Saturday, 26 November 2011 09:21

የጋዳፊ አቻ የሆኑት አምባገነን መሪ

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

ካሪሞቭ ለሴት ልጃቸው ስልጣናቸውን ለማስረከብ ተዘጋጅተዋል
አምባገነን መሪዎች በተለምዶ ከስልጣን የሚወርዱት፣ በከፍተኛ የጦር መኮንኖች በተወጠነ መፈንቅለ መንግስት (ኩዴታ) ወይም ለአመታት መንግስትን ሲቃወሙ በቆዩ የአማፂያን ሃይል አሸናፊነት ነው፡፡ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በኢስያ አገራት በርካታ አምባገነኖች በዚህ መንገድ ስልጣናቸውን ለቀዋል፡፡ ነገር ግን በ2011 ዓ.ም አምባገነኖች ከስልጣን የሚወገዱበት ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ ይህም ለዘመናት ታፍነውና ተረግጠው የኖሩ ሕዝቦች በቀሰቀሱት ሕዝባዊ አመጽ ከአንድም ሦስት አምባገነኖች ከሥልጣን ተገርስሰዋል፡፡

በግብጽ ሕዝባዊ አመፅ በተነሳ ወቅት ፖሊሶች ዳር ሆነው ከመታዘብ እንዲሁም በሙባረክ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር ካደረጉት ጥረት ውጪ የጐላ ጥፋት (ጥቃት) አልፈፀሙም፡፡ ከ300 በላይ ሰዎች ሊሞቱ የቻሉት በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው ፀብ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በቱኒዚያም ያለ ምንም ደም መፋሰስ ነው አምባገነኑ መሪ የተሰናበቱት፡፡ 
ሦስተኛው ባለተራ የሊቢያው ጋዳፊ ግን ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሳያንስ ሕዝባዊ አመጽ ያነሱትን ያንኳሰሱና የተሳደቡ ሲሆን ኋላም ላይ በጠራራ ፀሐይ በአውሮፕላን አስደብድበዋል፡ በዚህም ሳቢያ ተቃዋሚዎቹ ከሰላማዊ ሕዝባዊ አመጽ ወደለየለት ጦርነት በመግባት ከስምንት ወር ትግል በኋላ የጋዳፊን አገዛዝ ግባተ መሬት ፈጽመዋል፡፡
በዓለም ላይ አሁንም በርካታ አምባገነኖች እንዳሉ ቢታወቅም ከጋዳፊ ጋር የሚተካከል እንደሌለ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን “ፎሬን ፖሊሲ” የተሰኘው መጽሔት “UZBEKISTAN’S DICTATOR IS ANOTHER QADDAFI IN WAITING በሚል ርዕስ ያወጣው ዘገባ፤ የመካከለኛው እስያ አገር የሆነችው የዩዝቤኪስታን ፕሬዚዳንት ከጋዳፊ ጋር እንደሚተካከሉ ገልጿል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢስላም ካሪሞቭ ይባላል ስማቸው፡፡ ኢስላም ካሪሞቭ የተወለዱት እ.ኤ.አ በ1938 ዓ.ም ሳማርካንዳ በተባለ ቦታ ሲሆን፣ ከቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት በኢኮኖሚክስና በኢንጂነሪንግ ሁለት ዲግሪ ባለቤት ናቸው፡፡
ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላም ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ፣ በቅድሚያ ሥራ የጀመሩት የኤርክራፍት ኢንጂነር በመሆን ነበር፡፡ ከዚያም የኢኮኖሚ እቅድ አውጪ (Economic planner) ሆነው አገልግለዋል፡፡
