Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 09:31

11ኛው ታላቁ ሩጫ ዛሬና ነገ አዲስ አበባን ያደምቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የ2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ዛሬ በህፃናት የ2 ኪሎ ሜትር ሩጫ ተጀምሮ በነገው እለት 36ሺ ሯጮችን በሚያሳትፈው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ አበባን ሊያደምቅ ነው፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር ለህፃናት እንሩጥ በሚል መርህ ያዘጋጀውን ገቢ ማሰባሰብ ከሳምንት በፊት 1 ሚሊዮን ብር በማግኘት አሳክቷል፡፡

በነገው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ታላቅ ውድድር ከ300 በላይ የውጭ ዜጎች ከመላው ዓለም በመምጣት የሚሳተፉ ሲሆን ላለፉት 60 ዓመታትበሯጭነት ያሰለፉት የ95 ዓመቱ አንጋፋና ስምጥር አትሌት ዋሚ ቢራቱ በ11ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለ11 ጊዜ በመሮጥ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ ዛሬ በሚደረገውና 4ሺ ህፃናት በሚወዳደሩበት የ2 ኪሎሜትር ሩጫ ላይ ደግሞ ባለፉት ሶስት ዓመታት የሮጠው ካሌብ ዮናስ የተባለ ታዳጊ በውድድሩ ተሳትፎውን ከ5ኛ ዓመት ልደቱ ጋር መቀጠሉ ተወስቷል፡፡
በነገው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን በመሳተፍ ያለፈው ዓመት ሻምፒዮናነታቸውን ለማስጠበቅ አስመራ በቀለና ሱሌ ኡታራ ተጠብቀዋል፡፡ በተለይ በወንዶች ምድብ አስመራ በቀለ ከሁለቱ የኬንያ አትሌቶች ኒኮላስ ኪምኮምቤይ እና ፒተር ሌሙያ ከባድ ፉክክር እንደሚገጥመው ሲገለፅ በሴቶች ምድብ የአምናዋ ሻምፒዮን ሱሌ ኡታራ ከኢትዮጵያውያኖቹ አፀደ ባይሳና ቲኪ ገላና እንዲሁም ከኬንያዋ ቢትሪስ ኪፕላጋት ጋር ትያያዛለች፡፡ በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ኡልትራ የተባለው ይገዜ መለኪያ የተገጠመለት የመሮጫ ጫማ ተግባራዊ መደረጉን የገለፁት የውድድሩ አዘጋጆች ለሽልማት 140ሺ ብር መቅረቡን ያስታወቁ ሲሆን በወንድና በሴት አሸናፊ ለሚሆኑት ለእያንዳንዳቸው 20ሺ ብር ይበረከታል፡፡
በተያያዘ ዜና የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂና ስራ አስኪያጅ የሆነው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በቶኪዮ ማራቶን ለመሳተፍ ቀጠሮ እንደያዘ ታወቀ፡፡ ሃይሌ በቶኪዮ ማራቶን በመሳተፍ ለለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን የሚያስፈልገውን ሚኒማ ለማግኘት እንደሚያነጣጥር የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ የአትሌቱ ማናጀር ጆስ ሄርማንስ ያለበት የአተነፋፈስ ችግር መፍትሄ ማግኘቱን ሲገልፁ የቶክዮ ማራቶንን የሚሳተፈው በላቀ ብቃት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

Read 4349 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 09:33