Print this page
Saturday, 02 November 2013 11:25

“ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ማህበር ለአባይ” ምን እየሰራ ነው?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

አቶ ዘሪሁን አበበ ይግዛው ይባላሉ፡፡ የአባይን የውሀ ፖለቲካና የታላቁን ህዳሴ ግድብ ማዕከል አድርጐ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመው “የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ድጋፍ ለአባይ” ማህበር የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ ናቸው፡፡ የዛሬ አራት ወራት የተቋቋመው የሙያተኞች ማህበር እንዴት እንደተመሰረተ፣ ስለተመሰረተበት አላማ፣ ማህበሩ እስካሁን ስለተንቀሳቀሰባቸው ጉዳዮች፣ ስለ መስራቾቹና ስለ ወደፊት እቅዶቹ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ ዘሪሁን አበበ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡ አቶ ዘሪሁን አበበ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና በአለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያገኙ ሲሆን የማስተርስ ዲግሪያቸውን በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከስዊዘርላንድ ጄኔቫ አግኝተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባርና የስነ ዜጋ መምህር ናቸው፡፡

“አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ማህበር ለአባይ” (Ethiopian International Professional-support for Abay) (EIPSA) የተባለው ማህበር መቼና በማን ተቋቋመ?
EIPSA (ኢፕሳ) በሚል ምህፃረ-ቃል የምንጠራው ማህበር የተቋቋመው፣ በጁን 22 ቀን 2013 ዓ.ም ነው፡፡ ፅንሰ ሀሳቡን በዋናነት ያመነጩት ዶ/ር በላቸው ጨከነ ከለንደን እና ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ከካናዳ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉት ምሁራን ያላቸውን የግንኙነት መረብ በመጠቀም የተለያዩ በውሀ መስክ ላይ የሚሰሩ ምሁራንን፣ የህግ ባለሙያዎችን፣ የአለም አቀፍ ግንኙነት የፖለቲካ ተንታኞችን፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንን፣ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚወክሉ ግለሰቦችን፣ በተለያዩ የአለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመሰብሰብ መስራች ጉባኤ ተካሄደ፡፡
የት ነው መስራች ጉባኤው የተካሄደው?
መስራች ጉባኤው የተካሄደው በያለንበት አገር “ስካይፒ” በመጠቀም ነው፡፡ ለሚመለከታቸው ከ15-20 ለሚደርሱ ሰዎች ጥሪ ተደረገ፡፡ 15 ያህል ሰዎች ተገኝተው ኢፕሳ ተመሰረተ፡፡ በኋላ ግን ጋዜጣዊ መግለጫ በማውጣት፣ በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ተደረገ፡፡ ከ67% በላይ የሆኑ የማስተርስ ዲግሪ ምሩቃን፣ ከ17-20 በመቶ የሚሆኑ ፒኤችዲያቸውን በተለያየ መስክ የሰሩ ፕሮፌሰሮችና እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ ጥናት የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በማሰባሰብ የተቋቋመ የሙያተኞች ማህበር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ምን ያህል አባላት አሉት?
እውነት ለመናገር ማህበሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳዲስ አባላትን እያካተተ ነው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከመላው አለም የተውጣጡ ወደ መቶ ያህል አባላት አሉት፡፡
በማህበሩ ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊነቱን ወስደው እየሰሩ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በምሰረታው ጊዜ ነበሩ?
እኔ በወቅቱ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ነበርኩኝ፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን እየተከታተልኩኝ ነበር፡፡ ያኔ የማስተርስ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡
የዚህ ማህበር አባል እንድትሆን ማን ነው ያነሳሳህ?
አስቴር አስገዶም ትባላለች፡፡ ስዊድን ነው የምትኖረው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ናት። ጉዳዩን ከህግም ከሳይንስም አንፃር የምታይ ስትሆን ከስዊድን መንግስት ጋር ነው የምትሰራው፡፡ እርሷ ጠቁማኝ አባል ሆንኩና መስራች ጉባኤውን አካሄድን፡፡
ማህበሩ የተቋቋመባቸውን ዋና ዋና አላማዎች ብታብራራልኝ ….
