Saturday, 09 November 2013 11:57

የገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት በዱላ ቅብብል ውድድር ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ማራቶን የማዘጋጀት ሃሳብ አላቸው

                በሀዋሳ ከተማ የተገነባውን ገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት ህዳር 14 በይፋ ሲመረቅ ልዩ የ10 ኪሎሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር እንደሚካሄድ ታወቀ፡፡ በምረቃው ስነስርዓት ላይ በክብር እንግድነት እንዲገኙ ኡጋንዳዊው የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን የማራቶን ድርብ አሸናፊ ስቴፈን ኪፕሮች እና ኬንያዊ አትሌት ጄፈሪ ሙታይ ተጋብዘዋል፡፡ በሌላ ዜና ባልና ሚስቶቹ ማራቶኒስቶች አትሌት ገዛኸኝ አበራ እና አትሌት እልፍነሽ አለሙ በሚቀጥለው ዓመት አንድ የማራቶን ውድድር በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ማሰባቸውን ሲያስታወቁ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት የአገር ውስጥ ውድድሮች መብዛታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ስላመኑበት የነደፉት እቅድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አትሌት ገዛኸኝ አበራ እና አትሌት እልፍነሽ አለሙ ትናንት በዋና ፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ የሆቴልና ሪዞርት ምረቃው ከአትሌቲክስ ውድድር ጋር ማያያዝ ያስፈለገው ተተኪ አትሌቶች የእነሱን አርዓያ እንዲከተሉ ለማነሳሳት በማሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አትሌት እልፍነሽ አለሙ‹‹ ማንኛውም ሰው ዓላማዬ ብሎ ከሰራ ለየትኛውም ደረጃ ይደርሳል፡፡ በአሁን ዘመን ያሉ አትሌቶች ደከመን፣ ሰለቸን፤ ከሳን ፤ ጠቆርን ሳይሉ በትጋት መስራት አለባቸው፡፡ በስፖርቱ እኛ የደረስንበት ስኬት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከእኛ በላይ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው›› ብላለች፡፡ አትሌት ገዛኸኝ በበኩሉ ‹‹እኛ ሮጠን ሆቴሉን ሰርተናል፤ አትሌቱም እንደማንኛውም ህብረተሰብ በትጋት ከሰራ ይሳካለታል፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ በሆቴልና ሪዞርቱ ምረቃ ላይ የሚካሄደው የ10 ኪሎሜትር የዱላ ቅብብል ውድድሩ መነሻውና መድረሻው ገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት እንደሆነ የገለፀው አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ አንድ ክለብ ሁለት ሴት እና ሁለት ወንድ ባጣመረ የአራት አትሌቶች ቡድን ይወዳደሩበታል ብሏል፡፡

በዱላ ቅብብል ውድድሩ ለመሳተፍ 8 ክለቦች ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን የመከላከያ፤ የማረሚያ፤ የፖሊስ፤ የሙገር እና ሌሎች የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አሸናፊ ሊሆን የሚበቃው ቡድን የመጨረሻ ሯጭ የውድድሩ ርቀት ቢያንስ 100 ሜትሮች ሲቀሩት ለገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት ለሚጋበዘው የክብር እንግዳው የምረቃ ሪበኑን እንዲቆርጥ የሚያስረክበበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አትሌት ገዛኸኝ አበራ ገልጿል። አንደኛ ለሚጨርስ ቡድን 7ሺ ብር ፤ ለሁለተኛ 5ሺ ብር እንዲሁም ሶስተኛ ለሚወጣው ቡድን 3ሺ ብር ይበረከታል፡፡ ገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት አትሌት ገዛኸኝ አበራ በሲድኒ ኦሎምፒክ በማራቶን አሸንፎ ሲመጣ፣ የደቡብ ክልል መንግሥት በሃዋሳ ከተማ በሸለመው 25ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ ባለ 5 ኮከብ ደረጃ በመያዝ የተገነባ ነው፡፡ ለሆቴሉ ግንባታ እስካሁን 200 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን የገለፀው አትሌት ገዛኸኝ በአሁኑ ጊዜ 150 ሠራተኞች እንዳሉትና የማስፋፊያው ስራ ሲጠናቀቅ ለ500 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር እንጠብቃለን ብሏል፡፡ የገዛኸኝና እልፍነሽ ኢንቨስትመንት በሃዋሳ ከተማ ከሚገኘው ሆቴልና ሪዞርት ብቻ ሳይወሰን በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማም በቢሾፍቱ ሐይቅ ላይ ያሰሩት ባለ 5 ኮከብ ሪዞርት በቀጣዩ ዓመት እንደሚያስመርቁ ፤ በአዲስ አበባም በተለያዩ ቦታዎች የእንግዳ ማረፊያ ሕንፃዎችን እያስገነቡ እንደሆነና በጥቁር ውሃም ቦታ ተረክበው ምን መሥራት እንዳለባቸው እያሰቡ ናቸው፡፡

Read 4142 times