Saturday, 09 November 2013 11:17

ለመቀሌ የመጀመርያው ባለ “5 ኮከብ” ሆቴል ሥራ ጀምሯል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)
  • 270 ሚ.ብር የወጣበት ፕላኔት ሆቴል፤ ሁሉ ነገር ሲጠናቀቅ ወጪው 300ሚ. ይደርሳል
  • ባለቤቱ ወደ ንግድ የገቡት 150 ብር ይዘው ነው

ከመቀሌው ሰማዕታት ሐውልት ቁልቁል በእግር 4 ደቂቃ ቢጓዙ፣ እየተገነባ ካለው ስታዲየም ፊትለፊት ግርማ ተላብሶ ያገኙታል፤ ፕላኔት ሆቴልን፡፡ ሆቴሉን ውበት ያጐናፀፈው የሕንፃው ኪነ ጥበብ (አርኪቴክቸር) መሆኑን በምረቃው ላይ የተገኙ ብዙ እንግዶች ገልፀዋል፡፡ እንዲያውም አንድ ከአዲስ አበባ የሄዱ እንግዳ “እንደሳጥን ከቆሙ አንዳንድ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ሕንፃዎች ጋር መወዳደር ብቻ ሳይሆን፣ በውበት፣ አስር እጅ ያስከነዳቸዋል” ብለዋል፡፡ ገና ወደ ውስጥ ሲዘልቁ የተንጣለለ ሰፊ ክፍል (ሎቢ) ያገኛሉ፡፡ ፊት -ለፊት፤ ውሃ በተሞላ ገበቴ መሰል እምነበረድ ላይ የመሬት ቅርጽ የሆነው ሉል በኤሌክትሪክ ኃይል በውሃው ላይ ይሽከረከራል - ከግራ ወደ ቀኝ ወይም ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ።

ግራና ቀኝ ለእንግዳ ማረፊያ የሚያማምሩ ምቹ ሶፋዎች ይገኛሉ፡፡ ትንሽ ራቅ ብሎ ደግሞ ሎቢ ባር፣ የእንግዳ መቀበያና የተለያዩ ቢሮዎች አሉ፡፡ ከሚሽከረከረው ሉል ጀርባ፣ በካርድ የሚሠሩ ሁለት አሳንሰሮች (ሊፍቶች) እንግዶችን ወደተለያዩ ፎቆች ለማድረስ ቆመው ይጠበባበቃሉ፡፡ በሊፍቶቹ መኻል፣ አንደኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው ሬስቶራንት የሚያደርስና እስከ 10ኛ ፎቅ የሚዘልቅ ደረጃ አለ። የሦስተኛው ሊፍት መነሻ ደግሞ አንደኛ ፎቅ ላይ ነው፡፡ ሆቴሉን ልዩ የሚያደርገው 10ኛ ፎቅ ላይ ያለው ስካይ ባርና ሬስቶራንት ነው፡፡ እዚያ ሰገነት ላይ ሆነው መቀሌ ከተማንና ዙሪያ ገባዋን በአራቱም አቅጣጫ እየቃኙ መዝናናት በሀሴት ይሞላል፡፡ ፕላኔት ሆቴል 10 ፎቅና 80 የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ የሆቴሉ ግንባታና የዕቃ ግዢ 270 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፣ ለ140 ዜጐችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ያላለቁ ሥራዎችና ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ ወጪው ወደ 300 ሚሊዮን ብር፣ የሠራተኞቹ ቁጥር ደግሞ ወደ 200 ከፍ እንደሚል የሆቴሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት አቶ ይርዳው መኮንን ገልፀዋል፡፡

አቶ ይርዳው፣ ሆቴሉ የዛሬ ሳምንት በተመረቀበት ወቅት ከስድስት ዓመት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ግንባታው ተጠናቅቆ ለምረቃ በመብቃቱ በጣም መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ይርዳው፣ “በመቀሌ ከተማ የመጀመሪያ የሆነውን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል፣ እንደሚባለው ከሆነ በመቀሌ ብቻ ሳይሆን በትግራይም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም እዚህ የሠራሁት አተርፋለሁ ብዬ አይደለም። ትርፍ ብፈልግማ ኖሮ፣ ገንዘቤን በሦስት ዓመት በምመልስበት አዲስ አበባ እሠራ ነበር። እዚህ የሠራሁት፣ ብዙ ሺህ ወጣቶች ለሰላምና ለዲሞክራሲ በመታገል ሲወድቁ አይቻለሁ፡፡ እኔ ብከስር ገንዘብ እንጂ የሕይወት መስዋዕትነት አልከፍልም፡፡ “ለእነዚያ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው፣ ሰላምና ልማት ላጐናፀፉን ወጣቶች መታሰቢያ፣ ሌሎችም እኔን አይተው፣ የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲሠሩ፣ በልማቱ፣ ፈር ቀዳጅ ለመሆን ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ሳይረጋገጥ ሆቴሉ ባለ 5 ኮከብ መባሉ የከነከናቸው አንድ የሆቴሉ ማኔጅመንት አባል፣ “የሆቴልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ምን ምን ያሟላ ነው ባለ 5፣ 4፣ 3፣…መባል ያለበት’ በማለት የደረጃ መስፈርት እየሰራ ነው፡፡

