Monday, 18 November 2013 11:37

አስማተኞቹ እና ሚስጢራቸው

Written by 
Rate this item
(13 votes)

እኔ የተረዳሁትን ማንም ስላላወቀ እንጂ ሀሳቡ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ንግድ ማለት ቅይይር ማለት ነው፡፡ እንደ ልዋጭ። አንዱን እሴት ትቀበልና በእሱ ፋንታ ሌላውን ትሰጠዋለህ፡፡ ከልውውጡ የምታተርፈውን ነገር (እሴት) መሰብሰብ እና እንደገና በትርፍ ለመለወጥ መሞከር፡፡ ነጋዴ የመሆን ትርጉሙ በአጭሩ ይሄ ነው፡፡
የሚለወጠው ነገር የሚፈለግ መሆን አለበት፡፡ በዚህ በጨፈገገ ትውልድ ላይ እንደ ሳቅ የሚያስፈልግ ነገር የለም፡፡ ሳቅ ውስጡ የሌለው ማንም የለም፡፡ ሳቅን ፍለጋ ግን ገንዘቡን ከፍሎ “ኮሜዲ ሾ” ይገባል። ኮሜዲያን እንደ “አባ ገና” በትልቅ ስልቻ የሳቅ ገፀ በረከት ይዞ የሚዞር ይመስለዋል ታዳሚው፡፡ ግን ትልቅ ስልቻ ይቅርና ኪሱን የሚሞላ ሳቅ እንኳን ይዞ አይመጣም - እንዲያውም በተቃራኒው በኪሱ ያለው ለቅሶ ነው፡፡ እነሱ ታዳሚዎቹ በውስጣቸው ይዘው ያልመጡትን ሳቅ ኮሜዲያኑ ሊሰጣቸው አይችልም።
ኮሜዲያኑ አስማተኛ ነው፡፡ ማስመሰል ነው ስራው፡፡ ከተመልካቹ ሆድ ውስጥ ያወጣውን ሳቅ ከራሱ ሆድ ያፈለቀው አስመስሎ ማቅረብ፡፡ እኔ የገባኝ ሀሳብ ይሄ ነው፡፡ ሀሳቡን ተጠቅሜ የልዋጭ ሰራተኛ ሆንኩ፡፡ ከሰው ውስጥ የተደበቀውን ነገር ግልፅ አድርጌ መልሼ እሸጥለታለሁ፡፡ በሚስጥር፡፡
ሚስጥሩ፡- “If you don’t bring it here, you won’t find it here!” የሚል ቢሆንም፤ ሚስጥሩን ለታዳሚዬ ከገለፅኩለት አስማቴ ይነቃል፡፡ ሲነቃ፤ ጥበብ መሆኑ ይቀራል፡፡ ተራ የወሮበላ ማጭበርበር ይሆናል፡፡ መንገዱን ሳልገልፅ፤ መነሻውን እና መድረሻውን ብቻ ይፋ በማድረግ አስማቴን እሰራለሁ፡፡
መነሻው ይሄ ነው፡፡ መነሻው እንዲህ ነው። ሁሉም ሰው የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ አንዳንዱ መሳቅ ነው የሚፈልገው፤ ሌላው ማዘን፣ ሌላው ማፍቀር፣ ሌላው መክበር ወይንም መከበር … ሁሉም የሚፈልገው እና ሊያሟላው ያልቻለ አንድ ፍላጐት አለው፡፡ ያ ነው መነሻዬ፡፡ ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለው መንገድ የእኔ ሚስጢር ነው። መድረሻው ሁሉንም እንደየፍላጐታቸው መንካት መቻል ነው። መሳቅ የፈለገው ስቆ፣ ማልቀስ የፈለገው አልቅሶ፣ ማፍቀር የፈለገ ፍቅሩን አግኝቶ … ወደ ቤቱ እንዲሄድ ማድረግ፡፡ መነሻው ላይ ቃል እገባለሁ። ፍላጐቶች ሁሉ ስኬታቸውን እንደሚያገኙ፡፡ መድረሻው ላይ ብር እቀበላለሁ፡፡ ፍላጐታቸውን ከእነሱ ጋር ላገናኘሁበት፡፡
ጥበብ እና አስማተኝነት የደላላነትም ስራ ነው። ፈላጊ እና ፍላጐቱ የሚገናኙበት ምስጢር ግን ከእኔ ጋር ተደብቆ ይቆያል፡፡ የእኔ አስማተኝነት ያለው ሚስጢሩን እስከጠበቅሁ ድረስ ብቻ ነው። ከባድ የሚመስሉ ነገሮች ከብደው የሚቆዩት የክብደታቸው ምክንያት ሳይገለፅ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ ነው። ሁሉም ሚስጢር ሲጋለጥ አስቀያሚ እና ተራ ይሆናል፡፡ የኔ ሚስጢር ደግሞ በጣም ቀላሉ ነው። መስታወት ፊት ፈላጊውን ማቆም ነው፡፡ ራሱን በመስታወቱ እየተመለከተ… ግን መመልከቱን እንዳያውቅ በእኔ አማካኝነት የራሱ ምስል ነፀብራቅ እንዲታየው አደርጋለሁ፡፡ መሳቅ የፈለገ ደንበኛዬ ራሱን በእኔ ትርጓሜ ውስጥ ያያል፡፡ ከራሱ የማንነት ምስል በላይ የሚያስቅ ነገር ምን አለ?
