Saturday, 26 November 2011 09:16

“ሲጋራ ለማቆም….”

Written by  ዳኒ ኬኩ
Rate this item
(4 votes)

የንፋሱም ነፋስ ምንጩ ደፈረሰ
ምንም ሣንዝናና ፈተና ደረሰ፡፡….. ይህቺ ነገር ሠሞኑን በሲንግል መልክ ካምፓስ ውስጥ ብትለቀቅ ዘፋኙ ለፈተናና ለገና ደህና ጨላ መሠብሰቡ አይቀርም፡ ምክንያቱም ማሜ ስሪቱ /3 2/ እንዳለው “No money no study”……:: ማሜ ስሪቱን በመጀመሪያ ማስተዋወቅ ግድ ይለኛል፡፡ ማሜ ለማጥናት ጫት ሲጋራ ለውዝ …. ያስፈልገዋል፡፡ ፍሬሽ ማን እያለ የፈተና ወቅት ገንዘብ አልነበረውና ውጤቱ አ.ሽ.ቆ.ለ.ቆ.ለ እናም ለቀጣይ ሴሚስተር ውጤቱን 3.2 ለማምጣት “ፕሮቪሽን” ፈረመና ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ መዝናናት ሣያምረው ገንዘብን ሁሉ ሲጋራና ጫት እየገዛ በርትቶ አጠናና 3.2 አመጣ፡፡ ስሙም 3.2 ተባለ፡፡

ስሪቱ ከምንም በላይ ሲጋራ ይወዳል፡፡ ጠዋት ሲጋራ ካላጨሰ ከአልጋው አይወርድም፡፡ ምግብ በልቶ ሲጋራ ካላጨሰ ትርፍ አንጀት የሚይዘው ይመስለዋል፡ …..ማታ ከመተኛቱ በፊትም በሠላም ያዋልከን በሠላም……. የሚለውም ሲጋራ እያጨሰ ነው፡፡ ሲጋራ አታጭስ የሚል ጓደኛ የለውም፡፡ እንደ አፕላይ “አስጭሠን” የሚል እንጂ። አፕላይ የስሪቱ የቅርብ ጓደኛ ነው፡፡ የአፕላይ ትክክለኛ ስሙን ሬጅስትራሎች ካልሆኑ ስሪቱ እንኳ አያውቀውም፡፡ ማንኛውም ሠው ሲጋራ ሲያጨስ ካየ “አፕላይ” በማለት እንዲያስጨሱት “አፕሊኬሽን” ስለሚያስገባ “አፕላይ” ሆኖ ቀረ ስሙ፡ ኧረ እንደሚባለው ከሆነማ ሲጋራ እያጨሰም ቢሆን ሰው አፍ ላይ ሲጋራ ካየ “አፕላይ” ….. ይላል፡፡ 
በሆነ ወቅት ኮናል ዶይል የተባለ ዝነኛና ቀልደኛ ፈረንጅ “ሲጋራ ማጨስን ለማቆም በጣም ቀላል ነው፡እኔ ራሴ 100 ጊዜ አቁሜአለሁ” ብሎ አስፈግጓል፡…ይሄ ደግሞ ከአንድ ትልቅ ሠው አይጠበቅም” …. እያልኩ አፌ ላይ እንደመጣልኝ ስቀበጣጥር…”ባክህ” አለና አፕላይ አቋረጠኝ…. “ባክህ ትልቅ ብሎ ነገር የለም…. ትልቅ የእንትና ጡትና ኣክሱም ብቻ ነው” አለኝ ሲጋራውን እየማገ ፡፡….”እኔ ሴትና ሲጋራ ከወደቂጡ ነው የሚመቸኝ” ይላል “ለምንድነው ሰው የለኮሰውን ሲጋራ ብቻ አፕላይ” እያልክ የምታጨሰው ሲባል። ቢሆንም የሱ ሱስ ከስሪቱ ይሻላል፡፡ ስሪቱ….. ሲጋራውን ለኩሶ ማግ ማግ ያደርግና “ምነው እነዚህ ሲጋራ አምራቾች ረዘም ረዘም እያደረጉ ሲጋራውን ቢያመርቱ” ይላል፡፡
