Monday, 18 November 2013 10:29

ያደሩበት ጭቃ ከጭድ ይሞቃል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በዱሮ ጊዜ በአንድ መንደር አራት ክፉ ክፉ አለቆች ይኖሩ ነበር ይባላል፡፡ እነዚህም፤ አቶ ዓለም፣ አቶ ደመና፣ አቶ ሰማይ ነህ እና አቶ በላይ ይባላሉ፡፡
አቶ ዓለም ለምጣም ሲሆን ሰውን ከሥራ ማባረር የሚወድ ቂመኛና ክፉ ሰው ነው፡፡ በማርፈድ ከሥራ ያስወጣል፡፡ ቆማችሁ ስታወሩ አገኘኋችሁ ብሎ ከሥራ ያስወጣል፡፡ ስጠራችሁ ቶሎ አልመጣችሁም ብሎ ከሥራ ያባርራል፡፡
አቶ ዓለም ደግሞ ከባላገር መጥቶ የሠለጠነ፣ ከሁሉ የምበልጥ ነኝ ባይ፣ ትኩስ ዘናጭ ነው፡፡ ሆኖም ሌላው የለበሰው ማናቸውም ልብስ ያስቀናዋል። በዚህ ምክንያት ደህና የለበሰ ሰው ላይ መጮህ ነው፡፡ ሰበብ እየፈለገ መደንፋት ነው!
አቶ ሰማይ ነህ ደግሞ የሁሉ አለቃ ነኝ ባይ ነው፡፡ ዋና ሥራው መጠራጠር ነው፡፡ ምንም ነገር ይስማ “ይቺማ ነገር አላት” ይላል፡፡ አንድ ሰው ለጨዋታ ብሎ ቀና ነገር ሲነግረውም፤ “ከጀርባው ምን አለው? ምን ቢያስብ ነው?” ይላል፡፡
የመጨረሻው አቶ በላይ ነው፡፡ በላይ እንደስሙ የበላይ ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ የመጨረሻ ጣሪያ እሱ ነው፡፡ ግን መሀይም ነው! የተማረ ሲያይ ደሙ ይፈላል፡፡ “ወረቀት አደለም! ወረቀት አደለም! ዋናው ሥራ ነው! እዚህ ወረቀት እያንጋጋችሁ አትጐለቱ!” ይላል፤ ጠዋት ገና ሥራ ሲገባ!
እነዚህን ሰዎች በቅጡ የሚያውቅ ባለቅኔ እንዲህ ሲል ገጠመ ይባላል
“ዓለም ቡራቡሬ፣ ሁሉን ሰው አታላይ
ደመናውን አልፎ፣ አለ ጥቁር ሰማይ
የተማረው ከሥር፣ ያልተማረው በላይ”
                                                              * * *
የሀገራችን ቢሮክራሲ በመልካም ሰዎች ሳይሞላ መልካም አስተዳደር ማምጣት አዳጋች ነው፡፡ ከመግዛት ባህሪያችን፤ ከአለቅነት ባህሪያችን በፊት ሰው የሚያደርግ ልዩና መልካም ባህሪ ሊኖረን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ጀምሮ ከተኮተኮትንበት ግብረገብነት እስከ ትምህርት ወግ -ማዕረግ ድረስ የሠለጠነ አዕምሮና የበሰለ የህይወት ልምድ ውስጣችን መገንባት ይኖርበታል። ከዚያ፤ በሥራ ዓለም የምናገኘው የዕለት ተዕለት ልምድ፣ ከየሰዉ ጋር ያለንን መስተጋብር (Interaction)፣ ትዕግሥትና ሆደ - ሰፊነት፣ ትህትናና ክህሎት፤ ብሎም የአመራር ብቃት እየሠረፀብን ይመጣል፡፡
በዚህ ላይ ነው እንግዲህ ቅጥ ያለው የፖለቲካ አመለካከት ሲጨመርበት፣ በግድ እኔ ያመንኩትን እመን፣ ያን ካላረክ ጠላቴ ነህ፤ የሚል ሰው አንሆንም፤ የምንለው፡፡ ያመንከውን አምነህ፣ ተቻችለን አንድ መሥሪያ ቤት መኖር አያቅተንም ብለን ማሰብ፤ ጤናማና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው። ከማቃቃር ይልቅ ያቀራርበናል፡፡ ከማራራቅ ይልቅ ያስተቃቅፈናል፡፡ ከመጠፋፋት ይልቅ ያስተራርመናል፡፡
በእስተዛሬው የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዞአችን ወይ “ብቆጣም እመታሻለሁ፣ ብትቆጪም እመታሻለሁ” ማለት፤ አለበለዚያ ደግሞ “አሸናፊ ነኝ ያለኔ አታውራ”፤ “ተሸናፊ ነህ ስላንተ እንዳይወራ!” እንዳንል ያደርገናል፡፡
መልካም የስፖርት ድጋፍ ባህል መዳበር አለበት፡፡ በስንት ዘመን ዛሬ ያጋጠመንን ዕድል ተመስገን እንበል፡፡ ተጨዋቾቻችን በምንም መመዘኛ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ የሚመሰገን ነው፡፡ አንድ ከተመልካቾቻችን የሚጠበቅ ባህል አለ ዘላቂነት የሙሉ ጊዜ ድጋፍ የመስጠት ልምድ! ይሄ በአንድ ቀን ሊሆን የሚችል ባህሪ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም በልቦናችን ይደር ብናሸንፍ ወይም ብንመራ ቴሌቪዢናችንን የበለጠ እንደማንከፍተው ሁሉ፤ ብንሸነፍ ቴሌቪዥናችንን አንዘጋውም፡፡
ከአንድ የጭብጨባና የጩኸት ድጋፍ ድምጽ በአንድ ጊዜ ወደሚደብት የድብርት ድባብ አንግባ፡፡ በየትኛውም ማህበራዊ መስክ፣ ፖለቲካችንን ጨምሮ፤ የሞቅ ሞቅና የለብለብ አካሄድ ደግ አደለም፡፡ ዘላቂ እንሁን በአቋማችን እንግፋ፡፡
አለበለዚየ “ያደሩበት ጭቃ፣ ከጭድ ይሞቃል” ዓይነት ይሆንብናልና በአዎንታዊ ጉዟችን እንግፋ ማናቸውም ውጤት የነገ መንገዳችን መትጊየ ነው፡፡ ፈረንጆች፤ “all that had gone before was a preparation to this; And this is a preparation to this” ይላሉ፡፡ “እስካሁን ያለፍንበት ሁሉ እዚህ ለመድረስ ነበር፡፡ ይሄ ደሞ ለነገ መዘጋጃችን ነው” እንደማለት ነው፡፡
ድል ለዋሊያዎቻችን!

Read 4322 times