ማልቀስ ለፈለገውም ተመሳሳይ ነው፤ ከራስ ምስል በላይ የሚያስለቅስ ነገር ምን ይኖራል? … ግን ያጣውን ነገር ራሱ እንዳያገኝ፣ እኔ በእሱ እና የራሱ ምስል ነፀብራቅ መሀከል ቆሜ አስተረጉምለታለሁ። የራሱ ምስል በእኔ አማካኝነት ሲተረጐም ከማናደድ እስከ ማሳቅ፣ ከማሳቀቅ እስከ ማራቀቅ … ከተስፋ መቁረጥ እስከ ተስፋ ማግኘት ሊለዋወጥ ይችላል። አስማቴም ይኸው ነው፡፡ የጥበብ አስማት ሚስጢር።
ባለ ፍላጐቱ በራሱ አይን ነፀብራቁን ቢመለከት የሚያየው ፍላጐቱን እንጂ መድረሻውን አያይም። ራሱን በራሱ አይን ሲመለከት ጉድለት እንጂ ሙሉነት አይታየውም፡፡ ሁሉም ሰው ለራሱ እይታ ጉድለት ነው፡፡ እንደአጋጣሚ ሙሉ ቢሆን እንኳን ጉድለት ነው ለራሱ አይን የሚታየው፡፡ ስለዚህ አስማተኛ ያስፈልገዋል፡፡ ጉድለቱን ሞልቶ የሚነግረው። ሙሉነቱን ይዤ የምመጣው ከሌላ ቦታ አይደለም፡፡ ከራሱ ኪስ አውጥቼ ነው ወደ ፍላጐቱ የሚያደርሰውን ክፍያ የምሰጠው፡፡ ግን አስማት እንደመሆኑ፣ የሞላሁለትን ፍላጐቱን ይዞ ከትያትር ቤቱ ወጥቶ የወል ቤቱ ሲደርስ፣ ከአስማቱ በፊት ወደነበረው ማንነቱ ይመለስና ጐዶሎ ይሆናል፡፡
ሳንድሬላ በአስማተኛዋ አያቷ (አክስቷ) አማካኝነት ከአመዳም ገረድነት ወደ እፁብ ድንቅ ልዕልትነት ተቀየረች፡፡ አያቷ (አክስቷ) የከወነችው አስማት እኔ ያወራሁላችሁን ነው፡፡ ሳንድሬላን የቀየረቻት… ስለ ራሷ ያላትን አመለካከት በመቀየር ነው፡፡ ገረዲቱ በራሷ ፊት ስትቆም ይታያት የነበረውን ምስል ወደ ልዕልት ምስል ቀየረችው፡፡ ሳንድሬላ ውስጥ ቀድሞውኑ ልዕልት የመሆን ፍላጐት ወይንም ምኞት ባይኖር ኖሮ፣ በአስማተኛዋ አያቷ ሀይል ሆነ በጠንቋይ ድግምት ልትፈጠር፣ ልትለወጥ አትችልም ነበር፡፡ ፍላጐቷን እና መፍትሄዋን ከእራሷ ውስጥ አውጥታ አለበሰቻት፡፡ ከተቀዳደደ ልብሷ ውስጥ በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስ በአስማት አማካኝነት አለበሰቻት፡፡ ከራስ ምስሏ ጋር የተቆራኙትን አይጦች፣ በነጫጭ ፈረሶች ተካችላት፡፡ ዱባውን ደግሞ ወደ ሰረገላ፡፡
በአስማተኛ አያቷ የተለወጡ ማንነቷን ይዛ ልዑላኖቹ ጋር ተቀላቀለች፡፡ ህልሟን በጥበብ አስማት እውን አድርጋ ልዑል አፈቀረች፡፡ ስድስት ሰአት ከሌሊቱ ሲሆን … አስማቱ ወደ ቀድሞው ተፈጥሮው ተቀየረ፡፡ አይጥም አይጥ፣ ዱባውም ዱባ … ሳንድሬላም ተመልሶ ተራ አመዳም ገረድ ሆነች፡፡ አስማት እና ተአምር የሚለያዩት አንዱ ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ሌላኛው አስማት ሆኖ ይቀራል፡፡