ስሪቱ እና አፕላይ የሚያጨሱት እንደብዙሀኑ የካምፓስ አጪያሽ ያገር ውስጥ ሲጋራ ነው፡፡ እና “ይሄ ሲጋራ አይጎዳችሁም ወይ?” ብላቸው ስሪቱ “አንገቴን አረዘመው” ሲለኝ አፕላይ ደሞ “ቂጤን አጠበበው” በማለት የደረሠባቸውን ጉዳት ነገሩኝ፡ አንድ ሰሞን በኔ ምክር እና በስሪቱ ግልምጫ አፕላይ በሲጋራ ራሱን ለመቻል ወሰነ፡ የግቢው ክሊኒክ ነርስ አፕላይን መርምሮት ሣይሆን አዝኖለት፣ የቲቢ በሽተኞች የሚመገቡትን በፕሮቲን የበለፀገ ምግብ ካፌ እንዲመገብ ጽፎለት ነበረና ያንን የፕሮቲን ምግብ፣ በሚሠጠው ዳቦ ሣንዲዊች ሠርቶት በወረቀት ጠቅልሎ ካምፓሱ ፊት ለፊት የኮንቴነር ሱቅ ላለው ልጅ እየሰጠ በምትኩ ስምንት ሲጋራ መቀበል ጀመረ፡፡ “ይህንን ድርጊት ለአለም ህዝብ ማስተዋወቅ አለብን፡፡” አለ ስሪቱ ከልቡ እየተደሠተ “ለምን?” አልኩት ግራ ቢገባኝ፡፡ “እንዴ….አፕላይ እኮ በአለማችን ፕሮቲንን በኒኮቲን የለወጠ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡” አለኝ፡፡
53 ዓመት ሲጋራ ያጨሱ ሰውዬ አውቃለሁ፡ሰውዬው ሲበዛ እንቅልፋም ናቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲተኙ ነው የሚውሉት፤ መንገድ እንኳ በእግራቸው እየሄዱ በቁማቸው ናፕ ይወስዳሉ፡፡ ባጭሩ የማይተኙት ሲጋራ ሲያጨሱ ብቻ ነው፡፡…. ሲጋራ ለረጅም ጊዜ በማጨሣቸው የአለም ትልቁ ሱስ ያዛቸው፤ ሱሣቸው ለህመም ዳረጋቸውና ታመሙ፡፡ የእንቅልፋምነታቸው ነገርም ተጨማምሮ 24 ሠዓት አልጋ ላይ መዋል ጀመሩ፡፡….. አንድ ቀን እንደተኙ ሣይነቁ መሽቶ ነጋ፡፡ የመንደር አዋቂ ተፈልጎ ተጠራና መጥቶ ሲያረጋግጥ ሞተዋል፡፡ አንድ አልቅሶ የደከመው ሀዘንተኛ ለብርታት ይሁነኝ ብሎ ጓሮ ተደብቆ ሲጋራ ሲለኩስ …. ሞቶ የተባሉት ሽማግሌ የጓሮውን መስኮት ከፍተው ብቅ አሉ፡፡ …..”ሞተው በነበረ ጊዜ ምን ታየዎት?” ሲባሉ….. “ሲኦል ይመስለኛል…. ውስጤን ሀራራ እያቃጠለኝ …. ገላዬን እሣት እየለበለበኝ… ብዙ ሺ ኒያላዎችን ሲጋራ እያጨሱ ሲስቁብኝ……ሣጥናኤል ይመስለኛል በደስታ 2 ጊዜ በሽጉጥ ተኩሶ ግንባሬን መታኝና …. ውፍረቱ እንደእንትን ጡት….. ርዝመቱ ኣክሱምን የሚያህል ሲጋራ ሠጠኝና እንደለኮስኩ ነቃሁ” አሉ፡፡ …. የሚገርመው ነገር ሰውየው 53 አመት ሲጋራ አጭሰው “ሲጋራ ማጨስን ለማቆም በጣም ቀላል ነው፡፡” ይላሉ እሣቸው እንደ ዝነኛው ከናል ዶይል ለማስፈገግ አይደለም፡፡ በሠውየው እምነት ሲጋራ ማጨስን ለማቆም በመጀመሪያ …… አለመጀመር፡፡
“ቢዋሽ ምን አለበት”
“ታዲያ እንዴት ነሽ እያንዳንድሽ….” ይል ነበረ፡፡ ስድስቱንም ሚስቶቹን ሠብስቦ በአንድነት ሠላምታ ሲሰጣቸው፡፡ የጳጉሜው አራዳ፣ የድሮው የቀማኛ አለቃ፡፡ በዚህ ዘመን ውሽማ፣ ቅምጥ፣ የጭን ገረድ፣ ምናምን ሊታሰቡ ቀርቶ አንዷንም በቅጡ ማስተናገድ /ያውም በተማሪ አቅም/ ይከብዳል፡፡….. BPR ፍቅር ላይ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ፣የልቤን የስራ ሂደት የተረከበችው ልጅ እናትና አባቷ በተለምዶ፣ በጨለማ የሚተገብሩትን “ፍቅር” መሠረታዊ የአሠራር ሂደቱን ቀይራ ልታሣየኝ ቀርቶ ፍቅርን ራሱ ለማስጀመር ሂደቱን ወንዝ አድርጋብኝ አበሣዬን እያየሁ ነው፡፡……. በእርግጥ ቴዲ አፍሮንም ብቻ ሣይሆን እኔንም አይናፋርነቴ ጎድቶኛል፡፡ “አይናፋር ነኝ እኔ ከበፊትም” ባልኳት ዐይንህላፈር አለችኝ፡፡ ዐይን አውጣ ሆኜ ስቀርባት ደሞ ራሷ አይኔን ልታወጣው ደረሰች፡፡ ከዛ በኋላ በቃ ቀንደኛ የቸልሲ ደጋፊ ሆንኩኝ፡፡…… “ድሮግባ” ሲናደድ ያፈቀርኳትን ልጅ ስለሚመስል አድናቂው ነኝ፡፡
ትህትና “ውሸታም ነኝ” ብላ ነው የተዋወቀችኝ፡ ቢሆንም አላመንኳትም፡፡ ውሸታም ነቻ….. ከቲቲ ጋር የፍቅር ሣይሆን የምር ጓደኛሞች ነን፤ በፆታና በዲፓርትመንት ከመለያየታችን ውጪ በሌሎች ነገሮች እንመሣሠላለን፡፡ ቲቲ ከመሸ “ጣፋጭ እና “ትኩስ” ነገር አይመቻትም፡፡ እኔም ብሆን ቀዝቃዛ እና ጎምዛዛ ነገሮች ከፀሃይ ይልቅ ለጨረቃዋ እና ለክዋክብቶቹ ይስማሙልኛል፡፡ ቲቲን ስትጠጣ የሚያውቋት“ እንደሠው በምድር እንደአሣ በባህር፤ ሴቷ ኢትአንደር” ይሏታል፡፡ እኔን ደሞ ስጠጣ የሚያውቁኝ “ቲቲ” ይሉኛል፡፡
ከፎቁ ሰገነት ላይ ካለው ካፍቴሪያ እራት እየተገባበዝን እና የሐዋሳ ሀይቅን ፀሐይ ግባት እየታደምን ስንጭዋወት ቲቲ ምን ትለኛለች “በድሮ ዘመን በሐዋሳ ሀይቅ ላይ አንድ ፕሮፌሠር ጥናትና ምርምር አካሂዶ “የሐዋሣ ሀይቅ አሶች ለምግብነት አይሆኑም” አለ፡፡” ….. “ከዛስ?” አልኳት….. “ከዛማ በቃ በጥናትና ምርምሩ የተበሣጩ አንዳንድ ግለሰቦች በእልህ አሣ እያጠመዱ ጥሬውን መብላት ጀመሩ፡፡…. ከዛን ጊዜ በኋላ ፍሌቶ በዳጣ /ጥሬ አሣ በሚጥሚጣ/ መበላት ተጀመረ፡፡ ፕሮፌሠሩም በሀፍረት እንደተሸማቀቀ፣ ፀጉሩ እንደተመለጠ ሁለቱን እጆቹን የኃሊዮሽ አጣምሮ ወደ ወፍነት ተቀየረና አባኮዳ እየተባለ በሀይቁ ዙሪያ ይገኛል፡፡” አለችኝ ይቺ ውሸታም……፡፡
በታሠረ ላንቃ በኮልታፋ አንደበት፣
ፍቅር አቀዣብሮኝ ስንተፋተፍበት፣
ምን ምን እንዳወራው እኔ መች አቃለሁ፣
“አትዋሺ” ስትለኝ ብቻ እሠማሃለሁ፡፡
ኤግዛም ደርሶ ቴንሽን ይዞን እንኳን ለውሃ ሽንት የዘመድ ቀብር ቢኖር ከማልነሣበት ችከላ/ጥናት/ ላይ ቲቲ ደውላ ጠራችኝ ስራ እንደሌለብኝ ዋሸኋትና ሄድኩላት፡፡ “ባይገርምህ” ….. አለችኝ ገና እንደተገናኘን፡፡”ባይገርምህ ዛሬ እኮ ካፌ ገብቼ ምሣ በላሁ፡፡፡” …በአካባቢው “ፓፓራዚዎች”ወይንም ድንቃድንቅ ወሬዎችን የሚያስሱ ሴት የሶሻል ሣይንስ ተማሪዎች አልነበሩም እንጂ የቲቲ ካፌ ገብቶ ከተማሪ ጋር እየተጋፉ የካፖርት ቁልፍ የሚያካክል የአተር ክክ ያለበትን ሽሮ መብላቷ አስደናቂ ነገር ነው፡፡