ወደፖለቲካው ዓለም ከገቡም በኋላም እ.ኤ.አ በ1989 ዓ.ም በዩዝቤኪስታን ኮሚኒስት ፓርቲ ውስጥ ዋና ፀሐፊ በመሆን ተመረጡ፡፡ በዚያው ዓመት የቀድሞዋ ሶቭየት ስትፈራርስ ዩዝቤክስታንም እ.ኤ.አ 1995 በሕዝበ ውሳኔ ራሷን የቻለች አገር ሆነች፡፡ ዩዝቤክ ነፃ ከሆነች ጀምሮ እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ የሚገኙት ኢስላም ካሪሞቭ ናቸው፡፡ ከአራት አመት በኋላም ማለትም እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም ምርጫ ተካሂዶ እርሳቸው ተመረጡ፡፡ ይሁንና ሂዩማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ ታዛቢዎች፤ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ አይደለም በሚል ተቃወሙት፡፡
“Organization for security and Co-operation in Europe” የተባለው የአውሮፓ የምርጫ ታዛቢ ቡድን፤ በ1995 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል በ2000 ዓ.ም በዩዝቤክስታን በተካሄደው ምርጫ ታዛቢዎቹን አላከም ነበር፡፡
አሜሪካ በበኩሏ የ2000 ዓ.ም ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ካለመሆኑ ባሻገር የምርጫ መወዳደሪያው ሜዳ ለካሪሞቭ ያደላ እንደነበር በመግለጽ፤ የዩዝቤክ ሕዝቦች የሚፈልጉትን በትክክል ለመምረጥ አልቻሉም ስትል ምርጫውን ተቃውማለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም ደግሞ የፓርላማ ምርጫ ተካሂዶ ካሪሞቭ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫ እንዳያገኝ አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ካሪሞቭ፤ ዩዝቤክን ለ15 ዓመታት ያህል ሲገዙ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንዳይሆን ወይንም በማጭበርበር ብቻም አይደለም የሚታወቁት፡ ተቃዋሚዎቻቸውን በማሰር፣ በማንገላታትና በመግደልም ጭምር ነው፡፡ በ2006 ሳንጃር ኡማሮቭ የተባሉና የsunshine Uzbekistan ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ ለ11 ወር ያህል ከመታሰራቸው በተጨማሪ ድብደባና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከሶስት እስከ አስር አመት ተፈርዶባቸው ወህኒ ተወርውረዋል፡፡ ሚ/ር ካሪሞቭ ተቃዋሚ ለሆነ ግለሰብ ምህረት የላቸውም፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ራሳቸው የሚያሸንፉት ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ አደረጉ፡፡ ይህም ምርጫ እንደከዚህ በፊቶቹ የምርጫው መወዳደሪያ ለራሳቸው ያደላና ፍትሃዊ ያልነበረ ሲሆን፣ እንደተጠበቀው ራሳቸው አሸነፉ፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ የእርሳቸው ብቻ ማሸነፍ ያልተዋጠላቸው ዩዝቤካዊያን፤ በአንዲጃን ከተማ ሕዝባዊ ተቃውሞ አደረጉ፡፡
ይሁን እንጂ በሕዝባዊ አመጹ ላይ የተሳተፉ በርካታ ዜጐች በፖሊሲ ተይዘው የታሰሩ ሲሆን ግማሾቹ ደግሞ በካሪሞቭ ትዕዛዝ ተረሽነዋል፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ካሪሞቭ ጨፍጫፊ እንደሆኑ በመግለጽ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቃውሞ አቀረበ፡፡ ምዕራባዊያን አገራትም የካሪሞቭን ድርጊት አጥብቀው ኮነኑ፡፡ ይሁን እንጂ ለዓለም አቀፉ ተቃውሞ ቦታ ያልሰጡት ካሪሞቭ፣ ለአምነስቲ ሪፖርት አድርጋችኋል ያሏቸውን በአገራቸው የሚገኙትን የሰብዓዊ መብት ተቋም በመዝጋት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንም ወደ እስር ቤት አስገቧቸው፡፡