ጥበብ የራስን ምስል ከጉድለት ወደ ሙሉነት የምትቀይር መስታወት ናት፡፡ በመስታወቷ የሚታየውን ምስል ወደ ታዳሚው ፍላጐት የሚቀይረው ሰው ጥበበኛ ይባላል፡፡ ራስን በራስ የሚቀይር ልዋጭ እንደማለት ነው፡፡ ራስን በራስ አማካኝነት የሚቀይረው ባለሞያ ጥበበኛ ተብሎ ሲጠራ መስማት የተለመደ ቢሆንም፣ ዋናው ስሙ ግን አስማተኛ ነው፡፡
የጥበብ ታዳሚው ራሱን ይዞ ወደ ትርዒቱ ስፍራ ይመጣል፡፡ በፍላጐት ተሞልቶ፡፡ የትርዒቱ ስፍራ የስዕል ሸራ፣ የመጽሐፍ ገፆች ወይንም የትያትር መድረክ ሊሆን ይችላል፡፡ ከራሱ ውስጥ ስሜቶቹን እንደ ክራር እየቃኘ … ፍላጐቱን፣ ምኞቱን ከጉድለት አውጥቶ ሙሉ ያደርገዋል - ባለ ሞያው ከተራ ቃላቶች ውስጥ ለእያንዳንዱ ታዳሚው የሚሆን መፍትሄ ያገኛል፡፡
ማልቀስ ለሚፈልገው ለቅሶ … መሳቅ ለሚፈልገው ሳቅ፡፡ የሚስቅ እና የሚያለቅሰው ታዳሚው ራሱ ቢሆንም …ሳቁና ለቅሶው ግን በራሱ ላይ ነው፡፡ በራሱ አማካኝነት ነው፡፡ በትክክል የሚገጣጥመው ጥበበኛ ካገኘ… ማንኛውም ሰው በውስጡ ሙሉነት አለ፡፡ ልዕልቷ ሳንድሬላን ትሆናለች፤ በአስማተኛው አማካኝነት፡፡ ሳንድሬላም ልዕልቷን፡፡
ግን አሁን አሁን፤ አስማተኛ የመሆን ሳይሆን አስማተኛን የማጋለጥ ፍላጐት እያደረብኝ ነው፡፡ የቆዩ የአስማት ሚስጢሮች ካልተጋለጡ አዳዲሶቹ አይፈጠሩም፡፡ ጠንከር ያሉ ወይንም ፍቻቸው ቶሎ የማይደረስበት መንገዶችን ለመፍጠር ቀላሎቹ የአስማት ሚስጢሮች “tricks” መጋለጥ አለባቸው። እውነተኛ አስማተኛ የሚለየው … ከፍላጐት ወደ ግኝቱ በሰው ስሜት መሰላል አማካኝነት ሲወጣጣ … የተወጣጣበትን መሰላል በመደበቁ አይደለም። መንገዱን እየገለፀም… ማንም መንገዱን ተከትሎ እሱ የከወነውን አስማት መስራት ሲያቅተው ነው፡፡ ሚስጢርን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን መግለፅም አዳዲስ አስማቶች እንዲፈጠሩ በይበልጥ ያግዛል፡፡
ሚስጢሩ ቢገለፅ እንኳን ማንም ማከናወን የሚችለውን አስማት እየሰሩ እውነተኛ ጥበበኛ መሆን አይቻልም፡፡ የወል የአስማት ትርዒት፣ ይትባህል እንጂ ጥበብ አይሆንም፡፡ ሚስጢሩ ቢገለጥም ማከናወን ከባድ የሆነ አስማት ሳንድሬላን አንዴ ልዕልት ካደረጋት በኋላ፣ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ላይ ወደ አመዳም ገረድነት (ብቃት ባለው አስማተኛ በተሰራ ጥበብ ላይ) አትለወጥም፡፡ ልዕልት እንደሆነች ትቀራለች፡፡