እኛ ባለ 5 ኮከብ ያልነው፣ ሆቴሉ ሲወጠን ጀምሮ፣ ‘ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ምን ምን ማሟላት፣’ የአገልግሎት አሰጣጡስ ምን መምሰል አለበት፣…በማለት እያሟላን ስለሠራን ነው፡፡ ደረጃው የሚፀድቀው ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መስፈርት መሠረት ታይቶ ‘ይህ ይጐድለዋል አሟሉ፤ ወይም በቂ ነው’” በማለት ሲያረጋግጥ ነው” በማለት ገልፀዋል፡፡ አቶ ይርዳው፣ ስድስት ዓመት ሙሉ ለሦስትና ለአራት ወር ከቤተሰብ ተለይተው ውጭ አገር መቆየት ለእሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው ከባድ ፈተና እንደነበር ጠቅሰው፣ ቤተሰባቸው ባደረገላቸው ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ ለዚህ ውጤት በመብቃታቸው ቤተሰባቸውን ከልብ አመስግነዋል፡፡ የአቶ ይርዳውን ሐሳብ የአራት ልጆች እናት የሆኑት ባለቤታቸው ወ/ሮ ብርክቲ ተጠምቀም ይጋራሉ፡፡ የሆቴሉ ሥራ አልቆ ለምረቃ በመብቃቱ የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው፣ “ባለቤቴ ሦስትና አራት ወር ከቤተሰቡ ተለይቶ ይቆይ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉ በቤት ውስጥ ልጆች እያሳደጉ ውጭ መሥራት በጣም ከባድ ፈተና ነበር፡፡ የልጆች ናፍቆት ከባድ ነበር፡፡ በተለይ ትንሿ ልጃችን ምግብ እንኳ አትበላም ነበር፡፡ ብይ ስንላት፣ ‘እኔ ቤቱንም ምግቡንም አልፈልግም፡፡ አባቴን ብቻ ነው የምፈልገው” በማለት ታስቸግረን ነበር፡፡

ያ ሁሉ አልፎ ለዚህ በመብቃታችን እግዜርን አመሰግናለሁ” ብለዋል፡፡ ዛሬ ዓለምአቀፍ ደረጃ ያለው ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ይርዳው፤ ከ23 ዓመት በፊት ወላጆቻቸውን በግብርና የሚረዱ ወጣት ነበሩ። በቀድሞው አጠራር በአድዋ አውራጃ፣ በኃይሌ ወረዳ፣ በዛታ ቀበሌ በ1960 ዓ.ም የተወለዱት አቶ ይርዳው፤ ወደ ንግድ የገቡት 150 ብር ይዘው ነበር። በ1983 በሕዳር ወር ያቺን 150 ብር ይዘው ወደ መቀሌ ከተማ ሄዱ፡፡ በዚያች ብር የተፈጨ በርበሬ ይዘው እንጢቾ ወደተባለች ከተማ ወስደው መነገድ ጀመሩ፡፡ የንግድ ልምድ ስላልነበራቸው ንግድ የጀመሩበትን ገንዘብ በሙሉ ከሰሩ፡፡ አቶ ይርዳው በደረሰባቸው ኪሳራ ተስፋ አልቆረጡም፤ ለተመሳሳይ ሥራ ወደ አዲግራት ከተማ ሄዱ፡፡ እዚያም አንድ ጓደኛቸው መቶ ብር፣ አጐታቸው ደግሞ 150ብር ብድር አበድረዋቸው በ250 ብር እንደገና ንግድ ጀመሩ፡፡ በዚያ ገንዘብ ማር፣ ጤፍ፣ ቡና… ገዝተው ምዕራብ ትግራይ ሽሬና ሽራሮ ድረስ፣ እንዲሁም ወደ ጐንደር እየወሰዱ መነገድ ጀመሩ፡፡ እንደዚያ እያደረጉ ሲመላለሱ ቆይተው አንድ ሺህ ብር አተረፉ፡፡