ቲቲ እጅግ በጣም ሀብታም ቤተሰቦች ያላት ስትሆን ብቸኛ ወንድሟ “አሜሪካ” ነው የሚማረው፡ ውጪ ሀገር እንድትማር ቤተሰቦቿ ቢሹም አሻፈረኝ ብላ ነው ሀዋሣ ዩኒቨርስቲ የምትማረው፡፡…… “ሸገርን ቲቲ አትጠግባትም፤ እኔ የክልል ልጅ እንደመሆኔ አዲስ አበባን በተወሰኑ ልዩ አጋጣሚዎች ነው የማውቃት፡ ለምሣሌ… ፈጣሪ ነብሱን በገነት ያኑርልንና በክብር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ “ፈልጌ አስፈልጌ ያን ሠሞን ያጣኋት” በሚለው የዘፈን ክሊፕ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ብዙ ተቀያይራለች፡፡ ቢሆንም አዲሣባን በቲቲ እንዳወኳት ከሆነች፣ ለኔም ቢሆን ከስቴትም ይሁን ከህንድ አዱገነት ትሻለኛለች፡ …. የሆነው ሁሉ ይሁንና ቲቲ አንድም ቀን ካፌ በልታ አታውቅም፡ ዩኒቨርስቲው ያዘጋጀውን የካፌ ምግብ አንፈልግም ብለው በምትኩ የኮስት ሼሪንግ ገንዝብ እንደሚቀበሉት “Non Café” ዎች አይደለችም፡፡ /ምግቧን ታዲያ የት ትበላለች?/
የስብሰባው አበባ፣የታሸገ ውሃ፣ የስብሰባው አላማ የተፃፈበት ቲሸርት እና ኮፍያ፣ማስታወሻ ደብተር፣ ባግ …. እየተቀበሉ በአበሉ በማህበር ቤት ለመስራት እቁብ የሚጥሉት ወጣት ደሞዝተኞች እንኳን ከማይደፍሩት አሪፍ ሬስቶራንት ወር እስከ ወር ኮንትራት እየከፈለች ምግቧን ትጠቀማለች፡፡ ታዲያ የቲቲ ካፌ ገብቶ ከተማሪ ጋር እየተጋፉ ሽሮ መብላት “ዘ ኢንሣይደር” ላይ መቅረብ ይነሠው….. ነገሩ እየገረመኝ “እንዴት ገብተሽ በላሽ?” ስላት “በቃ …. ድንገት በካፌው ሣልፍ ተማሪዎቹ ገብተው ሲበሉ አየሁና እኔም ገብቼ በላሁ፡ ከዛልህ ሆዴ ቁርጠት በቁርጠት ሆነልህ ጩርር… ምናምን እያለ አላርም ማሠማት እንደጀመረ ወደ ክሊኒክ አመራሁ፡፡ ነርሱ መረመረኝና ለተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ ትንሽዬ ብልቃትና ስቴኪኒ ሠቶኝ ወደ ሽንት ቤት ላከኝ፡፡ “እርሜን” ዛሬ ካፌ ብበላ መታመሜ አናዶኝ ስለነበረ በቀጥታ ወደ ካፌው ኪችን ሄድኩና ትንሽ ወጥ በብልቃጡ ቀንሼ ለነርሱ መለስኩለት፡፡
…… ሀቅ ብለፈልፍ ምን ያደርግልኛል፣
እውነቴን ካላመንክ ብዋሽ ይሻለኛል፣
አንተን ካስገኘልኝ በልጦ ከእውነትነት
ከቶ ቢቀባጠር ቢዋሽ ምናለበት፡፡
ባለፈው ሰሞን ግቢ ውስጥ የሆነ ማስታወቂያ ተለጥፎ ነበረ፡፡ ማስታወቂያው “Non Café” ሆነው ካፌ ሲመገቡ ለተገኙ ተማሪዎች የወጣ የቅጣት ማስታወቂያ ነበረ “Non Café” ሆኖ ካፌ ሲመገብ የተገኘ ተማሪ የሚደርስበት የመጀመሪያ ቅጣት “Non Café” መሆኑ ቀርቶ ካፌ እንዲመገብ ማድረግ ነው፡፡….. እኛ ካፌ የምንመገብ ተማሪዎች ሣናጠፋ እየተቀጣን ነበረ ማለት ነው፡፡ ካፌው እንዲህ ማስፈራሪያ እየሆነ መመገባችን ምን ያህል ቆራጥ አላማ እንዳለን ያሣያል፡፡

 

Read 4772 times Last modified on Thursday, 01 December 2011 07:29