ማህበሩ የተቋቋመባቸው ከአምስት ያላነሱ አበይት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ያማከለ የባለሙያዎች ጥምረት (መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት) ከዚህ በፊት አልተቋቋመም፡፡ ሁለተኛው እና ዋናው፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ግብፃዊያን (ህዝቡ) የሚያውቁት፣ ግብፃዊያን ምሁራን የሚነግሯቸውን እንጂ እውነታውን አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህንን እውነታ ማሳወቅና የአለም አቀፉን ማህበረሰብ አመለካከት መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ፣ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የአባይ ተፋሰስ አገራት ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ ፎረም ያስፈልጋል ብለን አምነን የተነሳን ሲሆን ፎረም ሲኖር የሀሳብ መለዋወጥ ይኖራል፤ ትብብርን ማጠናከር ይቻላል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ አራተኛው፣ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበትና የሚገናኙበት የራሳቸው የሆነ የጋራ መድረክ ስላልነበራቸው እሱን መፍጠር አስፈላጊ ነበር፡፡ አምስተኛው ጉዳይ፣ ከታላቁ የአባይ ግድብ አንፃር የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ባልሆኑ የሌሎች አገር ዜጐች፡፡ የግድቡን መጠን፣ የሚገደብበትን ቦታና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ማለት ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊያን ምሁራን ለመመለስ ታስቦ የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የማህበሩ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ማህበሩ የተለያዩ የራሱ እሴቶች አሉት። በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ማህበር እንደመሆኑ፣ የተለያዩ ምሁራንና ተመራማሪዎች ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት ግድቡን ነው፡፡ ማህበሩ፤ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የምትሰራቸውን ማናቸውም ፕሮጀክቶች (በፖሊሲ ጥናት ሊሆን ይችላል) ላይ ከተለያየ አቅጣጫ እገዛ ለማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን አባላትን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ እያከናወነ ነው፡፡
መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ማህበር ነውና የማህበሩ አመሰራረት በምን ዘርፍ ነው?
እንዳልሽው መቀመጫው እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ነው፡፡ የማህበሩ አመሰራረት ዘርፍ በበጐ አድራጐት ስራ ነው፡፡ በእንግሊዝ ህግ መሰረት እንዲህ አይነት ማህበር ሊቋቋም የሚችለው በዋናነት በበጐ አድራጐት ማህበርነት ነው፡፡ እስካሁን የተሰራው የማህበሩን እግር የመትከል ስራ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢፕሳ አባላት ከአባይ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጽሑፎችን ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ዘርአይ ይህደጐ የሚባሉና በስኮትላንድ አበርዲን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ ምሁር፤ ሶስት የተለያዩ ጽሑፎችን ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር የግድቡ ሁኔታ እንዴት እንደሚታይ ጽፈዋል፡፡ እኔም ግብፃዊያን ምሁራን የሚጽፏቸውንና አባይን የተመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ በግብጽ ጋዜጦች ለሚወጡ ጽሑፎች ምላሽ የሚሆኑ ትንታኔዎችን ጽፌያለሁ፡፡ ካይሮ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ምሁርና የማህበሩ አባልም እንዲሁ በ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣና በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ጽፈዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው፡፡