ያንን ብር ይዘው ወደ ደሴ ሄዱ፡፡ በዚያን ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ተብሎ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚሸጥ ቡና ነበር፡፡ ያ ቡና ተለቅሞ “ቆሻሻ ቡና” ተብሎ የሚጣለውን ይዘው ወደ ሽራሮ እየወሰዱ መሸጥ ያዙ፡፡ በዚህ ዓይነት ሦስት ጊዜ ተመላልሰው ሲነግዱ ቆይተው፣ በአራተኛው ወደ ደሴ ሲመለሱ የቡናው ዋጋ ጨምሮ አገኙት፡፡ እሳቸው የሸጡት በ10.50 ሆኖ ወደ ደሴ ሲመለሱ 11 ብር ሆኖ ጠበቃቸው እስቲ አዲስ አበባ ልሞክር ብለው ሲመጡ የባሰውኑ 12 ብር ሆነባቸው፡፡ ይህ የሆነው በ1986 መስከረም ወር ነው፡፡ ጊዜው የት/ቤት መክፈቻ ስለነበር ደብተር ገዝተው ተመለሱ፡፡ ከደብተሩ ግን ትርፍ አላገኙም፡፡ ቡናውም፣ ደብተሩም ስላላዋጣቸው ወደ ሞያሌ ሄዱ፡፡ ከኬንያ ቆርቆሮ፣ የተለያዩ የፕላስቲክ ውጤቶችና ሌሎች ዕቃዎች እየገዙ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት መነገድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ዓይነት ለብዙ ዓመት በፍራንኮ ቫሉታ ሲሠሩ ቆይተው፣ ካፒታላቸው ጠርቀም ሲል ወደ ጅጅጋ ሐርትሸክ አመሩ፡፡ ነገር ግን እዚያ አልቀናቸውም፡፡ መንግሥት ንግዱን ሥርዓት ለማስያዝ፣ በፍራንኮ ቫሉታ የነበረውን በኤልሲ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) እንዲሠራ መመሪያ አወጣ፡፡ ይህ አሠራር ስላልተመቻቸው፣ ወደለመዷት ሞያሌ ተመለሱ፡፡ እዚያም ስላልተመቻቸው ወደ ዱባይ እየተመላለሱ መነገድ ጀመሩ፡፡ በዱባይ ብቻ አላቆሙም፡፡ ወደ ኢንዶኔዢያ ጃካርታ በመሄድ የተለያዩ ጨርቆች፣ ሸቀጣሸቀጥ፣ ሳሙና… እያመጡ መነገድ ያዙ፡፡ በዚህ ዓይነት ሲሠሩ ቆይተው፣ የንግድ ዘርፋቸውን ሙሉ በሙሉ ቀይረው ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ገቡ፡፡ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ ብረታ ብረት፣ ላሜራ፣ ሲሚንቶ እያመጡ መነገድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ዘርፍ እስካሁንም እየሰሩ ነው፡፡

ጋልቫናይዝድ ፓይፕ የውሃ መስመሮች ከሕንድ፣ ብስኩቶች ከቱሪክ፣ ያስመጣሉ፡፡ በአጠቃላይ፣ “ይርዳው አስመጪና ላኪ”፣ “ይርዳው የሱፐር ማርኬት ዕቃዎች አስመጪ” እና “ቢነር የጉምሩክ አስተላላፊ” የተባሉ ድርጅቶች አሏቸው - አቶ ይርዳው መኮንን፡፡ ፕላኔት ሆቴል አምስት ዓይነት አልጋዎች አሉት፡፡ ኤግዚኩቲቭ የሚባለው ሰፊ ክፍል ሲሆን፤ ሳሎን፣ ወጥ ቤትና፣ ሁለት መኝታ ክፍሎች አሉት። አንደኛው ክፍል ሁለት የልጆች አልጋ ሲኖረው ዋናው መኝታ ቤት ደግሞ ባልና ሚስት የሚተኙበት ነው፡፡ ይህ ክፍል ቪ አይ ፒ እንግዶች ከቤተሰብ ጋር ሲመጡ የሚያርፉበት ነው፡፡ ይህ ክፍሉ የግል ጃኩዚ፣ ስቲም ባዝና ሻወር አለው፡፡ ዋጋው ከቁርስ ጋር 3ሺህ ብር ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ሱት የሚባለው ክፍል፣ አንድ አልጋ ሲኖረው ጃኩዚና ስቲም ባዝ አለው፤ ዋጋው 1,500 ብር ነው፡፡ ስታንዳርድ ኩዊን የሚባለው ክፍል ሁለት አልጋ ስላለው ጥንድ ሆነው የሚመጡ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ኖርማል ሻወር ሲኖረው ዋጋው ደግሞ 1,100 ብር ነው፡፡ ስታንዳርድ ኪንግ የሚባለው ክፍል የራሱ ጃኩዚ አለው፡፡ ሁሉም ክፍሎች በረንዳ፣ ስልክ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የጥርስ ቡሩሽ ሳሙና፣ የፀጉር ሻምፖ፣ ሎሽን፣ ፀጉር ማድረቂያ፣ የሌሊት ልብስ (ጋዋን) ነጠላ ጫማ… አላቸው፡፡ በሆቴሉ ያደሩ እንግዶች በሙሉ፣ ኢንተርኔት፣ ጂም፣ ስቲም፣ ሳውና ባዝና ጃኩዚ፣ መዋኛ ገንዳ፣ ፑል ባር፣ ከሆቴል አውሮፕላን ማረፊያ ነፃ ትራንስፖርት መጠቀም ይችላሉ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይሄ ዓለምአቀፍ ደረጃን ያሟላ ዘመናዊ ሆቴል የመኪና ማቆሚያ የለውም፡፡ አቶ ይርዳው፣ ያለባቸውን ችግር ለሚመለከታቸው ክፍሎች አስረድተው ከኋላ ያለው 2ሺ ካ.ሜ ቦታ እንዲሰጣቸው ማመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡

Read 8184 times