይስላንድ ከሌሎች ሀገራት በተለየ ዘመን የጠገበ የስነጽሁፍ ታሪክ ባለቤትና የአለማችን ቁንጮ የስነጽሁፍና የደራሲያን ሀገር ልትሆን የቻለችበት ምክንያት ለመሆኑ ምንድን ነው?” ወጣቱ አይስላንዳዊ ቢዬን ሲጉርድሰን ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ፤ “ሀገራችን አይስላንድ የታሪክ ተራኪዎች ሀገር ናት፡፡ ሲመሽና ቅዝቃዜው ሲበረታ ሰብሰብ ብለን ታሪክ ከመተረክና ሲተረክ ከማዳመጥ በቀር ሌላ ስራ እኮ የለንም!” ለጊዜው ከዚህ የተሻለ መልስ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡

Read 6721 times Last modified on Saturday, 26 October 2013 14:39