ማህበሩ የራሱን ድረ ገጽ አዘጋጅቷል፡፡ በቅርቡ ከፍቶ ከግድቡና ከአባይ ውሃ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን መረጃ ወደ መረጃ ቋቱ ያፈሳል፡፡ በሌላ በኩል ዋና ዋና እቅዶች አሉት ማህበሩ፡፡ ጥናታዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት፣ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀትና የህዳሴው ግድብ የሚገነባበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድረስ በመሄድ ማንኛውም አይነት የሙያ እገዛ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ አባላቱ ከአለም አቀፍ ፖለቲካ፣ ከምህንድስና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከመሳሰሉት ባለሙያዎች የተውጣጡ ስለሆነ በእነዚህ ዘርፎች የተለያዩ ስራዎችን ለማከናወን አቅደናል፡፡ በዚህም መንገድ በአባይና በግድቡ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንችላለን፡፡
ሌላው የሰራው ነገር፣ ከብሔራዊ የግድቡ አስተባባሪ ጽ/ቤት ጋር ግንኙነት መስርተናል፡፡ ከተለያዩ ተቋማት ለምሳሌ ከመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ጋር በመደበኛም መደበኛ ባልሆነም መልኩ ግንኙነት ተመስርቷል፡፡
ከኢትዮጵያዊያን ምሁራን በፊት በካይሮ ዩኒቨርስቲ “የአባይ ቡድን” (Group of the Nile) የተባለ የምሁራን ማህበር ተመስርቶ የአባይና የህዳሴ ግድብ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አውቃለሁ። “ኢፕሳ” ከግብፃዊያን አይቶ ነው የተመሰረተው ይባላል፡፡ እስቲ ስለ ናይል ቡድን እና በእንቅስቃሴው ዙሪያ ያለህን መረጃ ንገረኝ …
እንዳልሽው ነው፤ “የናይል ቡድን” በካይሮ ዩኒቨርስቲ ከተለያየ የሙያ ዘርፍ የተቋቋመ ነው፡፡ ከመስኖ ምህንድስና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከመሳሰሉት የተውጣጡ ሙያተኞች ስብስብ ነው። በአጋጣሚ ይሁን ወይም ታስቦበት የአባይ ግሩፕ የሚባለው ስብስብ የቀድሞውን የውሃና የመስኖ ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ነስረዲን አለንአለምን ያካተተ ነው። በነገራችን ላይ ይሄ ቡድን እስካሁን አንድ ጽሑፍ ነው ያወጣው፡፡ እንደምታውቂው የተቋቋመው ኢትዮጵያ ግድብ መገንባቷን ተከትሎ ነው፡፡ ይህ ቡድን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እና ኢትዮጵያ ልትሰራቸው ያሰበቻቸው ሌሎች አራት ግድቦች ማለትም፡- ቤኮ አቦ፣ ናካራዶቢ እና ሌሎች ሁለት ግድቦችን መሰረት በማድረግ አንድ ጽሑፍ አውጥተዋል፡፡
ያ ጽሑፍ ግን የሚያጠነጥነው በአንድ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ የቀድሞ የ1959 ስምምነት እንዳይነካ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ የአለም አቀፍን ህግ ስንመለከት፤ ያ ህግ (ስምምነት) ዋጋ የለውም፤ ምክንያቱም ሌሎቹን ዘጠኙን የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ከአባይ ጋር የተያያዘ ብሔራዊ ጥቅም በትክክል ያገናዘበ አይደለም፡፡ ሌላው አለም አቀፍ ሙያተኞች ያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ ፅሁፍ አዘጋጅተዋል። እነሱ በዋናነት የህዳሴው ግድብ መጠን ማነስ አለበት፤ ምክንያቱም ብዙ ውሃ ይይዛል የሚል ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ጽሑፉ ቢወጣም መሰረተ-ቢስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከምን አንፃር ነው ግድቡ የሚያንሰው የሚለውን ምክንያታቸውን ስናይ፣ ኢትዮጵያ የግብፅ የውሀ ዋስትናን ይዛ ታስቀራለች የሚል ነው፡፡ እነሱ የሚያነሱት የውሀ ዋስትና (Water Security) ፅንሰ ሀሳብ በውል ያልተተነተነ፣ በተለያየ ዘርፍ ያሉ ምሁራን ስምምነት ላይ ያልደረሱበት አሻሚ ፅንስ ሀሳብ ነው፤ ይሁን እንጂ ዞሮ የሚጠጋው ወደ 1959ኙ ስምምነት ስለሆነ፣ ያንን እንድትቀበል ኢትዮጵያን ለመገፋፋት መንግስታቸውን የማነሳሳት ስራ ነው የሚሰሩት፡፡ ያ ደግሞ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም ለዚህ መልስ የሚሆን ፅሁፍ አዘጋጅቼ ለአንባቢያን አብቅቻለሁ፡፡
እስኪ የማህበራችሁ አወቃቀር ምን እንደሚመስል አብራራኝ …
ኢፕሳ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አለው፡፡ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው 10 አባላት አሉት፡፡ ከአስሩ አንዱ ጀነራል ዳይሬክተሩ ነው፡፡ ዋና ፀሀፊ አለው። የፋይናንስ ጉዳዮችን የሚመለከት አንድ ክፍል አለ። እዚህ ውስጥ ሰባት ዲፓርትመንቶች አሉ፡፡ ከሰባቱ አንደኛው የምህንድስና ክፍል ሲሆን ሁለተኛው የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል ነው፡፡ ሶስተኛው የአለም አቀፍ ህግና የአለም አቀፍ ጉዳዮች ክፍል ነው። አራተኛው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ነው፡፡ አሁን እኔ በሃላፊነት የምመራው ክፍል ማለት ነው፡፡ አምስተኛው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ነው፡፡ ስድስተኛ የምጣኔ ሀብት ክፍል አለ። በዋናነት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ማስተባበሪያ አስተዳደር ክፍልም አለ፡፡ በዚህ አወቃቀር ነው የተመሰረተው፡፡
በአሁኑ ሰዓት “ኢፕሳ”ን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ማን ናቸው?
ዋና ዳይሬክተራችን ዶ/ር በላቸው ጨከነ ይባላሉ፡፡ ለንደን ነው የሚኖሩት፡፡ ዋና ፀሀፊያችን ደግሞ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ናቸው፤ ካናዳ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ማህበሩ እንዲመሰረት ሀሳብ ያመነጩም ናቸው፡፡
የማህበሩ አባላት ግድቡን ጐብኝተዋል?
እንደ አጋጣሚ ሆኖ አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባላት የሚኖሩት በተለያዩ የአለም አገራት ነው። በመሆኑም ወደ ግድቡ እስካሁን የሄደ የለም፡፡ ሆኖም በቅርቡ አንዲት አባላችን ከእንግሊዝ ትመጣለች፡፡ ዶ/ር ምንትዋብ ትባላለች፡፡ ዶ/ር ምንትዋብ በዋናነት የምትመራው የምጣኔ ሀብት ክፍሉን ነው፡፡ እኔም እሷም ተነጋግረን አንዳንድ ነገሮችን ለማድረግ አስበናል፤ ነገር ግን በዋናነት ዌብሳይቱ በይፋ ስራ ከጀመረ በኋላ ዳይሬክተሩን፣ ዋና ፀሀፊውን እና ሌሎች አባላትን ጨምረን በግድቡ ዙሪያ ጥናት ለመስራትና በአካል ለመጐብኘት እቅድ ተይዟል፡፡
የማህበሩ የገቢ ምንጭ ምንድን ነው?
እስካሁን ማህበሩ ለሚያስፈልገው አንዳንድ ወጪ አባላት ከኪሳቸው ነው የሚያወጡት፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ማህበሩ በበጐ ፈቃደኝነት እና በበጐ ፈቃደኞች የተመሰረተ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ የአባልነት ግዴታ ምንድን ነው? በተቻለ መጠን ድጋፍ የሚያደርግና የተወሰነ ወጪ የሚሸፍን መሆን አለበት ነው፡፡ እስካሁን ሌላ ገቢ የለውም። ያው አባላት ከኪሳቸው በሚያወጡት ገንዘብ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አሁን ማህበሩ ከተመሰረተ አራተኛ ወሩን ይዟል፡፡
አባላቱ ከሙያቸው ውጭ ሌላ ምን ድጋፍ ይሰጣሉ? ለምሳሌ የፋይናንስ ድጋፍን በተመለከተ ምን ያስባሉ?