ፕሬዚዳንት ካሪሞቭ፤ በአንፃሩ አገራቸው ሰላምና ሕዝቡም እንደሚወዳቸው በመናገር፣ አገራቸው ላይ ሁከት እንዲፈጠር የሚያደርጉት አክራሪ ሙስሊሞችና አሸባሪዎች ናቸው በማለት ይቃወማሉ፡፡በተለይም “The Islamic movement of Turke stan” የተባለው እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን፤ በዩዝቤክስታን የእስልምና መንግስትን ለማስፈን ካለው ፍላጐት አንፃር የእርሳቸውን አገዛዝ ለመጣል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
በዚህም ምክንያት በርካታ የእስልምና ቡድኖች ሊታሰሩና ሊገደሉ ችለዋል፡፡ ካሪሞቭን ከጋዳፊ ጋር በማነፃፀር በ”ፎሬን ፖሊሲ” ላይ ጽሑፉን ያቀረበው ቶም ማሊኖዊስኪ፤ ጋዳፊ ተቃዋሚዎቻቸውን ሁሉ አክራሪ ሙስሊሞችና አልቃይዳ እንዳሉት ሁሉ ካሪሞቭም አክራሪ ሙስሊሞቹ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በመግለፃቸው ሁለቱም ሊመሳሰሉ ይችላሉ ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ1969 ዓ.ም ሥልጣን ሲይዙ ለሊቢያዊያን የተሻለና ዲሞክራሲያዊ አገዛዝን እንደሚያሰፍኑ ለሕዝቡ ቃል ሲገቡ፣ ተለሳልሰውና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ነበር፡፡
ካሪሞቭም በዩዝቤክ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን እንደያዙ፤ ካላቸው የካበተ ዕውቀትና ልምድ አንፃር አዲሲቷ ዩዝቤክን ከማዕከላዊ እስያ አገሮች ሁሉ የላቀች እንደሚያደርጓት የገለፁ ሲሆን፤ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫም በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ እንዲሁም ዜጐች ዲሞክራሲያዊ መብታቸው እንደሚጠበቅም ተናግረው ነበር፡፡
ታዲያ ተለሳልሰውና በሕዝብ ልብ ውስጥ ገብተው የነበሩት እነዚህ ሁለት መሪዎች፤ ኋላ ላይ ተቃዋሚዎችን አንድ በአንድ ማጥፋት ጀመሩ፡፡
ሁለቱም አያሌ ተቃዋሚዎችን አስረዋል ገድለዋል፡ ነገር ግን ካሪሞቭ ጋዳፊ ያላደረጉትን አንድ ነገር አድርገዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም ተቃዋሚ የነበሩትን የተወሰኑ ግለሰቦች ከእነ ሕይወታቸው እንዲቀበሩ አስደርገዋል፡፡
ሌላም ሁለቱ መሪዎች የሚመሳሰሉበት ነገር አለ፡፡ ጋዳፊ ስልጣናቸውን ለልጃቸው ለሰይፉ አል - ኢስላም ለማስተላለፍ ዝግጅት ላይ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን ፕሬዚዳንት ካሪሞቭም ለሴት ልጃቸው ስልጣናቸውን ለማስረከብ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ በብዙ ነገሮች የሚመሳሰሉ አምባገነን መሪዎች የሚለያዩበት ነገር አለ ከተባለ አሁን አንደኛው አምባገነን በህይወት አለመኖራቸው ሲሆን የጋዳፊን ሞት ተከትሎ የዓለማችን ቀንደኛ አምባገነን ፕሬዚዳንት የዩዝቤኪስታኑ ኢስላም ካሪሞቭ ሆነዋል፡፡
አሜሪካ የካሪሞቭን አምባገነንነት ብቻ ሳይሆን አረመኔያዊነትና ጨፍጫፊነት አሳምራ ብታውቅም በአፍጋኒስታን ለሰፈሩት 100ሺ የሚደርሱ ወታደሮቿ ስንቅና ትጥቅ የምታቀብለው የአፍጋኒስታን የድንበር አዋሳኝ በሆነችው ዩዝቤኪስታን በመሆኑ ለጊዜውም ቢሆን ካሪሞቭ ላይ ጫና መፍጠር አትፈልግም ያለው የ”ፎሬን ፖሊሲ” ፀሐፊ፤ ወደፊት ግን አሜሪካ እኚህን አምባገነን መሪ ከስልጣን ለማውረድ መንቀሳቀሷ እንደማይቀር ገልጿል፡፡

 

Read 5897 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 09:26