Saturday, 16 November 2013 14:11

ቻይናዊው የቴሌኮም ኢንጂነር በጅማ ፖሊስ እየተፈለገ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል የተባለው ቻይናዊ የዜድቲኢ ሰራተኛ ነው ተብሏል። ZTE፣ ለስራ ወደ ጅማ የሄደ ሰራተኛ የለንም፤ የተፈላጊውን ማንነት አጣራለሁ ብሏል። በጅማ ከተማ ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል የተባለው ቻይናዊ ኢንጂነር ዋንግ ዮንግ ለምርመራ እየተፈለገ ሲሆን፣ የጅማ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ከአዲስ አበባ ይዞ ለመውሰድ እያፈላለገ ነው።

ዋንግ ዮንግን በሚመለከት የዜድቲኢ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ዜድቲኢ ለስራ ወደ ጅማ የላከው ሰራተኛ፤ የለም፤ የተፈላጊውን ማንነት እናጣራለን ብለዋል። ከጅማ ፖሊስ ለቀረበ ጥያቄ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ፣ ዋንግ ዮንግ የቴሌኮም ኢንጂነርና የዜድቲኢ ሰራተኛ መሆኑን ገልጿል። የጅማ ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ተፈላጊውን ተጠርጣሪ ለመያዝ ሲያፈላልግ እንደቆየና ትናንት የዜድቲኢ ተወካዮችን እንዳነጋገረ ታውቋል።

ፖሊስ ዋንግ ዮንግን ለምርመራ ማፈላለግ የጀመረው፣ ጥቅምት አጋማሽ ላይ ጅማ ውስጥ “ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል” የሚል ጥቆማ ከአካባቢው ነዋሪ ከወ/ሮ ታደለች ተመስገን ከደረሰው በኋላ ነው። ጉዳዩም ከካሳ ክፍያ ጋር መያያዙ፣ ከኩባንያዎች ተቀናቃኝነት ጋር የተሳሰረ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። ወ/ሮ ታደለች ተመስገን፣ ከሁለት ወራት በፊት ስራ ላይ በአደጋ ህይወቱን ያጣ ሰራተኛ ቤተሰብ ናቸው። የአንድ የአገር ውስጥ ድርጅት ተቀጣሪ የነበረው ሰራተኛ በኢንተርኔት ማስፋፊያ ፕሮጀክት የፋይበር ኦፕቲክስ ዝርጋታ ላይ ነው በአደጋ የሞተው።

የሰራተኛው አሟሟት ላይ ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ቀጣሪው ድርጅት በበኩሉ፤ ሰራተኛው አስፈላጊ የጥንቃቄ አልባሳትና መሳሪያዎችን ሲጠቀም እንደነበር በፖሊስ ምርመራ መረጋገጡን ገልጿል። ከሟች ቤተሰብ ጋር በመነጋገር ቀጣሪው ድርጅት የመቶ ሺ ብር ካሳ የከፈለ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚመመራው ሁዋዌ በበኩሉ 200 ሺ ብር ድጋፍ እሰጣለሁ ብሏል። ከዚህ በኋላ ነው፣ ዋንግ ዮንግ ወደ ጅማ መጥቶ “ጋዜጠኛ ነኝ በማለት አጭበርብሯል” የተባለው።

ቻይናዊው ዋንግ ዮንግ መጥቶ እንዳገኛቸውና ሆቴል ድረስ ጠርቶ እንዳነጋገራቸው የጠቀሱት ወ/ሮ ታደለች፣ “ጋዜጠኛ ነኝ፤ ተጨማሪ ገንዘብ እንድታገኙ አደርጋለሁ፤ አዲስ አበባ እንሂድ” በማለት ሊያግባባቸው እንደሞከረ መናገራቸውን ምንጮች ገልፀዋል። ወ/ሮ ታደለች ለፖሊስ ያመለከትኩት ጥርጣሬ ስላደረብኝ ነው ማለታቸው የተገለፀ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ፤ ዋንግ ዮንግ ጋዜጠኛ ሳይሆን የቴሌኮም ኢንጂነርና የዜድቲኢ ሰራተኛ መሆኑን ያረጋገጠው ባለፈው ሳምንት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባገኘው መረጃ ነው ተብሏል። በእነዚህ መረጃዎች የተነሳ፣ ጉዳዩ በዜድቲኢ እና በሁዋዌ መካከል ካለው ተቀናቃኝነት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ መፈጠሩ አልቀረም። የዜድቲኢ የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ስለ ዋንግ ዮንግ ትናንት ተጠይቀው በሰጡን ምላሽ፣ ዜድቲኢ ለማንኛውም ስራ ወደ ጅማ የላከው ሰራተኛ እንደሌለ እርግጠኞች ነን፤ የሰውዬውን ማንነት አጣርተን እናሳውቃለን ብለዋል።

Read 2793 times