ማህበሩ የባለሙያዎች ስብስብ ነው፡፡ ስያሜውም ይህን ነው የሚገልፀው “የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ድጋፍ ለአባይ” ነው የሚሰኘው፡፡ ትኩረት ያደረገውም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እንደመሆኑ፣ በጐ አድራጐት ድርጅቱ ሙያዊ ድጋፍ ነው የሚያደርገው፡፡
ለምሳሌ ጥናታዊ ፅሁፎችን ይሰራል፡፡ አገሪቱ የሰለጠነ ባለሙያ እንዲኖራት የማድረግ አላማን የሰነቀም በመሆኑ የስኮላርሽፕ እድሎችን በማመቻቸት እና ወጣት ምሁራን የምዕራባዊያኑን ልምድ እንዲቀስሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ እንዲህ እንዲህ አይነት ድጋፎችን ይሰጣል፡፡ የንዘብ ድጋፍን በተመለከተ እስካሁን የታሰበ ነገር የለም፡፡ ማህበሩ በቀጣይ የልቀት ማዕከል (Center of Excellence) መሆን ይፈልጋል፡፡ ወደ ልቀት ማዕከልነት ሲያድግ፣ አገሪቷ የምታደርጋቸው ማንኛውም ከውሃ ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለፖሊሲ አውጭ አካላት ድጋፍ ማድረግ፣ እውቀት ለሚሹ አካላትም እንዲሁ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይቀጥላል፡፡
ማህበሩ ሲቋቋም ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ያገኛችሁት ምላሽ ምን ይመስላል?
ከመንግስት በኩል ደስ የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው፤ ምክንያቱም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ የመንግስት ፕሮጀክት ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን፣ ኢትዮጵያዊያንን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የሚቀጥል በመሆኑ፣ ከብሔራዊ የግድቡ አስተባባሪ ኮሚቴም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጐ የሆነ ምላሽና አብሮ የመስራትም አዝማሚያ ታይቷል፡፡
በግብጽ ካይሮ ዩኒቨርስቲ የተቋቋመው የናይል ቡድንም ሆነ የኢፕሳ ምሁራን ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ህዝቡን ለማሳመንና በጋራ ጥቅም ላይ ተስማምቶ ለመስራት ምን ያሰባችሁትን ነገር አለ?
ኢፕሳ ሲቋቋም በዋናነት ይዞ የተነሳው አቋም፣ አለምአቀፍ ህግጋትንና መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አንፃር የተለያዩ ህጐች አሉ፡፡ የተቋቋመበት አላማና አካሄዱ ግን አለምአቀፍ መርሆ ነው፡፡ ያ አለም አቀፍ መርሆ ደግሞ ፍትሀዊና ምክንያታዊ የሀብት ክፍፍል እና የውሃ አጠቃቀምን መሰረት አድርጐ የተነሳ ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የካይሮ የናይል ግሩፕና የኢትዮጵያው ኢፕሳ የሚያራምዱት አቋም በዓለም አቀፍ ህግጋት ስናየው ግራና ቀኝ የሚቆም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምታራምደውና ኢፕሳ የሚያራምደው አቋም ግን አንድ የአለም አቀፍ ህግን መሰረት ያደረገና ተቀባይነት ያለው ገዢ ሃሳብ ነው፡፡ ማህበራችን በአገራት መካከል ግንኙነት መጠንከር አለበት ይላል፡፡ እያንዳንዱ የተፋሰሱ ሀገራት አባይን ፍትሀዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብት አለው፤ ይህ በአለም አቀፍ ህግ የተደነገገ ነው። ስለዚህ ኢፕሳ ከማንኛውም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ከ460 ሚሊዮን በላይ የሆኑ በአባይ ተፋሰስ ለሚኖሩ ህዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ ዓላማው ነው፡፡ አሁን ካለው የአለም የሙቀት መጨመርና ሌሎች ችግሮች አንፃር አገራት ተስማምተው መስራታቸው የአማራጭ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር የተፋሰሱ አገራት የአባይን ውሃ መጠቀም ያለባቸው ፍትሀዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ኢፕሳ ይህን መሰረት አድርጐ ይንቀሳቀሳል። ስለሆነም ወደፊት ከካይሮው የናይል ቡድን ጋር አብሮ የመስራት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 5105 times