መለወጧ ባይቀር እንኳን፤ በሰአታት ውስጥ ሳይሆን ብዙ ዘመናት ይፈጅባታል፡፡ ለምሳሌ ዶስትዮቪስኪ እንደዛ አይነት አስማተኛ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ደግሞ ኧ. ሄሚንግዌይ አስማቱን የሚሰራበት ሚስጢር ቢገለፅ እንኳን ማንም ሊያከናውነው የማይችል የአስማት አይነት ነው የሚሰራው ባይ ነኝ፡፡
የአስማታቸው ሚስጢር ሲጋለጥ፤ ሁሉም በየቤቱ ደብዳቤ ለመፃፍ የሚጫጭረውን ያህል ጥበብ ፈጥረው የተገኙም አሉ፡፡ ቀላሉን የአስማት ሚስጢር በማጋለጥ… ከባባዶቹ እንዲፈጠሩ መንገድ ማመቻቸት ነው… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመርኩት ስራ፡፡ እናም እላለሁ፤ አስማተኛ አስማቱን በከረጢት ይዞ አይዞርም፡፡ አስማቱን የሚፈጥረው ከታዳሚዎቹ ፍላጐት እና ነፀብራቅ በመነሳት ነው፡፡ ታዳሚዎቹ ሀዘን፣ ደስታ፣ ተስፋ እና አንዳች ፍላጐት በውስጣቸው ቀብረው ወደ አስማተኛው ባይመጡ አስማተኛው ብቻውን የሚከውነው አንዳች ነገር ባልኖረው ነበር፡፡ If you don’t bring it here you won’t find it here! ይላችኋል፤ ጥበበኛው ባዶ ከረጢቱን እያሳየ፡፡
የአስማተኛው ጥሬ እቃዎች እናንተ ናችሁ፡፡ ጥሬ እቃዎቹን ከተራ ወደ እፁብ ድንቅነት የሚቀይርበት መንገድ ነው ሚስጥሩ፡፡ ጥበበኛ ሚስጢረኛ ነው። ምርጥ ሚስጢረኛ ግን ሚስጢሩን የሚደብቅ ሳይሆን ለመግለፅ የሚሞክር ነው፡፡ ሚስጢረኛ የሆነበትን ሚስጢር ለመፍታት በሚያደርገው ሙከራ እና ሂደት …እናንተን ከፍላጐታችሁ ወደ ግባችሁ ያደርሳችኋል፡፡ ሚስጢሩን ለመፍታት በሚሞክርበት ጊዜ ነው አስማቱ የሚፈጠረው፡፡ ከከባድ ሚስጥሮች ፍቺ የሚገኝ አስማት ነው ልዕለ - ጥበብ፡፡ የልዕለ ጠቢብም አሻራ:- ሚስጥርን መግለፅ እንጂ መደበቅ አይደለም፡፡ በተገለፀ ቁጥር የሚደበቅ ሚስጥርን ለመፍታት ጠንካራ አስማተኞች ያስፈልጉናል፡፡ እውነተኛ አስማተኞች፡፡ ካርታን ደርድሮ “ቀዩዋን ያየ” እያሉ የሚያጭበረብሩት…እውነተኛም፣ ሚስጥረኛም አስተማኛም አይደሉም። ምናልባት “ወሮበላ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግልፁን ሚስጢር የሚያደርግ እና ሚስጢሩን ለመግለፅ በሚሞክር መሀል የሰማይ እና የምድር ያህል ርቀት አለ፡፡ አንደኛው ወሮ በላ ይባላል፡፡ ሌላኛው አስማተኛ ነው፡፡ አስማተኝነትን ከሌላ አስማተኛ በመማር ሚስጢሮችን እና አፈታታቸውን አጥንቶ፣ “የጥበቡ ጥሪ አለኝ” የሚል ሊጀምር ይችላል፡፡
አዲስ አስማት መፍጠር ካልቻለ … ወይንም ካልሞከረ ግን በስተመጨረሻ የሚገባው ወደ ማጭበርበሩ ነው፡፡ ቀላልን ሚስጢር ከባድ አስመስሎ ወደመደበቁ፡፡


Read 12610 times